አዳማ፡- የውጭ ምንዛሪ እጥረት በሥራው ላይ ተጽእኖ እንደፈጠረበት የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብአቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ::ኢንስቲትዩቱ ከክልሎች ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ ምክክር አካሂዷል::
በምክክር መድረኩ ላይ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኢንዱስትሪ ዘርፍ አስተባባሪ ወይዘሮ ስምረት ግርማ እንዳስታወቁት ፤ የውጭ ምንዛሪ ውስንነት በኢንስቲትዩቱ ሥራው ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል:: ከውጭ የሚያስፈልጉ ጥሬ እቃዎችን ለማስገባት ችግር ሆኖበታል::
በዘርፉ የሚሰሩ ሥራዎች በብዛት ከውጭ በሚገቡ ጥሬ እቃዎች ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው ዕቃዎችን ገዝቶ ለማስገባት የሚያስፈልገውን ያህል የዶላር መጠን ማግኘት አልተቻለም ብለዋል::
ከዚህ ቀደም ከነበረው አንፃር ችግሩ ቢቃለልም አሁንም ግን የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ በሥራ ላይ እክል እንደሆነ መቀጠሉንም ያመለከቱት ወይዘሮ ስምረት ፣ በዓለም ላይ የተከሰተው የኮቪድ 19 እና በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች በኢንስቲትዩቱ ሥራዎች ላይ ተጨማሪ ችግር መሆናቸውን ገልፀዋል::
ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ ያሉ ኢንቨስትመንትን የማሳደግና የመሳብ ሥራን መስራቱን ፣ በጥናት በተደገፈ መልኩ ለኢንዱስትሪዎች አቅም ግንባታ ሥራዎችን ማከናከወኑን፣ እንዲሁም ለኢንዱስትሪዎቹ በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የገበያ የማፈላለግ ሥራ መስራቱን ጠቁመዋል::
ኢንስቲትዩቱ ከዚህ ቀደም የነበሩ የኃይል መቆራረጥ እና ከብድር አቅርቦት ጋር ተያይዞ ሲያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር መፍታቱን ገልፀዋል::
የትኛውም ተቋም ብቻውን መስራት እንደማይችል ጠቁመው፤ ተቋማት በቅንጅትና በትብብር ሊሰሩ ይገባቸዋል ብለዋል :: በአሁኑ ወቅት የቅንጅት ሥራ በሚፈለገው ደረጃ ተጠናክሯል ማለት ባይቻልም ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የተሻለ ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል::
ኢንስቲትዩቱ ከ15 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትስስር በመፍጠር እንደሚሰራ የገለጹት ምክትል ዳይሬክተሯ፤ የመድረኩ ዋንኛ ዓላማም በየትኛውም ዘርፍ የተሰሩ መልካም ነገሮችን በማስቀጠል ለቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመስራት መሆኑንም አመልክተዋል::
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2013