ዶክተር በለጠ ብርሃኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው። ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ በተመሰረተው ብሄራዊ ገለልተኛ የሳይንቲፊክ ቡድን እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ቡድን አስተባባሪ ነበሩ፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የዚሁ ቡድን አባል እንዲሁም በህዳሴ ግድቡ የቴክኒክ ባለሙያ ቡድን አባል ናቸው። ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንዲሁም አሜሪካ ከጣለችው የጉዞ ማዕቀብ ጋር በተያያዘ ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ አድርገዋል። መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡– ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከመነሻው ጀምሮ ላለፉት አስር አመታት ያጋጠሙትን መሰረታዊ ተግዳሮቶች ቢገልጹልን?
ዶክተር በለጠ፡– የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከመጀመሩ በፊት እኤአ በ1964 አካባቢ ጀምሮ በኢትዮጵያ በኩል በርካታ ወደ አምስት ዋና ዋና ግድቦችን በአባይ ወንዝ ላይ ለመስራት ጥናቶች መካሄዳቸው ይታወሳል። አጼ ኃይለስላሴን፣ ግብጾች ከእንግሊዞች ጋር ተባብረን ጣናን መቆጣጠር የምንችለውን ግድብ እንስራ ብለዋቸው ነበር። አጼ ኃይለስላሴም ለምን እናንተ? እኛ እንሰራዋለን በሚል የአሜሪካንን መንግስት እርዳታ ጠይቀው ጥናት እንዲጠና ተደርጓል። በወቅቱ ቦርደር ግድብ የተጠራው ግድብ ነው ዛሬ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ብለን በማጠናቀቅ ላይ ያለነው።
ይህንን ግድብ ለመገደብ ብዙ ተግዳሮቶች አጋጠመውናል። ዋናው ነገር የአቅም ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ እርዳታ አስፈላጊ ነበር። እንደምንም ተብሎ የመሰረተ ድንጋይ ሲቀመጥ የመጀመሪያው ጩኸት የነበረው የታችኛዎቹ ተፋሰስ አገራት የግድቡ መገንባት አስጊ ነው የሚል ነበር። ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት ምላሹ የነበረው የሚያሰጋ አለመሆኑን በየትኛውም ቴክኒካዊ አካሄድ ማየት እንደሚቻል ከመጥቀሱም በተጨማሪ ግብዣም አቀርቦላቸዋል።
ይሁንና በዚህ ምላሽ ሳይረኩ አብረን አላጠናነውም የሚል ጥያቄ ማንሳት ጀመሩ። በዚህም ቢሆን መንግስት የመረጠው እምቢታን ሳይሆን አብረን እናጠናዋለን የሚለውን ነው። ስለዚህ ሶስቱ አገራት ያሉበት ዓለም አቀፍ የጥናት ቡድን ተቋቋመ። ኢትዮጵያ ለቡድኑ አጠቃላይ ከዲዛይኑ ጀምሮ ያለውን ሁሉ አጥንታ ከ153 ገጽ በላይ ጥራዝ ሰነድ ለቡድኑ ሰጠች፤ ከዚህ በኋላ ግድቡ ይጎዳናል የሚለውን ትተው አይጎዳም ወደሚለው መጡ።
ብዙ ሳይቆዩ ደግሞ የግድቡ ቁመት ይጠር ማለት ጀመሩ። ለዚህም የተለያዩ ማስረጃዎች ቀርቦላቸው። በዚህም ግድቡ ቀድመው ከተሰሩ ግድቦች ይልቅ የተሻለ ቴክኖሎጂን የተጠቀመ ነውና የሚያሰጋ ነገር የለውም ሲባል ደግሞ ሌላ ጥያቄ ይዘው መጡ። ግድቡ ሲጠና የአካባቢያዊና የማህበረሰባዊ ተጽዕኖ ግምገማ እንዲሁም የውሃ ፍሰት ጥናት ኢትዮጵያ ብታጠናም እኛ በሰጠነው የመጀመሪያ መረጃ መሰረት ሳይሆን በሁለተኛ መረጃ በመሆኑ ጥናቱ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው በሚል የቴክኒካል ኮሚቴ ተቋቋመ።
በጉዳዩ ዙሪያ ጥናቱን የሚያጠና አማካሪ ለመቅጠር ከዓመት በላይ ጊዜ ወስዷል። እንዲያውም ሆኖ አጥጋቢ የሆነ ሳይሆን የቀደመውን እኤአ በ1959 የተፈራሙትን የግብጽን ውል ያካተተ ነገር ይዞ በመምጣቱ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት አልነበረውም። ምክንያቱም ግብጽ 55 ነጥብ 5 በመቶውን ውሃ ለራሷ፣ 18 ነጥብ 5 ለሱዳን 10 በመቶውን ለአካባቢው በመስጠቷ ሌሎቹን የተፋሰሱ አገሮች ባዶ አስቀርታችሁ የተዋዋላችሁትን ውል በመነሻነት አንጠቀምም ስትል ኢትዮጵያ ሳትቀበለው ቀረች።
ሁሉም ከድርሻው አኳያ ይታይ የሚል ነገር በመቀመጡ ብዙ ክርክር ተፈጠረ። መስማማትም አልተቻለም። ከዚህ ክርክር ውስጥ ነጥሮ የወጣውና በዋናነት የሚያነጋግረው በመሪዎች የተፈረመው የመርህ ስምምነት ነውና በሚያዘን መሰረት የውሃ አያያዝና አለቃቀቅ ላይ እንስራ የሚለውሆነ።
ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ከሶስቱ አገራት አምስት አምስት ባለሙያዎች ያለበት ቡድን ተቋቋመ። በገለልተኛነትም ውሳኔ ሳይሆን አስተያየት እንዲሰጡ ተደረገ። ለዚህም ነው ብሄራዊ ገለልተኛ የሳይንቲፊክ ቡድን የተባለው።
ይህንንም ሐሳብ ያመጣችው ኢትዮጵያ ናት። ይህም ጥሩ የሚባል እምርታ ማሳየት ችሏል። ከነበሩ የድርድር ሂደቶች ውስጥ አንድ የተሻለ ምዕራፍ አመጣ የሚባለው ይኸው ቡድን ነው። እንደውሃው ፍሰትና አቅም በሶስት ዓመት ለመሙላት ነበር የኢትዮጵያ ፍላጎት። የግብጽና ሱዳን ፍላጎት ደግሞ እስከ 11 ዓመት ድረስ እንዲጎተት ነው። ነገር ግን በጣምም ሳይፈጠን እንዲሁም ሳይጎተት ከአራት እስከ ሰባት ዓመት ሊፈጅ በሚችለው ላይ ስምምት ላይ ተደረሰ። ሳይንቲፊክ ቡድኑ ይህን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቀረበ።
እንዲያም ሆኖ ግብጾች ሁሉንም በአሉታዊ ጎኑ የሚያዩ በመሆናቸው አሜሪካ ድረስ ሄደው አቤቱታ አቀረቡ። የተባበሩት መንግስታት ላይ እንዲሁ ጉዳዩን አቀረቡ። በዚህም ኢትዮጵያ ተገቢ ምላሽ ሰጥታለች። በወቅቱ የአሜሪካንን ፕሬዚዳንት አግዙን ተብለው በመጠየቃቸው የአሜሪካንም መንግስት ፍላጎት አሳየ። በመሆኑም የአሜሪካ መንግስት በአገራቱ መካከል ሰላም እንዲፈጠር በሚል ዲፕሎማሲያዊ መንገድ መሄድን አማራጭ አደረገ። ኢትዮጵያም በጎ የሆነ ዲፕሎማሲ ነው በሚል ይህን ጽንሰ ሐሳብ ተቀበለች። ምክንያቱም የግድብ መገንባቷ መብቷ እስከተጠበቀ ድረስ ከማንም ጋር መነጋገር ተጽዕኖ አያመጣም በሚል ነው። ዋናው ትልቁ እና ቀዩ መስመር የውሃ መጠቀም መብቷ ግን መነካት የለበትም የሚለው ነው።
ይህን መሰረት ያደረገ ውይይት በሚካሄድበት ጊዜ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ያሉት ነገር ቢኖር እናንተ ኢትዮጵያውያን በዓለም አንደኛ የሆነ ግድብ በመስራት የቀረውን ልትከለክሉና ልታስጠሙ ነው እንዴ የሚል ነበር። ነገር ግን የኢትዮጵያ ምላሽ የነበረው ግድባችን የሃይድሮፓወር ግድብ መሆኑና ውሃው የኤሌክትሪክ ኃይል ካመነጨ በኋላ ተመልሶ የሚወርድ በመሆኑ የሚከለክል ነገር እንደሌለ የሚገልጽ ነው።
በተጨማሪም ግድቡ በዓለም አንደኛ ሳይሆን በሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ሲለካ ከአፍሪካ አንደኛ ይሆናል እንጂ እንዲያውም የግብጾች አስዋን ግድብ በመጠን ከእኛ ይበልጣል የሚል ነው። ፕሬዚዳንቱ ይህን ከሰሙ በኋላ መለስ ብለው የሃይድሮፓወር ግድብ ከሆነማ ጥሩ ነው፤ ግድቡ ሲጠናቀቅ መጥቼ ሪቫን እቆርጣለሁ ነበር ያሉት።
በኋላ ላይ ግን ሂደታችሁን በታዛቢነት እንመልከት ወደሚለው ተመጣ፤ አስታራቂነትና ሸምጋይነት ነገር ከሌለው መልካም ነው ስትል ኢትዮጵያ ተቀበለች። ወደ አራት ስብሰባዎችን ባደረግንባቸው ወቅት እነሱ ፖለቲካዊ ለማድረግ በማሰባቸው ቴክኒካዊ የሆኑ አጀንዳዎችን ሁሉ አፈረሷቸው። በመጨረሻም እኤአ 2020 ጥር ላይ አካሄዳቸው ተገቢ አለመሆኑን ለመግለጽ ሞከርን። እናመቻች የሚለውን ነገርም እንደማንቀበልና በታዛቢነት ብቻ የምንቀበል በመሆናችን በታዛቢነታችሁ መቀጠል ትችላላችሁ አልናቸው። ነገር ግን እነርሱም መልሰው ሳትስማሙ መስራት አትችሉም ወደሚለው በማቅናታቸው ከአሜሪካ ጋር አለመግባባት ሊፈጠር ችሏል።
የኮሮና ጉዳይ በመምጣቱና ጉዞም ማድረግ ባለመቻሉ ውይይቶች ለተወሰነ ጊዜ ተቋረጡ። በተጀመረም ጊዜ አሜሪካንን ጨምሮ ደቡብ አፍሪካና የአውሮፓ ህብረት በታዛቢነት እንዲገቡ ተደረገ። የሚያሳዝነው ነገር የሱዳን አቋም መለዋወጥ መጀመሩ ነው። የተለያየ ምክንያት እያመጣች ውይይቱን ማቋረጥ ጀመረች። የማቋረጧም ምስጢር በጉዳዩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሬን ላማክር የሚል ቢሆንም አማክራ ትመጣለች እያለን በመጠባበቅ ላይ ሳለን ነው ሌላ ደብዳቤ ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ጻፈች። የተባሩት መንግስታት ደግሞ የሰጠው ምላሽ የአፍሪካ ህብረት ይቀጥልበት የሚል ነበር።
እንዲያም ሆኖ እኛ በተገኘው ስብሰባ ሁሉ እንል የነበረው አንደኛውን ዙር ውሃ እንሞላለን የሚል ነው። በዚህም ሳንሰማ ነው የተሞላውና ተጎድተናል የሚል አቤቱታ ሲያሰሙ ነበር። በመሆኑም ድርድር አቆሙ። ድርድሩ በሰባት ወር ውስጥ ሰባት ጊዜ ተቋረጠ።
በቅርቡ ደግሞ ከጥር በኋላ የአፍሪካ ህብረት ከደቡብ አፍሪካ ወደ ዴሞክራቲክ ኮንጎው የሊቀመንበርነቱ ተራ ሽግግር ነበርና የዴሞክራቲክ ኮንጎው ሊቀመንበር ጉዳዩን በአግባቡ አጥንተው ግንዛቤ እስኪወስዱ ጊዜ ወሰደ። ውይይቱ ከቆይታ በኋላ ኪንሻሳ ላይ የተጠራ ቢሆንም ረብ ያለው አልነበረም። በመሃል ግን ኢትዮጵያ የማትስማማበትን ነገር ይዘው መጡ። ኢትዮጵያ ሽምግልና እርቅ የሚባል ነገር ውስጥ መግባት እንደማትፈልግ ደጋግማ አስታውቃለች።
ኪኒሻሳ ላይ ስንሄድም ውይይቱን የበጠበጠው ይኸው ሐሳብ ነበር። እንዲያም ሆኑ የዴሞክራቲክ ኮንጎው ሊቀመንበር ወደ ሶስቱም አገሮች በመንቀሳቀስ ሐሳብ እንዲንሸራሸር አድርገዋል። በቀጣይም ለውይይት ይጠራሉ የሚል ግምት አለን።
አዲስ ዘመን፡– ግድቡ በቀጣዩ ሐምሌ ወር ውስጥ ሁለተኛው ዙር ውሃ እንደሚሞላ በመንግስት በኩል ቁርጠኝነቱ መኖሩ ይታወቃል፤ ግብጽ ደግሞ ከቀናት በፊት ባወጣችው መረጃ ሙሌቱ ያለድርድር እንደማይሆን እየገለጸች ነውና መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ?
ዶክተር በለጠ፡– በመሰረቱ ድርድሩና ሙሌቱ አይገናኙም። የተለያዩ አካሄዶች ናቸው። ሙሌቱ የሚከተለው ኮንስትራክሽኑን ነው። እነሱ ራሳቸው የሁለቱንም ልዩነቶች ብቻ ሳይሆን ሙሌቱ ምንን ተከትለው እንደሚከናወን አሳምረው ያውቃሉ። ለምሳሌ 4 ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የመጀመሪያ ሙሌት ሲሆን፣ ተርባይኖችን ከመግጠም ጋር እንዲሁም ቀጥሎ 13 ነጥብ 5 ቢሊዮኑ ከፍ ያለው ሁለተኛው ዙር ሙሌት ነው ፣ ሌሎችን 11 ተርባይኖች ከመግጠም ጋር ተያይዞ የሚመጣ ነው። ይህ ከግንባታው ጋር ተያይዞ የሚካሄድ ነው። በመሆኑም ድርድሩ ተፈረመም አልተፈረመም ሙሌቱ ግንባታውን ጠብቆ የሚሄድ ነው። እነሱ ግን ይህን ስለሚያውቁት ላለመቀበል ጉዳዩን ያስጮሁታል።
ግብጾች የአስዋንን ግድብ ሲገነቡ ምንም መረጃ ለማንም አልሰጡም፤ እኤአ የ1959ኙን ውል ሲዋዋሉ አላማከሩም፤ ሮዛሪስ የሚባለውን ግድብ ሱዳኖች እንዲገነቡ ነው የፈቀዱላቸው። ይህን ሁሉ ሲያደርጉ ኢትዮጵያንና ሌሎቹን ቀሪ አገሮች አላወያዩም። ውሃውን ከአስዋን አውጥተው ቶሺካ ወደሚባል ከተፋሰሱ ውጭ ወዳለ ካናል ሲዘረጉ ማንንም አላማከሩም።
ኢትዮጵያ ግን የመሰረት ድንጋይ ከተጣለ ጀምሮ ስራዋን የጀመረችው ኑና እዩ በሚል ነው። በእርግጥ ይህ ሁሉ ግዴታዋ አልነበረም። ነገር ግን ከእናንተ ጋር የሙሌት ስርዓቱን እናውጣ ማለቷ ትብብር ነው። በእርግጥ የቴክኒካል ባለሙያዎቹ ይግባባሉ። እነሱ ግን ነገሩ ወደፖለቲካው ስለሚወስዱት ነው የሚያስቸግረው።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የውሃ ሙሌቱ የሚጎዳን አይደለም ማለታቸው የሚታወቅ ነው፤ ይህን ማለታቸው እንደማይጎዳቸው ስለሚያቁም ጭምር ነው። ምክንያቱም የቴክኒክ ስራው ምንም አይነት ጉዳት እንደማያደርስባቸው ጠንቅቀው ያውቁታል። ራሱ የአሁኑ የሱዳን የውሃ ሀብትና የመስኖ ልማት ሚኒስትር ይህን ቀመር በወቅቱ ስንቀምር አንዱ የባለሙያዎች ቡድን አባል የነበሩ ናቸው። ስለሆነም ጉዳዩን አሳምረው ያውቁታል። የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት እንደማይጎዳቸው፤ እንዳልጎዳቸውም ያውቁታል። ይሁንና የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎችን በማምጣት ተጎዳን ሲሉ እንደነበር የሚታወስ ነው።
እነሱ የሚፈልጉት ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ራሷን በራሷ ወደፊት ማልማት እንዳትችል የሚከለክል ህግ በዚህ አጋጣሚ መያዝ ነው። እኛ ደግሞ እያልን ያለነው የምንስማማው በግድቡ የውሃ ሙሌት ላይ ብቻ ነው የሚል ነው። የኢትዮጵያ የውሃ መጠቀም መብቷ መታየት አለበት። ይህን ጉዳይ መሰረት አድርገን ነው ሌላ ህግ ውስጥ መግባት የምንችለው እያልን ነው። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በጥሩ ሁኔታ እየተጓዘች ነው ። የግድቡን ሁለተኛ ዙር ውሃ ለመሙላት ያለው የአየር ጸባይም ጥሩ የሚባል ነው። የዚያን ያህል የውሃ እጥረት አይኖርም።
አዲስ ዘመን፡– ግብጽ አንዴ የህዳሴው ግድብ ሁለተኛው ዙር ውሃ ቢሞላ ብዙም የሚጎዳን አይደለም ስትል ነበር፤ ይህ ሐሳብ ተሽሮ ደግሞ ያለድርድር አይሆንም ማለት መጀመሯም ተደምጧልና ይህ አቋሟ የግብጽን ግራ መጋባት ወይስ ኢትዮጵያን ግራማጋባት መፈለጓን ነው የሚያሳየው?
ዶክተር በለጠ፡– በመሰረቱ ሁለቱም ነው ማለት ይቻላል። አንደኛ መነሻው የእነርሱ ግራ መጋባትን የሚያሳይ ነው። ሁሌም የግብጽ ችግር በውስጣቸው ያለውን ውጥረት ትተው ወደዓለም አቀፉ ሲያተኩሩ የሚመጣባቸው ችግር ነው። ሁሌም አጀንዳ አድርገው ማቅረብ የሚችሉት የአባይን ጉዳይ ነው። ግብጾች የአባይን ጉዳይ ካላራገቡ በዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ዘንድ እንረሳለን የሚል ስጋት አላቸው።
የፍልስጤምና የእስራኤል ጉዳይ ውስጥ መግባት በመፈለጋቸው የናይልን ጉዳይ በትንሹም ቢሆን ተወት አድርገውት ነበር። ለዚህም ነበር የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለፓርላማው የሁለተኛው ዙር ውሃ ቢሞላም ብዙ ጉዳት አይኖረውም ሲሉ የገለጹት።
ቀደም ሲል ግብጽ ለህዝቡ ታቀርብ የነበረው ትርክት የናይል ውሃ ባለቤት የግብጽ ህዝብ እንደሆነ ነው። ፖለቲካቸውም የሚመሰረተው በዚህ ጉዳይ ነው። በየጊዜው የሚመጡ መሪዎቻቸው የመጀመሪያቸው ነገር የናይል ውሃን መብት ማስከበር መሆኑን እንደሚናገሩ ሁሉ አልሲሲም ያሉት የናይልን ነገር አስከብራለሁ በሚል ነው ስልጣናቸውን የተቆናጠጡት። በመሆኑም ከዚህም የተነሳ ነው ውስጣዊና ውጫዊ ግራ መጋባት የሚያጠቃቸው።
ልክ ይህንን ይዘው ጉዳዩን ወደእኛ ሲያመጡት ደግሞ እኛ በነገሮች ሁሉ እንድንጨነቅ ይፈልጋሉ። በእርግጥ እኔ አንድ የማምነው ነገር አለ፤ ግብጾች መቼም ቢሆን አደጋ አያደርሱብንም የሚል ነው፤ ወደጦርነትም መግባት አይፈልጉም የሚል አተያይ አለኝ። ምክንያቱም ግድቡ በአንድም ሆነ በሌላ እንደሚጠቅማቸው ያውቁታል። ስለዚህም ግድቡ ላይ ጥቃት ማድረስ አይፈልጉም። ነገር ግን ማጥቃት የሚፍልጉት ግድቡን ሳይሆን ስነ ልቦናችንን ነው። ወታደራዊ ጦርነት ውስጥ የሚገቡት የማህበረሰቡን ስነ ልቦና ለማስጨነቅ ነው። በመሆኑም የእነሱ ፍላጎት እኛ በስነ ልቦናችን ላይ ጫና በመፍጠር ግራ እንድንጋባ ነው። ለዚህም ነው የተለያዩ አጀንዳዎችን በመፍጠር ስነ ልቦናችን ላይ ጫና ለመፍጠር የሚጥሩት።
አዲስ ዘመን፡– በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ እየተደረገ ያለው ጫና ከሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በኋላ ምን ሊሆን ይችላል ተብሎ ይታሰባል?
ዶክተር በለጠ፡– ኢትዮጵያ ግድቧን እንዳትሞላ እንቅፋት የሚሆናት የውጭ ጉዳይ ብዙም የለም፤ ምናልባት የውስጣችን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር። የውስጣችን ሰላም የሚደፈርስ ከሆነ ለስራችን እንቅፋት ሊሆን ይችላል። እንደዛ እንዳይሆን ደግሞ ሁላችንም ለውስጣችን ሰላም መሆን ቅድሚያ መስጠት ብልህነት ነው የሚመስለኝ። እስካሁን ባለን ቅድመ ትንበያ ግድቡን ለመሙላት ወቅቱ ጥሩ ነው። የክረምቱ ወቅት ከሚጠበቀው በላይ ነው። ውሃ የማግኘት ሁኔታው ስጋት የለበትም። ይህ ከሆነ ደግሞ ሊያዘገየን የሚችል ነገር አይኖርም። ነገር ግን የውስጥ ሰላማችንን መጠበቅ የግድ ነው። ስለአባይ ስንል ጭምር የውስጥ ሰላማችንን አክብረን ብንጓዝ መልካም ነው የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡– ስለታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድር ጉዳይ ሲነሳ ስማቸው የሚነሳው የሶስቱ አገራት ብቻ ናቸው፤ ነገር ግን የአባይ ተፋሰስ አገራት 11 ናቸው፤ ለመሆኑ የነዚህ አገራት ሚና ምን መሆን አለበት ይላሉ?
ዶክተር በለጠ፡– በመሰረቱ ጥያቄው ልክ ነው፤ ምክንያቱም አንድም እየጠየቅን ያለነው ነገር ይህንኑ ነው። በውሃ አጠቃቀም ጉዳይ ከሆነ የምንደራደረው ከእኛ ጋር ብቻ አይደለም ድርድሩ መሆን ያለበት ከ11ዱም የተፋሰሱ ሀገራት መካከል ነው። ጉዳዩ ውሃ መልቀቅና መሙላትን ከሆነ የሚመለከተው ሶስታችን ስለሆንን በሱ ጉዳይ ላይ ብቻ መነጋገር እንችላለን የሚል ነው። እነርሱም ማለትም 11ዱ አገራት እስካሁን ዝም ያሉት ውሃ በመልቀቅና በመሙላት ላይ ነው የሚነጋገሩት በሚል ነው። ወደ ውሃ አጠቃቀምና ክፍፍል የሚመጣ ከሆነ ግን እነሱንም የሚመለከት ጉዳይ ነው። የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን ደቡብ ሱዳን በወቅቱ ስላልነበረች ሳትፈርም ብትዘገይም አሁን ግን እፈርማለሁም፤ አጸድቃለሁ ብላለች።
ኢትዮጵያ ሁሌም ቢሆን ማንንም መጎዳት አትሻም፤ መርህ አድርጋ እየተንቀሳቀሰች ያለውም አብረን መልማት አለብን በሚል ነው። ከዚህም የተነሳ በቅርቡ እንኳ ችግኝ በማፍላት ጎረቤት አገሮችንም ጭምር በማንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያ እንደ ላይኛዎቹ ተፋሰስ አገራት ይህን ማድረግ ብዙም አይጠበቅባትም ነበር። ኢትዮጵያ በተሻጋሪ ወንዞቿ ከጂቡቲና ኤርትራ ካልሆነ በስተቀር ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር ትገናኛለች። እንዲህ ሆና እንኳ ብቻዬን ልልማ እያለች አይደለም። በሁሉም ወንዞች ስንመለከት ከፍተኛውን አበርክቶ ያላት ኢትዮጵያ ናት። አገራችን ፐብሊክ ዲፕሎማሲውን በመስራት አኳያ ውጤታማ ናት ማለት ይቻላል። ባለፈው ጊዜ ዑጋንዳ የትብብር ማዕቀፉን ማጽደቋን ተከትሎ የፐብሊክ ዲፕሎማሲው ሄዶ ምስጋናውን አቅርቧል።
አዲስ ዘመን፡– ግብጽ አሁን አሁን ወደ ድርድር መግባትን የፈለገች ትመስላለች ቀደም ሲል እያሳየችው ከነበረው ባህሪ አንጻር ሲታይ ይህ ጤናማ አካሄድ ነው ብለው ያስባሉ?
ዶክተር በለጠ፡– ሁሉንም ጤናማ ነው ብለን አናስብም፤ ወደጤናማው አካሄድ መምጣት ከቻሉ እና የላይኛዎቹን አገሮች የመጠቀም መብት ያከበረ ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ ከሆኑ ምንም ችግር የለውም። በመልካምነት ከመጡ እሰየው ነው።
የግብጽ መቀያየር የሚያሳድረው ተጽዕኖ የዚያን ያህል ነው። በግድቡ ላይ ብዙ የተለየ ተጽዕኖ አያመጣም። በውሃ ግድብ ላይ እንደሚሰራ አንድ ባለሙያ ይህን የግብጽን መቀያየር እንደ ጥሩ አጋጣሚ ነው የምመለከተው። ምክንያት ብትይኝ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ለአባይ ውሃ ያለውን ትኩረትና ግንዛቤ ከፍ እንዲል በማድረጉ ነው። ስለዚህ በህዳሴ ግድብ ላይ ብቻ ተንጠልጥለን የምንቀር ሳንሆን ሌላም ግድብ የመስራት ተነሳሽነትን መፍጠር ይችላል። እነሱ ምንም እንኳ የስነ ልቦና ጫና ለማሳደር ቢሞክሩም ኢትዮጵያውያኑ ግን የእንችላለንን መንፈስ እንዲያሳድጉ አድርጓቸዋል የሚል አተያይ አለኝ። በእርግጥ አንድ ቦታ ላይ እኛ ደካማ ነን ብዬ አስባለሁ። ይኸውም ያለንን እውቀት በአግባቡ አልሸጥንም የሚል ነው። አስሮ የያዘን ባህላችን ሳይሆን አይቀርምና እንዲህ ነን ለማለት ብዙ ርቀት መሄድ እንቸገራለን። እነሱ ደግሞ በዚህ እንዲጠቀሙበት እድል ሰጥቷቸዋል። እንዲያም ሆኖ ግብጽ የትኛውንም አይነት ወታደራዊ ስምምነት ከፈለገችው አገር ጋር ብታደርግ በዚህ ጉዳይ የስነ ልቦና ጫና ሊያድርብንም አይገባም።
አዲስ ዘመን፡– በኢትዮጵያ መንግስት በኩል በቀጣይ መቶ ግድብ እንገድባለን መባሉን ተከትሎ ግብጽንና ሱዳንን የዚያ ያህል ያነጋገረበት ዋና ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ?
ዶክተር በለጠ፡– እኛ እኮ በመርሆዎቹ ስምምነት ላይ የተስማማነው በውሃ መልቀቅና መሙላት ስርዓት ላይ እንግባባለን በሚል ነው። እነሱ ግን የሚፈልጉት በዚህ ግድብ አማካይነት ኢትዮጵያ ወደፊት የምታለማውን ነገር መቆጣጠር ነው። ከዚህም የተነሳ ነው በእያንዳንዱ ድርድርና ውይይት ጊዜ አሳሪ ህግ እንዲሆንላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የሚያሳድሩት። ለዚህም ነው ገና መቶ ግድብ እንገድባለን የሚለው ሐሳብ ያስበረገጋቸው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ እንዳትጠቀም እና ታስራ እንድትቀመጥ ነው የሚፈልጉት። እኛ ደግሞ መበርታትም ያለብን እዚህ ላይ ነው። ኢትዮጵያውያን በጠነከርን ቁጥር ግብጾች እየተረበሹ ይመጣሉ።
አዲስ ዘመን፡– አሜሪካውያኑ በኢትዮጵያ ላይ የጉዞ ማዕቀብ መጣላቸው ግልጽ ነው፤ ይህ በህዳሴ ግድቡ ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ይኖር ይሆን?
ዶክተር በለጠ፡– በቀጥታ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚያመጣ ተጽዕኖ ላይኖር ይችላል። ነገር ግን ድርድሩ በአንድም ሆነ በሌላ የተለያየ ቦታ ላይ ይሄዳል። ስለሆነም ኃላፊዎች በነጻነት ሄደው የማይደራደሩ ሲሆን በተወሰነ መልኩ በስሜት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል ። ከዚህ ባሻገር ጉዳዩ ዓለም አቀፋዊ በመሆኑ ሌሎቹ ላይ ጫና ሊፈጥር ይችላል። በተለይ ደግሞ ዘርፈ ብዙ የሆኑ በህዳሴ ግድቡ ላይ የሚሳተፉ በከፊል የአሜሪካ ድርሻ ያለባቸው የጀርመን ኩባንያዎች ላይ ትንሽ ስጋት ሊያድርባቸው ይችል ይሆናል። ከጥቅማቸው አኳያ በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲሻክር አይፈልጉ ይሆናል እንጂ አሜሪካ የጉዞ ማዕቀብ መጣሏ በህዳሴ ግድቡ ላይ በቀጥታ የሚፈጥረው ተጽዕኖ አይኖረውም።
አዲስ ዘመን፡– አሁን አሁን ኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለ የምዕራባውያኑም ሆነ የአሜሪካ ጫና ምንን ያመላክታል?
ዶክተር በለጠ፡– እንደእኔ የየራሳቸው ፍላጎት ስለሚኖር ነው ብዬ አምናለሁ። ከዚህ በተጨማሪ ያለንበት ቀጣና በዓለም አቀፉ ዘንድ ትኩረት የሚጣልበት ማዕከል ነው። በመሆኑም የተለያየ ፍላጎት ያለበት ነው። ሌላው ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ፕሮጀክቶቻቸውን እየሰሩ ያሉት ከቻይና ጋር ነው። እንደሱ መሆኑ ደግሞ አሜሪካውያኑንና ምዕራባውያኑን አያስደስታቸውም። ስለሆነም አገራቱ ከእነሱ ጋር እንዲሰሩ ይፈልጋሉ።
ቀደም ሲል እንደሚታወቀው አሜሪካውያኑ ከሌሎቹ ጋር የነበራቸው ውጥረት የርዕዮተ ዓለም ነበር፣ አሁን ደግሞ የኢኮኖሚ ሆኗል። ትልቁ የኢኮኖሚ ውጥረት እየተባባሰ ያለው በአሜሪካና በቻይና መካከል እየሆነ ነው። እነሱ በዚህ ጉዳይ እስካልተናበቡ ድረስ አፍሪካ አገሮች ላይ ጫና እያሳደሩ መሄዳቸው አይቀርም። ሌላዋ ግብጽ ደግሞ በየሄደችበት አገር የናይል ጉዳይ እያለች መወትወቷ ስለማይቀር ለምንድን ነው ይህ ጉዳይ የማይቋጨው ወደሚለው ስለሚሄዱም ጭምር ነው በእኛ ላይ ጫናውን የሚያሳድሩት።
አዲስ ዘመን፡– አሜሪካ ከጣለችው ማዕቀብ ጋር ተያይዞ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሊፈጠር የሚችል ችግር ይኖራል ተብሎ ይታሰብ ይሆን?
ዶክተር በለጠ፡– በእርግጥ አሁን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ወሳኝ ማዕከል ነው። በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ካሉት አገሮች መካከል ትልቅ አቅም ያላት እንደመሆኗ ኢትዮጵያ ላይ ጫና መደረግ ሲጀምር ሌሎቹ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ስጋት ሊያድርባቸው ይችላል። ከዚህ ባለፈ ደግሞ የትኛውም አገር ቢሆን ራሷን ኃያል ነኝ ከምትልና እንደኃያል ከምትቆጠር አገር ጋር ተጣልቶ መኖር አይፈልግም። የኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ቢገደብ ለምሳሌ ጎረቤት አገር ከሆኑ የጂቡቲ አገር ኢኮኖሚ ይጎዳል። በተጨማሪም የደህንነት ነገር ያሰጋቸዋል።
ሌላው ቢቀር ቀጣናው ላይ ችግር ቢኖርና ሰዎች ስደተኛ ቢሆኑ ይህ ሁሉ የት ነው የሚሰደደው። የሚሰደደው በጎረቤት አገሮች እንደመሆኑ ለእነሱ ይህም ስጋት ሊሆን ይችላልና በቀጣናው ስጋት ይፈጠራል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በቀጣናው ላይ ተፈላጊና ጠቃሚ ሚና ያላት አገር ናት። ይህ በመሆኑም በቀጣናው ያሉ አገራት ኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለው ጫና አግባብ አይደለምና ነጻ መሆን አለባት ብለው ዓለም አቀፉን ማህበረስ ሊጠይቁ ይገባል። ምክንያቱም እነሱም ተጠቃሚ የሚሆኑት ከአካባቢያቸው ደህንነት ነው። ከቀጣናው አገራት ጋር ማህበረሰባዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸው ጥብቅ ነው። እነሱ ዘንድ አንዳች ችግር ቢፈጠር በመጀመሪያ የሚሰደዱት አውሮፓ ሳይሆን እኛ ዘንድ ነው ብለው ያስባሉ።
በነገራችን ላይ ግብጽ የምትጠቀምበት ስትራቴጂ አንዱ ይህ ነው፤ ህዝቤ በቁጥር ብዙ ነውና ቢራብ ወይም በደህንነቱ ላይ አደጋ ቢጋረጥበት ተሰዶ የሚመጣው በአቅራቢያዬ ባሉ አውሮፓ አገራት ነው ትላለች። ወደ እናንተ ቢሰደድ ደግሞ የሚጎዳው የእናንተኑ ኢኮኖሚ ነው። ጠብታ ውሃ ቢቋረጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ከስራ ውጭ ይሆናል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ሁሉም ወደአውሮፓ አገር ይሰደዳል ነው የምትለው። ስለዚህ ልክ እንደእሷ ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ ያለው ጫና ለሱዳንም፣ ለሱማሊያም፣ ለጅቡቲም ሆነ ለኬንያ፣ ለኤርትራና ለደቡብ ሱዳንም ጭምር ጫና ነው። ስለዚህ እነዚህ አገራት በአንድነት ድምጻቸውን ማሰማት አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡– ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ መከተል ያለብን ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ምን መሆን አለበት ይላሉ?
ዶክተር በለጠ፡– እንደ እኔ ከዚህ ትንሽ ከፍ ማለት አለበት ባይ ነኝ። በእርግጥ ኢትዮጵያ የያዘችው መርህ ትክክል ነው። ነገር ግን መርሁውን የምንግባባበት ምጣኔ አናሳ ነው ባይ ነኝ። ለህዝባችንም ሆነ ለዲያስፖራው እንዲሁም ለዓለም አቀፉ ማህብረሰብ የያዝነው መርህ ተገቢ መሆኑን፣ ላለንበትም ቀጣና ጠቃሚነቱን፣ ዓላማችን ለብቻችን መልማት ሳይሆን ለሌሎቹም ጭምር መሆኑን በአግባቡ ማሳወቅ መቻል ይጠበቅብናል። ሌላው ቀርቶ ሱዳንንና ግብጽንም ከመጥቀም አንጻር እየሰራን ስለመሆናችን ማሳወቅ ይጠበቅብናል።
አብዛኛውን ጊዜ ግን የእኛ ዲፕሎማሲ የተንጠለጠለው በጊዜያዊ ስሜት ላይ ነው። አጀንዳው ሲግል ሁላችንም እንግላለን። ሲቀዘቅዝ ደግሞ እንቀዘቅዛለን። እንዲህ አይነቱ አካሄድ ደግሞ አጀንዳ የምንሰጣቸው እኛ ሳንሆን እነሱ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። ዲፕሎማሲያችን እኛ አጀንዳ እየሰጠን እንድንሄድ ማድረግ አለበት። አሁን ግን እየተጀማመሩ ያሉ ነገሮች ግን ጥሩ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡኝ ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር በለጠ፡– እኔም አመሰግናለሁ። ሚዲያው በዚህ ጉዳይ ደጋግሞ መስራት ይጠበቅበታል።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2013