አዲስ አበባ፡- በትምህርት ዘርፍ የተመዘገበውን ከፍተኛ ውጤት በሌሎችም የልማት ዘርፎች መድገም ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ትናንት አራት ሺ 188 የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ርዕሰ መምህርንና ሱፐርቫይዘሮችን እውቅናና ሽልማት ተበርክቷል፡፡
በመርሐ-ግብሩ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች በአዲስ አበባ ከተማ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የ10ኛና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች፣ መምህራንና የትምህርት ዘርፍ አመራሮች የሽልማትና የእውቅና መርሐ-ግብር በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት፤ በትምህርት ዘርፍ የተመዘገበውን የላቀ ውጤት በሌሎችም ዘርፎች መድገም ይገባል፡፡
እውቅናው የኮሮና ወረርሽኝና ወቅታዊ የአገር ሁኔታ ሳይበግራቸው ለቆሙለት አላማ በፅናትና በትጋት በመስራት ላበረከቱት የላቀ ውጤት የተሰጠ ነው፡፡ ለቀጣይም በተሻለ ትጋት የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ብዙ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚደረገውን አገራዊ ጥረት እንዲያግዙ ያበረታታቸዋል ብለዋል፡፡
ባለፉት ሶስት ዓመታት በነበሩ ፈታኝ ውጣ ውረዶች የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ብርቱ መምህራን፣ አመራሮችና የመምህራን ማህበራት ትጋት ሁሉንም ተግዳራቶች ተቋቁሞ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል፡፡
ይህም እኛ ኢትዮጵያውያን እንችላለን ብለን እጅ ለእጅ ተያይዘን ከሰራን የማንወጣው ነገር እንደሌለ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ እውቅና የተሰጣቸው ሁሉ በቀጣይ አገራቸው የሰጠቻቸውን ተልዕኮ በበለጠ ትጋት እንዲሰሩና የአገራቸውን ብልፅግና ሊያፋጥኑ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ‹‹ትምህርት በቤቴ››ና ሌሎች የማስተማሪያ ዘዴዎች ተግባር ላይ መዋላቸውን አስታውሰዋል፡፡ በትግበራውም ከ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ተፈታኞች መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 669 በማምጣት የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደቻለም ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው፤ ‹‹እውቅናው ለትምህርት ዘርፉ አማራሮችና መምህርን በቀጣይም ብቃታቸውን እንዲያሳድጉና ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ ያበረታታቸዋል›› ብለዋል፡፡
የኮቪድ ወረርሽኝ ትምህርትን እንዳያስተጓጎል ለመከላከልና የኮቪድ ፕሮቶኮልን ለመጠበቅ የሚያግዙ ሁለት ሺህ 330 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተው አገልግሎት መጀመራቸውንና የወረርሽኝ ተጋላጭነት ስጋት ለመቀነስ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ ለተማሪዎች የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች አቅርቦትና ምገባ መርሐ ግብርን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረው፤ በቅርብ የተጀመረው የሴቶችና የወንዶች አዳሪ ትምህርት ቤቶች አበረታች ውጤት እንደታየባቸው ጠቁመዋል፡፡
ሙሳ ሙሀመድ
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2013