ወይዘሮ ሣራ ዘመኑ ሠናይ በዚህ በልጆች አምድ ለወላጆች መልእክትን ማሰተላለፍ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ወይዘሮ ሣራ የህክምና ባለሙያ ሲሆኑ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሀን ለወላጆች የተለያዩ ሀሳቦችን እያነሱ ያካፍላሉ። እኔን ማግኘት የሚፈልግ ሰው ካለ በዚህ (Enatleenat@ gmail.com) የኢሜል አድራሻ ያግኘኝ ብለዋል።
እኛ ወላጆች ያለን በንግግር የመግባባት አቅም ከልጆቻችን ጋር ለሚኖረን ግንኙነት በጣም ወሳኝ ነው። ጥሩ በንግግር የመግባባት ልምድ ካለን ከልጆቻችን ጋር ያለን ግንኙነት የተቀራረበ ይሆናል። በአንፃሩ ደግሞ ይህንን ልምድ ካላዳበርን ግንኙነታችንን የተራራቀ ያደርገዋል። ስለዚህ እንዴት ይህንን ልምድ እናዳብር? ጥሩ የንግግር መግባባትስ ምን ይመስላል? ከዚህ በታች ሦስት አመላካቾችን እንመልከት።
የመጀመሪያው አመላካች “ከልጆቻችን ጋር ምን ያህል የንግግር ጊዜ አለን?” የሚለው ነው። ከልጆቻችን ጋር ጥሩ የንግግር ልምድ ሊኖረን የሚችለው አስፈላጊነቱን ተገንዝበን የሚገባውን ጊዜና ቦታ ስንሰጠው ነው። ለምሣሌ ልጆቻችን ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ስለቀን ውሏቸው ለመጠየቅ ጥሩ አጋጣሚ ነው። በተመሳሳይ ከጓደኞቻቸው ጋር ወጥተው ተጫውተው ረጅም ጊዜ ኣሳልፈው ሲመለሱም ስላሳለፉት ጊዜ ለማውራት ዕድል አለን። ቀኑን ሙሉ እቤት ውስጥም ውለው ሲያሳልፉም አብረን ቁጭ ብለን ለመጫወትና ለመነጋገር ዕድል እናገኛለን። እነዚህን ሁሉ ዕድሎች እንደ አግባቡ እየተጠቀምን የመነጋገሪያ ጊዜ ማመቻቸትና በንግግር የመግባባት አቅማችን መሠረታዊ ነው።
ሁለተኛው አመላካች የማዳመጥ ልምዳችን ምን ያህል የዳበረ ነው የሚለው ነው። አብዛኛውን ጊዜ ቁጭ ብለን ከልጆቻችን ጋር ስናወራ እነርሱ የሚነግሩን ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ እኛ ልንነግራቸው የምንፈልገው ላይ የበለጠ እናተኩራለን። ጥሩ በንግግር የመግባባት አቅም የመናገርን ችሎታ ብቻ ሳይሆን በተለይ ደግሞ የማዳመጥን ችሎታ ይጠይቃል።
በምናዳምጥበት ጊዜ ሙሉ ሃሳባችንን ለንግግራችን መስጠት ያስፈልጋል። ወግ በአይን ይገባል እንደሚባለው ዓይን ለዓይን እየተያዩ ማውራት አስፈላጊ ልምድ ነው። ልጆች በምናዳምጣቸውም ጊዜ የሚናገሩትን ቃላት ብቻ ሳይሆን መከታተል ያለብን የሰውነታቸውንም ቋንቋ ጭምር ነው መሆን ያለበት። በዚህ መልክ የማዳመጥና የሚነግሩንን የመረዳት ችሎታቸውን ማዳበር በንግግር ለመግባባት አቅማችን ወሳኝ ነው።
ሦስተኛው አመላካች ደግሞ በንግግራችን ጊዜ የልጆቻችንን ስሜት ምን ያህል እንጠብቃለን? ወይም እናከብራለን? የሚለው ነው። ልጆቻችን ከቀን ወደ ቀን በሚያጋጥማቸው ነገሮች ዙሪያ በሆነ ጉዳይ በጣም ተናደው ወይም በጣም አዝነው እናገኛቸው ይሆናል። በዚህ ስሜት ውስጥ ሆነው ስናወራቸው ድምፅ ከፍ አድርገው በማውራትም ሆነ ወይም በማልቀስ ስሜታቸውን ይገልጹ ይሆናል። በዚህን ጊዜ አንተ ምን ያጮህሃል? ወይም አንቺ ምን ያስለቅስሻል? በሚል አነጋገር ስሜታቸውን ማጣጣል የለብንም። በዚህ ፋንታ የተሰማቸውን ንዴት ወይም ሀዘን እንደምንረዳቸው በመንገር ስሜታቸውን ጤናማ በሆነ መንገድ እንዲገልጹት ቦታ መስጠት ይገባናል።
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሦስት አመላካቾች ከልጆቻችን ጋር ምን ያህል በንግግር የመግባባት አቅም እንዳለን ያሳዩናል። አቅማችንን በእነዚህ መንገዶች በመለየት ለማዳበር እንትጋ። መቼም ልጅ ለልጁ ነውና ልጆቻችን ለሀገር የሚበጁ ድንቅ ፍጥረቶች የሆኑልን ዘንድ እንበርታ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሰኔ 20 ቀን 2013 ዓ.ም