ውድ አንባቢዎቻችን ባለፈው ሳምንት ጉዳት ማለት ምን ማለት እንደሆነ እና የጉዳት መነሻዎች፣ ምንጮችና አይነቶችን ዘርዘር አድርገን አይተናል። በዚህ ጽሁፋችን ተከታዩን ክፍል ይዘን ለመቅረብ ቃል በገባነው መሰረት የጉዳት ካሳ አይነቶችንና ከዚሁ ጋር ተያያዥ የሆኑ የህግ ፍሬ ነገሮችን እንደሚከተለው ዘርዘር አድርገን ይዘን ቀርበናል።
ስለ ጉዳት ኪሳራ በ1952 ዓ.ም በወጣው የኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 13 ምዕራፍ 1 ክፍል 3 ንዑስ ክፍል 1 ስር ተደንግጎ ይገኛል። ከውል ወይም ከውል ውጭ ለሚደርስ የጉዳት ኃላፊነት ሕግ ዓላማው ከውል ወይም ከውል ግንኙነት ውጭ በሆነ ሁኔታ በአንድ ሕግ በተጠበቀ መብት ላይ ጉዳት ሲደርስ ጉዳት አድራሹ ወይም ለጉዳቱ ሕጉ ኃላፊ የሚያደርገው ሰው ጉዳቱን እንዲያስተካክለው ማድረግ ነው።
ከፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2090 (1) እና 2090 ስር ከተቀመጠው ድንጋጌ ካሳ ለአንድ ጉዳት ለደረሰበት ሰው የጉዳት መጠኑ ተተምኖ ለዚያ ጉዳት መጠን የሚሰጠው ጥቅም ወይም ገንዘብ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ይህ ለተጎጂው የሚሰጠው ጥቅም ለጉዳቱ ፈንታ ሆኖ ጉዳቱን ለማስተካከል ሲባል ነው።
ከታች በዝርዝር እንደምንመለከተው የካሳ ዓይነቶች የተለያዩ ቢሆኑም ዋነኛው የካሳ አይነት ከጉዳቱ ጋር ተመዛዛኝ የሆነ በገንዘብ የመካስ ዘዴ ነው። በሌላ በኩል በተጎጂው ላይ የደረሰውን ጉዳት በትክክል ለመገመት የማይቻል በሆነ ጊዜ በርትዕ የካሳውን ልክ መወሰን ስለሚቻል ተጎጂ በደረሰበት ጉዳት የገንዘብ ካሳ እንዲያገኝ ከመወሰን ሌላም በሌሎች አማራጮች ጉዳቱ መካስ እንደሚቻል በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2118-2123 ድንጋጌዎች ተመልክቷል። ለአብነትም የተወሰደውን ዕቃ ለተጎጂ በመመለስ ወይም በዓይነት መመለስ ወዘተ… ተጠቃሽ ነው።
የጉዳት ካሳ ዓይነቶች በአብዛኛው የጉዳት ካሳ የገንዘብ ጉዳት ካሳ እና የአካል ጉዳት ካሳ በመባል ይታወቃሉ። የአካል ጉዳት የሚያደርሰው የገንዘብ ኪሳራን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል።
የመጀመሪያው ጉዳቱን ለማስተካከል የሚወጣ ወጪ ነው። ይህም ተጎጂ የተጎዳውን አካል አሳክሞ ለማዳን የሚከፈለውን እንደቁስሉ አደጋ በኋላም ቢሆን የደረሰው የአካል ጉዳት ላስከተለባቸው ችግሮች ማቅለያ የሚከፈለውን ገንዘብ ሲሆን፤ እንደ ሕክምና፣ ትራንስፖርት፣ ለአልሚ ምግቦች እና ለመሳሰሉት አስፈላጊ ነገሮች የሚደረገውን ክፍያ ያጠቃልላል። ይህ ገንዘብ ከተጎጂው ሀብት ላይ እየተቀነሰ የሚከፈል ነው። ይህ ከኪስ የሚከፈል ወጪ አብዛኛውን ጊዜ በደረሰኞች ሊደገፍ ስለሚችል አስልቶ ለተጎጂው ማስከፈል እምብዛም አያስቸግርም።
ሌላው የገቢ ማጣት ኪሳራ ሲሆን፤ ይህ ኪሳራ በትክክል አስልቶ ለተጎጂው ካሳ ማስከፈል በጣም አስቸጋሪ ነው። በዋናነት የአካል መጉደል የሚያስከትለው ገቢ ማጣት ወይም መቋረጥ ነው። የአካል ጥቅሙ ሥራን ሰርቶ ገቢ ማስገኘት ብቻ ነው ባይባልም ገቢ ማስገኘቱ የታወቀ ስለሆነ በጉዳት ወቅት ያለው ገቢ ይቋረጣል።
የአካል ጉዳት ካሳ ደግሞ ተቀጥሮ ወይም በደመወዝ ይተዳደር ለነበረ አካል ጉዳተኛ የሚከፈል ካሳ፣ በግል ሥራ ይተዳደር ለነበረ የሚከፈል ካሳ፣ ሥራ ለሌለው አካል ጉዳተኛ የሚከፈል ካሳ፣ ሥራ ለመስራት ለማይችል አካል ጉዳተኛ የሚከፈል ካሳ እና በአደጋ ሰው ሲሞት የሚከፈል የመተዳደሪያ ቀለብ ይባላሉ።
ካሳ ለማግኘት መሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች እዚህ ላይ ካሳ ጠያቂዎች ሊገነዘቧቸውና ሊያሟሏቸው የሚገቡት ጉዳዮች ጉዳቱ የደረሰው በሕጋዊ ጥቅም ላይ መሆን ያለበት መሆኑን፤ ተጎጂው ያገኝ የነበረውና የተቋረጠበት ጥቅም ሕገ ወጥ ወይም ለኅሊና ተቃራኒ ከሆነ፤ ለምሳሌ ገቢው በቁማር ወይም በሴተኛ አዳሪነት ወይም በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ የተመሰረተ ከሆነ ካሳ ሊጠይቅ የማይችል መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል።
በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2029 ስር እንደተመለከተው ጥፋት ታስቦ ወይም በቸልተኝነት እንዲሁም ተግባርን በመፈፀም ወይም ለመፈፀም ሊከሰት ይችላል። በዚህም ጉዳት ይደርሳል በጥፋቱ ጉዳቱን ያደረሰው ሰው ተጎጂውን የመካስ በሕግ ኃላፊነት አለበት። ካሳ ለማግኘት ጉዳት መድረሱን ማስረዳት ያስፈልጋል።
አንድ ጉዳት በገንዘብ ሊተመን በሚችል ጥቅም ላይ ሲደርስ የደረሰውን ጉዳት ለማመጣጠን ወይም ኪሳራውን ሙሉ ለማድረግ ቀላል ሲሆን፤ በሌላ በኩል የደረሰውን በገንዘብ መተመን በማይቻል መብት ወይም ጥቅም ሲሆን ግን ካሳውን ለማመጣጠን እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል።
ምክንያቱም የደረሰው ጉዳት በገንዘብ በመካስ ሊመለስ የማይችል በመሆኑ ነው። የጉዳት ካሳው ከደረሰው ኪሳራ እኩል መሆን አለበት ተብሎ ቢደነገግም የአካል ጉዳት በደረሰበትና ህይወት ባለፈበት ጉዳይ የኪሳራውን መጠን እርግጠኛ በመሆን ይህን ያህል ነው ብሎ መገመት አስቸጋሪና የማይቻል ነው።
የጉዳት ካሳ ጠያቂዎች በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2141 ስር እንደተመለከተው የደረሰበትን ጉዳት ልክና የጉዳት አድራሹን ኃላፊነት በማስረዳት ክስ ማቅረብ የሚችለው ጉዳት የደረሰበት ሰው ነው። በሕጉ መሰረት ጉዳት የደረሰበት ሰው ሲባል ተጎጂ የተባለው በቀጥታ ጉዳት ያረፈበት ሰው ወይም ይህ ሰው በመጎዳቱ ምክንያት በተዘዋዋሪ ጉዳቱ የሚያገኛቸው ሌሎች ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ (በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2095 እና 2144 በግልጽ ተደንግጓል)። በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2142 መሰረት የካሳ ጥያቄ ከሳሽ የደረሰበትን ወይም የሚደርስበትን ጉዳት ልክ ብቻ ሳይሆን የጉዳት አድራሹንም ኃላፊነት የማስረዳት ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል።
የጉዳት ካሳ የመክፈል ኃላፊነት የጉዳት ካሳ የመክፈል ኃላፊነት የሚኖርባቸው የጉዳት ካሳ ሕጉ ኃላፊ የሚያደርጋቸው ሰዎች የደረሰውን ጉዳት በካሳ መልክ ለማስተካከል የጣለባቸው ናቸው። ለአብነት አንድ ተሽከርካሪ በሌላ ሰው ጥቅም ወይም መብት ላይ ጉዳት ቢያደርስ አሽከርካሪው ወይም (እና) የተሽከርካሪው ባለቤት የጉዳት ካሳ ኃላፊነት ይኖርባቸዋል። በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2081 (1) መሰረት መኪና ወይም ባለሞተር ተሽከርካሪው ለሚያደርሰው ጉዳት ባለመኪናው ኃላፊ እንደሚሆን ተጠቅሷል።
የተሽከርካሪው ባለቤት ከደረሰው የጉዳት ኃላፊነት ማምለጥ የሚችለው ከሚከተሉት ሶስት አማራጮች አንዱ ሲሆንለት ብቻ ነው። ማለትም በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2081 (2) መሰረት መኪናው ጉዳቱን ባደረሰበት ጊዜ የተሰረቀ መሆኑን በማስረዳት፣ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2982 መሰረት በደረሰበት ወቅት ለሌላ ሰው ጥቅም በሌላ ሰው እጅ የነበረ መሆኑን በማስረዳት እንዲሁም በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2088 (2) መሰረት ጉዳቱ የደረሰው በተጎጂው ወይም በተከሳሹ ሙሉ ጥፋት መሆኑን ካስረዳ ነው።
በአጠቃላይ ስለ ጉዳት ካሳ ልንረዳው የሚገባው ጉዳይ ጉዳት የደረሰበት ሰው የግድ መካስ እንደለበት ሲሆን፤ ጉዳት በፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 2090 እና 91 ስር በተደነገገው በመሰረት ተመጣጣኝ በሆነ የገንዘብ መጠን ነው የሚካሰው። ጉዳት የደረሰበት ሰው ተካሰ ሚባለው ጉዳቱ ከመድረሱ በፊት ወደ ነበረበት ቦታ ሲመለስ ነው። ተጎጂውን ወደ ነበረበት ቦታ ለመመለስ ለጉዳቱ ኃላፊ የሆነው ሰው ከጉዳቱ እኩል የሆነ ካሳ እንዲከፍል ማድረግ ያስፈልጋል። መርሁም ጉዳት እኩል ሆኗል ካሳ ስለሚል። ለደረሰው ጉዳት ካሳ ከላይ እንዳየነው ገንዘብ በመክፈል ሊሆን ይችላል ወይም ምትክ ንብረት በመስጠት ወይም በሌላ አኳኋን ሊፈፀም ይችላል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2013