የልብስ ስፌት ሞያ ፍቅር ያደረባቸቸው በትውልድ አካባቢያቸው አንድ እግር ብቻ ያለው ሰው ልብስ ሲሰፋ ተመልክተው ነው። ገና በልጅነታቸው በውስጣቸው ሲንቀለቀል የነበረውን የልብስ ስፌት ፍላጎት ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከአጎታቸው ጋር በመስራት ‹‹ሀ›› ብለው ጀምረዋል። በተለያዩ የልብስ ስፌት ቤቶች ውስጥ ተቀጥረውም ሰርተዋል። በሂደትም የራሳቸውን አነስተኛ የልብስ ስፌት መደብር ከፍተው ከአዲስ አበባ እስከ ጅማ፤ ከጅማ እስከ ድሬዳዋ ድረስ ተዘዋውረው ሰርተዋል።
ከዚሁ የልብስ ስፌት ስራቸው ጎን ለጎንም በሶማሌ ጦርነት ተሳትፈው ሀገራቸውን ከጠላት ለመከላከል የዜግነት ግዴታቸውን ተወጥተዋል። ለረጅም አመታት በቆዩበት የልብስ ስፌት ስራም ሞያውን ለሌሎች ሰዎች በማስተላለፍ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል። የልብስ ስፌት ቤታቸው ከአንድም ሁለት ጊዜ በእሳት ቢወድምም ተስፋ ባለመቁረጥ ዛሬም የሚወዱትን ስራ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እያከናወኑ ይገኛሉ – የያምራል ልብስ ስፌት ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ዮሃንስ ገብረሕይወት።
አቶ ዮሀንስ እድገትና ውልደታቸው በትግራይ ክልል በቀድሞው አድዋ አውራጃ ራማ ወረዳ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ አካባቢያቸው የጀመሩ ቢሆንም እስከ ሶስተኛ ክፍል ከተከታተሉ በኋላ ትምህርታቸውን አቋርጠው በአስራ አንድ አመታቸው ወደ አዲስ አበባ መጡ። ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላም በአፍሪካ አንድነት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ስድስተኛ ክፍል ተከታተሉ። ሆኖም በግዜው የሀገሪቱ ሁኔታ የተረጋጋ ባለመሆኑ ትምህርታቸውን መቀጥል አልቻሉም።
ትምህርታቸውን ከስድስተኛ ክፍል አቋርጠው ከአጎታቸው የልብስ ስፌት ሞያን ቀስመው ጣልያን ሰፈር አካባቢ አብረው መስራት ጀመሩ። ጥቂት እንደሰሩም ፒያሳ ሲኒማ አምፒር ጎን በአንድ ዘመናዊ የልብስ ስፌት ውስጥ ተቀጥረው ለሶስት አመታት አገለገሉ። በወቅቱ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ ጥሩ ያልነበረ በመሆኑና በአዲስ አበባ ከተማም እንደልብ መስራት የማይቻልበት ሁኔታ በመፈጠሩ ለተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ጅማ አጋሮ አቀኑ። በጅማ የልብስ ስፌት ስራን ለሁለት አመታት ተቀጥረው ሲሰሩ ቆዩ።
ከሁለት አመት በኋላ ዳግም ወደ አዲስ አበባ ቢመለሱም አሁንም ሁኔታው ጥሩ ባለመሆኑ ወደ ድሬዳዋ አቅጣጫ ቀይረው ሄዱ። በድሬዳዋም ከስድስተኛ ክፍል ያቋረጡትን ትምህርት በማታ መርሃ ግብር ቀጥለው እስከ ስምንተኛ ክፍል ተከታተሉ። ከስምንተኛ ክፍል ትምህርት በኋላም ፊታቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ ልብስ ስፌት ስራው አዞሩ። በድሬዳዋ አንደኛ መንገድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አፍሮ የተሰኘ ልብስ ስፌት በትንሽ ገንዘብና አነስተኛ ሲንጀር ከፍተው መስራት ቀጠሉ ። ይሁንና ወቅቱ ሀገሪቱ በሶማሌ የተወረረችበት በመሆኑ በብሄራዊ ውትድርና ውስጥ በመግባት ለሁለት አመት ያህል ጠላትን ተዋጉ። ጦርነቱ በኢትዮጵያ አሸናፊነት እንደተጠናቀቀ ከግዳጅ መልስ ዳግም ወደ ድሬዳዋ ተመልሰው የልብስ ስፌት ስራውን ቀጠሉ።
በድሬዳዋ ታይዋን ገበያ አዳራሽ የራሳቸውን ልብስ ስፌት ዳግም በመክፈት ስራውን ተያያዙት ። በልብስ ስፌት ሞያቸው በተለይ ደግሞ በወይዛዝርት ልብስ ስፌት በድሬዳዋ እውቅናን አተረፉ። የተሻለ ገቢም ማግኘት ቻሉ። እዛው ድሬዳዋ እንዳሉም ትዳር መስርተው ልጆች ወለዱ። በልብስ ስፌት ስራ በድሬዳዋ ለበርካታ አመታት በመቆየትም ጥሩ ግዜ አሳለፉ።
በመሀል ላይ ግን ያልጠበቁት ነገር ተከሰተ። በድሬዳዋ ልብስ በሚሰፉበት አዳራሽ እሳት በመነሳቱ የእራሳቸውም መደብር ሙሉ በሙሉ በእሳት ጋየ ። ተስፋ ባለመቁረጥም እንደገና ከዜሮ በመነሳት ሌላ የልብስ ስፌት መደብር እዛው ከፍተው የሚወዱትን የልብስ ስፌት ስራ ቀጠሉ። በድሬዳዋ የልብስ ስፌት ስራ ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ የመንግስት ለውጥ ሲመጣ ድሬዳዋን ለቀው ወደ አዲስ አበባ መጡ።
ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላም የልብስ ስፌት ስራውን ለማስቀጠል ነገሮች አልጋ በአልጋ አልሆኑላቸውም። በሂደት ግን በኮልፌ የገበያ አዳራሽ መደበር ይዘው የልብስ ስፌት ስራ ጀመሩ። ጥቂት ሰርተው ወደ ትርፍ ሊሸጋገሩ ሲሉ ድሬዳዋ ያጋጠማቸው እሳት እዚህም አገኛቸው። የኮልፌ የገበያ አዳራሽ ሲቃጠል የእርሳቸው የልብስ ስፌት መደብር ከነሙሉ ንብረቱ ወደመ።
አሁንም ተስፋ ባለመቁረጥ እንደገና ኮተቤ መንገድ ላምበረት አካባቢ መጥተው የቀበሌ ቤት በአነስተኛ ገንዘብ ተከራይተው ትእግስት ዮሃንስ የጨርቃጨርቅና ልብስ ስፌት ድርጅት በሚል ስያሜ በአነስተኛ ወጪ ስራ ጀመሩ። ከዛ ግዜ ጀምሮ አስካሁን ድረስ በዚሁ ቦታ ላይ የልብስ ስፌት ስራን እየሰሩ ይገኛሉ። በቅርቡም ድርጅቱን ያምራል የልብስ ስፌት ድርጅት በሚል ሰይመዋል ።
በአሁኑ ግዜም የልብስ ስፌት ድርጅታቸው ከጓንትና ከካልሲ ውጪ ማንኛውንም የልብስ ስፌት ስራዎችን ይሰራል። ማንኛውንም በትእዛዝ የሚመጡ የቱታ፣ ሽርጥ፣ ኮትና ሱሪ፣ ገዋን፣ የሆስፒታልና የትምህርት ቤቶች የደምብ ልብሶች፣ የተማሪዎች ዩኒፎርም፣ የተለያዩ መስሪያ ቤቶች የደምብ ልብሶች ስራዎችን ያከናውናል። የተለያዩ ጨረታዎች ላይ በመሳተፍም የልብስ ስፌት ስራዎችን ይሰራል።
ልብስ ለማሰራት የሚፈልጉ ደምበኞች ወደ ድርጅቱ ሲመጡ ተለክተው እንደየፍላጎታቸው ይሰራሉ ። በትእዛዝ የሚሰሩ ስራዎች ደግሞ ጨረታዎችን በመወዳደርና በማሸነፍ ውል በመዋዋል ነው የሚሰሩት። በአብዛኛውም ልብስ በማቅረብ ለተለያዩ የግልና የመንግስት ተቋማት የልብስ ስፌት ስራዎችንም ድርጅቱ ያከናውናል። ለስራው በግብአትነት የሚውሉ ክሮችን፣ ቁልፎችንና ጨርቆችንም ከመርካቶ አከፋፋዮች ያስመጣል።
ድርጅቱ ሰራተኞችን በቋሚነት ቀጥሮ ባያሰራም ስራ ሲመጣ ሰራተኞችን በኮንትራት ቀጥሮ ያሰማራል። እንደስራው ብዛትም እስከ አስር የሚሆኑ ሰራተኞችን በማሳተፍ ያሰራል። በትንሽ ገንዘብ ስራውን የጀመረው ድርጅታቸው በአሁኑ ግዜ ያን ያህል የሚጋነን ባይሆንም እስከ 200 ሺ ብር የሚጠጋ ካፒታል አለው።
ወድቆ በመነሳት በልብስ ስፌት ስራ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱት አቶ ዮሃንስ የልብስ ስፌት ስራ ገና ያልተነካ የስራ ዘርፍ ከመሆኑ አኳያ በቀጣይ ስራውን አስፍተው የመስራት እቅድ እንዳላቸው ይናገራሉ። በተለይ ደግሞ ለልብስ ስፌት ስራው የሚያስፈልጉ ዘመናዊ የመስፊያ ማሽኖችን በበቂ ሁኔታ በማሟላትና አቅማቸውንም በመገንባት ስራውን በዘመናዊ መልኩ ለማከናወን ውጥን አላቸው። ለዚህም በቂ ካፒታልና የሰው ሃይል እንደሚያስፈልጋቸው ያመለክታሉ።
ከግል ባንኮችና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር ለማግኘት በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበው እንደነበርና ሆኖም ካርታ አልያም ሌላ ንብረት እንደማስያዢያ እንዲያቀርቡ በመጠየቃቸው ብድሩን በቀላሉ ማግኘትእንዳልቻሉም ያስረዳሉ። ሞያው እንዳላቸውና ገንዘቡ ከተገኘ የልብስ ስፌት ስራውን በተሻለ ደረጃ ለመስራት ራዕይ ሰንቀዋል። ሆኖም ግን ውጤታማ ለመሆን ሞራልና ዕቅድ ቢኖራቸውም በኢኮኖሚ የአቅም ውስንነት ምክንያት የልብስ ስፌት ስራውን ማሳደግ እንዳልቻሉም ይጠቁማሉ።
የልብስ ስፌት ስራ ገና ብዙ ሊሰራበት የሚችል የሞያ ዘርፍ ቢሆንም ስራውን ለማከናወን ዋነኛና መሰረታዊ ችግሩ በቂ አቅም አለመኖር ነው ይላሉ። ከዚህ ውጪ ግን ሌላ ችግር እንደሌለው ያሰምራሉ። ከዚህ አንፃር በተለይ በአነስተኛ ደረጃ በዚህ የስራ ዘርፍ ተሰማርተው ላሉ ሰዎች በመንግስት በኩል የገንዘብ ብድር አቅርቦት ሊኖር እንደሚገባ ይጠቁማሉ።
ወደዚህ የልብስ ሰፌት ሞያ ለመግባት ያናሳሳቸው በትውልድ አካባቢያቸው ገና ልጅ እያሉ የተመለከቱን አንድ እግር ብቻ ያለው ልብስ ሰፊ መሆኑን የሚያስታውሱት አቶ ዮሃንስ ከዛ ግዜ ጀምሮ ስራውን እንደሚወዱትና እንደሚያከብሩት አሁንም እየሰሩበት እንደሚገኙ፤ ነገር ግን አቅም ስላነሳቸው የማይተውት ሞያ መሆኑን ይገልፃሉ። አቅሙን ካገኙ አንድ ቀን ሞያውን ወደተሻለ ደረጃ እንደሚያደርሱትም ይተማመናሉ።
አቶ ዮሃንስ በዚህ የልብስ ስፌት ስራ በሞያው እርካታ ቢኖርኝም ውጤት ለማምጣት ግን ገና ይቀረኛል ይላሉ። ውጤት ላለመምጣቱ ደግሞ ከአንድም ሁለት ግዜ ንብረታቸው በእሳት መውደሙን በምክንያትንት ያነሳሉ። አሁንም ግን በሞያው ሌት ተቀን ቢሰሩ እንደማይሰለቹና አንድ ቀን ለውጤት እንደሚበቁም ይናገራሉ። ለዚህም በዘርፉ ያሉ አዳዲስ ነገሮችን ለመመማርና የተማሩትን ወደተግባር ለመለወጥ ሁሌም ጥረት እንደሚያደርጉ ያስረዳሉ።
ሁሉንም ነገር ከመንግስት ጠብቆ የማይቻል ከመሆኑ አኳያ ወደዚህ የልብስ ስፌት ስራ የሚገቡ ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ስራውን ለማሳደግ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው ይጠቁማሉ። መነሻ ነገር ካገኙ በአነስተኛ አቅም ስራውን ጀምረው ከፍ ወዳለ ደረጃ መድረስ እንደሚችሉም ይመክራሉ።
እርሳቸው ካካበቱት የረጅም ግዜ የልብስ ስፌት ሞያ በመነሳትም ወደሞያው ለሚቀላቀሉ አዳዲስ ሰዎች የልብስ ስፌት ስራ ጥሩና ወደውት የሚሰሩት መሆኑን ተናግረዋል። በተለይ ወደዚህ ሞያ የሚገቡ ወጣቶች በግዚያዊ ትርፍ ሳይዘናጉ ጥራትን በማስቀደም የወደፊቱን ውጤት አስበው ስራቸውን ማከናወን እንደሚገባቸው ይመክራሉ። ማየት ያለባቸው ነገር ደምበኞቻቸው ምን ያህል በስራቸው መርካታቸውን መሆኑንም ይጠቁማሉ።
አቶ ዮሃንስ ለሞያቸው መስዋትነት በመክፈልና ወድቆ በመነሳት ተስፋ ሳይቆርጡ ለረጅም አመታት በልብስ ስፌት ሞያ ቆይተው የተሻለ ውጤት ለማምጣት እያደረጉ ያሉትን ጥረት እያደነቅን ሌሎች ወጣቶችም የእርሳቸውን ፅናት በአርያነት በመከተል በዘርፉ ገብተው ለውጤት አንዲተጉ መልእክታችንን እናስተላልፋለን። ሰላም!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2013