በፊንፊኔ ዙሪያ የሰንዳፋ በኬ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ባይሳ ባጫ ከኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ ጋር ተያይዞ ሊገጥማቸው የሚችለውን የምግብ እጥረት ለመቋቋም እርሳቸውና ጎረቤቶቻቸው ከዋና የእርሻ ሥራቸው በተጨማሪ በአካባቢያቸው ያለውን ቦረቦር መሬት በተፈጥሮ ሀብት ሥራ አክመው ፍራፍሬና አትክልት በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ።በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት በስተጀርባ ካሉት ነዋሪዎች መካከል አንዷና የቀበሌ 18 ነዋሪዋ ወይዘሮ ምትኬ ወይሶም የግንፍሌን ወንዝ በመጠቀም በከተማ ግብርና ሥራ መሳተፋቸውን ይጠቅሳሉ።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ታደሰ እንዳብራሩት መንግስት ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ የሚገጥመውን የምግብ እጥረት ስጋት ከወዲሁ ለማስቀረት በየዘርፉ ብዙ ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል። በተለይ በግብርናው ዘርፍ ከኮቪድ ጋር ተያይዞ ሊገጥም የሚችለውን የምግብ እጥረት ከወዲሁ ለማስቀረት ‹‹የማይታረስ መሬት አይኖርም›› በሚል ምርትና ምርታማነትን መጨመር የሚያስችሉ እርምጃዎችን በመውሰድ ሰፊ ሥራ ተከናውኗል።የምግብ እጥረት ችግርን ከወዲሁ ለመቅረፍ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤና ጥበቃ ሥራው ላይ ለየት ያለ ሥራ እንዲሰራ አቅጣጫ በሚኒስቴሩ አቅጣጫ መቀመጡንም አስታውሰዋል።
‹‹ምርትና ምርታማነት ያለ ተፈጥሮ ሀብት ሥራ ውጤታማ አይሆንም›› የሚሉት ዳይሬክተሩ የተፈጥሮ ሀብት ሥራ ሳይሰሩ እጅ አጣጥፎ በመቀመጥ አመታዊ ምርት መጠበቅ ሞኝነት እንደሆነ ይናገራሉ። የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ መሬት ላይ ተወርዶ ሲታይ የሚያስገኘው ጥቅም የትኞቹም ዓይነት የግብርና ቴክኖሎጂዎችና ግብዓቶች ከሚያስገኙት በእጅጉ እንደሚልቅም ያስረዳሉ።
ከአፈር ልማት ሥራው ጋር ቅርበት እንዳለው የሚነገረው ዩሪያ፣ ዳፕ እና በሰው ሠራሽ መንገድ የሚዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንኳን እንደማይስተካከለውም ይጠቁማሉ። ለዚህም ተፈጥሮ ሀብት የልማት የሁሉ መሰረትና መነሻ፤ በተለይ ለግብርናው ዘርፍ የጀርባ አጥንት መሆኑን አስረድተዋል።እንደአፈር ያለ የተፈጥሮ ሀብት ሲለማ ወንዞችና ምንጮች እንደሚጎለብቱና በተደላደለ ሁኔታ በመስኖ ማልማትም እንደሚቻል ይጠቅሳሉ። ከዘንድሮ የእርሻው ወቅት የሚጠበቀውን ያህል ምርት ለማግኘትም መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫና መመሪያ መሰረት ወደ ሥራ መገባቱን ይጠቁማሉ።
‹‹ግብርና ሰፊ እንቅስቃሴዎችን የያዘ ባህር ነው›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ከነዚህ መካከል ደግሞ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ሥራዎች ክንውን ቀዳሚውን የሚይዝ ዋነኛ የዘርፉ አካል እንደሆነ ይጠቅሳሉ።በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተራቆቱና ከጥቅም ውጪ የሆኑ መሬቶች መኖራቸውንም አመልክተው፤በየጊዜው በነዚህ መሬቶች አማካኝነት ተጠርጎ የሚሄድ አፈር እንዳለም ያብራራሉ።ይሄ አፈር ደግሞ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ የውሃ አካላት ላይ ከበድ ያለ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ይጠቁማሉ።
የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት ይሄን አሉታዊ ተፅዕኖ በማሻሻል ረገድ የሚሰራ ክፍል መደራጀቱንም ዳይሬክተሩ ይናገራሉ። በየዓመቱ የታቀደውን ምርት ለማግኘት በክፍሉ ሁለት አብይት ተግባራት እንደሚከናወኑና ከዚህም አንደኛው በበጋ ወቅት በርካታ ሰዎች ወጥተው የሚሰሩት የተፋሰስ ሥራ ወይም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ይጠቀሳል።በዚሁ መሰረት የተፋሰስ ሥራ በየትኛው አካባቢ እንደሚከናወንና የመሬት መራቆቱ ጉዳትም ምን ያህል ደረጃ ላይ እንደሆነ የተፋሰስ ልማት ዕቅድ መዘጋጀቱንና ዕቅዱን መሠረት ያደረገ ሥራም በክፍሉ መከናወኑን አስረድተዋል።
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት እንደ ሀገር በግብርናው ከኮቪድ ጋር ተያይዞ የሚገጥመውን የምግብ እጥረት አስቀድሞ ለመከላከል ምርትና ምርታማነትን መጨመር ዓይነተኛ መፍትሔ መሆኑ በመንግስት ግንዛቤ አግኝቷል። በየዘርፉ ችግሩን ከመዋጋት ጎን ለጎንም ምርታማነትን ለመጨመር ያስተላለፈውን መመሪያ በውጤታማነት ለመፈፀም እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል። ግብርናን ለማዘመንና ወደሚፈለገው ደረጃ ለማሻገር ብሎም የተቀመጠውን ዓላማም ለማሳካት ዘርፉን በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ መደገፍ ይገባል።
በ2012/13 ምርት ዘመን የሚጠበቀውን 460 ሚሊዮን ኩንታል እህል ለማግኘትም መጀመሪያ በተፈጥሮ ሀብት ላይ በደንብ መሠራት አለበት። ተፈጥሮ ሀብት ላይ የተጣለ መሰረት በማስፈለጉም ቸል ሳይባል ወቅታቸውን ጠብቀው የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።የተለያዩ የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራዎችም በርብርብ ተሰርተዋል። አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ብሎም የግብርናው ዘርፍ ባለድርሻ አካላትና መላው ሕብረተሰብም በዚህ ሥራ አካባቢውን እንዲንከባከብ ማድረግ ተችሏል።
አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ባለቤት እንደመሆኑ በሥራው ግንባር ቀደም ሆኖም ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በተለይ የከብቶችን ሰውነት በማጎልበት ምርታማነታቸውን ከሚጨምረው ለምለም ግጦሽ ጀምሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማትን ተጠቃሚ የሆነው ሰፊው አርብቶ አደር በነቂስ ወጥቶ የተሳተፈበት ሁኔታም ነበር። በዚህ ሥራ ላይ አርሶ አደሩም በቂና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑም ተለይቷል። ባለፉት ዓመታት አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ በተፈጥሮ ሀብት የካበተ ልምድ ቀስሟል። ነገር ግን ይሄ ዕውቀቱ በየጊዜው ከሚወጡ አዳዲስ አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎች ጋር እንዲራመድ ማድረግ የግድ ይላል።
ዳይሬክተሩ እንደሚገልፁት የግብርና ሚኒስቴር ይህን ታሳቢ አድርጎ ዘንድሮ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ እንደ አገር ባለማቸው አንድ ሺህ 500 ተፋሰሶች ለሚሳተፉ 13 ሚሊዮን አርሶና አርብቶ አደሮች፣ ባለሙያዎች እንዲሁም ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ባለ ድርሻ አካላት ግንዛቤ አስጨብጧል። የልማት ሥራው በግብዓት፣ በቴክኖሎጂ፣ በአሠራርና በሌሎች ሥራውን ማቀላጠፍ በሚያስችሉ መንገዶች መደገፍ እንደሚገባው አምኖም በዚሁ አግባብ ተንቀሳቅሷል። በተያዘው ዓመት እንደ አገር ከጥር አንድ ጀምሮ በወር ውስጥ ላሉት የሥራ ቀናቶች የሚቆይ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ በዘመቻ ሥራውን ሲያከናወን ቆይቷል።
በኦሮሚያ ፣በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በአማራ ክልሎች የአፈር ዕቀባ፣የጎርፍ መቀልበሻ፣ጎርፍ ማስወገጃ፣የአፈር ለምነትን የሚጨምሩና ሌሎች ሥራዎች በስፋት ተሰርተዋል። ሥራው በዋናነት ሲሰራ የቆየው በእርሻ ማሳ ላይ ሲሆን በተለይ በከፍታ ቦታዎች ላይ ያሉ ማሳዎች በጎርፍ ተጠራርገው እንዳይወሰዱ በልዩ ትኩረት ተሰርቷል። የማይታረስ የወል ቦታ ላይም እንዲሁ ዘላቂነት ያለው ጥቅም የሚሰጥ ሥራ ማከናወን ተችሏል። የተጎዳ የተፈጥሮ ሀብት መልሶ እንዲያገግም የማድረግ ሥራም ትኩረት ተሰጥቶት ሲከናወን ቆይቷል ።
አሁንም የመሬት መራቆት የአገሪቱ ከፍተኛ ችግር እንደሆነ የሚገልፁት ዳይሬክተሩ፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ዘላቂነት ያለው የተፈጥሮ ሀብት ሥራ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማሉ። የመሬት መራቆትን ተከትሎ የሚመጣው የአፈር መሸርሸር ለሀገሪቱ ተጨማሪ ስጋት የሆነውም መሬትን በአግባቡ ባለመንከባከብ ምክንያት መሆኑን ይገልፃሉ። ችግሮቹ ስጋት ብቻ ሳይሆኑ ምርትና ምርታማነትን እንደሚቀንሱም በተጨባጭ መታየቱን ያስረዳሉ። በዚህም በአገሪቱ ኢኮኖሚ እና በምግብ ዋስትና ዕድገት ላይ ተፅዕኖም እንደሚፈጥሩ ይጠቅሳሉ።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ እነዚህን ፈርጀ ብዙ ችግሮች ለመከላከል ምርትና ምርታማነትን የሚያስቀጥሉ ተግባራትን ማከናወን ያስፈልጋል። ችግኝ መትከልም ዓይነተኛ መፍትሔ ነው። የተራቆተ መሬት የመከለል፣ ቦረቦር መሬቶችን በኖራና በተለያዩ ሳይንሳዊ ዘዴዎች የማከምና የማልማት ሂደትም ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። የድንጋይና የእንጨት ክትር የማበጀት እንዲሁም የተፋሰስና ጥምር ደን እርሻ ልማት ሥራዎች ማከናወን ወሳኝ ነው። እነዚህ ሥራዎች የዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ቀድሞ በተጀመረባቸው በኦሮሚያ፣በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአማራና በሌሎች ክልሎች ተከናውነዋል።
በዘንድሮ የምርት ዘመንም እንደ አገር ተለይተው ለመሠራት በዕቅድ ከተያዙት 400 ሺህ ሄክታር የሚሆኑ መሬቶች ከመጎዳታቸው የተነሳ ከንክኪ ነፃ እንዲሆኑ ተደርጓል። 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ቦታዎችም የሥነ አካላዊ ሥራ ሲሰራባቸው ቆይቷል ። ደለል ሞልቶ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል እርከኖችን ወደ ላይ ከፍ የማድረግ የእርከን ካብ ፣ ቦዮችን የመጥረግ ፣የተለያዩ የጥገና ሥራዎች የመሥራት ዕቅዶች ተለይተው ተይዘዋል። በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ሥራ አዲስ ከመሥራት ባሻገር አምና፣ካቻምና እና ከዚያም በፊት የተሰሩ ሥራዎችን መልሶ የመጠገን ሥራዎችም ተከናውነዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት በዚህ መልኩ የተሰሩ ተመሳሳይ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበባቸውም ይገኛል። በአንዳንድ ክልሎች በተከታታይ አሥር ዓመታት በተሠራው አካላዊና ሥነ ሕይወታዊ ሥራ በዋነኝነት ከ21 ሺህ ተፋሰሶች ውስጥ ሰባት ሺህ ተፋሰሶች ዘለቄታዊ ሀብት ማመንጨት ችለዋል። በቅርቡ እንደ አማራ ክልል የዘንድሮ ተፈጥሮ ሀብት ሥራ ጥር አራት 2013 ዓ.ም የተጀመረበት ላይ አርማጮሆ ወረዳ ላይ 80 በመቶው የአካባቢው አርሶ አደር የጥምር ደን እርሻ ባለቤት መሆኑን ማየት ተችሏል።ጥምር ደን እርሻ የሥነ አካላዊ ሥራ በመሆኑ መሬቱን ያጠነክራል፤ በሌላ በኩል የምግብ ምንጭ፣ ገንዘብ ማግኛና የአረንጓዴ ልማት ሽፋን ይሆናል።
በአማራ ክልል አርጎባ ወረዳ፣ በሰሜን ሸዋ ዞን፣ በኦሮሚያ ክልል ሐረርጌ፣ አምቦ፣ሜጫ በደቡብ ወላይታ፣ሀዲያ እርከን ተሰርቶና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አርሶ አደሮች፣ሥራ አጥ ወጣቶች፣ሴቶችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደ ፍራፍሬ ያሉ ቋሚ ተክሎችን በመትከል ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ፣ ሕይወታቸውን መምራትና መለወጥ፣አኗኗራቸውንም ማዘመንና የምግብ ዋስትናቸውንና ተጠቃሚ ነታቸውን ማረጋገጥ ችለዋል። በነዚህ አካባቢዎች ልቅ ግጦሽ የሚያስቀሩ ሣርን እንደ ሥጋ ቅርጫ አስቀምጠው ዕጣ ተጣጥለው የሚረካከቡበት ቀጣይነት ማረጋገጥ ያስቻሉ ሥራዎች ተሰርተዋል ። በዚህ መንገድ በርካታ አካባቢዎች የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን፣ የጎርፍ መጠንና ደለልን መቀነስ እንዲሁም የካርቦን ዳይኦክሳይድን ምጣኔ በማመጣጠን ውጤታማ መሆን ችለዋል።
በተጨማሪም ችግኞች ባለቤት እንዲኖራቸው ተደርጓል። ይሄን ማደረጉ የደን ሽፋን ከፍ እንዲልና በሥራው የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ አስችሏል። ለአብነትም ከ2003 ዓ.ም በፊት 6 ነጥብ 5 ከመቶ የነበረው የአማራ ክልል የደን ሽፋን በክልሉ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ በተደራጀና በንቅናቄ መልማት ከጀመረ ወዲህ በተሰራው ሥራ የክልሉን የደን ሽፋን ወደ 14 ነጥብ 6 በመቶ ማሳደግ ተችሏል። እንዲህ ዓይነቱን ተግባር አጠናክሮ ለመቀጠልም የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራው ከዘመቻ ሥራ ወጥቶ እንዲሠራ ማድረግ ያስፈልጋል በሚል አቅጣጫ በሥፋት እየተሰራበት መሆኑን አቶ ተፈራ አመልክተዋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2013