መሬት ዘላቂ ንብረት ነው የሚል እምነት በመኖሩ ሰዎች መሬትን ብለው ሲጋጩ
ይታያሉ፡፡ መሬት መጠለያ መስሪያ ዘላቂ ሃብት ብቻ ሳይሆን የቤተሰብ የኢኮኖሚ ምሰሶ ሆኖ ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ ሃብት በመሆኑም ጭምር ነው፡፡ የዛሬው አባት መሬቱን አርሶ ልጆቹን ይቀልባል፡፡ የነገው ልጅም በአባቱ መሬት ላይ የቤተሰቡን ህይወት ያስቀጥላል፡፡ መሬቱ ከተቀማ ተጎጂው እየኖረበት ያለ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ጉዳቱ የሚወርደው ነገ የሚወለደው ልጅ ድረስ ዘላቂ ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ በኢትዮጵያውያን ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ክርክር የተለመደ ነው፡፡
‹‹መሬታችንን ተነጥቀናል፤ ያለአግባብ እኛ ብቻ ሳንሆን ቤተሰባችንም ለአደጋ እና ለጉዳት ተጋልጠዋል፡፡›› ሲሉ ወደ ዝግጅት ክፍላችን መጥተዋል፡፡ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ከሃላባ ዞን ዌራ ጅዶ ወረዳ በንዶ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ 16 የሚደርሱ አርሶ አደሮችን የወከሉ ሶስት ግለሰቦች ፍረዱኝ ብለው ወደ አዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል መጥተዋል፡፡
አቤቱታ አቅራቢዎቹ እንደሚናገሩት፤ ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ ለይዞታው ግብር እየከፈሉ የቆዩበት መሬት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በኢንደስትሪ ስም ተወስዶባቸዋል፡፡ አያይዘውም ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር የተቸገሩ መሆናቸውን እና በገጠር መሬት የመጠቀም ህገመንግስታዊ መብታቸው የተጣሰ መሆኑን በመግለፅ፤ የሚመለከተውን አካል በማነጋገር ችግራቸው እንዲፈታ በማለት አቤቱታቸውን ይዘው ቢሯችን ድረስ መጥተዋል፡፡
ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ከሃላባ ዞን ዌራ ድጆ ወረዳ ከበንዶ ቀበሌ በመምጣት አቤቱታ ያቀረቡት አቶ ሃሰን አጌቦ እንባቸውን እያፈሰሱ እንደሚገልፁት፤ መሬታቸውን ያለአግባብ ተነጥቀዋል፡፡ በዚህ ሳቢያ ብዙ ዋጋ እየከፈሉ ነው፡፡ ሰሞኑን ‹‹ለምን መሬታችን ያለአግባብ ይወሰዳል›› ብለው ያለቀሱት ሚስታቸው ከነህፃን ልጃቸው እስር ቤት እንዲገቡ ተደርገዋል፡፡
‹‹ሄርጳ የተሰኘ የኢንደስትሪ አልሚ በመቆፈሪያ ማሽን በመሬቱ የነበረውን ቡቃያ ሳያስቀር መሬቱን ለሁለት ሰንጥቆ ለአርሶ አደሮቹ በሚል ሁለት ሁለት ጥማድ መሬት አስቀርቶ ሌላውን እንዲወስድ ተደርጓል፡፡ አርሰን የምንበላበትን መሬታችንን ለመኖሪያ ቤት እና ለጓሮ አትክልት የሚሆን መሬት ብቻ ትቶልን ‹ለኢንደስትሪ ልማት ይፈለጋል› በሚል ከእያንዳንዳችን ስድስት ስድስት ጥማድ መሬት ወሰደብን፡፡ በመጀመሪያ መሬቱ ለኢንደስትሪ አልሚ በሚል ስም ተነጠቅን፡፡››ይላሉ፡፡
እንደአቶ ሃሰን ገለፃ፤ ለክልሉ ጥያቄ አቀረቡ፡፡በክልል ብቻ አላበቁም ለአላባ ዞን እና ለወረዳውም ጥያቄ በማቅረባቸው ኢንዱስትሪው በአካባቢ እንዳይገባ፤ እንዳይነካ ተባለ፡፡ ይህን ያሉት የቀድሞዎቹ አመራሮች ሲሆኑ፤ በአርሶ አደሮቹ አቤቱታ ምክንያት መሬቱን የተከለከለው ኢንቨስተር ተነጥቆ ለእነርሱ ለአርሶ አደሮቹ መሬቱን ከመመለስ ይልቅ አመራሮቹ ለራሳቸው ተከፋፈሉት፡፡
‹‹በዛ ሰዓት ይህን ያደረጉት በቅርብ የነበሩ የቀበሌ እና የወረዳ አርሶ አደሮች በመሆናቸው ፈርተን ተውን፡፡ ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ራሳችን እያወጣን እያረስን የምርቱን እኩሌታ ለአመራሮቹ ለመስጠት ተገደድን፡፡ የበላይ አመራር ሲመጣ እነርሱን ከማጋለጥ ይልቅ፤ በፍራቻ የራሳችን መሬት ነው፤ ምርቱም ለራሳችን ነው እንል ነበር፡፡ ይህን ያደረጉ ከቀበሌ አራት ከወረዳ ሁለት እና ሶስት የሚሆኑ አመራሮች ነበሩ፡፡›› ካሉ በኋላ፤ በለውጡ ወቅት ይህንን በማጋለጣቸው ምክንያት የአርሶ አደሮቹን ምርት ሲካፈሉ የነበሩ አመራሮች ከስልጣናቸው እንዲወርዱ መደረጉን ያስረዳሉ፡፡
አመራሮች የራሳቸውን መሬት ወስደው እያስፈራሩ በገዛ ጉልበታቸው እያሳረሱ ምርቱን እየነጠቁ የቆዩ ቢሆንም፤ ከዛ በኋላ ግን አመራሮቹ ተጋልጠው መሬቱን ቢነጠቁም መሬቱ በድጋሚ ሙሉ ለሙሉ አርሶ አደሮቹ እንዲጠቀምበት አለመደረጉን ያስረዳሉ፡፡
እንደአቶ ሃሰን ገለፃ፤ በክልሉ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ መሰረት ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ፅህፈት ቤት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡ ችግሩ ይፈታ መሬቱ ከአርሶ አደሮች እንደተወሰደ ሁሉም ያውቃል በሚል ‹‹የመሬታችን ይመለስልን›› ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡ ለዝግጅት ክፍላችን ይዘው በመጡት የስም ዝርዝር መሰረት 16ቱም አባወራ እያንዳንዳቸው ስድስት ጥማድ መሬት ተቆርጦባቸዋል፡፡ መሬቱ እንዲመለስ ቀበሌ፣ ወረዳ እና ዞን ቢመላለሱም ፍትህ የሰጣቸው የለም፡፡ በ16ቱ አርሶ አደር አባወራ ስር ከአራት መቶ ያላነሱ ሰዎች በዚህ መሬት ላይ ኑሯቸው የተመሰረተ ቢሆንም፤ ሲጠራ አቤት ብሎ መሬቱን ይገባችኋል ብሎ የሰጣቸው አካል የለም፡፡
ከክልሉ የእርሻ እና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ለሃላባ ዞን እና ለዌራ ድጆ ወረዳ ደብዳቤ ቢላክም ዞኑ እና ወረዳው ምላሽ አልሰጡም ይላሉ፡፡ ክልሉ ለዞኑ ‹‹የአርሶ አደሮቹን ቦታ አይተህ ሁኔታውን አረጋግጠህ ሪፖርት ላክ ቢልም ዞኑ ቦታውን ለማየት ፈቃደኛ አልሆነም›› ካሉ በኋላ፤ ደብዳቤው ለዞን ብቻ ሳይሆን ለወረዳውም ጭምር የተላከ ቢሆንም የዌራ ድጆ ወረዳ የመሬቱን ችግር አይቶ ምላሽ አለመስጠቱን ይናገራሉ፡፡
‹‹ እኔ በበኩሌ ሁለት ጥማድ ቤት ሰርቶ ለቤተሰቤ ቀለብ የሚሆን ምርት የማያመርት በመሆኑ፤ ሌሎች ሰዎች በያዙት መሬት ላይ በማረስ የማገኘውን ምርት ለግማሽ በማካፈል ቤተሰቦቼን እያኖርኩ ነው›› ይላሉ፡፡
የስምንት ጥማድ መሬት ግብር ለዓመታት ሲከፍሉ መቆየታቸውን ተናግረው፤ በክርክሩ ምክንያት ከሶስት ዓመት ወዲህ መሬቱ እንዳልታረሰ እና የእነርሱ ከብቶች ይውሉበት እንደነበር ጠቅሰው፤ አሁን ግን መሬቱ ተሸንሽኖ ከሌላ ቦታ የተነሱ ሰዎች በዛ መሬት ላይ እንዲሰፍሩ እየተደረገ ቤት መስራት መጀመራቸውን ይገልፃሉ፡፡
ሌላው ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ከሃላባ ዞን ዌራ ድጆ ወረዳ ከበንዶ ቀበሌ በመምጣት አቤቱታ ያቀረቡት ደግሞ አቶ ሰዒዲ ሃሚድ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚናገሩት ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ በመሬቱ ላይ ገብረዋል፡፡ የተወሰዱባቸው ስድስት ጥማድ መሬት ነው፡፡ እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች መሬቱ የተወሰደባቸው መጠን በተመሳሳይ ሁኔታ ነው፡፡
‹‹አመራሩ እንደኢትዮጵያዊ ከማየት ይልቅ አግልሎን መሬታችንን ለሔርጳ ኢንዱስትሪ ሰጠብን፡፡ የዘራነው እና የበቀለው ስንዴ እና በቆሎ ደርሶ ሳይታጨድ አንስተው ለኢንደስትሪው ሰጥተናል ፡፡›› በማለት ከአቶ ሃሰን ጋር ተመሳሳይ ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡
‹‹በነፍሳችን አስፈራርተው የራሳችንን መሬት ነጥቀው እያረስን ለአመራሮች እንድናካፍል ተገደን ኖረናል፡፡›› በማለት የሚናገሩት 13 የቤተሰብ አባላትን የሚያስተዳድሩት አቶ ሰዒድ፤ በኋላ በተነሳው ክርክር መሬቱ እንደውም ለመሬት ባንክ ገቢ ይሆናል ብለው መነጠቃቸውንም ይገልፃሉ፡፡ አርሶ አደሮቹ ‹‹በስህተት ወደ መሬት ባንክ አታስገቡት፤ አትፍረዱብን ይዞታችን ነው፡፡ ችግራችንን አቃልሉን፡፡›› በማለት መብታቸውን ቢጠይቁም ፍትህ አለማግኘታቸውንም ያብራራሉ፡፡
አቶ ሰዒድ እንዳሉት፤ መብታቸውን እየጠየቁ ችግራቸው ሳይፈታ እና ምላሽ ሳይሰጣቸው እነርሱ ሁለት ሁለት ጥማድ መሬት ብቻ ተሰጥቷቸው ቀድመው በያዙት ስድስት ስድስት ጥማድ መሬት ላይ ሌላ ሰው አምጥተው እያስቀመጡ መሆኑ ግራ አጋብቷቸዋል፡፡
‹‹ቦታው ድረስ ሔዳችሁ ያለውን ታሪክ አጣሩልን ይዞታችንን አረጋግጡልን›› በማለት በእንባ የታጀበ ጥያቄ በየደረጃው ቢያቀርቡም መፍትሔ ማጣታቸውን ያመለክታሉ፡፡ ቀድሞም ቢሆን መሬቱን ከተነጠቁ በኋላ እየኖሩ የነበረው ለሰዎች በእኩሌታ እያረሱ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ግን 13 የቤተሰብ አባላትን የያዘ ሰው በሌሎች መሬት ላይ አርሶ ምርት አካፍሎ መኖር ከባድ መሆኑን እና የፈለገው አካል ቦታው ድረስ ሄዶ ችግሩን እንዲፈታላቸው የሚሹ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡
ሌላኛው አቤቱታ አቅራቢ አቶ በድሩ ሽኩር የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው፡፡ እናት እና አባታቸው እዛው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በሃላባ ዞን ዌራ ድጆ ወረዳ በንዶ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ቤተሰባቸው እዛም እዚም የሚኖሩ ናቸው፡፡ መሬቱ ላይ በማረስ እናት እና አባታቸው የሚኖሩበት ከመሆኑም ባሻገር፤ አሥር ልጆቻቸው እና እናት እና አባታቸውን ጨምሮ 12 የቤተሰባቸው አባላት የሚተዳደሩት በዛው መሬት ላይ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡
እንደአቶ በድሩ ገለፃ፤ እጅግ አነስተኛ መሬት በመቅረቱ አሁን ከጓሮ ልማት ውጪ ሌላ እርሻ ማካሔድ ባለመቻላቸው ቤተሰባቸው ተቸግሯል፡፡ ቀደም ሲል ድንበራቸው ከዋርካ ያለፈ ቢሆንም እየገፉ እየገፉ ዋርካውን አልፈው መሬቱን ከመውሰድ ባሻገር ጭራሽ በሙሉ ለሔርጳ ኢንደስትሪ በሚል መሬቱ ተወሰደባቸው፡፡
እንደእነ አቶ ሰዒድ ሃሚድ ሁሉ የገዛ መሬታቸውን የወረዳ እና የቀበሌ አመራር ተከፋፍሎት ምርታቸውን እኩል ማካፈል የግድ ሆኖ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ሆኖም የወረዳ እና የቀበሌ አመራሮቹን የእነርሱ ተቃዋሚ ከክልል ሄዶ ከሶ እነርሱ እንዲታሰሩ እና ከስራቸው እንዲነሱ ቢደረግም፤ መሬቱ ለባለሃብቱም ሆነ ለአርሶ አደሮቹ አለመሰጠቱን ያብራራሉ፡፡ አርሶ አደሩ የእነርሱ ካልሆነ የኔ ነው ቢልም ባለሃብቱም ሰሚ ማጣቱን ያመለክታሉ፡፡
አቶ በድሩ፤ አሁን ደግሞ አመራር ቢቀየርም ከሌላ ቦታ ሰዎችን አምጥተው በመሬቱ ላይ ማስፈር ጀምረዋል፡፡ ሰፋሪዎቹ የመጡት ከሌላ ቀበሌ ሲሆን፤ ጉዳዩን መንግስት ይወቅልን፤ ህዝብ ይስማን እና መፍትሔ እናግኝ ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ሄደው ጥያቄ ያቀረቡ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፤ ጥያቄያችሁን በፅሁፍ ግለፁ ሲባል በሰዓቱ በፅሁፍ መግለፅ ባለመቻላቸው በሌላ ጊዜ አስፅፈው በተሰጣቸው ቁጥር እና በተነገራቸው መሰረት በፋክስ መልዕክት መላካቸውን ተናግረዋል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደተናገሩት፤ ኢንቨስተሩ ማለትም አቶ ሄርጳ ፈይሳም ቅሬታ እያቀረቡ መሆኑን ለመሬቱም ካርታ የተሰጣቸው በመሆኑ፤ ‹‹ለአርሶ አደሮቹ ካልተሰጠ እኔ ካርታ ስላለኝ መሬቱ የሚገባው ለእኔ ነው›› ብለው በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡ ነገር ግን ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደገለፁት፤ ባለሃብቱ መሬቱን በወሰደበት ጊዜም ቢሆን ካሳ አልተሰጣቸውም ነበር፡፡ ለእዚህ እና ሌሎችም ተያያዥ መረጃዎች የቀበሌ እና የወረዳ እንዲሁም የዞን እና የክልል መስተዳድሮችን እንዲሁም ባለሃብቱን እና ሌሎች ምስክሮችን መጠየቅ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
በበንዶ ቀበሌ ሲሰሩ የነበሩት አቶ አብድልቀድር ሽኩሌ እንደሚገልፁት፤ በቅድሚያ መሬቱን አርሶ አደሮች የነበሩበት ሲሆን፤ ለኢንደስትሪ ተብሎ መሬቱ ከአርሶ አደሮቹ ላይ እንዲወሰድ ተደርጓል፡፡ በኋላም ከባለሃብቱ በመንጠቅ አመራሮች በመሬቱ ለራሳቸው ማሳረስ ጀምረው ነበር፡፡ በኋላም የቀበሌው ነዋሪዎች ክልል እና ዞን ድረስ ሄደው ቅሬታ በማቅረባቸው እና አመራሮቹ ስልጣናቸውን ተጠቅመው የግለሰብን ይዞታ በመንጠቅ ሃብት አካብተዋል ማለታቸውን ተከትሎ መሬቱ ታግዶ ወደ መሬት ባንክ ገብቷል ተባለ፡፡
አሁን ደግሞ መሬቱ ላይ ሌሎች ሰዎች እንዲሰፍሩ መደረጉን፤ ለቀዳሚዎቹ አርሶ አደሮች ሁለት ሁለት ጥማድ ብቻ በማስቀረት ቆርጠው መውሰዳቸውን አቶ አብድልቀድር የሚያውቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሬቱ ኢንቨስተሩ ሰርቶ አልምቶ እንደማያውቅ እና ነገር ግን አርሶ አደሮቹ ሲያርሱበት እንደነበረ አስታውሰው፤ ከባለሃብቱ ይልቅ በአርሶ አደሮቹ ማሽላ እና በቆሎ ይመረት እንደነበረ እና አመራሮቹም ምርቱን ሲካፈሉ ህዝቡ በመክሰሱ አመራሮቹ መነሳታቸውን ገልፀዋል፡፡
አቶ አብድልቀድር እንደሚያስረዱት፤ መሬቱ በቅድሚያ የአርሶ አደሮቹ እንደነበር የሚካድ አይደለም፡፡ በመቀጠል ለኢንቨስተር ተሰጠ፡፡ እንደገና ከኢንቨስተሩ ነጥቀው አመራሮቹ ይዙት፤ አመራሮች ሲከሰሱ ደግሞ ወደ መሬት ባንክ ገባ፡፡ በመጨረሻም አሁን ሌሎች ሰዎች እንዲሰፍሩበት ተደርጓል፡፡
አቤቱታ አቅራቢዎቹ ለባለሃብቱ ሲሰጥም ለመሬቱ ካሳ እንዳልተሰጣቸው እና አሁንም ድረስ ችግራቸው አለመፈታቱን እንደሚያውቁ አቶ አብድልቀድር ምስክር ነኝ ሲሉ አስረድተዋል፡፡
መሬቱ ከአርሶ አደሮቹ ላይ ተነጥቆ ተሰጥቷቸዋል የተባሉት አቶ ሔርጳ ፈይሳ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በአካባቢው መሬቱን ለማልማት የገቡት በ1997 ዓ.ም ነበር፡፡ በጊዜው በቦታው አሁን አቤቱታ እያቀረቡ ያሉት አርሶ አደሮች አልነበሩም፡፡ ይዞታው የማንም
አልነበረም፡፡ አካባቢው ላይ ከፀጥታ ጋር ተያይዞ ችግር ስለነበር በጊዜው ልማቱን አቁመው ነበር፡፡ በኋላ በ2000 ዓ.ም ውላቸውን አድሰው አካባቢውን መንጥረው ለልማት ምቹ ካደረጉት በኋላ አንዳንድ ሰዎች በህገወጥ መንገድ አካባቢው ላይ ቤት መስራት እና ማረስ ጀመሩ፡፡
በጊዜው ድርጊቱን የቀበሌ አመራር ከማስቆም ይልቅ የጥቅም ትስስር በመፍጠር ድርጊቱ መቀጠሉን ያመለክታሉ፡፡ እስከ 2005 ዓ.ም ህገወጥ ሰፋሪ የበዛባቸው መሆኑን አመልክተው፤ በውላቸው መሰረት በየዓመቱ 25 በመቶ ማልማት ይጠበቅባቸው እንደነበር፤ ሆኖም ግን በአካባቢው ሰላም እንዳልነበር እና መንግስትም ተገቢውን ጥበቃ ሳያደርግላቸው በመዘግየቱ መሬቱ በህገወጦች ሊከበብ መቻሉን ያስረዳሉ፡፡
በድጋሚ 2005 ዓ.ም ላይ ከዞኑ ጋር ህገወጥ ሰፋሪዎቹን ማስነሳት ከባድ ነው በሚል 152 ሔክታር የነበረው መሬት 39 ሔክታር መሬት ተቀንሶ የአርሶ አደሮቹ ቤታቸው እንዳይነካ መሬት እየተቆረጠ ይሰጣቸው በማለት አዲስ ውል በመግባት ህገወጥ ሰፋሪዎቹ እንዳይጎዱ በሚል በመስማማት ወደ ሥራ መግባታቸውን አቶ ሔርጳ ያስታውሳሉ፡፡
ሆኖም ግን አቤቱታ አቅራቢዎቹ አርሶ አደሮች ቦታውን እንደያዙት እና በኋላ ደግሞ የቀበሌ እና የወረዳ አመራሮች ከእርሳቸውም ሆነ ከአርሶ አደሮቹ ላይ ነጥቀው መሬቱን እራሳቸው ወስደውት እንደነበር ያስረዳሉ፡፡
እንደአቶ ሔርጳ ገለፃ፤ በጊዜው አርሶ አደሮቹ ቦታውን በህገወጥ መንገድ የያዙት በመሆኑ በ2000 ዓ.ም የነበረው ውል ተቀይሮ በ2005 ዓ.ም እንደገና አዲስ ውል ገብተዋል፡፡ 151 ሔክታር የነበረው መሬት ተቀንሶ የተሰጠባቸው ቢሆንም፤ በድጋሚ በካርታው ውስጥ የነበረው ጭራሽ ተቀንሶ በሌሎች መያዝ በመጀመሩ እርሳቸውም ክስ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
በቆሎ እና በርበሬን የመሳሰሉ የግብርና ምርቶችን የሚያለሙት አቶ ሔርጳ እነርሱ በአንድ ጎን ሌሎቹ በአንድ ጎን ሆነው ያለሙ እንደነበር በመጥቀስ፤ መጀመሪያ የባለሃብት ነው ተብሎ ተወስዷል፡፡ ባለሃብቱ ካልወሰደ መሬቱ የሚገባው ለኛ ነው ብለው አርሶ አደሮቹም እየተከራከሩ ነው ይላሉ፡፡
እንደ አቶ ሔርጳ ገለፃ፤ እርሳቸው መሬቱ የእነርሱ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ካርታ አላቸው፡፡ እነርሱ በእጃቸው ካለው ካርታ ባሻገር ዞኑም ሆነ ክልሉ ጉዳዩን የሚያውቀው ነው፡፡ ሆኖም ግን አርሶ አደሮቹ ‹‹መሬቱ ለኛ ይገባል›› እያሉ ነው፡፡ በመሃል ሌሎች እየሰፈሩበት ነው፡፡ የክልል የኢንቨስትመንት ቢሮ ደግሞ ከቀጠሮ ውጪ ምላሽ አልሰጠም፡፡ ቦታው ድረስ በአካል ሄዶ ያየ እና መፍትሔ ያስገኘ አካል የለም ብለዋል፡፡
በእርግጥ መሬቱ ላይ አሁን ደግሞ በድጋሚ ከቀበሌ ጋር በመመሳጠር በመሬቱ ላይ በድጋሚ ሌሎች ሰዎች እየሰፈሩ መሆናቸውን የወረዳዎች እጅም የሚኖርበት ሁኔታ መኖሩን የሚናገሩት አቶ ሔርጳ፤ ይህንን አቤቱታ ለወረዳ እና ለዞን ማቅረባቸውን እና ምለሽ ከመስጠት ይልቅ እንዲሁ ‹‹ቆዩ›› እያሏቸው በመንገላታት ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
አቤቱታ አቅራቢዎቹ ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ ቦታው ላይ ነበርን በሚል ለቀረበው አቤቱታ አቶ ሔርጳ ይህ ፍፁም ከእውነት የራቀ ነው ይላሉ፡፡ እርሳቸው ቦታው ምድረ በዳ ጫካ እንደነበር እና እነርሱ ቦታውን ለልማት ምቹ ሲያደርጉት ከአጎራባች ስልጤ ዞን ሳንቁራ ከሚባል አካባቢ በተለያየ መልኩ ገብተው መያዛቸውን እና አያያዛቸውም በመደበኛ መልክ አለመሆኑን ይናገራሉ፡ ፡ አሁንም በቂ መንደር እንዳላቸው አቶ ሔርጳ ያመለክታሉ፡፡
አመራሩ ጊዜ ስጡን እያለ እነርሱም ጊዜ ለመስጠት ቢሞክሩም አሁንም ህገወጥ ግንባታ መቀጠሉን ይናገራሉ፡፡ ግብር እየገበሩበት ቢሆንም ነገር ግን አሁንም ለሌላ እየተሰጠ ነው ይላሉ፡፡ ቀድሞም ቢሆን የወረዳ እና የቀበሌ አመራሮች የኢንቨስትመንት መሬቱን በሙስና መውሰዳቸው ከተረጋገጠ በኋላ መሬት ባንክ ገባ ተብሏል የሚሉት አቶ ሔርጳ፤ ነገር ግን በህጋዊ መንገድ የተከራዩትን እና ግብር እየከፈሉበት ያለውን መሬት ባንክ ገብቷል ማለት ተገቢ አይደለም በማለት አቤት ቢሉም የሚሰማ ጠፍቷል ይላሉ፡፡ አሁን ላይ ስራ ማቆማቸውን እና ተስፋ ወደ መቁረጥ መድረሳቸውንም ተናግረዋል፡፡
ለክልሉ ለወረዳው እና ለዞኑ ጥያቄውን በማቅረብ ምላሽ እንዲሰጡን በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ክልሉ ጉዳዩን ስለማላውቀው አጣርቼ ምላሽ እሰጣለሁ ብሏል፡፡ ከዛ በኋላ በተደጋጋሚ ብንደውልም የስልካችን ጥሪ ምላሽ አላገኘም፡፡ ለዞን እና ለወረዳ አስተዳዳሪዎች በተደጋጋሚ ብንደውልም በእነርሱ በኩልም የተገኘ ምላሽ አልነበረም፡፡
አቤቱታ አቅራቢዎቹ ግን የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል መንግስት የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ በግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም ለሃላባ ዞን የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ የተላከውን ደብዳቤ አቅርበዋል፡፡ በደብዳቤው የእነከማል አለየ አቤቱታ በሚል የቀረበ ጉዳይ ሲሆን፤ በዞኑ ዌራድጆ ወረዳ በንዶ ቀበሌ 16 የሚደርሱ አርሶ አደሮች ለረዥም ጊዜ በይዞታነት ይዘው ለመንግስት ግብር እየገበሩ ሲጠቀሙበት የቆዩበት መሬት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በኢንደስትሪ ልማት ስም ስለተወሰደባቸው ቤተሰባቸውን ማስተዳደር የተቸገሩ ስለመሆኑ እና በገጠር መሬት የመጠቀም ህገመንግስታዊ መብታቸው ይከበር ዘንድ ጥያቄያቸው መቅረቡ ተመላክቷል፡፡
በዚሁ መሰረት ጉዳዩ እውነትነት ካለው የዜጎችን በገጠር መሬት ይዞታ ህገመንግስታዊ የመጠቀም መብታቸውን ስለሚጋፋ ጉዳዩን ወረዳው አጣርቶ በክልሉ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ መሰረት ምላሽ እንዲሰጣቸው አሳስቧል፡፡
በዚህ በኩል የወረዳ እና የዞን እንዲሁም የክልል አመራሮችን በስልክ ለማግኘት ጥረት ከማድረግ ባሻገር፤ ባለሃብቱም የካርታቸውን ኮፒ እና ግብር የከፈሉበትን ማስረጃ እንዲልኩልን ብንጠይቅም ምንም እንኳ ፈቃደኝነታቸውን ቢናገሩም ይህ ዘገባ ለህትመት እስከገባበት ሰዓት ድረስ ሰነዱን ሳይልኩልን ቀርተዋል፡፡
በአቤቱታ አቅራቢዎቹ በኩል ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ እንዲሁም ሌሎቹም በተለያየ ጊዜ ‹‹ግብር ከፍለናል›› ብለው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ለእርሻ ሥራ መጠቀሚያ ብቻ የተከፈለበት የገቢ ደረሰኝ ቢያቀርቡም የሚገብሩበትን የመሬቱን ስፋት የሚያሳይ አይደለም፡፡
በአጠቃለይ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አርሶ አደሮች ደረሰብን ያሉትን በደል ለማጣራት የአላባ ዞንና ዌራ ድጆ ወረዳን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ በስልክ በተደጋጋሚ አመራሮችን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ስልኮቻቸው ባለመነሳታቸው ሊሳካልንም አልቻለም፡፡ሆኖም በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ አለኝ የሚል አካል ካለ ዝግጅት ክፍላችን ክፍት መሆኑን እንገልጻለን፡፡
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2013