በዘፈኑ የሰው ልጅ ፍቅርና አንድነትን ሰብኳል። በዘፈኑ ብዙዎችን አስጨፍሯል፤ አስደስቷል፤ አስተምሯል፤ አስገንዝቧል። በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ አካባቢ ተወልዶ ያደገው ድምጻዊ ታሪኩ ጋንካሲ “ዲሽታግና“ በሚለው ዘፈኑ ይታወቃል። በሁለት ወር ውስጥ ስድስት ሚሊዮን በላይ ዩቱዩብ ተመልካች ዘፈኑን አድምጦለታል፣አይቶለታል።
የደቡብ ኦሞ ዞን የአሪ ብሄረሰብ ልጅ ነኝ የሚለው ታሪኩ ጋንካሲ “በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት አረንጓዴ ተክልና አረንጓዴ አስተሳሰብ ነው የሚል ሀሳብ አለው።እኔ የአርሶ አደር ልጅ ነኝ። ኢትዮጵያ ትልቁ ውበቷ አረንጓዴ ተክል ነው። አረንጓዴ ተክል ሲያዩት ያምራል፣ ቀልብን ይማርካል፣ የገቢ ምንጭም ይሆናል። የወንዝና የምንጭም መፍለቂያ ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያን አረንጓዴ ማልበስ አስፈላጊ በመሆኑ ከዛሬ ጀምሮ በየአካባቢያችን ችግኝ መትከልና መንከባከብ ያስፈልጋል ይላል።
“የኢትዮጵያን መሬት ብቻ አይደለም አረንጓዴ የሚለብሰው የሰው አስተሳሳብም አረንጓዴ መልበስ አለበት“ የሚለው ድምጻዊ ታሪኩ ፤በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚታየው ግጭትና ጥቃት የሰው ልጅ አእምሮ አረንጓዴ ባለመልበሱ ነው ይላል። ውስጣችንን አረንጓዴ ተክል ማድረግ ያለብን። ይህን ማድረግ ስንችል ሆደ ሰፊነት፣ ደግነትና መተሳሰብ በውስጣችን እንደሚያሰርጹ ይናገራል።
ጥላቻና ክፉ ተግባራት ከእኛ ይርቃሉ። በኢትዮጵያችንም የሰላም አየር ይነፍሳል። እናም የኢትዮጵያን ምድር አረንጓዴ ለማልበስ እንደምንሰራው ሁሉ የሰው አእምሮንም አረንጓዴ ማልበስ ያስፈልጋል። ያኔ በኢትዮጵያችን ዘላቂ ሰላም ይሰፍናል ብሏል።
ለኢትዮጵያ ሕዝብ በፍቅር ዘምሬለሁ፤ ሕዝቡም ዘፈኔን ወዶታል ያለው ድምጻዊ ታሪኩ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፈለገው ፍቅር ዘላቂ እንዲሆን የሰው አእምሮ አረንጓዴ መልበስ አለበት፤ የኢትዮጵያ ምድርም በአረንጓዴ ማልበሳችን የምንፈልገው ሰላም፣አንድነትና ፍቅር ያመጣልናል። አካባቢያችንም ለአይንም ይማርካል፣ ውሃ የማይጠፋበት ስለሚሆን የትኛውንም ልማት ለማካሄድ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር እምነቱ ከፍ ያለ ነው ።
በዚህም እናድጋለን፣ እንለወጣለን፤ ኢትዮጵያ ከለማችና ሀብታም ከሆነች ሁሉም በየቤቱ እንደፍላጎቱ የሚበላውና የሚጠጣው ከተገኘ ፍቅር ሊጨምርልን ስለሚችል እስኪ አንድ ሁለት ዓመት እርስ በርስ የቃላት እሰጣ አገባውን ትተን ብናለማ ሰላምና ፍቅርን ዘላቂ በማድረግ በኩል ተጨባጭ ውጤት ማምጣት እንችላለን ሲል ገልጿል።
መንግስትም የደን ክምችት አነስተኛ በሆኑባቸውና በተራቆቱ አካባቢዎች ኢትዮጵያን አረንጓዴ በማልበስ ይበልጥ ትኩረት አድርጎ ቢሰራ ጥሩ መሆኑን የተናገረው ድምጻዊ ታሪኩ፤ ለኢትዮጵያ ዕድገት፣ ስኬት፣ ሰላምና ፍቅርን ተመኝቷል።
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 22 ቀን 2013 ዓ.ም