ዛሬ ዛሬ የአገራችን አርሶ አደር እንደ አንዳንድ ገበሬ ‹‹ ሰኔ በጋው መስከረም ክረምቱ›› እየተባለ የሚተረትበት አይደለም። አሁን ላይ አብዛኛው አርሶ አደር በዓመት አንድና ሁለቴ ብቻ ሳይሆን ሦስቴ እያመረተ መሆኑ በአይን የሚታይ ተጨባጭ ምስክር ነው። ምርቱን በተሻለ ዋጋ ሸጦ የተሻለ ገቢ እያገኘም ይገኛል። የዚህኑ ያህልም አኗኗሩ ዘምኗል። ልጆቹን ማስተማር፣ ማልበስ፣ ተመጣጣኝ ምግብ መመገብ፣ ቴክኖሎጂን መጠቀም፤ ምርትና ምርታማነቱን ማሳደግና ሕይወቱን በተሻለ ደረጃ ለመምራት ችሏል። በሀገራችን በምግብ ራስን መቻል የተያዘውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስም ደፋ ቀና እያለ ይገኛል።
በተለይ በዘንድሮ ክረምት ሀገሩን ከተረጅነት ለማውጣት ምንም መሬት ጦም እንዳያድር በተያዘው አቅጣጫ መሰረት ውጤታማ ስራ ለመስራት ቆርጦ ተነስቷል። የቅድመ ዝግጅት ስራዎችንም አከናውናል። የአብዛኛውን የማሳ ዝግጅቱን አጠናቅቆ ወደ ዘር መግባቱም ማሳያ ነው።
‹‹አሁን ላይ የእርሻ ማሳ ዝግጅቱን አጠናቅቄ ወደ ዘር መዝራት ገብቻለሁ›› ያሉን አርሶ አደር ነገራ በዳዳ ናቸው። አርሶ አደር ነገራ ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው በኦሮሚያ ክልል ጭልሞ ደን አካባቢ ነዋሪ ናቸው።
አርሶ አደሩ እንዳሉት ፤ ዘንድሮ ዘር እየዘሩ ያሉት ድካምን የሚያስቀርና ጊዜ የማያባክን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ነው። ምርጥ ዘር፣ ማዳበርያና ጸረ ተባይ ኬሚካል በክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አማካኝነት ወደ አካባቢያቸው ዘልቆ በሕብረት ሥራ ማህበራት በኩል የቀረበላቸው የእርሻ ዝግጅት ከመጀመሩ በፊት በመሆኑ አልተቸገሩም። የዘር መዝርያ ቴክኖሎጂውን አምና በመኸር ምርት ዘመን ያመረቱትን በተሻለ ዋጋ ሸጠው ጥሩ ገቢ በማግኘታቸው የገዙት እንደሆነም አልሸሸጉም። በዘንድሮ የመኸር ምርትም የተሻለ ምርት አምርተው የተሻለ ገቢ እንደሚያገኙ ተስፋ ሰንቀዋል።
ሌላው በደቡብ ክልል ቦርቾ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አውቶ ማዳም ማሳቸውን ሁለት ዙር አርሰዋል። በቅርቡ ወደ ዘር መዝራት እንደሚገቡ ይናገራሉ።
‹‹የበቆሎ ዘር በእጄ ይገኛል›› ብለውናል ዘርም ሆነ ማንኛውም ግብዓት ወደ አካባቢያቸው በጊዜ መድረሱን በማከል። አካባቢያቸው በአብዛኛው ዝናብ አጠር ቢሆንም የዘንድሮ የዝናብ ሁኔታ ምቹ በመሆኑ በድርቅ ምክንያት ምርታማነቱ ይቀንሳል የሚል ስጋት እንደሌላቸውም ይጠቅሳሉ።
አርሶ አደር አለሜ ደሞዝ በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ የምትገኘው ቃናት ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። አርሶ አደሩ እንደነገሩን የአካባቢያቸው የአየር ንብረት ወይና ደጋ ነው። ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስና ማሽላ ለማምረትም እጅግ ምቹ ነው ። አሁን ላይ ማሳቸውን እስከ አራት ጊዜ ደጋግመው በማረስና በማለስለስ ማሽላ ዘርተዋል። ቀድሞ ከሦስት ኩንታል ያልበለጠ በሚያገኙበት በዚህ ማሳ ያዘጋጁትን ኮምፖስትና በጊዜ ወደ አካባቢያቸው የደረሰውን ግብዓት በመጠቀማቸው 10 ኩንታል ማሽላ አገኛለሁ የሚል ዕምነት አላቸው። ከሚደግፏቸው የግብርና ባለሙያዎች ካገኙትም ሆነ ወደ ማሳ ዝግጅት ሲገቡ በተጨባጭ ካዩት እንደተረዱት የዝናቡ ሁኔታ ለመኸሩ እርሻ ምቹ ነው።
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ ‹‹የዝናቡ ሁኔታ ለመኸሩ የእርሻ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ጅማሮው መልካም ነው›› በማለት ነው የዘንድሮ የመኸር ምርት ዝግጅትን አስመልክቶ የሰጡንን ማብራሪያ የጀመሩት። ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት የዝናቡ ሁኔታ እንደ ሀገር በተለይ በረጃጅም ጊዜ ከሚደርሱ ሰብሎች አንፃር ያለበት አርሶ አደሩን እጅግ የሚያበረታታ ነው። የብዕር ሰብሎችን ጨምሮ ስንዴ ገብስ፣ በቆሎና ማሽላ ለመዝራትና ማሳ ለማዘጋጀት ምቹ ነው። እስከ አሁን በነበረው የማሳ ዝግጅትም ምቹ መሆኑ ታይቷል። የመኸር እርሻ ከጥር መጀመሪያ ጀምሮ የሚዘሩ አካባቢዎች ላይ ተጠናቅቋል። መረጃዎች በወቅቱ ለግብርና ሚኒስቴር ከመድረሳቸው አንፃር ያሉ ክፍተቶች እንደተጠበቁ ሆነው ዳይሬክቶሬቱ እያደረገው ባለው ክትትልና ቁጥጥር እንደ በቆሎ፣ማሽላ ያሉትን ሰብሎች በመዝራት ላይ ናቸው። በቀጣይ ወደ ጥራጥሬ ሰብሎች ላይ ለመሸጋገርም ዝግጅት እየተደረገ ያለበት ሁኔታ መኖሩ ተረጋግጧል። በአብዛኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተለይም ከፀጥታ ጋር ተያይዞ ችግር ባለበት ትግራይ ክልል እርሻ እየታረሰ ነው። የረጅም ጊዜ ሰብል በሚሰጡ አካባቢዎች ማሳ በድግግሞሽ እርሻ ታርሶና ተዘጋጅቶ በዘር ተሸፍኗል። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ሁለተኛና ሦስተኛ እርሻ ላይ የደረሰበት አለ።
በልግ በአብዛኛው ቢዘራም የክረምቱን ዝናብ ተጠቅሞ ቶሎ መዝራት የማይቻልባቸው ወደ ኋላ የቀሩ አካባቢዎች አሉ። ይሄ የሚኖረውን ተፅዕኖ ዳይሬክቶሬቱ ገምግሞ ድጋፍ የሚያደርግበት ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ በእነዚህ አካባቢዎች የበልግ እርሻን ወደ መኸር ማዞር ታይቷል። በተጨማሪም በተወሰኑ በልግ አምራች አካባቢዎች ማሳው በበልግ ምርት በመያዙ ወደ ማሳ ዝግጅትና ዘር ከመግባት አንፃር የመዘግየት ነገር ይታያል። ሆኖም እነዚህ አካባቢዎች የበልግ ምርቱን በማንሳት በቀጣይ ወር ወደ መኸር ምርት ማሳ ዝግጅትና ዘር መዝራት ሂደት ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ነገር ግን ሙሉ በሙሉ በተወሰነ ደረጃ ከበልግ ወደ መኸር የሚገቡ አካባቢዎች ሁለተኛ የዘር ወቅታቸው ወደ ነሐሴና ሀምሌ መጨረሻ ሊሄድና እርሻቸውን ዘግይተው የሚጀምሩበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።
በአጠቃላይ የመኸር እርሻ ሂደቱ እንደ ሀገር ሲቃኝ ከ80 በመቶ በላይ ማሳ ታርሶ ለዘር የተዘጋጀበት ሁኔታ አለ። በዘንድሮ 2013/2014 የምርት ዘመን በአጠቃላይ የሚታረሰው 12 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ ነው።
አቶ ኢሳያስ የምርት ዘመኑን የግብዓት ዝግጅትና አቅርቦትን አስመልክተው እንደገለፁልን ዘንድሮ ግብዓት አቅርቦት ከአፈር ማዳበርያ ጀምሮ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የሆነው የማሳ ዝግጅት ሥራውን ከመጀመሩ አስቀድሞ ነው። ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ከ300 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ጭማሪ ያለው የተሻለ ግብዓት አቅርቦት ተደርጓል። እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ከሀገሪቱ ሁሉም አካባቢ ከሚገኙ አርሶ አደሮች በተሰበሰበው ፍላጎት መሰረት ለምርት ዘመኑ 18 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ የሚያስፈልግ መሆኑ ተለይቷል። በተመሳሳይም ኬሚካልና ሌሎች ግብዓቶች ፍላጎት በልየታ የታወቁበት ሂደት ነበር። ይሄን ተንተርሶም እንደ ሀገር አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ምርጥ ዘር ለምርት ዘመኑ ለማቅረብ በዕቅድ ተይዟል። ግብዓቶቹን ትግራይ ክልልን ጨምሮ ለሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ ተችሏል።
የግብዓት አቅርቦቱ ከአምናም ከታች አምናም በእጅጉ የተሻለ ነው። በተለይ ለትግራይ ክልል ያለበት ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ገብቶ በክልሉ ከተጠየቀው በላይ ግብዓት አቅርቦት የተደረገበት ሁኔታ መኖሩን ነው የተናገሩት። ግብዓት ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎችም ለማድረስ በሰፊው እየተሰራ መገኘቱን አቶ ኢሳያስ አብራርተዋል።
በመኸር ምርት ዘመን የሚሳተፉትን አርሶ አደሮች እንዲሁም ማግኘት የታሰበውን ምርት አስመልክተንም ላነሳንላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተውን ነበር። እንደ ምላሻቸው ታድያ በዘንድሮ የምርት ዘመን በ12 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ ላይ የሚሳተፉት አርሶ አደሮች 18 ሚሊዮን ናቸው። ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀውም ምርት 374 ሚሊዮን ኩንታል ነው። ይሄ የምርት ዘመኑ ሂደት የ10 ዓመቱ ዕቅድ የመጀመሪያ ምዕራፍ እንደመሆኑና ለስኬቱ እንደተደረገው ጥረት የተሻለ ስኬት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
አርሶ አደሩን ከመኸር ምርት ሂደት ሊያስተጓጉሉ ይችላሉ ተብለው የታሰቡ ስጋቶች መኖራቸውንም ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል። ጎርፍ፣ ኮቪድ 19ና አንበጣ ከስጋቶቹ ዋንኞቹ ተጠቃሾች ናቸው።
‹‹የዝናብ ሁኔታን በተመለከተ ለአርሶ አደሩ በተከታታይ መረጃ እንዲደርሰው ይደረጋል›› ያሉት አቶ ኢሳያስ ከባድ ዝናብ ሊያጋጥም እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ነው የጠቀሱት። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ለጎርፍ የሚጋለጡ አካባቢዎች አሉ። በነዚህ አካባቢዎች ማሳ ላይ ውሃ እንዳይተኛ ከማድረግ ጀምሮ ቅድመ ዝግጅቶች ሊደረግ ይገባል። ለዚህም በአደጋ መከላከል የሚመራ የጎርፍ ቴክኒካል ኮሚቴ ዝግጁ መሆኑን ነው የጠቀሱት። ሌላው ስጋት ደግሞ አንበጣ ነው። አንበጣ በአሁን ወቅት እየተቀዛቀዘ መጥቷል። ቢሆንም አማራ ምዕራባዊ ክፍል፣ የትግራይ ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች፣ የኦሮሚያ ምስራቅ ሀረርጌ፣ ምዕራብ ሀረርጌ፣ የምዕራብና ምስራቅ ጉጂ፣ የባሌና ምስራቅ ባሌ፣ የቦረና እንዲሁም በደቡብ ክልል የኬንያ አዋሳኝ የሆኑ የመጀመሪያ ተጠቂ አካባቢዎች ናቸው። በመሆኑም በሶማሊያ፣ በኬንያ መግቢያ አካባቢዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል። የደቡብ ኦሞ ዞን በደቡብ ክልል የመግቢያ ቦታዎች እንደመሆናቸው ባለፉት ዓመታት ከነበረው ተሞክሮ አንፃር ያልተፈለፈለ አንበጣ ካለ አርሶ አደሩ ቁጥጥር መደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ግብርና ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ የእርሻና የምግብ ድርጅት እንዲሁም ከምስራቅ አፍሪካ የአንበጣ መከላከያ ድርጅት ጋር በመተባበር ትንበያዎችን በወቅቱ በማውጣት፣ የማስጠንቀቂያ መልዕክቶች ከመስጠት ጀምሮ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየሰራ መገኘቱንም ተናግረዋል። ‹‹የዝናብ እጥረት ባይኖርም አርሶ አደሩ የሚያገኘውን ዝናብ እንዲሁም ያለውን ጊዜ በአግባቡ መጠቀም አለበት›› ብለዋል።
‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ አርሶ አደሩ ኮቪድ እንደሄደ አድርጎ የመወሰድ ግንዛቤ ይዟል›› የሚሉት ዳይሬክተሩ የመከላከል ኮሚቴ ቅስቀሳዎችም እየተዳከሙ መጥተው የነበሩ መሆናቸውን አስታውሰዋል። አሁን ላይ ይሄን ለመቀየር አርሶ አደሩ አስቸኳይ ጉዳይ ካልገጠመው በቀር እንቅስቃሴ እንዳያደርግ፣ መሰብሰቦችን እንዲቀንስና ደቦዎችን ማካሄድ እንደሌለበት ተነግሮት እየተገበረ ይገኛል።
ስድስተኛው ሀገር አቀፍ አጠቃላይ ምርጫ በመጪው ሰኔ እንደሚካሄድና ይሄ ወር አርሶ አደሩ በሥራ የሚጠመድበት በመሆኑ ሥራው መስተጓጎል ይገጥመው ይሆንስ? ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፦
‹‹አርሶ አደሩ አስተዋይ ነው። ሲወስንም በአግባቡ የሚወስን የሕብረተሰብ ክፍል ነው። ካርድ መውሰድ ባለበት ጊዜ ይወስዳል። መምረጥ ባለበት ቀን ኃላፊነት እንዳለበት አውቆ ይመርጣል። የሚደረጉ የምርጫ ቅስቀሳዎችን ባለው ጊዜ ያዳምጣል። ግብርና ሚኒስቴር ይሄን ያበረታታል። ይሄ ደግሞ የእርሻ ሥራውን የሚያስተጓጉል አይደለም። ምክንያቱም ከዚህ ውጪ ለምርጫ ከሚንቀሳቀሱ ሰዎች በስተቀር አርሶ አደሩ ሙሉ በሙሉ ትኩረቱ ሥራ ላይ ነው። በመሆኑም የእርሻ ስራው መስተጓጎል አይኖርም ባይ ናቸው። የመኸር ቅድመ ዝግጅት ስራው ከጅማሮው ካማረ ፍፃሜው የተስተካከለ ከሆነ የታቀደው 374 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። እኛም የሚገኘው ምርት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ከተረጅነት የሚያላቅቅ እንዲሆን በመመኘት ጽሑፋችን ደመደምን።
የመኸር እርሻ ቅድመ ዝግጅት ስራ ተጠናቋል፤
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2013