የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በፓሪስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን ለመምረጥ የማጣሪያ (የሰዓት ማሟያ) ውድድሮችን ዛሬ በስፔን ማላጋ ያካሂዳል:: በመጪው ነሐሴ ወር/2016 ዓ.ም በሚደረገው ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ከ800 ሜትር እስከ ማራቶን ባሉት ርቀቶች የሚወክሉ አትሌቶች ተመርጠው ከሚያዚያ ወር መጨረሻ አንስቶ ወደ ዝግጅት መግባታቸው ይታወቃል:: ዛሬ ማላጋ ላይ በሚደረገው የሰዓት ማሟያ ውድድርም የዓለም አትሌቲክስ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ያስቀመጠውን ሰዓት የሚያሟሉ የመጨረሻዎቹ አትሌቶች የሚለዩበት ይሆናል::
በፌዴሬሽኑ አዘጋጅነት የሚካሄደው ይህ የማጣሪያ ውድድር በሴትና ወንድ 10ሺ ሜትር እንዲሁም በወንዶች 800 ሜትር እና የ1ሺ500 ሜትር ይካሄዳል:: በሌሎች ርቀቶች ዓመቱን ሙሉ በሚከናወኑ ርቀቶች አትሌቶች ባስመዘገቡት ሰዓት መሰረት ለብሄራዊ ቡድን የሚመረጡ ሲሆን፤ በ10ሺ ሜትር ርቀት ደግሞ ውደድሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተመናመኑ በመሆናቸው አትሌቶችን ለመምረጥ የዛሬው የማጣሪያ ውድድር አስፈልጋል:: በመሆኑም ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ተቋም ያስቀመጠውን ሰዓት ለማስመዝገብ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እርስበርስ የሚፎካከሩ ይሆናል::
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመካከለኛ ርቀት ሴቶች ኢትዮጵያ ሳይጠበቅ ተፎካካሪና ውጤታማ በመሆን ላይ ትገኛለች:: በአንጻሩ በወንዶች 800 እና 1ሺ500 ሜትር ርቀቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የአትሌቶች ተሳትፎና ውጤታማነት እየቀነሰ መምጣቱ ታይቷል:: እስካሁን ድረስም ለፓሪሱ ኦሊምፒክ ተሳትፎ የሚያበቃ ሰዓት መመዝገብ አልቻለም:: ይህም ‹‹ኢትዮጵያ ፓሪስ ላይ በመካከለኛ ርቀት በወንዶች ተወካይ ታገኝ ይሆን?›› የሚል ጥያቄ ፈጥራል:: የዛሬው የማጣሪያ ውድድርም ለዚህ ጥያቄ መልስ ይኖረዋል::
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በእነዚህ ርቀቶች ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በመሆን አሯሯጮችን በመመደብ ሰዓቱ ተሟልቶ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን ለመለየት ማጣሪያውን ማዘጋጀቱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሃንስ እንግዳ ገልፀዋል:: በማጣሪያው ላይ ከእጩ አትሌቶቹ ባለፈ ሰዓት ለማሟላት ፍላጎት ያላቸው አትሌቶችም ወጪያቸውን ራሳቸው ሸፍነው እንደሚሳተፉ ታውቋል::
ከማራቶን ውጪ ባሉት ርቀቶች የሰዓት ማሟያ ጊዜ ገደቡ ገና ቢሆንም የዛሬው ማጣሪያ የ10ሺ ሜትር ተሰላፊ አትሌቶች ተለይተው ወደመጨረሻው የኦሊምፒክ ዝግጅት ይገባሉ:: በመካከለኛ ርቀት አትሌቶች ባላቸው ሰዓት መሰረት ሚኒማ ሊያሟሉ ይችላሉ በሚል ተመርጠው ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል:: የዓለም አትሌቲክስ ለ800 ሜትር 1፡44.70 እንዲሁም ለ1ሺ500 ሜትር 3፡33.50 የሆነ ሰዓት ያስቀመጠ ሲሆን፤ ይህም ሰዓት በየጊዜው እየጠበበ ስለመምጣቱ ለመረዳት ይቻላል:: በዛሬው ማጣሪያ ይህ የማይሟላ ቢሆንም በማህበሩ እስከተገደበው የሰዓት ማሟያ ጊዜ ድረስ የሚኖሩ ሌሎች ውድድሮችን በመዝጋት ወደመጨረሻው የዝግጅት ምዕራፍ የሚገባ መሆኑንም ኃላፊው አስረድተዋል::
ነገር ግን በቀጣይ በሚካሄዱት ውድድሮች ላይ የመግቢያ ሰዓት ላይሟላም ስለሚችል የዛሬው የማጣሪያ ውድድር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል:: ቡድኑ ሆቴል ገብቶ ዝግጅት ከጀመረ ከአንድ ወር በላይ ስላስቆጠረ ኢትዮጵያን ወክለው በኦሊምፒክ የሚካፈሉ አትሌቶች ይኖራሉ ተብሎም ይጠበቃል:: አትሌቶች በኦሊምፒክ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ሰዓት በተለያዩ ውድድሮች ላይ እንደሚያስመዘግቡ ይታወቃል፣ በዚህም በሃገርም ሆነ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ዘመናዊ (ኤሌክትሮኒክስ) ሰዓት መመዝገቢያ መያዝ ያለባቸው ሲሆን፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ግን ለዚህ ምቹ ሊሆኑ አልቻሉም:: ኢትዮጵያ ከምትገኝበት የቦታ አቀማመጥ ጋር ተያይዞ ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ከባድ በመሆኑ ምክንያት ባለፉት ዓመታት በሄንግሎ የሰዓት ማሟያ ውድድር ሲደረግ ቆይቷል::
ባለፈው ዓመት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የማጣሪያ ውድድሩን ሃዋሳ ላይ ለማካሄድ ታቅዶ ዕውቅና ቢገኝም ሚኒማ ማሟላት ባይቻልስ የሚለው ስጋት ፌዴሬሽኑ በድጋሚ ፊቱን ወደ ውጪ ሃገራት እንዲያዞር አድርጎታል:: በተለይ የ10ሺ ሜትር ርቀት ሚኒማ በየጊዜው እየተቀነሰ መሆኑን ተከትሎ ሰዓቱ ሊሟላ በሚችልበት ስፍራ ማጣሪያውን ከማድረግ ውጪ አማራጭ ባለመኖሩ የዛሬውን ውድድር ስፔን ላይ ለማድረግ መገደዱንም ኃላፊው አስገንዝበዋል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2016 ዓ.ም