ወይዘሪት በላይነሽ ጌታቸው የተወለደችው በደቡብ ወሎ ዞን ወራኤሉ ከተማ አካባቢ ነው። በላይነሽ እህትም ወንድምም ያልነበራት ለአናቷም ለአባቷም ብቸኛ ልጅ ነች። የልጅነት ጊዜዋን እንደማንኛውም የአካባቢው ልጅ በእረኝነትና በጨዋታ ያሳለፈች ቢሆንም አባቷ በዘመኑ የትምህርትን ጥቅም የተገነዘቡ በመሆናቸው ገና በልጅነቷ ትምህርት ቤት እንድትገባ አድርገዋት ነበር። እናም እስከ ስምንተኛ ክፍል በመማርም ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ችላ ቆይታ ነበር። ነገር ግን በአስራ ዘጠኝ ዘጠና አራት ዓ.ም የበላይነሽ አባት በድንገት ስላረፉ ነገሮች ባሉበት መቀጠል የማይችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል።
በወቅቱ አንድ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲያስተምር የነበረ ወጣት ሊያገባት እንደሚፈልግ ለቤተሰቦቿ ጥያቄ ያቀርባል። እናቷም ጥያቄውን ተቀብለው እሷም በአካል እንደምታውቀው ሲረዱ ውሳኔው የሷ መሆኑን በመንገር ነገር ግን እሳቸው ብታገባው እንደሚመርጡና የምትወደውንም ትምህርቷን እንደሚያስተምራት ይነግሯታል። በላይነሽ ግን ለማግባት ሀሳብ እንደሌላትና ትምህርቷንም ለመቀጠል በቂ ሀብት አባቷ ስላፈሩላት ጥያቄውን እንደማትቀበለው ትናገራለች።
ወጣቱ ግን የሆዱን በሆዱ ይዞ ጥያቄውን አለመቀበሏም እንዳላስከፋው በመግለጽ ከቤተሰቡ ጋር መደበኛ ግንኙነት ይጀምራል። በ1995 ዓ.ም እሷ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ እያለች ሰውየው አብዛኛውን የእረፍት ጊዜ የሚያሳልፈው እነሱ ግቢ ነበር። በዚህም እቤታቸው ይኖር ከነበረ የእናቷ ወንድም ልጅ ጋር በጣም ስለተግባቡ ለአዳር ወደተከራየበት ቤት ከማቅናቱ ውጪ ኑሮውን በሙሉ ያደረገው እቤታቸው ነበር። ለበላይነሸም አንዳንድ ጊዜ የሚከብዳት ነገር ሲኖር ያስጠናታል፤ የምትፈልገው መጽሐፍም ካለ ያቀርብላት ነበር። በዚህ ሁኔታ ወራቶች ካለፉ በኋላ ወጣቱ የጀመረውን ዓመት ጨርሶ ትምህርቱን ለመቀጠል ሀሳብ እንዳለውና ከተቻለ አዲስ አበባ ካልሆነም ባህርዳር ለመሄድ እየተዘጋጀ መሆኑን ይነግራታል። ከወራት በኋላ ደግሞ ለቀጣይ ዓመት አንድ የግል ትምህርት ቤት በመምህርነት ሊቀጥረው መስማማቱን ይነግራትና የተጀመረው ዓመት ሲጠናቀቅ ኑሮውን ጠቅሎ አዲስ አበባ ለማድረግ መወሰኑን ይነግራታል።
አያይዞም እሷም ትምህርቷን ማቋረጥ እንደማይኖርባት በመንገር ምን አልባት ከሱ ጋር ላለመሆን የተስማማችው ለትምህርቷ አስባ ከሆነ እሱም ተመሳሳይ ሀሳብ እንዳለውና ዲግሪውን ሳይዝ ልጅ ለመውለድ ሀሳብ እንደሌለው ይነግራታል። ነገር ግን ፈቃዷ ከሆነ እሷም ትምህርቷን ስትጨርስ እሱም ተዘጋጅቶ አብሯት ለመሆን እንደሚፈልግና የረጅም ጊዜ እቅድ እንዳለውም ይነግራታል።
በላይነሽ ያቀረበላትን ሀሳብ ባትቀበለውም ለትምህርት ያለውን አቋም ታደነቅ ስለነበር ቀረቤታቸው እየተጠናከረ ይመጣል። በአጎቷ ልጅና በእናቷ ጥያቄ መሠረትም ሠራተኛ በሌለው ጊዜ እቤት እያመጣ ልብሱን ታጥብለት ትጀምራለች። አንድ ቀን ደግሞ የታጠበለትን ልብስ ሳይወስድ በመቆየቱ እቤቱ ይዛለት ትሄዳለች። እዚያም ስትደርስ ትንሽ አሞት እንደነበር ይነግራትና የሚያስፈልገውን ነገር ስታደርግለት ቆይታ አመሻሽ ላይ ወደ ቤቷ ትመለሳለች። ይህኛው ግንኙነት ግን እየተደጋገመ ይመጣና በላይነሽ ምክንያት ባይኖራትም ለጥናት ብቻ ወጣቱ የተከራየበትን ቤት መዳረሻዋ ታደርጋለች። ቁልፉን ያከራዩት ሰዎች ዘንድ ያስቀምጥ ስለነበርም እቤቱ ሄዳ ለመዋል የሱ መኖር አያስፈልጋትም ነበር።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ በድጋሜ የፍቅር ጥያቄ ያቀርብላትና ትምህርቷን እስክትጨርስ እንደሚጠብቃት በመንገር ቢያንስ ቃል እንድትገባለት ይጠይቃታል። እሷም ጥያቄውን ተቀብላ ነገር ግን ትምህርቷን ጨርሳ እስክትመረቅ ምንም ነገር ውስጥ እንደማይገቡ ቃል ተግባብተው የአዲሱን ጓደኝነት ምዕራፍ ይጀምራሉ።
በተደጋጋሚ ወደ እሱ ጋር የምታደርገው መመላለስ ጥርጣሬ የፈጠረባቸው እናት ግን ነገሩ ወደ ሌላ የሚዞር ከሆነ ከማርገዟ በፊት ሽምግሌ ተልኮ በወግ በማዕረግ ማግባት እንዳለባት ያሳስቧታል። እሷ ግን ነገሩ ይፋ ከወጣ እሱም የልብ ልብ ያገኝና ሌላ ነገር ተፈጥሮ ላረግዝ እችላለሁ በማለት ትቃወማለች። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች እናቷና የአጎቷ ልጅ የዘመድ ለቅሶ ሲሄዱ ብቻዋን እንዳታድር ወጣቱ መምህር አብሯት ያድር ዘንድ ይጠይቋታል። ብዙ ጊዜ ብቻቸውን አብረው ስላሳለፉ ምንም አይፈጠረም በሚል እሳቤ ቤተሰቦቿ እስኪመለሱ ሦስት ቀንና ሌሊቶችን አብረው ያሳልፋሉ። በእነዚህ ጊዜያትም እቤት ውስጥ ያሉትን ከብቶች ከመንከባከብ ጀምሮ ሁሉንም ሥራዎች የሚከውኑት አብረው ነበር።
በላይነሽ አብረው ለመሆን ስለተስማሙና ቃል ስለተግባቡ ተጠንቅቀው የፈለጉትን ማድረግ እንደሚችሉ ደግጋሞ የነገራትን በግማሽ ልቧ ትቀበለውና ውሏቸውን ብቻ ሳይሆን አዳራቸውንም አብረው ማድረግ ይጀምራሉ። በዚህ ሁኔታ የተጀመረው ተጨማሪው ግንኙነት ቤተሰቦቿ ከተመለሱም በኋላ እሱ ቤት እየሄደች አብሮ ማደር ይቀጥላሉ።
ከወራት በኋላ ግን በላይነሽ የወር አበባዋ እንደቀረ አወቀች። ወደ ጤና ጣቢያ በመሄድ እርግዝናው እውን መሆኑን ሲያረጋግጡላት ደግሞ ያላሰበችው መከራ ከፊቷ መደቀኑን ትረዳለች። የዚያኑ ቀን ማታም ትጠብቀውና የሆነውን ሁሉ ትነግረዋለች። እሱ ግን ማርገዟ ምንም ማለት እንዳልሆነና በፍጹም መረጋጋት እንዳለባት ይነግራታል። ይልቁንም ልትወልድ የምትችለው ክረምት ውስጥ በመሆኑ ትምህርቷም ላይ የሚፈጥረው ችግር እንደማይኖር በመግለጽ ባለችበት እንድትቀጥል ይነግራታል። በላይነሽ ግን እሱ ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ መዘጋጀቱን አስታውሳ ነገሩን እንዴት እንደዚህ በቀላሉ ሊያይ እንደቻለ ትጠይቀዋለች። አሁንም በተረጋጋ መንፈስ የሱ መሄድ የሚፈጥረው ነገር እንደማይኖር፣ እሷ ከፈለገች ደግሞ መቅረት እንደሚችልም ይነግራታል።
ለቀናት ስትብሰለሰል ከቆየች በኋላ አብሮ አደጓ ለሆነችና አግብታ የወለደች ጓደኛዋ ጋር በመሄድ ነገሩን ታዋያታለች። ጓደኛዋም የተፈጠረው ነገር አንዴ ተፈጥሯል ማስወረድ የሚባል ነገር እንዳትሞክሪ የዘላለም ጤናሽ ይዛባል። ይሄ ነገር ደግሞ ደብቀውት የማይዘለቅ በመሆኑ ቶሎ ለእናትሽ ንገሪያት። መስማቷ ለማይቀር ከውጭ ሰው ከሰማች ታዝንብሻለች ትላታለች። በላይነሽ በድጋሜ ቀናትን ካሳለፈች በኋላ የጓደኛዋን ምክር ተቀብላ አንድ ቀን አመሻሽ ላይ እናቷን ቤተ ክርስቲያን ይዛ በመሄድ የገጠማትን ችግር ትነግራቸዋለች። የእናትየው ምላሽ ግን በላይነሽ ከምትጠብቀው አልያም እሷ ውስጥ ካለው ሀሳብ ጋር በፍጹም የተለየ ሆኖ ታገኘዋለች።
እናት የተነገራቸውን ነገር የተቀበሉት እሷ እንደጠበቀችው ተደናግጠውና ጉድ ጉድ ብለው ሳይሆን የለመኑት ነገር የደረሰላቸው ይመስል አምላካቸውን በማመስገን ነበር። ቀጠል አድርገውም አሁን የሆነው ሆኗል ንገሪውና ሽማግሌ ይላክ ቀኑን ስትቆርጡ እኔም የአባትሽን ቤተሰቦች ጠርቼ እጠብቃችኋለሁ አሁን ሆድሽም ሳይገፋ ጽንሱም ሳይበረታ ሁሉም ነገር ማለቅ አለበት ይሏታል። በላይነሽ በፍጹም ግራ መጋባት ለእናቷ ምንም ሳትል ወደ ቤት ይመለሳሉ። ከዚህ በኋላ እናትም መቼ ሽማግሌዎቹ እንደሚመጡ እንድትነግራቸው ደጋግመው ሲጠይቁ ከቆዩ በኋላ ይብስ ብለው አንድ ቀን ነገሩን ለአባቷ ዘመዶች እንደነገሩና እየጠበቁ መሆናቸውን በመግለጽ ቶሎ እንድታሳውቃቸው ይነግሯታል።
የሚሆነው ሁሉ እውነት እውነት ሳይመስላት ለልጁ የሆነውን ሁሉ የእናቷንም መልዕክት ጨምራ ትነግረዋለች። እሱም ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ ከዚህ ውጪ ምንም አማራጭ እንደሌላቸውና እሱም የአዲስ አበባውን ሥራና ትምህርት መሰረዙንና ለሰዎቹም ማስታወቁን ይነግራታል። ይህን ጊዜ ለእሷ አስጨናቂ የሆነው ነገር የእኔ በምትላቸው ሰዎች ዘንድ በደስታ ተቀባይነት ማግኘቱ ግራ ይገባትና በታላቅነት ያሳደጋትና አለኝ ለምትለው ወንድሟ ለመንገር ትወስንና ጊዜ ጠብቃ እሱንም የሆነውን የተፈጠረውን ሁሉ ትነግረዋለች። በዝምታ ሲያዳምጣት ከቆየ በኋላ እና ቀኑን መቼ ቆረጣችሁ ይላታል። በላይነሽ ነገሩ ሁሉ ግራ እየገባት ይመጣል። ይደነግጣል አልያም ይቆጣል ብላ የጠበቀችውም ሰው ነገሩን እንደቀላል ሲመለከተው መጠርጠር ትጀምራለች።
በድጋሚ ግራ እንደገባት ቀናትን ካሳለፈች በኋላ የአጎቷን ልጅ ቤተክርስቲያን ወስዳ የሚያውቀው ነገር እንዳለ ሳይደብቅ እንዲነግራት ታስገድደዋለች። እሱም አሁን ስለተፈጠረው ነገር የሚያውቀው ነገር ባይኖርም አባቷ ከማረፋቸው በፊት ልጄን በወግ በማዕረግ ድረሽ ትልቅ ሰው እንድታደርጊያት፤ ብለው ቃል እንዳስገቧቸው፤ እሳቸውም በሕይወት እያሉ አንድ ልጃቸው አግብታ ስትወልድ ማየት እንዳለባቸው እናትየው ሲናገሩ መስማቱን ይነግራታል። ይሄኔ እሷ ባላሰበችው መንገድ የሦስት ጉልቻ ሕይወት ሲጠመድላት እንደነበርና እሷም ሳታስተውል እንደገባችበት ትረዳለች። የአጎቷ ልጅ ግን መናደዷን ሲመለከት እንድትረጋጋ በማድረግ ወደ እናቷ ይዟት ይሄዳል። እናትም የአንድ ልጃቸውን ወግ ማዕረግ ለማየት እንደሚፈልጉና ይህንን ለአባቷ የገቡት ቃል በመሆኑ ነገሩን በደስታ መቀበላቸውን፤ ነገር ግን ተነጋግረው የሰሩት ምንም ነገር እንደሌለ ይነግሯታል። ጨምረውም «ትዳርን የተቃና የሚያደርገው ፈልገሽ መግባትና አለመግባትሽ ብቻ ሳይሆን ከገባሽ በኋላ የሚኖራችሁ ስምምነትና መቻቻል ነው» ይሏታል። ሰርጉም እንደ ነገሩ ይደገስና ከሰርጓ አራት ወራት በኋላ ወንድ ልጅ ለመገላገል ትበቃለች።
በላይነሽ የተፈጠረውን ነገር ተቀብላ ትምህርቷንም እየተማረች ልጇንም እያሳደገች ለሦስት ዓመታት ያህል ከቆየች በኋላ አዲስ ወሬ ትሰማለች። ባለቤቷ ከዚህ ቀደም ትዳር የመሠረተ ልጅም የወለደ መሆኑ ይነገራታል። ይህን ጊዜ ወደ ቤተሰቦቹ ቤት ለምን ይዟት እንደማይሄድ፣ ከቤተሰቦቹም ወንድምና እህቱ ብቻ እየመጡ ያዩዋት የነበረው ምክንያት ቢኖራቸው የሚል ነገር ይፈጠርባታል። በግሏ ነገሩን ለማጣራት ትንሽ ከሞከረች በኋላ እንደማይሳካ ሲገባት በቀጥታ እሱን ትጠይቀዋለች። ነገሩ እውነት መሆኑን ነገር ግን ወደ እነሱ አካባቢ ከመምጣቱ ከሦስት ዓመታት በፊት በሕጋዊ መንገድ ከሚስቱ መለያየቱን በአሁኑ ወቅትም የዘጠኝ ዓመት ልጅ እንዳለው፤ ነገር ግን ይህንን ቢነግራት ልትለየው ስለምትችል እስከ ጊዜው ብሎ እንደደበቃት ይነግራታል።
በዚህ ወቅት ደግሞ በላይነሽ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ወስዳ ነጥቧም ትምህርቷን ለመቀጠል አልሞላላት ብሎ በብስጭት ውስጥ ነበረች። እናም አድመው የሰሩብኝን ተቀብዬ አልኖርም ብላ ለራሷ ቃል ትገባና አዲስ የሕይወት መስመር ለመጀመር ለራሷ ቃል ገብታ ዝግጅት ትጀምራለች። የአላማዋ መድረሻ ደግሞ የገጠር ኑሮን እርግፍ አድርጋ ትታ አዲስ አበባ መከተም ሲሆን ለዚህም ቀድማ የምታውቃትንና አዲስ አበባ የምትኖር ጓደኛዋን መጠቀም ሆነ። ቀስ እያለችም መረጃ ስታሰባስብ ከቆየች በኋላ ለጓደኛዋ ከባለቤቷ ጋር መስማማት እንዳልቻለችና የገጠር ኑሮም እንደበቃት ትነግራታለች። ለእናቷም ይህንን አጫውታቸው ልጁን ይዘሽ አትሄጂም እንዳሏትና እሷም ብቻዋን አዲስ አበባ ለመግባት መወሰኗን በማዋየት ሥራ እስከምታገኝ ድረስ ማረፊያ እንድትሆናት ትጠይቃታለች።
ጓደኛዋም ኮተቤ ካራ አካባቢ ትንሽ ምግብ ቤት ከፍታ እየሰራች በመሆኑ ካልከበደሽ ከእኔ ጋር እየሰራሽ ትቆያለሽ፤ ካልሆነም አንድ ሥራ ፈልገን የፈቀድሽውን ትሰሪያለሽ፤ ነገር ግን ጠፍተሽ መጥተሽ ከቤተሰቦችሽ እንዳታቀያይሚኝ በማለት ብትመጣ እንደምትቀበላት ቃል ትገባላታለች። በላይነሽም ጊዜ መርጣ ገበያ አቅንተው በግና እህል ሸጠው በተመለሱ ማግስት እናቷ እንዳይቀየሟት የይቅርታ ደብዳቤ አስቀምጣ እቤት ያለውን ብር ይዛ ጉዞዋን ወደ ሸገር ታደርጋለች።
አዲስ አበባ ገብታም ከጓደኛዋ ጋር በትንሿ ምግብ ቤት እየሰራች ትንሽ ከሰነበተች በኋላ የራሷን ቤት ተከራይታ መኖር ትጀምራለች። ይህ ሁሉ ሲሆን ቀስ እያለች እናቷና ልጇ ያሉበትን ሁኔታ ታጣራ ነበር። ለካስ ቤተሰቦቿ ያሉበትን ሁኔታ እንደሚነገራት ሁሉ ለባለቤቷም እሷ ያለችበትን ሁኔታ ሹክ የሚለው ሰው ነበር። እናም አዲስ አበባ ከገባችና ዓመት ከስድስት ወር ካሳለፈች በኋላ፣ የተላከላትን ፖስታ ስትከፍተው፣ ባለቤቷ አንድ ቀን ሊገናኙና አብረው ሊሆኑ እንደሚችሉ በመግለጽ ትዳርም ሳትመሰርት ልጅም ሳትወልድ እንድትጠብቀው በማሳሰብ የልጇን ፎቶ አብሮ ልኮላት ታገኛለች።
ነገሩ እውነት የሚሆን ባይመስላትም አንደኛ ልጇ ያለበትን ሁኔታ በማወቋ ሁለተኛ ባለቤቷም ከያዙኝ ልቀቁኝ በዚህ መንገድ መምጣቱ እያስደሰታት ኑሮዋን ትቀጥላለች። በዚህ ጊዜ ግን ጓደኛዋ የሥራ ቦታ መቀየር ስለፈለገች ምግብና አረቄ የሚሸጥባትን ትንሽ ጎጆ በስምምነት በትንሽ ክፍያ ለበላይነሽ አዛውራላት ነበር። በላይነሽ አዲስ አበባ በመግባት ለመቀጠል ያሰበችው የትምህርቷ ጉዳይ ባይሳካም ነገን ተስፋ በማድረግ በዚያች ቤት በምትሰራው ሥራ እራሷን እያስተዳደረች መኖርን ትቀጥላለች።
በአጠቃላይ አገሯን ለቃ ከወጣች ከሁለት ዓመት ከሦስት ወር በኋላ አንድ እሁድ ጓደኛዋ ለብርቱ ጉዳይ እንደምትፈልጋት ትቀጥራትና ታገኛታለች። እንደመጣችም አንድ ክርስትና ስላለብኝ አብረሽኝ እንድትሄጂ ፈልጌ ነው፤ ልብስ ቀይሪና ተነሽ እንሂድ ትላታለች። ሥራ የምታግዛትን ልጅ ትለምንና ወደማታወቀው የክርስትና ፕሮግራም ጉዞ ትቀጥላለች። ጣፎ አካባቢ ደርሰው ወደ ውስጥ ትንሽ የእግር መንገድ ከተጓዙ በኋላ አንድ ግቢ አንኳኩተው ይገባሉ። በመጀመሪያ በሩን ከከፈቱት ልጆች መካከል የጓደኛዋ ልጅ አንዱ ነበር። በላይነሽ ምንም የገባት ነገር ስላልነበር ስሙን ጠርታ ሰላም ስትለው በአንጻሩ እናትየው ለምን ወጣህ ብላ ታንባርቅበታለች።
የዚህን ጊዜ በላይነሽ የልጁ እዚህ መገኘት እንዴት ሊከሰት እንደቻለ ግራ ይገባትና ብቻውን ልከሽው ነው? ስትል ጓደኛዋን ትጠይቃለች። ጓዳኛዋም አይ አይደለም ነይ ውስጥ ገብተን እናውራ ብላ ይዛት ወደ ውስጥ ትገባለች። የጓደኛዋን እግር እየተከተለች የገባችው በላይነሽ ግን በቤት ውስጥ የጠበቃት የማታወቀው የልደት ዝግጅት ሳይሆን ባለቤቷና ልጇ ነበሩ።
በድንጋጤ ባለችበት የደነዘዘችው በላይነሽ ማልቀስ የጀመረችው ባለቤቷ ሂድና ሰላም በላት ብሎ ልጇን ወደ እሷ ሲገፋው ነበር። ከቆይታ በኋላ ደግሞ ነገሩን ሁሉ ሆን ብለው እንዳዘጋጁትና ባሏም አዲስ አበባ ሲመላለስ ቆይቶ ሥራ መጀመሩን ይህንንም ቤት ተከራይቶ እንደሆነና ፈቃዷ ከሆነ አብረው እንዲሆኑ ይጠይቃታል። የእህል ውሃ ነገር ሲባል አላምንም ነበር የምትለው በላይነሽ ዛሬ ሦስተኛ ልጇን ወልዳ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ያደረሰች ሲሆን ባለቤቷ ከመጀመሪያ ሚስቱ የወለደውንም ልጅ እያሳደገች ትገኛለች።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2013