አርቬ ጎና በሲዳማ ክልል የምትገኝ ወረዳ ነች። በወረዳዋ ያለችው ሩሙዳሞ ቀበሌ በቡና አብቃይነት ትታወቃለች። በቀበሌዋ የሚገኙ አርሶ አደሮች ቡና በማምረት ይታወቃሉ። ይሁንና ካለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በላይ የአንድ ኪሎ ቡና ዋጋ ከአንድ ኪሎ በቆሎ ባነሰ ዋጋ ይሸጣሉ። የቡና ዋጋ በዚህ ደረጃ በማሽቆልቆሉ ማሳቸውን በበቆሎ ለመተካት ተገደው ነበር። ለቡና ገበያው መዳከም ዋናው ምክንያት ቡናው ባለቤት አልባ መሆኑ እንደነበር አርሶ አደሮቹ ያስታውሳሉ።
ይሁንና በ2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ በአርሶ አደሩ ዘንድ መነቃቃት በመፈጠሩ የቀበሌዋ አርሶ አደሮች ቡናቸውን ነቅለው በቆሎ በዘሩበት ማሳ ዳግም ቡና መትከል ጀመሩ። በቀበሌዋ ከሚገኙ አርሶ አደሮች መካከል ሩሙዳሞ እሸት ቡና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አባላት ቀዳሚዎቹ ናቸው። የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ፓስተር ቦጋለ ወልደሐና እንደሚናገሩት በገበሬ ማህበር ስር የተደራጁት ስድስት ሆነው ነው። ሁሉም በቡና እርሻ የሚተዳደሩ፣ በቡና ላይ ለመሥራት ፍላጎት ያላቸውና የሚግባቡ አርሶ አደሮች ናቸው። የጠየቁት የባንክ ብድር ባይደርስላቸውም በየፊናቸው ከነበራቸው የቡና ማሳ ካገኙት ገቢ በመክፈል የራሳቸው በሆነ ሁለት ነጥብ አምስት ሄክታር ማሳ ላይ ቡና አለሙ።
በ2009 ዓ.ም ቡና ማጠብና ማቅረብ የሚያስችላቸውን ንግድ ፈቃድም አግኝተዋል። በ2010 እና በ2011 ዓ.ም ፈጥነው ምርታቸውን ለኢትዮጵያ ቡና ገበያ ማቅረብ ጀመሩ። ማህበሩ እንዲህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይታወቃል፤ የሀገሪቷን ስምም በማህበሩ አማካይነት ይጠራል ብለው አልገመቱም። ከራሳቸው አልፈው ለቀበሌዋ ብሎም ለወረዳውና ለክልሉ ቡና አብቃይ አርሶ አደሮች ሰፊ ገበያ መፍጠር መቻላቸውንም አላሰቡትም። በማህበር የተደራጁት ‹‹ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ›› እንዲሉ በጋራ ሆነው ቡናቸውን በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ ነበር።
አባላቱ በ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣንና በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ከሚደገፈው future Ethiopia Value Chain Activity ጋር በመተባበር ለመጀመሪያ ጊዜ ባዘጋጀው የቡና ቅምሻ ውድድር ተሳተፉ። ሥራ አስኪያጁ እንደነገሩን ያቀረቡት በሁለት ነጥብ አምስት ሄክታር ማሳቸው ያመረቱትን የራሳቸውን ቡና ነበር። በቡናውም ሁለተኛ፣ ሦስተኛና ስምንተኛ ከፍተኛ ደረጃን በማግኘት አሸነፉ። ሁለተኛ የወጣው ቡናቸው በዓለም ገበያ ለጨረታ የቀረበው 88 ጊዜ መሆኑንም ነው የነገሩን። በተያያዘም ከ50 በላይ የውጭው ዓለም ሀገራትም ቡናቸውን ለመግዛት ጠይቀዋቸዋል። አባላቱ ከሦስት ብር በታች በመሸጡ ተስፋ ቆርጠውበት የነበረው ቡና እንዲህ ተፈላጊ ሲሆን ማየታቸውን ማመን አልቻሉም። ግማሽ ኪሎ ግራሙ በ107 እና 108 ዶላር ሲሸጥም በአድናቆት ተደመሙ። አባላቱ በዘንድሮውና ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ በሚገኘው በዓለም አቀፉ የምርጥ ቡና ቅምሻም ተወዳድረዋል።
የተሳተፉት 24 ኬሻ የተበጠረና የተለቀመ ደረቅ ቡና በማቅረብ ነው። በዚህም አንድ ሺህ 848 የቡና ናሙና አቅራቢዎች በተሳተፉበት ሂደት 150ዎቹ ምርጦች ውስጥ መግባት ችለዋል። ከ150ዎቹ መካከልም ቅምሻ ተደርጎ በተካሄደው ውድድር 40ዎቹ ውስጥ የመግባት ዕድል አግኝተዋል። ግንቦት 13 እና 16 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው የኦን ላይን ውድድርና ደረጃ ይፋ በሆነበት መድረክ ከአንድ እስከ ዘጠኝ ባሉት ውስጥ መግባት ችለዋል። ሥራ አስኪያጁ እንደሚሉት ይኼ ደረጃ አምና ሁለተኛ ከወጡበት ጋር ሲነጻፀር ዝቅ ያለ ነው። ቢሆንም ለአባላቱ እጅግ ከፍተኛ ነው። ምክንያቱም ብዙ የሰሩ ተወዳዳሪዎች ወደ ኋላ በቀሩበት ከባድ ውድድር 10ሮቹ ውስጥ መግባት ለነሱ በቀላሉ የሚታይ ዕድል አይደለም።
ይኼን ውጤት የተንተራሰው ምርታቸው በቀጣይ የሰኔ ወር በኦን ላይን በዓለም ገበያ ጨረታ ሲቀርብ በተሻለ ዋጋ እንደሚሸጥም ተስፋ አላቸው። ከጥራትም ሆነ አምና ማፍራት ከቻሉት ደንበኛ አኳያ ከአምናው የበለጠ እንጂ ያነሰ ዋጋ እንደማያገኙም እርግጠኞች ናቸው። ሥራ አስኪያጁ እንደነገሩን የሲዳማ ቡና በገበያ እጅግ ተፈላጊ ነው። ለዚህም በግንቦት 13ቱና 16ቱ የኦን ላይን ውድድርና ደረጃ መግለጫ ከአንድ እስከ አምስት ባሉት ደረጃዎች ውስጥ በመግባት በአራቱ አሸናፊ የሆነው ቡና ናሙና በሙሉ የሲዳማ መሆኑ ምስክር ነው። የሀረር፣ የሊሙ፣ የይርጋ ጨፌ፣ የጌዴዎ ተብለው ከተዘረጉት ውስጥ አምናም ትኩረት አግኝቶ በመመረጥ ከአንድ እስከ ሦስት ወጥቶ የነበረው የሲዳማ ቡና ነው ብለዋል።
‹‹ተመራጭነትን ማግኘት የቻልነው ጠንክረን በመሥራታችን ነው›› በማለት በአትሌቲክሱ የበቆጂ ልጆች ተብለው እንደሚጠሩት በቡናው የሲዳማ ልጆች ተብለው መታወቅና ሀገራቸውን ማስጠራት እንፈልጋለን ይላሉ። በቀጣይም አሸናፊነቱ ከእጃቸው እንዳያመልጥ የሲዳማ ቡና አብቃይ አርሶ አደሮች እጅ ለእጅ በመያያዝ የበለጠ ጠንክረው ይሰራሉ። ለዚህም አሁን ላይ በሀገራችን በቡና ላይ የበለጠ የሚሰራበትና ሀገርንና ወገንን መጥቀም የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ባይ ናቸው።
በ2013 መስከረም ላይ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በአቅራቢነታቸው ላይ የላኪነት ፈቃድን ጨምሮ የሰጣቸው መሆኑንም በማሳያነት ይጠቅሳሉ። አሁን ላይ ከተለያዩ ነጋዴዎች ጋር በመገናኘት ቡና እየሰበሰቡ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ባላቸው መጋዘን በማከማቸት ናሙና እየላኩ ይገኛሉ። ናሙናው አንድ ኪሎ ግራም ቡና እስከ ስምንት ዶላር የመሸጥ ዓላማ ያለው ነው። በስልክና በዌብ ሳይት እያገኙት እንዳለ ምላሽ ቡናቸውን የመግዛት ፍላጎት ያላቸው ብዙ ሀገሮች አግኝተዋል። ለአንድ ኪሎ እስከ ዘጠኝ ዶላር ከሰጧቸው ጋር እየተደራዱ ሲሆን፤ ከውድድሩ በኋላም በዚሁ ዋጋ እንሸጣለን ብለው ያምናሉ።
‹‹የመጀመሪያውን ውድድር ካሸነፍን በኋላ ነው የራሳችንን ብቻ ሳይሆን የመላው አርቬጎና ወረዳን እና የሩሙዳሞ ቀበሌ አርሶ አደሮችን ታሪክ የበለጠ መቀየር የቻልነው›› የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ‹‹ከማሸነፋችን በፊትም ቡና ለገበያ የምናቀርበው ከማሳችን ብቻ ሳይሆን ከአካባቢያችን አርሶ አደሮች በተሻለ ዋጋ በመግዛት ነበር›› ብለውናል። አቅራቢና አጣቢነት መስክ ላይ የተሰማሩም እንደመሆናቸው አርሶ አደሩን አቀናጅተው ሥራውን በማጠናከር ቀጥለዋል። 50 ብቻ የነበሩትን ደንበኞቻቸውንም በብዙ እጥፍ አስፍተዋል። ከእያንዳንዱና ከቡና ጣቢያ የሚገዙት በተሻለ ዋጋ መሆኑን ሲገልፁም ‹‹አርሶ አደሩ አንዱን ኪሎ ግራም እሸት ቡና 27 ብር ቢሸጥልን በዋጋው ላይ ሁለት ብር እንጨምርለታለን›› ይላሉ። የየራሳቸው የቡና ማሳ ያላቸው እንደመሆናቸው በሚያቀርቡት ላይ ከራሳቸውም የሚጨምሩበት አለ። ብዙውን የሚያቀርቡትን ቡና የሚሰበስቡት ግን በአካባቢያቸው ካሉት አነስተኛና ሰፋፊ ማሳ ካላቸው የሩሙዳሞ ቀበሌ አርሶ አደሮች ነው።
የሩሙዳሞ ቀበሌ ነዋሪዋ ቡና አብቃይ ሴት አርሶ አደር ፀሐይ በአርባ አንዷ ናቸው። በጓራቸው ያላቸው የቡና ማሳ አነስተኛ ቢሆንም በማህበሩ ገበያ ተፈጥሮላቸዋል። በዚህ ገበያ አቅም ፈጥረው በማህበር ተደራጅተው እንደሚንቀሳቀሱት የአካባቢያቸው አርሶ አደሮች በሰፊ ማሳ ላይ ቡና በማምረት በአቅራቢና ላኪነት የመሰማራት የረጅም ጊዜ ህልም እንዳላቸው አጫውተውናል። ‹‹ህልሜን ዕውን ለማድረግ የማሳዬን ምርታማነት የሚጨምሩ ቴከኖሎጂዎችን እየተጠቀምኩ ነው›› ብለውናል። ለዚህ ያነሳሳቸው ማህበሩ በአካባቢያቸው ተመስርቶ ሲንቀሳቀስና ሴት አርሶ አደሮችን ሲያበረታታ ማየታቸው መሆኑንም አልሸሸጉም።
አባላቱ ከአርሶ አደሯ በእጅጉ የጠነከረ አቅም ያላቸውና በቋሚነት ብቻ ቡና የሚያቀርቡላቸው 300 ደንበኞችም አፍርተዋል። የቀበሌውን አርሶ አደርም ሆነ የራሳቸውን አቅም በዚህ መልኩ ነው የገነቡት።
የማህበሩ ሂሳብ ሹም አቶ አሰፋ ኃይለማርያም እንደሚናገሩት አባላቱ ከባዶ ተነስተው የመሰረቱትን ማህበር ካፒታል ዛሬ ላይ 20 ሚሊዮን ብር ደርሷል። ለእርሳቸውና ለሌሎች ለአካባቢው ነዋሪዎችም የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል። እሳቸው በሚያገኙት ደመወዝ አምስት ልጆቻቸውን ጨምሮ ከባለቤታቸው ጋር ሰባት ቤተሰብ ያስተዳድራሉ፤ ልጆቻቸውንም ያስተምራሉ። ከወር ደመወዛቸው ውጪ በማህበሩ በተለያየ መንገድ ይደጎማሉ። በየበዓላቱ ቡና ሲያቀርቡ የሚሰጣቸው ጉርሻ አለ። ባለፈው ዓመት ማህበሩ ሲያሸንፍም ዳጎስ ያለ ጉርሻ አግኝተዋል። አባላቱም ከማህበሩ ከሚያገኙት ገቢ በየግላቸው የራሳቸውን፣ የቤተሰባቸውን አኗኗር አሻሽለዋል። የቡና ማሳቸውን እስከ ማስፋፋት፣ የቡና ማጠቢያና ማበጠሪያ ማሽን፣ ቤት፣ መኪና እስከ መግዛት፣ ሆቴልና የተለያየ የንግድ ድርጅት እስከ መክፈት በመድረስ ተጠቃሚነታቸውን አረጋግጠዋል። ለዚህም የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ በግላቸው የቡና ማበጠሪያ ማሽን እስከ መግዛት በመድረስ የፈጠሩትን አቅም በማሳያነት ይጠቅሳሉ።
የአርቬ ጎና ወረዳንና የሩሙዳሞ ቀበሌን አርሶ አደሮች ቡና ገበያ ማስፋት ችለዋል። ከመቶ በላይ ለሆነ የአካባቢው ማህበረሰብም ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። ቡና በሚለቀምበት፣ በሚኮተኮትበትና በሚተከልበት ጊዜ ቁጥሩ ከእጥፍ በላይ የሚጨምር ጊዚያዊ የሥራ ዕድልም የከፈቱበት ሁኔታ አለ።
‹‹በቋሚም በጊዚያዊም ከፈጠሩት የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎች 80 በመቶው ሴቶች ናቸው›› ያለችን ደግሞ ራሷን ለአብነት የጠቀሰችልንና በማህበሩ በገንዘብ ያዢነት የምታገለግለው ወጣት ተዋበች ኤጋታ ናት። ወጣቷ በወር አምስት ሺህ ብር እየተከፈላት ትሰራለች። አንድ ጊዚያዊ ሠራተኛ ቢያንስ በወር አንድ ሺህ ብር እንደሚያገኝም ገልፃለች። በሙያዋ ያላትን ሰርተፍኬት ወደ ዲፕሎማና ዲግሪ እንድታሳድግ በማህበሩ ትታገዛለች። የሥራ ማትጊያ የምታገኝበት ጊዜም አለ። ማህበሩ ሴት አባላት የሉትም። ምክንያቱ ደግሞ ለሴቶች ልጆቻቸውንና ቤታቸውን ትተው ጫካ ውለው እያደሩ ቡና መልቀም እንዲሁም በዚሁ አካባቢ በሚደረጉ ዝግጅቶች መሣተፍ እጅግ ከባድ በመሆኑ ነው።
ስለዚህም በወረዳውና በቀበሌው ቡና በማጠብና በማቅረብ የሚሰማሩ ሴቶች የሉም። ቡና ላኪዎች ቢኖሩም ጥቂት ናቸው። ማህበሩ ሴት አርሶ አደሮች የገንዘብ አቅም ፈጥረው ከወንዶች ጋራ እንዲሰሩ ያበረታታል። እሷም ሴቶች በሕይወታቸው ላይ ፈጣን ለውጥ ለማምጣት በዚህ መንገድ እንዲሰሩ ትመክራለች።
እኛም ከማህበሩ እንቅስቃሴ እንደተገነዘብነው በዓለም ደረጃ ማህበራቸውን፣ ክልላቸውን ሲዳማንና በአጠቃላይ ሀገራቸውን ማሳወቅና ማስጠራት ችለዋል። ለዚህ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያደረገላቸው ለ20 ዓመታት ብራዚል ስትሳተፍበት በቆየችው ዓለም አቀፉ የምርጥ ቡና ቅምሻ ውድድር አምና አሸናፊ መሆናቸው ነው። ሥራ አስኪያጁ ፓስተር ቦጋለ ‹‹ተወዳዳሪ መሆን ውጤታማ ያደርጋል›› ይላሉ። ውድድሩ ለአባላቱ የበለጠ እንዲሰሩ መነቃቃትን የፈጠረላቸው መሆኑንም አክለዋል። በሲዳማ ብሎም በወረዳቸውና በቀበሌያቸው የሚገኙ ብዙ ቡና አብቃይ አርሶ አደሮች የገበያ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ አስችሏል።
የሲዳማ ቡና በዓለም ገበያ እንዲታወቅ ለማድረግ የሩሙዳሞ አካባቢ ኦርጋኒክ ቡና ሰርተፍኬት እያስጠኑ ይገኛሉ። ለአርሶ አደሩም ስልጠና እየሰጡ ነው። ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያመጣው ቡና ነው። የሀገራችን ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃም ይፈለጋል። የአረቢክና ሌሎች የቡና ዝርያዎች በኢትዮጵያ ይገኛል። ሆኖም የቀድሞው ስርዓት ገበያውን አዳክሞት ቆይቷል። በመሆኑም መስራችዋና መገኛዋ ኢትዮጵያ እያለች እነ ብራዚል፣ ኮሎምቢያ ቬትናምና ታንዛንያ ቀድመው ሄደዋል። 20 ዓመት ሙሉ ብራዚል ነበረች ስትወዳደር የቆየችው። ከለውጡ በኋላ መንግስት በከፈተው ዕድል መሰረት አምና በምርጥ ቡና ቅምሻ ውድድር ኢትዮጵያም መወዳደር አለባት ተብሎ ከገባች በኋላ በውድድሩ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ተችሏል። ውድድሩ የሀገሪቱን ቡና ወደ ታዋቂነቱ መመለስ ችሏል። መንግስትም፣ አርሶ አደሩም፣ ላኪውም፣ ነጋዴውም ጥሩ ገቢ እንዲያገኝ አስችሏል። በተጨማሪም ቡና አዋጭ መሆኑ ታምኖበት በአሁን ወቅት መንግስት ከአረንጓዴ ልማት ጋር በማያያዝ ሊሰራበት እየሞከረ መሆኑን ለማየት ችለናል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2013