ህገወጦች ከወረዳው አመራሮች ባገኙት ከስምንት በላይ ሼዶች እና የማምረቻ መሳሪያዎቻችን ወድመውብን ተስርቀውብናል ፤ ህዝብ ይፍረደን ሲሉ በጥቃቅን እና አነስተኛ የተደራጁ የብሎኬት አምራች ማህበራት ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አቤት ብለዋል። ይህ ድርጊት የተፈጸመው በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ስሙ ቡልቡላ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ነው።
አቶ አዲሱ ክፍሌ ይባላሉ:: የአዲሱ ፣ብርሃን እና ጓደኞቻቸው የብሎኬት ማምረቻ አባል እና በቡልቡላ የሚገኙ የብሎኬት አምራች ማህበራት ሰብሳቢ ናቸው። እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ የብሎኬት አምራች ማህበራቱ ሃያ – ሰማንያ የተሰኘው የቡልቡላ ኮንዶሚኒየም ፕሮጀክት መጀመር ጋር ተያይዞ በ2004 ዓ.ም የብሎኬት አምራች ማህበሩ ተመሰረተ።
የቡልቡላ ሃያ – ሰማንያ ኮንዶሚኒየም ተገንብቶ ሲያልቅ የብሎኬት ማምረት ሥራውም አብሮ ቆመ የሚሉት አቶ አዲሱ፤ ምክንያቱም ማህበራቱ ብሎኬት የሚያመርቱት ለመንግሥት እና ለመንግሥት ተቋማት ብቻ መሆኑ ነው። ስለዚህ የመንግሥት የግንባታ ሥራ በቆመበት ጊዜ አብረው ሥራ እንደሚያቆሙ ይገልጻሉ። ‹‹እኛ በግላችን ሲሚንቶ ገዝተን ለግለሰቦች እና ለግል ድርጅቶች በማምረት ማከፋፈል አንችልም። ስለዚህ የመንግሥት የግንባታ ሥራ በማይኖርበት ሰዓት የእኛም ብሎኬት የማምረት ሥራ አብሮ ይቆማል›› ይላሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአርባ – ስልሳ ኮንዶሚኒየም ፕሮጀክት መጀመር ጋር ተያይዞ የገበያ ትስስር ስለተፈጠረላቸው ለ40/60 ፕሮጀክት ብሎኬት በማምረት እና በማስረከብ ሥራ መጀመራቸውን አቶ አዲሱ ይናገራሉ። የ40/60 ፕሮጀክትም ስላለቀ አዲስ ሳይት እስኪጀመር ድረስ ማህበራቱ ለባለፉት ሁለት ዓመታት ያለምንም ሥራ እንዲቀመጡ መገደዳቸውን አቶ አዲሱ ይናገራሉ።
ባለሼዶቹ በዚህ ሂደት ላይ እያሉ በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 12 አስተዳደር ኃላፊ በውል ባልታወቀ ምክንያት የብሎኬት አምራች ማህበራቱን “እኔ እዚህ ቦታ ላይ ተሹሜ ከመጣሁ ጀምሮ አላውቃችሁም” እንዳሏቸው የሚናገሩት አቶ አዲሱ፤ ‹‹የግዴታ እርሱ ተሹሞ ሲመጣ እያንዳንዳቸውን እየመጣን ልንተዋወቅዎት አይገባም›› በማለት መግለጻቸው ይናገራሉ። አስተዳዳሪው ስለማህበራቱ ወይም ስለሼዶቹ ማወቅ ከፈለጉ በወረዳው የሚገኘውን የሼዶች ፋይል ማየት ይችሉ እንደነበር ጠቁመዋል። ባለሼዶችን በአካል ማነጋገር ከፈለጉ ፋይሎች ውስጥ ባለው የስልክ አድራሻ በመጠቀም እና በመጥራት ማነጋገር ይችሉ እንደነበር ገልጸዋል። ነገር ግን ዋና አስተዳደሩ ትልቁ ችግራቸው እነሱን የማወቅ እና ያለማወቅ ጉዳይ እንዳልሆነ ነው አቶ አዲሱ የሚናገሩት።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ማህበራቱ ስለማንነታቸው የሚገልጽ ማስረጃ ለዋና አስተዳዳሪው ያቀርባሉ። አስተዳዳሪውም ማስረጃውን ከተመለከቱ በኋላ ማህበራቱ ለምን ሥራ እንዳቆሙ ይጠይቋቸዋል። ሥራ ያቆሙበትን ዋና ምክንያት የብሎኬት አምራች ማህበሩ ከመንግሥት ውጪ ላሉ ተጠቃሚዎች በግላቸው ማምረት እንደማይችሉ እና በዚህም ምክንያት ሥራ ማቆማቸውን ለአስተዳዳሪው ያብራራሉ። በዚህም ከወረዳው ከዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋር መግባባት ላይ መደረሳቸውን አቶ አዲሱ አመላክተዋል።
እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ ፤ በመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም ሼዱ እና በውስጡ የነበሩ ንብረቶችን ጨምሮ ተዘረፉ። የንብረቱ መዘረፍ ሳያንስ «የካባ ድንጋይ» በሚያወጡ የአካባቢው ሰዎች ሼዶች ተገንብተውበት የነበረ ቦታ እንዳልሆነ ሆነው ከጥቅም ውጪ ሆኑ። ይህንንም ወረዳ 12 ለሚገኘው ጥቃቅን እና አነስተኛ ቢሮ እና ለሰላም እና ጸጥታም ዘርፍ አመለከቱ። “የካባ ድንጋይ” የሚያወጡት ሰዎች በሼዱ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ ከፖሊስ ጋር በቦታው ድረስ በመገኘት ተመለከቱ። የ“ካባ ድንጋይ” የሚያወጡት ሰዎች ፈቃድ አላችሁ ወይ ? ተብለው ሲጠየቁ ፈቃድ የለንም ብለው መለሱ። ፈቃድ ስለሌላቸው በጸጥታ አካላት እንዲያቆሙ ተደረገ። ነገር ግን የጸጥታ አካላት አስቁመዋቸው ከተመለሱ ከአንድ ቀን በኋላ ልጆቹ የወረዳ 12ት አስተዳደር በማነገጋር “የካባ ድንጋይ” የማውጣት ሥራውን ማከናወናቸውን ቀጠሉ።
በዚህ ጊዜ የብሎኬት አምረች ማህበራቱም ጉዳዩን ለሚመለከታቸው አካላት አቤት ማለታቸውን ይናገራሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከወረዳ እስከ ክፍለ ከተማ የሚገኙ የጥቃቅን እና አነስተኛ ቢሮ እና የሼድ አስተዳደር ኃላፊዎች ከአቅማችን በላይ መሆኑን ነገሩን የሚሉት አቶ አዲሱ ፤ የቦሌ ክፍለ ከተማ የመስሪያ ቦታዎች አስተዳደር ኃላፊ ደግሞ የተፈጠረውን ችግር ቦታው ድረስ በመሄድ እንዳዩት ነገር ግን የተፈጠረውን ችግር ለማስቆም ችግሩ ከአቅማችን በላይ መሆኑን እንደገለጹላቸው ጠቁመዋል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ የመስሪያ ቦታዎች ኃላፊ ተፈጠረ ስለተባለው ችግር ኮሚቴ አዋቅረው ቦታው ድረስ በመሄድ እንደተመለከቱት እና ቦታው ላይ ያለው ጉዳይ የመሬት ጉዳይ እንጂ የቆርቆሮ እና የእንጨት ጉዳይ አለመሆኑን እንዳስረዷቸው አቶ አዲሱ ይናገራሉ።
እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ ፤ የቦሌ ክፍለ ከተማ የመስሪያ ቦታዎች ኃላፊም ለወረዳ 12 ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስለጉዳዩ በተደጋጋሚ ጊዜ ቢያናግሯቸውም የወረዳ 12 አስተዳዳሪው ምንም ዓይነት መልስ ሊሰጡ አልቻሉም። በዚህ የተነሳ የቦሌ ክፍለ ከተማ የመስሪያ ቦታዎች ኃላፊም ጉዳዩ ካቅማቸው በላይ እንደሆነ በመግለጽ ሳህሊተ ምህረት አካባቢ ለሚገኘው የከተማ አስተዳደሩ የመስሪያ ቦታዎች አስተዳደር አቤት እንዲሉ እንደነገሯቸው ተናግረዋል።
‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ ከኦሮሚያ ወጣት ማህበር ነው ተደራጅተን ነው የተላክነው የሚሉ ወጣቶች ሼዱ በሚገኝበት ቦታ ላይ የግንባታ ፈቃድ ይዘው መጡ የሚሉት አቶ አዲሱ፤ ለተደራጁት ወጣቶች የወረዳ 12 የግንባታ ፈቃድ ቢሮ ኃላፊ የግንባታ ፈቃድ ሊሰጡ ቦታው ላይ ማግኘታቸውን ይገልጻሉ። በዚህ ጊዜ ቦታው ላይ በብሎኬት ማምረት የተደራጁት ማህበራቱ “ቦታው ላይ ሼድ እያለ ለምንድን ነው በላያችን ላይ የግንባታ ፈቃድ ሚሰጠው?” ብለው የወረዳውን የግንባታ ቢሮ ኃላፊው መጠየቃቸውን ጨምር አቶ አዲሱ ይናገራሉ።
ይህን ተከትሎ የወረዳ 12 የግንባታ ፈቃድ ኃላፊው “እናንተን አናቃችሁም። ቦታው የእኛ ነው የምትሉ ከሆነ ደግሞ የሰነድ ማረጋገጫ አምጡ!” አሉን። “እኛም ህጋዊ ማህበራት ስለሆንን ሁላችንም የሼድ ኪራይ ስምምነት ፣ የሼድ ፈቃድ ስምምነታችንን ፣ የግብር መክፍያ መለያ ቁጥር ፣ የንግድ ፈቃድ ፣ የተደራጀንበትን ወዘተ ኮፒ አድርገን ከማመልከቻ ጋር በማቅረብ የግንባታ ፈቃዱ እንዳይሰጥ እና እንዲታገድ ብለን ጠየቅን።” ሲሉ አቶ አዲሱ ይገልጻሉ።
የማሳገጃ ማመልከቻውንም ግንቦት 2 ቀን 2013 ዓ.ም ለግንባታ ፈቃድ ቢሮ ማስገባታቸውን እና ለግንቦት ስድስት 2013 ዓ.ም እንደተቀጠሩ የጠቆሙት አቶ አዲሱ ፤ ይሁን እንጂ ስለጉዳዩ ጠርቶ ሊያናግራቸው ፈቃደኛ የሆነ አካል አለመኖሩን አቶ አዲሱ አመልክተዋል። ምላሽ የሚሰጣቸው ሰው በማጣታቸው የብሎኬት አምራች የማህበራቱ በራሳቸው ገፍተው ሄደው የወረዳውን አስተዳደር በሚጠይቁበት ጊዜ “ሼዱ ነው እንጂ የእናንተ መሬት የመንግሥት ነው” የሚል ቅንነት የጎደለው ምላሽ እንደተሰጣቸው አቶ አዲሱ ይናገራሉ።
ብሎኬት አምራች ማህበራቱም መሬት የመንግሥት መሆኑን ጠንቅቀው እንደሚያውቁ ለአስተዳደሪው እንዳስረዱ የጠቆሙት አቶ አዲሱ ፤ “መንግሥት ማለት ህዝብ ማለት ነው። እኛም ደግሞ አንድ የህዝብ አካል ነን። ስለዚህ እኛም እንደ አንድ የህዝብ አካል በመሬቱ የመጠቀም መብት አለን” በማለት ለማስረዳት መሞከራቸውን አቶ አዲሱ ጠቁመዋል። በዚህ ወቅት የብሎኬት አምራች የማህበራቱ ያነሱት ሃሳብ ትክክል መሆኑን ተማምተው በቦታውም የመጠቀም መብት እንዳላቸው ስምምነት ላይ መደረሱን ይናገራሉ።
ይህን ተከትሎ የወረዳው አስተዳዳሪ በቦታው የመጠቀም መብታቸውን በትክክል የሚቀበል ከሆነ በደብዳቤ መልስ እንዲሰጣቸው ይጠይቀሉ። ነገር ግን ይህንን ለማድረግ የወረዳው አስተዳደር ፈቃደኛ ሊሆን እንዳልቻለ አቶ አዲሱ ተናግረዋል። እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ፤ የወረዳ አስተዳደሩ በጹሑፍ ማረጋገጫ ለመስጠት ፈቃደኛ ስላልሆነ የብሎኬት አምራች ማህበሩ ሌላ አማራጭ ሃሳብ አቀረበ። ወረዳው መሬቱ ለአርሶአደሮች ይገባል ካለ ለአርሶ አደሮችም መሬት ይስጥ ማህበሩንም በስርዓት ያስተናግድ ወይም የምትክ ቦታ ሰጥቶ ያሰናብትን የሚል አማራጭ ሃሳብ አቀረበ።
የብሎኬት አምራች ማህበሩ ያመጣው አማራጭ ሃሳብ በደብዳቤ እንዲያስገቡ አስተዳዳሪው በጠየቀን መሰረት ያሉትን አማራጭ ሃሳቦች በደብዳቤ መጠየቃቸውን የሚናገሩት አቶ አዲሱ ፤ ደብዳቤው ለአስተዳዳሪው የተሰጠው በ2013 ዓ.ም በስድስተኛው ወር ቢሆንም ደብዳቤውን ለመሬት ማኔጅመንት እና ለቀጠና ኃላፊዎች ይህ ቦታ ለማን እንደሚገባ ተጣርቶ በቃለ ጉባኤ ተያይዞ እንዲላክ ተመርቶበት እንደነበር ይናገራሉ። የወረዳው የመሬት ማኔጅመንት ቦታውን ከተመለከተ በኋላ መሬት ላይ ያለውን ሐቅ ተገንዝቦ ከሼዱ ማህበራት ጋር ምንም ጥያቄ እንደሌለው ማሳወቁን እና ሼዱ የተገነባበት መሬት የኔ ነው የሚል አካል እንደሌለ በመግለጽ መሬቱ አሁን ላይ በብሎኬት አምራች ማህበራት ስም እንደሚገኝ ምላሽ መሰጠቱን አቶ አዲሱ ይናገራሉ።
እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ ፤ ከመሬት ማኔጅመንት ውሳኔ በኋላ ጉዳዩ በቀጠና ኃላፊዎች እንዲጣራ ተላከ። የቀጠና ኃላፊዎችም ስለጉዳዩ አጣርተው ቃለጉባኤ እንዲያዙ ቢናገሩም ቃለ ጉባኤው ላይ ፊርማ ይቀረዋል በሚል ተልካሻ ምክንያት እና የሕፃን ጨዋታ በሚመስል አካሄድ እስከዛሬ ድረስ መፍትሔ ላይ መድረስ አልተቻለም። በቡልቡላ መንግሥት የሚሰጠው የሼዶችን መስሪያ ቦታ እንጂ ሼድ አልገነባም። በመሆኑም ማህበራት በራሳቸው ወጪ ሼዶቹን መገንባታቸውን የሚገልጹት አቶ አዲሱ ፣ እንደመመሪያው ሼዶችን መንግሥት ሠርቶ መስጠት እንደነበረበት አመላክተዋል።
ማህበራቱ በሠሩት ሼድ አዲስ መንገድ አሠርተው ፣ ባለ 3 ፌዝ ትራንስፎርመር መብራት እና ውሃ አስገብተው ምንም ያልነበረበትን ቦታ ካለሙ በኋላ በህገወጥ መንገድ የግንባታ ፈቃድ መስጠቱ የሚያስተዛዝብ እና በፍጹም ተቀባይነት ሌለው እንደሆነ ይገልጻሉ። “ከሼዱ ዙሪያ በህገወጥ መልኩ በሼዶች የተያዘ ትርፍ ቦታ ከተገኘ የሚመለከተውን አካል አጥርቶ እና ህጉን ጠብቆ መሥራት እና ማልማት አንድ ነገር ነው። ነገር ግን እኛም ደግሞ እዚህ ቦታ ላይ በቃችሁ መንግሥት ቦታውን ሊያለማው ፈልጓል ከተባለም ማህበራቱን ለማሰናበት የራሱ አግባብ የሆነ አካሄድ አለው። ነገር ማንም ከመሬት ተነስቶ ፈቃድ አውጥቻለሁ ተነስ ብሎ ሊያባርር አይገባም” ሲሉ አቶ አዲሱ ገልጸዋል።
ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ የወረዳው ካቢኔ የተሳተፉበት የሼድ ማፍረስ እና የማሽኖች ዝርፊያ ተፈፅሞብናል የሚሉት አቶ አዲሱ ፤ ይህም የሆነው የግንባታ ፈቃድ በላያቸው ላይ ለማውጣት እንዲመቻቸው በማሰብ መሆኑን አመላክተዋል።
“አሁን ላይ ሼዱ ተዘርፏል። ለወረዳ አስተዳደሩ ለጊዜው እንኳን የላሰቲክ ሼድ እንሥራ ብንል አይፈቀድልንም። ምክንያቱም ጥያቄው የቦታ ነው። ለዚህም ነው የወረዳ 12 ዋና ሥራ አስፈጻሚው በተደጋጋሚ ስለጉዳዩ ብናመለክትም ለጥያቄው ምላሽ ሊሰጠን ፈቃደኛ ያልሆነው” ሲሉ የቦሌ ክፍለ ከተማ የመስሪያ ቤቶች ኃላፊ እንደነገሯቸው አቶ አዲሱ ጠቁመዋል።
በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 12 የሥራ ፈጠራ የሥራ ሂደት ተወካይ ምላሽ በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 12 የሥራ ፈጠራ የሥራ ሂደት ተወካይ የሆኑት አቶ አሰማኸኝ አያሌው እንደገለጹት ፤ ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት በብሎኬት በማምረት የተሰማሩ ከ20 በላይ ሼዶች ነበሩ። ነገር ግን አሁን ላይ ማህበራቶቹ ከአደራጃቸው መስሪያ ቤት እውቅና ውጪ ይሠሩበት የነበረው ቦታው ለሌላ አካል ስለተሰጠ ትወጣላችሁ እንደሚባሉ መረጃዎች ደርሰውናል። ማህበራቱ ምትክ ቦታ እስኪያገኙ ድረስ ተንሳፋችሁ ትቀመጣላችሁ መባላቸውንም ገልጸውልናል።
አቶ አሰማኸኝ ገለፃ ፤ አንድ ማህበር ፈረሰ ማለት ተጠያቂ የሚሆነው የሥራ እድል ፈጠራ ቢሮ ነው። ማህበራትን ለማፍረስ ከተፈለገ የሚጠበቅበት ህጋዊ አካሄድ አለ። ዝም ብሎ ማንም ከመሬት ተነስቶ ማፍረስ አይችልም። ከአደራጀው አካል ውጪ ማህበራት እንዲፈርሱ ከተደረገ የሥራ ፈጠራ መስሪያ ቤት ሼዶቹ ሥራ ላይ እንዳሉ አደርጎ ስለሚቆጥር ከማህበራቱ ጋር ያልተገባ ግጭት ውስጥ ይከታል።
ሼዶቹ በህገ ወጥ መልኩ እየተገፉ መሆናቸውን የወረዳ ሥራ ፈጠራ መስሪያ ቤቱ በማየቱ አጥጋቢ የሆነ ምላሽ ማህበራቱ እንዲገኙ ለማድረግ ማህበራቱ እንዲደራጁ እስከላይ ድረስ ሊጠይቁ እንደሚችሉ አቅጣጫዎችን በመጠቆም ግፊት ማድረጋቸውን አቶ አሰማኸኝ ይናገራሉ። በወረዳው የሚገኘው የሥራ እድል ፈጠራ መስሪያ ቤት ማህበራቱ የገጠማቸውን ችግር በራሱ መፍታት ያልቻለበት ዋነኛው ምክንያት የሼድ አስተዳደር የሚባለው መዋቅር በወረዳ ደረጃ አለመኖሩ ነው ሚሉት አቶ አሰማኸኝ ፤ መዋቅሩ በክፍለ ከተማ ደረጃ እና በከተማ ደረጃ ብቻ እንደሚገኝ አመላክተዋል። ሼዶች ችግር ሲደርስባቸውም በወረዳ ደረጃ ሊፈታ ያልቻለው በመዋቅሩ ምክንያት መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል።
አቶ አሰማኸኝ እንደሚሉት ፤ ከላይ የተጠቀሱት አይነት ችግሮችን የሼድ አስተዳደሮች በቅርበት ስለማያውቁት ለባለሼዶች አውንታዊ ምላሽ እየተሰጠ አይደለም። ስለዚህ በወረዳ ደረጃ የሚፈጠሩ ቅሬታዎችን ለመፍታት በጣም አስቸጋሪ አድርጎታል። የወረዳው የሥራ ፈጠራ ቢሮ ማህበራቱን በተለያዩ አግባቦች ከመቆጣጠር እና የሼዱን ኪራይ ከማዋዋል ውጪ ምንም ስልጣን እንደሌለው ጠቁመው ፤ ማህበራቱ የሚደርስባቸውን ከማየት በስተቀር ችግራቸውን እየፈቱላቸው እንዳልሆነ ጠቁመዋል።
አሁን ላይ “የካባ ድንጋይ” በሚያወጡት ህገወጦች ህጋዊ በሆኑ ማህበራት ላይ እያደረሱት ያለውን በደል መቃወማቸውን የሚናገሩት አቶ አሰማኸኝ፤ ሼዶች ላይ ችግር እየፈጠሩ ያሉ ሰዎችን በወረዳም ደረጃ ወይም በሥራ እድል ፈጠራ በህጋዊ መልኩ ያልተደራጁ እና እውቅና እንደሌላቸው ገልጸዋል። እንደ አቶ አሰማኸኝ እነኚህ ህገወጥ የሆኑ እና ራሳቸውን “በካባ ድንጋይ” ማውጣት ያደራጁ ሰዎች በቦታው ሄደው ለማየት ሲሞክሩ በቦታው አይገኙም። በመሆኑም እነዚህን ህገወጥ የሚባሉ ሰዎች እነማን ናቸው የሚለውን ለማወቅ አልተቻለም። እነኚህ አካላት ከላይ ካሉ አመራሮች ጋር ግንኙነት አላቸው።
ለሥራ እድል ፈጠራ በተጨማሪ የደረሰው መረጃ ባይኖርም የከተማ አስተዳደሩ በጻፈው ደብዳቤ ሼዱ እንዲነሳ የሚል ትዕዛዝ ማስተላለፉን ሰምተናል የሚሉት አቶ አሰማኸኝ፤ ነገር ግን የሼዶች አስተዳደር በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም የሚያውቀው ነገር አለመኖሩን አመላክተዋል። ሼዱ የተሠራበት ቦታ ካርታ እንደወጣበት በሼድ አስተዳደር ስር የተደረጁት ሰዎች ቢገልጹም የወረዳው የሥራ እድል ፈጠራ ግን ስለጉዳዩ ተጨባጭ መረጃ ማግኘት እንዳልቻለ አመላክተዋል።
የወረዳ 12 ግንባታ ፈቃድ ተወካይ ምላሽ
የወረዳ 12 ግንባታ ፈቃድ ተወካይ የሆኑት አቶ በልስቲ ታደሰ እንደገለጹት፤ አዲስ የግንባታ ፈቃድ በሼዶች ላይ ተደርበው የመጡት ችግኝ ለማልማት የተደራጁ ማህበራት ናቸው። ይህ ማህበር በውስጡ ያሉ የአባላቱ ብዛት እስከ 150 እንደሚደርሱ ተወካዩ ይናገራሉ። እነዚህን ማህበራት ደግሞ የወረዳ 12 አስተባባሪ ኮሚቴ ተብሎ በሚጠራው አካል በወሰነው መሰረት በቦታው ላይ ጊዜያዊ የቤቶች የግንባታ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ወደ ግንባታ ፈቃድ ቢሮ ጉዳያቸውን መራላቸው። በዚህ ጊዜ በወረዳ 12 አስተባበሪ ኮሚቴ የተደራጁት ወጣቶች ለግንባታ ፈቃድ የተጠየቀው ሼዶች ያሉበትን ቦታ ጨምሮ ነበር። የግንባታ ቢሮውም ሼዶች ያሉበትን ጨምሮ በአዲስ ለተደራጁት ሰዎች የግንባታ ፈቃድ ለመስጠት ቦታው ድረስ በመሄድ ቦታውን ከገመገመ በኋላ ቦታው ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለወረዳው አስተባባሪ ኮሚቴ ሪፖርት አደረገ።
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም የማህበራቶች ስም ማን ይባላል? ብለን የግንባታ ፈቃድ ቢሮውን ተወካይ አቶ በልስቲን ጠየቅን። ተወካዮም “የማህበራቶችን ስም አላውቅም!” አሉ። ነገር ግን ለግንባታ ፈቃድ የጠየቁት ሰዎች ሙሉ ሰነድ ከቢሯቸው ይገኝ ነበር። ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም በአዲስ የተደራጀው ማህበር ሙሉ ሰነዳቸው በቢሮው እንደሚገኝ አረጋግጦ ስለነበር “በአዲስ የተደራጁት ማህበራት ሰነድ ከቢሯችሁ እንደሚገኝ መረጃው አለን። ይህንን ምን ይላሉ?” ስንል ተጨማሪ ጥያቄ ለተወካዩ አቀረብንላቸው። ተወካዩም በአዲስ የተደራጀው ማህበር ሰነድ በቢሯቸው እንደሚገኝ አመኑ። የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም “ታዲያ ለምንድን ነው የግንባታ ፈቃድ የሰጣችኋቸውን እና ማስረጃቸው በእጃችሁ ስላሉት ሰዎች የማህበር ስም አላውቅም የምትሉት ?” ሲል ተወካዩን ጠየቀ። ተወካዩም ስለማህበሩ ብዙ ለማብራራት አልፈለጉም። እዚህ ላይ ፍርዱን ለህዝብ ትተናል።
በመጨረሻም ከማህበራቱ የሰነድ መረጃዎችን በማየት አዲስ የተመሰረተው እና የግንባታ ፈቃድ የተሰጠው ማህበር የሐሮ ደንበል የመረዳጃ ማህበር የሚል ስም ያለው መሆኑን ተረዳን። እንደ አቶ በልስቲ ገለጻ፤ የግንባታ ፈቃድ ሊሰጥ ሲል ወጣቶች መጥተው ሼዱ የእነሱ መሆኑን ነገሩን። ነገር ግን ስለሼዱ የግንባታ ፈቃድ ጽህፈት ቤቱ ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም። በዚህ ጊዜ ሼዱ የእኛ ነው የሚሉትን ወጣቶች ሼዱ የእነሱ ስለመሆኑ የሚያስረዳ መረጃ እንዲያመጡ ተጠየቁ። በማግስቱ መረጃቸውንም አመጡልኝ። በዚህ መረጃ ተመርኩዘን ልጆችን ስናነጋግር ልጆቹ የሼድ ውል አላቸው ፣ በቦታው የመሥራት መብት አላቸው። ይህ በመሆኑ የችግኝ ማህበራቱ ያሳዩን የግንባታ ፈቃድ ውድቅ አደረግነው ብለዋል።
ይህን ተከትሎ ለወረዳው አስተባበሪ ኮሚቴው እና ለባለሼዶቹ አዲስ ለተደራጁት ልጆች ሼዶች ላይ ጨምሮ የግንባታ ፈቃድ መስጠታችን ስህተት እንደሆነ ሪፖርት ማድረጋቸውን ይናገራሉ። በመሆኑም ከሼዶች ጀርባ ወንዙን በመጠቀም የአረንጓዴ ልማቱን ለማልማት እንዲችሉ ለማድረግ ጊዜያዊ የግንባታ ፈቃድ ፈቅደናል።
እንደአቶ በልስቲ ገለጻ ፤ ሼድ ባለበት ቦታ ላይ ፈቃድ ለመስጠት ምንም አይነት የህግ መሰረት ስለሌለ አስተባባሪው ኮሚቴ እንደወሰነው በዚያው እንዲያስተናግዳቸው ተደርጓል። ስለሆነም ሼዱ ላይ ምንም አይነት የግንባታ ፈቃድ እንዳይሰጥ ተከልክሏል። ስለዚህ በሼዱ የተደራጁት ወጣቶች በነፃነት ሥራቸውን ማከናወን ይችላሉ።
በቦሌ ክፍለከተማ የወረዳ 12 የሰላም እና ጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ ምላሽ
በቦሌ ክፍለከተማ የወረዳ 12 የሰላም እና ጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ መሃመድ ሻዱ በበኩላቸው አሁን ላይ ጥቃቅን እና አነስተኛ የተደራጁበት ቦታ የመንግሥት ቦታ ነው። በምን ምክንያት ሥራ እንዳቆሙ ባናውቅም ማህበራቱ ሥራ አቁመው ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ የአርሶ አደር ልጆች ይዞታው የእኛ ነው ብለው መጡ። የአርሶ አደር ልጆች ነን ያሉት አካላት በመንግሥት ያልተደራጁ እና ራሳቸውን በማደራጀት የተደራጀን ነን አሉ። ማስረጃም አለን በሚል እዚያ ቦታ ገብተው ሥራ ጀምረው ነበር። ነገር ግን የተደራጃችሁበትን ማስረጃ አቅርቡ ብሎ የወረዳው የሰላም እና የጸጥታ ዘርፍ አካላት ቢጠየቁም በድንጋይ ማውጣት የተሰማሩት አካላት ህጋዊ ማስረጃ ማቅረብ አልቻሉም። በመሆኑም እንደ ጸጥታ ዘርፍ ከፖሊስ ጋር ቦታው ድረስ በመሄድ ልጆች ይሠሩት የነበረውን ሥራ እንዲያቆሙ ተድርጓል።
ስለሆነም አሁን ላይ ምንም አይነት የድንጋይ ማውጣት ሥራ እየተካሄደ አይደለም። ስለዚህ መንግሥት በህጋዊ መንገድ ያደራጃቸው ድርጅቶች አሁን ላይ ሥራቸውን ማከናወን ይችላሉ። አሁን ላይ በቦታው ከነጭራሹ የተፈጠረ ችግርም የለም። መሬት ላይ ያለው ሃቅ ይኸው ነው። ስለሆንም በብሎኬት ማምረት የተደራጁ አካላት ሼዳቸው ሄደው ሥራ እንዲጀምሩ እና ሥራ በሚሠሩበት ሰዓት ችግር የሚፈጥር አካል ካለ ችግር በሚፈጠሩ ኃይሎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የህግ በላይነትን እንደሚያስከብሩ አቶ ሙሃመድ ገልጸዋል።
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ከመረመራቸው ሰነዶች በመነሳት “ከስድስተኛው ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ ከጥቃቅን እና አነስተኛ ፣ ከሼድ አስተዳደር እና የሼድ ባለቤቶች ህገወጥ የካባ ድንጋይ የሚያመርቱ አካላት መኖራቸውን ገልፀው። እነኝህ አካላትም ለሼዳቸው ህልውና ስጋት ስለሆኑ አስቁሙሉን ብለው ጠይቀዋችሁ ነበር። እናንተግን ማስቆም አልቻላችሁም። ይህን እንዴት ይመለከቱታል” ሲል የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ለአቶ መሃመድ ጥያቄ አንስቶ ነበር። አቶ ሙሃመድም “ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ማስቆማቸውን እና ነገር ግን አሁን ሼዱ ባለበት ቦታ ላይ እየተደረገ ያለ የካባ ድንጋይ ማውጣት ማስቆማቸውን ገልጸው፤ ድንጋይ የሚያወጣ አካል ካለም በህግ እንደሚጠየቁ ለዝግጀት ክፍላችን በልበሙሉነት ተናግረዋል።
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ከአሁን በኋላ ለሚፈጠሩ ችግሮች ሙሉ ኃላፊነት ትወስዳ ላችሁ ? ብሎ አቶ ሙሃመድን ጠየቀ። አቶ ሙሃመድም “ይህ ሥራችን እና ኃላፊነታችን ስለሆነ ከአሁን በኋላ ለሚፈጠሩ ችግሮች ኃላፊነት እንወስዳለን” ሲሉ መለሱ። ይሁን እንጂ ከቃለ ምልልሱ አስር ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ችግሩ ተፈጠረበት በተባለው ቦታ በአካል ተገኝቶ ለማየት እንደቻለው ወደ ስምንት ሼዶች በህገወጥ ሰዎች ተዘርፈው እና ፈርሰው እንዲሁም የቀሩት ሼዶች ከጀርባ ላይ አንድ በሜትር በማይሞላ እርቀት ላይ ህገ ወጥ የድንጋይ አምራቾች ድንጋይ ሲቆፍሩ እና ከባለሼዶች ጋር አምባጓሮ ፈጥረው ተመልክተናል። በዚህ ወቅት የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም አስቁመነዋል ያላችሁት የድንጋይ ቁፋሮ መቼ ቆመ? ብሎ በስልክ ለአቶ ሙሃመድ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። አቶ ሙሃመድም እየተሳለቁ ጥቆማውን ስለሰጣችሁ እናመስግናለን ብለው ስልኩን ዘጉ።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2013