የግብርናው ዘርፍ የሀገሪቱ የጀርባ አጥንት እንደሆነ ይታወቃል። ይሁን እንጂ የግብርና ሥራው በባህላዊ መንገድ ዝናብን ጠብቆ በዓመት አንዴ የሚከናወን በመሆኑ በሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ ሳያስገኝ ቆይቷል። ኢትዮጵያ ባለፉት 10 አመታት ግብርና መር ኢንዱስትሪ ስትከተል ብትቆይም በዚህም ውጤታማ የሚባል የሚጠበቀውን ያህል ለውጥ አልተገኘም። ክፍተቶች ቢኖሩም ተስፋው አልተሟጠጠም። በ2030 ዘላቂ የልማት ግብ በአስር አመት መሪ ዕቅድ የተሸጋገረ ግብርናን ዕውን ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል። ዕቅዱን እውን ለማድረግም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በጋራ በመረባረብ በመሥራት ላይ ናቸው።
ከነዚህ መካከልም ፕሪሳይስ ኮንሰልት ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አንዱ ሲሆን፣ ተቋሙ ስትራቴጂ፣ አቅጣጫ፣ ፖሊሲንና ሌሎች ጉዳዮችን መሰረት በማድረግ በጤና፣ በፋይናንስ ምጣኔ ሀብትና በግብርናው ዘርፍ የሚሰራ ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው። አሁን ላይ በነዚሁ ላይ የስምንት ወር የሙከራ ፕሮጀክት ቀርጾ እየሰራ ይገኛል። ፕሪሳይስ በቅርቡ በግብርናው ዘርፍ የፖሊሲ አቅጣጫዎችና የሕግ ማዕቀፎችን የተመለከቱ ተግዳሮቶችን መፍታት በሚያስችል ዙርያ በሁለት ባለሙያዎች ያስጠናቸውን ጥናቶች ይፋ ባደረገበት መድረክ ላይ ተገኝተን ነበር። የፕሪሳይስ አማካሪ ወይዘሮ ሄለን ጌታው እንዲሁም የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት አቶ አማረ ለማ በመድረኩ ጥናቱን አቅርበው ነበር። ጥናት አቅራቢዎቹ በጥናት ግኝታቸው በግብርናው ዘርፍ ያሉ የፖሊሲ ተግዳሮቶች በቅድመ ጥናት ነጥረው መውጣታቸውንና በግብርናው ዘርፍ ቅድሚያ በተሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት መደረጉን ጠቁመዋል።
እንደ ጥናት አቅራቢዎቹ በተለይም የፋይናንስ አቅም ለግብርናው ዘርፍ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል። የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ አማረ ለማ ለግብርናው ዘርፍ ዕድገት የገንዘብ አቅርቦት ወሳኝ ነው። በዘርፉ ያሉ ጉድለቶች ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ናቸው። ቢሆኑም የገንዘብ እጥረት የዘርፉን ዕድገት ሰቅዘው ከያዙት መካከል አንዱ ነው። ገንዘቡን ከማቅረብ ጎን ለጎን ገንዘቡን በትክክል ለታለመለት ዓላማ ማዋልም እንዲሁ ክፍተት መሆኑን አንስተዋል።
ለምሳሌ ያህል የጠቀሱትም፤ አንድ ፕሮጀክት ፋይናንስ ከተደረገ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አለበት። ለውጤቱም የፕሮጀክቱ ዘላቂ አስተማማኝነት ወሳኝ ነው። አስተማማኝ ከሆነ ሙስናና ብልሹ አሰራርን መከላከል በሚያስችል ቁጥጥርና ክትትል ስርዓት መታገዝ አለበት። ፕሪሳይስ ያስጠናው ጥናት በዚህ መልኩ ዘላቂና የታለመለትን ውጤት እንዲያመጣ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን በጥናቱ መመላከቱን ገልፀውልናል። ይሄ አሰራር ሙስናን ያጠፋና ውድድር እንዲኖር ስለሚያደርግ ጥሩ ሥራ እንዲሰራ እንደሚያግዝም የኢኮኖሚ ባለሙያው በአቀረቡት ጥናት ማጠቃለያ ላይ ተናግረዋል።
ሌላዋ በግብርናው ተግዳራቶች ዙርያ ጥናት ያቀረቡት ወይዘሮ ሄለን ጌታው በበኩላቸው ጥራትና ደህንነቱ የተጠበቀ ምርት ማምረትና ማቅረብ ከተቻለ በግብርናው ዘርፍ የሚፈለገው ውጤት እንደሚመጣ ገልፀዋል። ከዚህ አኳያ በተለይ በአግሮ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩና ምርታቸውን ወደ ውጪ የሚልኩ ተቋሞች ምርታቸው ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ማድረግ እንዳለባቸው መክረዋል። በርበሬ ላይ ውሃ ማርከፍከፍ፣ ጥራቱና ደህንነቱ ያልተጠበቀ ምርት ወደ ውጪ ለመላክ መሞከር ሀገርንም ላኪውንም እንደሚጎዳ ጠቁመዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከውጪ የምታስገባው ምርት መጠን ከፍተኛ ቢሆንም የምትልከው እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን አስታውሰዋል። ጥናታቸው የዚህን ሚዛን ማመጣጠን የሚያስችል መሆኑን በመጥቀስ ነው ሀሳባቸውን የቋጩት።
በመድረኩ የመግቢያ ንግግር ያደረጉት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ወይዘሪት ምህረት ታምር እንደተናገሩት የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ ጤናና የፋይናንስ ምጣኔ ሀብትን ጨምሮ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ ድጋፍ ማድረግ ሲሆን፣ በተለይም በዘርፉ ንግድ ላይ የተሰማሩ ለማህበረሰባዊ ቁጠባዊ ዕድገት የሚጠበቅባቸውን አስተዋጾ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ነው። እንደሀገር በግብርናው ዘርፍ ያለው ዕምቅ ሀብት ቢኖርም በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ባለመዋሉ የአመራረት ዘዴው በቴክኖሎጂ መታገዝ ይኖርበታል። በቴክኖሎጂ የታገዘ ምርት ማምረት ጠቀሜታው ዘርፈብዙ ነው።
ከዚህ ውስጥ አንዱ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ሌላው ደግሞ ብክነትን መቀነስና ጥራትን መጨመር፣ እንዲሁም እሴት በመጨመር ተጠቃሚነትን ከፍ ማድረግ ነው። በተለይም እሴት መጨመር ምርትን ለረጅም ጊዜ ለማቆየት ይረዳል። ይህ ደግሞ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያግዛል። ወደ ውጪ የሚላከውን የግብርና ውጤትና ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባን ምርት ለማመጣጠንም ይረዳል። ይሄን ታሳቢ ያደረገ ሥራ ለመሥራት ደግሞ ግብርናው በማቀነባበር ሥራ ላይ ከተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ ያስፈልጋል። የዚህም ጥቅም ጥራት ያለው ምርት ለማቅረብ ይረዳል። ግብርናውና ኢንደስትሪው ተመጋጋቢ መሆናቸው ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ሚናቸው የጎላ ይሆናል። በመሆኑም በትኩረት መሰራቱ ጥቅሙን ከፍተኛ ያደርገዋል።
እነዚህ ተግባራት የሚፈፀሙባቸው የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎች አጋዥ መሆን ይኖርባቸዋል። ፕሪሳይስ በህግ ማዕቀፎች ክፍተቶች ካሉ የፈተሸና የመረመረ ሳይንሳዊ ጥናት ያካሂዳል። ያሉትን ክፍተቶችና የመፍትሄ ሀሳቦችንም ለሚመለከተው አካል ያቀርባል። አፈፃፀማቸውንም ይከታተላል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም በተለያየ መልኩ ድጋፍ ያደርጋል።
እንደ አስተባባሪዋ ወይዘሪት ምህረት ማብራሪያ ተቋማቸው በተለይ የግብርናው ዘርፍ ወደ ኢንዱስትሪው መር ኢኮኖሚ ሽግግር እንዲያደርግ በትኩረት እየሰራ ይገኛል። በግብርና ሥራ ኑሮውን የሚመራው አርሶ አደር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ ያመረተውንም ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን ለውጪ ገበያም በማቅረብ ገቢውን በማሳደግ ኑሮውን ማሻሻል ይኖርበታል። እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ደግሞ በጥናት የተደገፈ እገዛ ያስፈልገዋል።
ተቋሙም በጥናት የተደገፈ ሥራ በመስራት ሚናውን በመወጣት ላይ ይገኛል። አርሶአደሩ በቀን ሶስቴ መመገብ በመቻሉ ብቻ ኑሮው ተለውጧል ማለት አይቻልም። ይሄን መቀየርና አርሶ አደሩ የተመጣጠነ ምግብ መብላት እንዲችል ማድረግ ያስፈልጋል። በቂና የተመጣጠነ ምግብ ያገኘ ማህበረሰብ ጤናማ አምራች ዜጋ ይሆናል። ተቋሙ አስጠንቶ ይፋ ያደረገው የጥናት ውጤትም ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የሚደረገው ሽግግር እንዲሳካ፣ ለዚህም የግብርና ፋይናንስ አስፈላጊ መሆኑን ለማመላከት እንደሆነ አመልክተዋል። የግብርና ምርት ጥራትና ቁጥጥርም በጥናቱ ተካትቷል።
ወይዘሪት ምህረት የግብርና ፋይናንስ አስፈላጊነት ላይም ባደረጉት ገለፃ የግብርናው ዘርፍ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት አዋጪ ከሆኑት መካከል ይጠቀሳል። ይሄን ታሳቢ በማድረግ ሀገሪቱ ግብርና መር የኢንደስትሪ ሽግግር ብትከተልም ቁጠባዊ ዕድገት ማስመዝገብ አልተቻለም። ይህ ደግሞ ወደ 22 ሚሊዮን በምግብ ራሳቸውን ያልቻሉ የማህበረሰብ ክፍሎች እንዲገኙ ምክንያት ሆኗል። ለዚህ ተግዳሮት መነሻ ይሆናል ተብሎ የታሰበውና በጥናት የተደገፈው ሀሳብ ከፋይናንስ አቅርቦት ጋር ይያያዛል። እስካሁን ባለው አሰራር የግብርና ዘርፉ ማግኘት ያለበትን ያህል የፋይናንስ አቅርቦት አላገኘም። ላለማግኘቱ ምክንያቶቹ የተለያዩ ሲሆኑ፣ ግብርና ተኮር የሆነ ባንክና ኢንሹራንስ አገልግሎት አለመኖር ይጠቀሳል።
የግብርና ሥራ በተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭ በመሆኑ በምርትና ምርታማነት ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው። በመሆኑም የመድን አገልግሎት ያስፈልገዋል። አርሶ አደሮች የብድር አገልግሎት ሊመቻችላቸው ይገባል። ሌላው እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ተግዳሮት፤ የፋይናንስ ሀብት ክፍፍልና ምደባ የግብርና ዘርፉን የፋይናንስ ፍላጎት መሰረት አለማድረጉ ነው።
በቅርቡ ባንኮች ከሚሰጡት ብድር አምስት በመቶ የሚሆነው ለግብርናው ዘርፍ እንዲውል በብሄራዊ ባንክ የተሰጠው ውሳኔ በዘርፉ የሚጠበቀውን ለማሳካት ጥሩ አስተዋጾ ያለው መሆኑን ወይዘሪት ምህረት ገልጸዋል። ውሳኔው የዘርፉን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ቢሆን ደግሞ የበለጠ ዘርፉን ለማሻሻል አስተዋጾ ይኖረዋል ብለዋል። የፋይናንስ አገልግሎት አካታችነት አለመስፋፋት ሌላው የዘርፉ ዕድገት ማነቆ እንደሆነ፣ በተለይም አነስተኛ ይዞታ ካላቸው አርሶ አደሮች አሰፋፈር ጋር ተያይዞ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል፣ በጥናቱ መካተቱን ጠቅሰዋል። እንደ አስተባባሪዋ፤ የፋይናንስ አቅርቦቱ ሁሉንም ፍላጎቶች እንዲያሟላ ማድረግ አንዱ መፍትሄ ሲሆን፣ ምርጥ ዘርን፣ ማዳበርያን፣ ቴክኖሎጂንና ሌሎች ግብዓቶችን ባካተተ መልኩ እንዲቀርብ ማድረግም ጥቅሙ የጎላ ነው። ፖሊሲና ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ሥራ ቢገባም የተሻለ ውጤት ለማምጣት ተግባራዊነቱ ላይ ማተኮር እንደሚገባ ይመክራሉ።
የግብርና ተኮር ባንክና የመድን ድርጅት ተቋቁሞ ዘርፉን በሚመጥን መልኩ አገልግሎት እንዲያቀርቡ ቢደረግ፣ በመንግስት በኩልም የመንግስት ድጎማ ፈንድ ተመድቦ አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች ተደራሽ የሚደረግበት ስትራቴጂ ቢዘጋጅ፣ የግብርናውን ዘርፍ የሚያግዝ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ተደራሽ ቢሆን፣ በአጠቃላይ ከፋይናንስ አቅርቦቱ ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮችን መፍታት ግብርናውን ወደ ዕድገት ለማሸጋገር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ወይዘሪት ምህረት አስረድተዋል። ይህ ሲሆን ደግሞ አርሶ አደሩ ተመጣጣኝ የምግብ አቅርቦት፣ የጤና እና የትምህርት አገልግሎቶች ለማግኘት ያስችለዋል።
አስተባባሪዋ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የተሻሻለ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖረው ከማድረግ አንጻር የተጠናውን ሌላኛውን ጥናት መፍትሄ አስመልክተውም በሰጡት ማብራርያ የፋይናንስ አቅርቦት መኖር አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ የተለያዩ ግብዓቶችን እንዲጠቀም ያስችላል። ይሄን ተከትሎም ምርትና ምርታማነት የሚሻሻልበት ዕድል ይፈጠራል። ቀጣይነት ያለው መሻሻል ይኖራል። የተለያዩ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማግኘት ያስችላል። ይሄ በሚሆንበት ጊዜ ድህነት ይቀንሳል። የተለያዩ ምርትና ምርማነት የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎችን ሥራ ላይ በማዋል እንዲሁም ከራስ ምርትም ሆነ ከገበያ በመግዛትና በመጠቀም የሕዝቡን በምግብ ራስን የመቻል ዓላማ ከዳር ያደርሳል። ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንፃርም ቀላል የማይባል አስተዋጾ አለው። የብድር አገልግሎት ሲሻሻል ለግብርና ምርት አመቺ የሆነው ግን በተለያየ ምክንያት ሥራ ላይ ያልዋለው መሬት ወደ ሥራ የሚገባበት ዕድል ይሰጣል። የዋጋ ንረትና ጠቅላላ የምጣኔ ሀብት ላይ ትልቅ አስተዋጾ ያበረክታል። በአጠቃላይ የፋይናንስ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ መኖር የአካባቢ ጥበቃን ያሻሽላል። የተለያዩ አመራረት ዘዴዎችን ወይም ቴክኖሎጂዎችን የመግዛትና ሥራ ላይ የማዋል ጥቅምን ይሰጣል። የጥናት ግኝቱ ግብርና መሩን ኢኮኖሚ ወደ እንዲስትሪ እንደሚያሻግረው ተስፋ ተጥሎበታል። እኛም የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ እየተመኘን ጽሑፋችንን ቋጨን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2013