የዛሬው የፍረዱኝ አምዳችን ወደ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳዳር ቀበሌ 02 ነዋሪ ይዞን ይጓዛል:: ‹‹ ከነባር ቦታችን ላይ የመሬት የካሣ ክፍያ ተከፍሎን እንድንነሳ ከተደረገ በኋላ በከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት በተወሰነልን የካሳ ክፍያ መሠረት አብረውኝ ለነበሩት ስምንት ተነሺዎች የካሣ ክፍያ ሲከፈልላቸው ለእኔ ብቻ እንዳይከፈለኝ ተከልክያለሁ:: እስካሁን ያፈራሁት ንብረትና የሥራ መሣሪያ ተቃጥሎብኛል፤ የካሣ ክፍያው የቀበሌው አስተዳዳር እንዳይከፈለኝ በማድረጉ ምክንያት አንዳችም ነገር ሳልይዝ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ተዳርጌያለሁ›› በማለት ህዝብና መንግሥት ይፍረዱኝ ሲሉ ለዝግጅት ክፍላችን አቤቱታ ያቀረቡ ባለጉዳይ ቅሬታ ይመለከታል። ዝግጅት ክፍሉም ፍርዱን ለእናንተው በመተው፤ የቅሬታ አቅራቢዎቹን እሮሮና ምሬት በመመርመር የሚመለከታቸውን አካላት ምላሽ አካትቶ ያዘጋጀውን ጽሁፍ እንደሚከተለው ልናስቃኛችሁ ወደደን ።
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳዳር ቀበሌ 02 ነዋሪ የሆኑት አቶ አቤሴሎም ነጋሽ ለ33 ዓመታት በቀበሌው ለዶሮ እርባታ ተብሎ በተሰጣቸው ህጋዊ ቦታ ላይ ይኖሩ ነበር:: የድሬዳዋ ከተማ አስተዳዳር መሬትና ልማት ቢሮ በ1980 ዓ.ም ለዶሮ እርባታ የሚሆን ቦታ እንዲሰጣቸው በጠየቁት መሠረት ግምቱ 2500 /ሁለት ሺህ አምስት መቶ/ ካሬ ሜትር ቦታ ህጋዊ በሆነ መንገድ የተፈቀደላቸው መሆኑን ይገልፃሉ:: የተሰጣቸውን የቦታው ፕላን መሠረት በማድረግ ተገቢውን ግብር እየከፈሉ የዶሮ እርባታ ሥራቸውን አስፋፍተውና አጠናክረው እየስሩ እንደነበር ጠቅሰው፤ ሆኖም ግን የዶሮ እርባታና የእርሻ ቦታቸው ላይ በርካታ ተክሎችን በመተከል በርካታ ሥራዎችን እየሥሩ በነበሩበት ወቅት ያላሰቡትና ያላለሙት ጉዳይ እንደገጠማቸው ያወጋሉ::
አቶ አቤሴሎም ስለ ገጠማቸው ጉዳይ ሲያስረዱ በእሳቸው ነባር ይዞታ አቅራቢያ በ1995 ዓ.ም የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን ይቋቋማል:: የቤተክርስቲያኗን መቋቋምን ተከትሎ ቤተክርሰቲያኗ በጠየቀችው መሰረት ማስፋፊያ ቦታ ምክንያት አካባቢው ላይ የነበሩት ሰዎች እንዲነሱ ተደርጓል:: አቶ አቤሴሎም እንደሚሉት በዚህም መሠረት እሳቸውን ጨምሮ በአካባቢ ላይ የሚኖሩ ዘጠኝ ተነሺዎች ከቦታው ላይ እንዲነሱ ይወሰናል:: እነዚህ ተነሺዎች ከቤተክርስቲያን ምስረታ በፊት የነበሩ በመሆናቸው፤ ከቦታቸው ላይ ሲነሱ ምትክ መሬትና የካሳ ክፍያ ማግኘት ይገባቸዋል ሲል የድሬዳዋ ከተማ አስተዳዳር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ውሳኔ ያስተላልፋል::
የከተማዋ ከንቲባ ጽህፈት ቤት መጋቢት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ለአንድ ማህበርና ለስምንቱ ተነሺዎች ያስተላለፈው ውሳኔ በመልካ ጀብዱ በሚገኘው ቦታ ለግለሰቦቹ የመኖሪያ ቦታ የሚሆን ለእያንዳንዳቸው 160 ካሬ የሆነ ምትክ ቦታና የካሳ ክፍያ ህጉ በሚፈቅደው መሠረት በሁለት ሳምንት ውስጥ በአስቸኳይ እንዲሰጣቸው የሚል እንደነበርም ያወጋሉ:: ‹‹በጽህፈት ቤቱ የተወሰነው ምትክ ቦታና የካሳ ክፍያ ከእኔ ነባር ይዞታ ጋር ምንም እንኳን ባይመጣጠንም ቦታው የተለቀቀው ለእምነት ቦታ መሆኑን አክብሬ የተወሰነልኝ ምትክ ቦታና የካሳ ክፍያ አሜን ብዬ ለመቀበል አላመነታሁም ነበር›› የሚሉት አቶ አቤሴሎም ይህም በመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመሬትልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ባለሙያዎች በቦታው ላይ የሚገኘውን ንብረት በመመልከትና በማጣራት ካሳ ግምት መገመታቸውን አመልክተዋል:: ባለሙያዎቹ የካሳ ክፍያ ግምት ብለው ያስቀመጡላቸው ብር የሚያንሳቸው መሆኑን በመግለጽ ቅሬታ አቅርበው በቅሬታቸው መሠረት እንደገና እንዲታይላቸው ይደረጋል:: እንደገና ታይቶ እንዲገመላቸው በተደረገው መሠረት የተገመተላቸውን የካሳ ግምት ተስማምተው መቀበላቸውን ይገልፃሉ::
በመጀመሪያ የካሳ ግምት መሬቱ ላይ ያለው ንብረት ና ሀብትን መሠረት በማድረግ የተገመተው ሲሆን የተሰጠው የካሣ ግምት ብር አንድ መቶ ስልሳ ሰባት ሺህ ስድስት መቶ አራት ብር ከ74/100 ሳንቲም የነበረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባቀረቡት ይስተካከልልኝ ጥያቄ መሠረት በድጋሜ ታይቶ የተስተካካለው ግምት መጠን አንድ መቶ ዘጠና ሶስት ሺህ አራት መቶ ስልሳ ሁለት ብር ከ67/100 ሆኖ የተሰተካካለ መሆኑን ያስረዳሉ:፡
ይህ የካሳ ግምት ከተሰጣቸው በኋላ የመሬት ማኔጀመንት አስፈላጊውን ማጣራት ካደረገ በኋላ ወደ ቀበሌ እንደላካቸው ይናገራሉ:: ይሁን እንጂ የተመራላቸውን ደብዳቤ ለቀበሌው ከሰጡ በኋላ የቀበሌ አስተዳዳርና አንዳንድ ሰዎች አንድ ላይ በመመሳጠር ለዶሮ እርባታ ተብሎ በተሰጣቸው መሬት ላይ የነበረውን የዶሮ እርባታ ቦታ አፍርሰው ፣ ዶሮዎቹን ገድለው፤ ለሥራ የሚጠቀሙባቸውን መሳሪያዎች በማውደም ቤታቸውን ማቃጠላቸውን እና እሳቸው ላይ ዛቻና የተለያዩ ማስፈራሪያ በማድረግ ህይወታቸው ስጋት ላይ በመጣላቸው ምክንያት ለህይወታቸው ስለፈሩ መሸሻቸውን ይገልፃሉ::
‹‹በህጋዊ መንገድ ተመርቼ የተሰጠኝንና ከ30 ዓመት በላይ የኖርኩበትን ቦታ በእነዚህ ህገወጦች በመውደሙ ምክንያት ለኢኮኖሚያዊ ኪሳራ በመዳረግና የሞራል ውድቀት ደርሶብኝ ለነፍስ ያሉ ሰዎች አሰጠግተውኝ ነው እየኖርኩ ያለሁት›› ያሉት አቶ አቤሴሎም፤ ‹‹በእነዚህ ሁሉ ዓመታት በጉብዝናዬ ወቅት ሩጬ ተሯሩጩ ያፈራሁትን ንብረት በመጦሪያዬ ጊዜ ካፈራሁት ንብረት ሳልሆን፤ የከተማ አስተዳደሩ የወሰነልኝ የካሣ ክፍያ ቀበሌ ሳይሰጠኝ ከሁሉም ሳልሆን ባዶ እጄ ቀርቻለሁና ህዝብ ይፍረዱኝ ›› ሲሉ ብሶታቸውን ሲቃ እየተናነቃቸው ይገልፃሉ::
አቶ አቤሴሎም ቦታው ላይ ያፈሩትና የተገመተላቸው ንብረት አይነት ማሽላ፣ ኪኒን ዛፍ፣ ግራር ዛፍ፣ ጃንቦ ሎሚ ያላፈራ እና የውሃ ጉድጓድ ወዘተ መሆናቸው ጠቅሰው፤ ምንም እንኳን ምትክ የተባለው የ160 ካሬ ሜትር ቦታ ለሁሉም ተነሺዎች እስካሁን ያልተሰጠ ቢሆንም፤ ከእሳቸው ጋር አብረው እንዲነሱ ለተወሰነባቸው ስምንት ተነሺዎች የከንቲባ ጽህፈት ቤት በሰጠው ውሳኔ መሠረት ተገቢው የካሳ ክፍያ ተሰጣቷቸው፤ እስካሁን ድረስ ከቤት ንብረታቸው ሳይፈናቀሉ በቀደሞ በነበሩት ቦታቸው ላይ ኑራቸውን መቀጠላቸውን ይናገራሉ:: እሳቸው ግን ከቦታቸው ከመፈናቀላቸው ባሻገር ከሀብት ንብረታቸው ሳይሆኑ፤ ምንም አይነት የካሳ ክፍያም ሆነ ምትክ ቦታ ሳያገኙ እስካሁን ያለምንም መፍትሔ እየተጉላሉ እንደሚገኙ ነው የሚናገሩት ::
የመሬትና ልማትና ማኔጀመንት ቢሮ ለተነሺዎቹ የካሣ ግምት ከሰጠ በኋላ ከቦታው ተነሺ ለሆኑት ግለሰቦች የሚሰጠው ግምት ላይ ቅሬታ ያለው አካል ካለ እንዲቀርብ የሚል ማስታወቂያ ወጥቶ ነበር የሚሉት አቶ አቤሴሎም፤ የመሬትና ልማትና ማኔጀመንት ቢሮው አስፈላጊውን ማጣራት ካደረገ በኋላ ዘጠኙ አባላት ላይ ቅሬታ ያላቸው ነዋሪዎች ካሉ በተከታታይ አምስት ቀናት ቅሬታቸውን ለቀበሌ 02 መሬት ልማትና ማኔጅመንት ማስተባበሪያ ማቅረብ እንደሚችሉ ገልፆ እንደነበር ያስታወሳሉ::
በወቅቱ ቅሬታ ያቀረበ አንድም ሰው ባለመገኘቱ ግምቱ እንዲሰጠን ለቀበሌ የተመራላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ የይሁንና ቅሬታ አለኝ ብሎ የመጣ አካል በሌለበት ሁኔታ ምክንያቱን ምን እንደሆነ በውል በማያውቁት ነገር ምንም አይነት ክፍያ ሳይሰጣቸው መቆየታቸውን ያብራራሉ:: እንደገናም የመሬት ልማት አስተዳዳር ተነሺዎችን አስመልክቶ በድጋሜ በድሬዳዋ አስተዳደር ለቀበሌ 02 ነዋሪዎች እንዳስታወቀው፤ በቀበሌው ምህድስና ባለሙያዎች በተመረጡ መንደሮች ጉዳዩን ለመከታተል የተመረጠው ኮሚቴ አስፈላጊውን ማጣራት ቦታ ድረስ በመሄድ ያጣሩ ስለሆነ በብሎክና ፓርሴል ላይ ቅሬታ ያላቸው ነዋሪዎች ካሉ ቅርበው ቅሬታችሁን እንዲያቀርቡ አስታወቆ እንደነበር አስታውሰዋል::
የመሬት ልማትና ማኔጀመንት ቢሮ የተነሺ ግለሰቦቹ ይዞታ ሕጋዊ ለማድረግ በጠየቁት ጥያቄ መሠረት ይዞታው የማን ነው የሚለውን ነገር የተጣራ መሆኑን የሚጠቀሱት አቶ አቤሴሎም፤ የካሳ ግምቱን ካስወሰኑ በኋላ ወደ ድሬዳዋ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ይዘው ሲሄዱ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ጉዳዩን ከተመለከተ በኋላ ወደ ቀበሌ እንደመራላቸው ያሰረዳሉ:: ሆኖም ግን በድሬዳዋ አስተዳደር የቀበሌ 2 አስተዳደር በማያውቁት ሁኔታ ምትክ ቦታና የካሳ ክፍያ ለመፈፀም ፍቃደኛ እንዳልሆነ የያስረዳሉ:: ‹‹ ቀበሌ ሥራ አስፈፃሚ ግን ስልጣኑ መከታ በማድረግ የካሳ ክፍያው እንዳይከፈለኝ በማድረግ ምክንያቱን በማላውቀም ጉዳይ እያጉላላኝ ይገኛል ይላሉ››::
የተወሰነላቸው የካሳ ክፍያ እንዳልተፈፀመላቸው የሚገልጽ ደብዳቤ መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም እንደገና ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳዳር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ያቀርባሉ:: እስካሁን በከንቲባ ጽህፈት ቤት የተወሰነላቸው የካሳ ክፍያ ለማግኘት እንዳልቻሉና በቀበሌው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ምክንያት ለከፍተኛ መጉላላትና እንግልት የተዳረጉ መሆኑን በመግለጽ ቢሮው እንዲያውቀው በማድረጋቸውበወቅቱ የነበሩት መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ ጉዳዩን በማጤን በድጋሜ ለቀበሌው አስተዳዳር ጽህፈት ቤት ጉዳዩን እንደመሩላቸው ይናገራሉ::
የከንቲባ ጽህፈት ቤት ከወሰነላቸው ውሳኔ አንድ ብርም የካሳ ክፍያ ሳያገኙ፤ የፈረሰባቸው የዶሮ እርቦታ ቦታ እና የውሃ ቢርካ ግምት የካሳ ክፍያ ያልተሰጣቸው መሆኑን ገልፀው አቤቱታቸውን ዳግም ቢያቀርቡም መፍትሄ ግን ማግኘት አልቻሉም:: የመሬት ልማት አስተዳደር አቤቱታቸውን ተቀብሎ ወደ ቀበሌ 2 በመራላቸው መሰረት አቶ አቤሴሎም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በድጋሜ ጉዳዩን ይዘው ወደ 02 ቀበሌ አስተዳደር መመልሳቸውን ጠቁመው፤ የቀበሌ አስተዳደሩ ጉዳዩን ከመጤፍ ሳይቆጥረው ምንም አይነት መልስ አልሰጣቸውም:: መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ እስካሁን እያጉላላቸው በመሆኑ አሁን ላይ ለጉዳያቸው እልባት ሳያገኙ ተሰላቸተው መተዋቸውን ይገልፃሉ:: ለዚሁ ሁሉ መጎላላት የዳረጋቸው የቀበሌ አስተዳደር እስካሁን ድረስ ምንም ምላሽ ሳይሰጥ ዝም በማለቱ መሆኑንም አክለው ገልፀዋል::
ይሁን እንጂ ቦታው ነባር ይዞታቸው መሆኑን የሚያመላክቱ በርካታ ማስረጃዎች እንዳላቸው የሚገልጹት አቶ አቤሴሎም፤ በወቅቱ የኢፌዴሪ የከተማ ልማትና የቤት ሚኒስቴር በቀን 30 ቀን 10 1980 ዓ.ም ለሐረርጌ ክፍለ ሀገር የከተማ ልማትና ቤት ሚኒስቴር ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት በተጻፈው ደብዳቤ አቶ አቤሴሎም ነጋሽ በድሬዳዋ ከተማ የዶሮ እርባታ ድርጅት ለማቋቋም ቦታ እንዲሰጣቸው በጠየቁት መሰረት በቁጥር አቀ2137/1/1/80 የጻፉት ደብዳቤ ምላሽ ከነአባሪው እጃቸው ላይ ይገኛል:: አቶ አቤሴሎም በወቅቱ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረትም በአቅራቢያ ግምቱ 2500 /ሁለት ሺህ አምስት መቶ ካሬ ሜትር ቦታ ተፈቅዶላቸዋል::
የድሬዳዋ የከተማ ልማት ጽህፈት ቤት ለድሬዳዋ አጠቃላይ ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ አቶ አቤሴሌም ነጋሽ ግንቦት 27 ቀን1980 ዓ.ም የዶሮ እርባታ ድርጅት ለማቋቋም ቦታው ፕላን አስነስተው በማቅረብ ሥራውን ለመጀመር ፈቃድ ይሰጠኝ ብለው መጠየቃቸውን አስታውሶ በዚህ መሠረት ጽ/ቤቱ ስፈራው ድረስ በመሄድ ቦታውን እንደተመለከተና የተጠየቀው ለልማት ሥራ መሆኑን ማረጋገጡንና ያቀዱትን የዶሮ እርባታ ሥራ ለመጀመር እንደሚችሉ አሳውቆ ነበር::
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳዳር ከንቲባ ጽህፈት ቤት በመጋቢት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ በአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኙት አንድ ማህበርና ስምንት ቤተሰቦች የምትክ ቦታ ጉዳይ ለመወሰን አጀንዳ አድርጎ በመወያየት የውሳኔ አስተላልፎ ነበር:: የከተማዋ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ለቤተክርስቲያኗ ጥያቄ ተገቢውንና ወቅታዊ ምላሽ ለመስጠት ቀደም ሲል ለቤተክርስቲያኗ የተሰጠው ማስፋፊያ ቦታ ላይ የሚገኙ አንድ ማህበርና ስምንት ተነሺዎች የካሳ ክፍያ እና ምትክ ቦታ የሚሰጥበትን ሁኔታ በዝርዝር ተወያይቶ ውሳኔ ያስተላለፈ መሆኑን የሚገልጽ ነው::
የከተማ አስተዳዳር በወቅቱ የሰጠው ውሳኔ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሰማቸው ለተዘረዘሩ 9 ተነሺዎች በሁለት ሳምንት ውስጥ በአስቸኳይ መልካጀብዱ በሚገኘው 97 ሄክታር መሬት ላይ ለማህበሩ አሁን ያላቸውን አይነት አነስተኛ ጽህፈት ቤት የሚሰሩበት ቦታ እንዲሁም ለግለሰቦቹ የመኖሪያ ቦታ ማለትም ለእያንዳንዳቸው ከ160 ካሬ ሜትር አሁን ያለውን የሠላም ስጋት ከግምት ውስጥ በማስገባት በአስቸኳይ እንዲሰጣቸውና ከቤተክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዲያስወጧቸው ወሰኗል:: የካሳ ክፍያን በተመለከተ አስፈላጊና ህጋዊውን የአሰራር ሂደት ተከትሎ በሶስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የይዞታቸው ግምት ተሰርቶ እንዲከፈላቸው መወሰኑን የሚገልጽ ነው:: ሆኖም ግን በከንቲባ ጽ/ቤትም ይሁን በመሬት ልማት ማኔጅመንት ጽ/ቤቱ የተላለፉ ትዕዛዞች በቀበሌው አስተዳደር እምቢተኝነት ምክንያት ተፈፃሚ አልሆኑም::
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የቀበሌ 02 አስተዳደር ምላሽ
ግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ድሬዳዋ ከተማ ተገኝተን ወደ የቀበሌ 02 አስተዳደር ጽህፈት ቤት በሄድንበት ወቅት ቢሮ ያገኘናቸው የቀበሌ 02 ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰይድ አሊን ነው:: ለአቶ ሰይድ ስለ ጉዳይ ካስረዳናቸው በኋላ መልስ እንዲስጡን ስንጠይቃቸው ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ከሆኑ ገና አራት ወራቸው በመሆኑ ጉዳዩን በጥልቀት እንደማያውቁት በመግለጽ ሆኖም ግን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ከአምስት ዓመታት በላይ እዚያ ቦታ ላይ የቆዩ በመሆኑ ጉዳዩን በሚገባ እንደሚያወቁት ይገልፃሉ:: በዕለቱ ለስብሰባ ሌላ ቦታ ላይ መሆናቸውን እንዳማይመለሱ ከነገሩን በኋላ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጉዳዩን በደንብ የሚያወቁት ስለሆነ እሳቸው እንደመጡ ምላሽ እንደሚሰጡ ነግረው አሰናብተውናል::
በማግስቱም ዋና ሥራ አስፈፃሚውን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል:: በወቅቱ ቢሮ ያላገኘናቸው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ቀበሌ 02 ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ወንድማገኝ በሻ በበኩላቸው በስልክ አግኝተናቸው ምላሽ ሰጥተውናል:: አቶ ወንድማገኝ እንደሚሉት፤ ስለጉዳዩ በደንብ እንደሚያወቁ በመግለጽ አቶ አቤሴሎም የራሳቸው መኖሪያ ቤት ያላቸው በመሆኑ ምትክ ቦታና ካሳ ማግኘት መብት የላቸውም :: የመንግሥት ቦታን ለሌላ ሰው በሽያጭ ያስተላለፉበት ሁኔታ መኖሩንም ይገልፃሉ:: የእሳቸው ቤት ህገወጥ በመሆኑ የቀበሌው ደንብ ማስከበር ያፈረሰውና በአሁን ወቅት ቦታው ላይ ምንም ቤት የሌለ በመሆኑ ያገኘነው ፍርስራሽና ረጅም ጊዜ የቆየ ነገር በመሆኑ አቶ አቤሴሎም እንደሚሉት ቤት ተብሎ የሚነሳ ምንም ነገር የለም የሚሉት አቶ ወንድማገኝ፤ አቶ አቤሴሎም የቤተክርስቲያን ቦታውን ለሌላ ሰው በሽያጭ ያስተላለፉት መሆኑን ጠቅሰው፤ይህንን መነሻ ተደርጎ በቀበሌው ደንብ ማስከበር አማካኝነት መፍረሱን አመልክተዋል::
እንደ አቶ ወንድማገኝ ገለፃ፤ የከተማዋ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ውሳኔ ቢያስተላልፍም ቦታው ትክክለኛ ስለመሆኑ ቀበሌው ማረጋጋጫ ሲሰጥ ነው ክፍያው የሚፈፀመው:: ስለዚህ አቶ አቤሴሎም ቤት አለው ብለን ማረጋገጫ መስጠት አንችልም:: እኛ እንደቀበሌ አስተዳዳር ቤቱን ህገወጥ ግንባታ በመሆኑ በደንብ ማስከበር በመፍረሱ ምክንያት በቦታው ላይ ምንም አይነት ቤት ስላላየን እና አሁን የካሳ ክፍያ የጠየቁበት ቦታ ይዞታቸው አለመሆኑን እንዲሁም የራሳቸው ቤትና ይዞታ ያላቸው መሆኑን እናውቃለን:: ይህ ቦታ የቤተክርሲቲያኗን ቦታ በህገወጥ መንገድ በመውረር ያገኙት ሲሆን፤ ሊያውም ለሌላ ሰው ሰጥተው ስለነበር የቤተክርስቲያን ይዞታ ላይ የሰሩት በመሆኑ እንዲፈርስ ተደርጓል ብለዋል::
እኛም ታዲያ አቶ አቤሴሎም ከመሬት ልማት ማኔጀመንት የተሰጣቸው ህጋዊ የሰነድ ማረጋጋጫ ከየት አገኙት ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ አቶ ወንድማገኝ የሰጡት ምላሽ ህጋዊ መሆኑ በጥቃቅንና አነስተኛ ለሥራ የተሰጠ ሊሆን ይችላል እንጂ ነባር ይዞት አይደለም :: በጥቃቅንና አነስተኛ ለሥራ ቦታ የተሰጠ ካለ እንኳን የሚሰራው ለአምስት አመት ብቻ ነው:: እኛ ያየነው የሰነድ ማስረጃ እሳቸው ሌላ ቦታ ላይ ቤት እንዳላቸው ማህደራቸውን ጠቅሰን፤ በአካባቢ የሚገኙ ኮሚቴዎች፣ ማህበረሰቡንና ቤተክርስቲያን ጨምሮ ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጡ ስለምናደርግ የበለጠ መረጃ ለማግኘት መጥታችሁ በጋራ ማየት እንችላለን:: እሳቸው በስፋት የመሬት ወረራ ላይ የተሳተፉ ሰው ናቸው ይላሉ::
አቶ አቤሴሎም ጨምሮ በከንቲባ ጽህፈት ቤት ውሳኔ የተሰጣቸው ስምንቱ ተነሺዎችስ ምን ላይይገኛሉ? ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ አቶ ወንድማገኝ የሰጡት ምላሽ ሌሎቹን አስመልክቶ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ ከሚመለከተው አካል ምንም አይነት መረጃ አልተሰጠንም፤ ቤተክርስቲያኗም ይህ መልስ ከተሰጠ በኋላ ይነሱልኝ ብላ አልመጣችም ይላሉ:: ግን እኮ ቤተክርስቲያኗ ሁሉም እንዲነሱላት ነው የጠየቀቸው? ስንል በድጋሜ ላቀረብንላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ አዎን ሲጀመር ቦታው የቤተክርስቲያን ነው:: ታዲያ ከእነዚህ ሁሉ ሰዎች የሳቸው ብቻ እንዴት ህገወጥ ሊሆን ይችላል? ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ ‹‹እሳቸው ናቸው ያንን ሁሉ ቦታ በህገወጥ መንገድ የሸጡት፤ ብዙ ቦታዎችን ሸጠዋል:: ››ሲሉ እኛም ለእነዚያ ሁሉ ሰዎች መሬቱን የሸጡት እሳቸው ናቸው ስንል ጥያቄ አስከትለን:: አክለው የቤተክርስቲያኗን ቦታ ከመሸጥ ጋር ተያይዞ ብዙ ሥራዎች በስፋት ይሰሩ የነበሩት እሳቸው ናቸው ሲሉ ተናግረዋል::
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት ማኔጀመንት ምላሽ
የድሬዳዋ ከተማ ማስተዳዳር የመሬት ልማትና ማኔጅመነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገበየው ጥላሁን ስለጉዳዩ ስንጠይቃቸው በቀን በርካታ ባለጉዳዮችን የሚያስተናግድ ሰለሆነ ጉዳዩን እንደማያስታውሱት ገልፀው፤ ባለጉዳዩ ወዲያኑ ወደ ቢሮአቸው መምጣት የሚችሉ ከሆነ ጉዳዩን መመልከት እንደሚችሉ ይጠቁማሉ :: ኃላፊው በተናገሩት መሠረት ባለጉዳዩን በአካል ካገኘዋቸው በኋላ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል:: በእኛ በኩል በወቅቱ የባለጉዳዩን ማመልከቻ ተመልክተን ያለውን ነገር ጨርስን ወደ ቀበሌ እንዲሄዱ አደርገን ነበር፤ ግን የቀበሌው አስተዳደር ይህንን ጉዳይ ለምን እንዳልፈፀመላቸው አናውቅም:: እሳቸውም በወቅቱ አልተፈፀምልኝም የሚል ቅሬታን ይዘው ወደ ቢሮ ተመልሰው አለመምጣታቸውን ጠቅሰው፤ ነገር ግን ጉዳዩ ከሰሙ በኋላ ወደ ቀበሌ 02 አስተዳደር ስልክ በመደወል የአቤቱታ አቅራቢው ጉዳይ ለምን እንዳልተፈፀመላቸው ባደረጉት ማጣራት ከቀበሌ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ያገኙት ምላሽ አቤቱታ አቅራቢው መሬቱ የእሳቸው ስላልሆነ የጠየቁት የካሣ ክፍያ አይገባቸው የሚል ነው::
አቶ ገበየሁ እንደሚሉት ቀበሌው ይህንን ሲል ለመሬትልማትና ማኔጀመንት ቢሮ በደብዳቤ ማሳወቅ ነበርበት፤ ሆኖ ግን አሁንም አይገባቸውም የሚልበትን እያንዳንዱ ጉዳይ ምክንያት ጠቅሶ በደብዳቤ ለመሬትልማትና ማኔጀመንት ቢሮ ማሳወቅ አለበት:: በህጉ መሰረት ባለጉዳዩ የካሳ ክፍያ የማይገባቸው ከሆነ የሚታይ ሲሆን፤ የቀበሌ አስተዳዳሩ አይገባቸውም ስላለ ብቻ አቤቱታ አቅራቢ አይገባቸው ማለት ሳይሆን ጉዳዩ ተጣርቶ መፍትሔ እንዲሰጥ ይደረጋል ብለዋል::
የቀበሌ አስተዳደሩ እንደሚለው የባለጉዳይ ቤቱ ቢፈርስም መረጃ ስለሚኖር መረጃ መሠረት ተደርጎ ለባለጉዳዮ ካሳ ክፍያ ይሰጣል:: ቦታው ኖረም አልኖረም አግባብነት ያለው መረጃ ካለ ካሣው እንዲሰጥ ይደረጋል:: የቀበሌ አስተዳደሩ ካሣ አግባብነት የለውም የሚልበትን ምክንያት ካለው እንዲያሳውቀን በማድረግ ቀበሌው የሚሰጠውን መልስ ካየን በኋላ ለባለጉዳዩ የካሳ ክፍያ ይገባቸዋል ወይስ አይገባቸው የሚለው የሚወሰን ይሆናል:: የቀበሌ አስተዳዳሩ በሰጠው መልስ ላይ አስፈላጊውን የማጣራት ሥራ የሚሰራ መሆኑን ይገልፃሉ::
እስካሁን ባለው አሰራር ቀበሌው የካሳ ክፍያው አይፈፀም የሚሉት አቶ ገበየሁ፤ ነገር ግን የባለጉዳዩን መረጃ ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የሚሰጠው የቀበሌው አስተዳዳር መሆኑን ይገልፃሉ:: ባለጉዳዩ ወደ ለቀበሌ የተመራላቸውን ደብዳቤ ይዘው ሄደው ቀበሌው ተገቢውን ምላሽ ሲከለክላቸው ወደ መሬት ልማት ጽ/ ቤት በመመለስ ማሳወቅ እንደነበረባቸው ጠቁመው፤ ባለጉዳዩ ይህንን አድርገው ቢሆን ጉዳዩን በቅርበትና ወዲያወኑ መፍታት ይቻል ነበር ብለዋል:: አሁንም ግን የቀበሌ አስተዳዳር ለባለጉዳዮ የካሳ ክፍያ አይገባቸው ሲል ያለበትን ምክንያት በመረጃ አስደግፎ ማቅረብ ይኖርበታል:: ከእንግዲህ ጉዳዩ ትኩረት የሚሻው በመሆኑ ተከታትለው ለባለጉዳዩ የመሬት ካሳ ክፍያ ይገባቸዋል ወይስ አይገባቸውም የሚለው በመለየት መፍትሔ ይሰጣቸዋል ሲሉ ሐሳባቸውን አጠቃለዋል::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2013