ሠላም ልጆች እንዴት ናችሁ? በዚህ ባለንበት ሰኔ ወር በሀገራችን አንድ ትልቅ ጉዳይ ተከናውኖ ነበር፤ እሱም ምርጫ ነው። ምርጫ ማለት ሀገራችንን ሊመራ የሚችል ከህዝብ ውስጥ የወጣ መሪ የሚመረጥበት (አዲስ መንግሥት የሚመሠረትበት) የሀገሪቱ ህዝቦች በሙሉ የምርጫ ድምፅ የሚሰጡበት ሂደት ነው።
ምርጫ ለአንድ ሀገር የሚያስፈልጋት ህዝቦች በነፃነት ሣይሸማቀቁ የሚመራቸውን መሪ ማስቀመጥ እንዲሁም እነሱ በመረጡት ሰው መመራት እንዲችሉ ነው። ልጆቼ መቼም ሁሉም ሰው መሪ መሆን አይችልም አይደል? ሁሉም ሰው በየራሱ በተሰጠው ፀጋ ነው መኖር የሚችለው። እናም መሪ የሚሆኑት የተወሰኑ ሰዎች ቢሆኑም ሁሉም ዜጎች ለሀገራቸው የመሪውን ያህል እያሰቡ የየእለት ሥራቸውን በአግባቡ ይወጣሉ።
ዘንድሮ ሰኔ 14 2013 ዓ.ም የተደረገው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ወደ ምርጫ ጣቢያው መጥተው ነበር። አቶ የሺዋስ በምርጫ ተወዳዳሪ ሲሆኑ፤ የምርጫ ሂደት ምን እንደሚመስል ለልጆቻቸው ሲያስረዱ ነበር።
ልጆቹም አባታቸውን እየተከተሉ አባታቸው የሚያደርጉትን በጥንቃቄ ይመለከቱ ጀመር። አባታቸው መርጠው ወደ ውጭ ሲወጡ ነበር ቅዱስን እና ሕሊና የሺዋስን ልናናግር የቻልነው።
ሕሊና የአስሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ናት። “ከአባቴ ጋር ወደ ምርጫ ጣቢያ የመጣሁት አባቴ የምርጫ ሄደትን እንድመለከት ስለሚፈለግ ነው” የምትለው ሕሊና በምርጫ ጣቢያ መገኘቷ እንዳስደሰታትም ትናገራለች።
ሌሎች ልጆችም ትልልቅ ሰዎች ለሀገር የሚሰሩትን ነገር እየተማሩ ቢያድጉ መልካም እንደሆነ ተናግራ ወላጆችም ልጆቻቸው ሁሉንም ነገር አንዲያውቁ ቢረዷቸው መልካም እንደሆነ ትገልፃለች።
የሕሊና ታላቅ ወንድም ደግሞ ሕፃናት ምንም እንኳን ልጆች ቢሆኑም ሀገራቸው የእነሱም ናትና ትልልቅ ሰዎች ስለ ሀገራቸው የሚሰሩትን ነገር ማወቅ እንደሚገባቸው ይናገራል።
ቅዱስ የሺዋስ አሁን የ13 ዓመት ልጅ ቢሆንም ከአምስት ዓመት በኋላ አሥራ ስምንት ዓመት ስለሚሞላው ሀገራዊ ምርጫ ላይ በመራጭነት መሳተፍ ይችላል።
ልጆቼ የቅዱስና የሕሊና አባት አቶ የሺዋስ ልጆቻቸው ስለምርጫ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያደረጉ ሲሆን፤ ልጆቹም አባታቸው ባደረጉት ማብራሪያ በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ ነግረውናል።
እናንተ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልዶች ናችሁ። ሁሉም ትልልቅ ሰዎች ሲያረጁ እናንተ ደግሞ ትልልቅ ሰው ስለምትሆኑ ሀገርን ወደፊት ለማስቀጠል ከናንተ የሚቀድም አይኖርም። ስለዚህም ልጆቼ በሚገባ መማር ጠቅላላ እውቀት ለማግኘትም በደንብ የተለያዩ መፃህፍትን ማንበብ ይገባችኋል። ጎበዝ ሀገራችሁን የምትወዱ፣ እርስ በእርስ የምትከባበሩ፣ ከሁሉም በላይ ያለ ልዩነት የምትዋደዱ ሁኑ እሺ። መልካም ሠንበት ይሁንላችሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሰኔ 20 ቀን 2013 ዓ.ም