አዲስ አበባ፡– ወጣቱ ትውልድ ወቅታዊ የሆኑ ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደጎን በመተው ከአባት አርበኞች ልምድ በመቅሰም ለሀገር አንድነት ዘብ ሊቆም እንደሚገባ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ሰይድ አህመድ አሳሰቡ::
ዶክተር ሰይድ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ አባት አርበኞች ተጋድሎ አድርገው ጠላቶቻቸውን አሳፍረው በመመለስ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ከፍ ያደረጉበት ምስጢር በአንድነት መቆማቸው ነው::
አባት አርበኞች በአንድነት ዘምተው፣ በአንድ ኮዳ ጠጥተው፣ በአንድ ጉድጓድ አብረው ተቀብረው ለአሁኑ ትውልድ ነፃ አገር እንዳስረከቡ ያመለከቱት ዶክተር ሰይድ፣ ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ ጠላት የፈለገውን ድንበር ተሻግሮ ቢመጣም እንደማያሸንፋቸው ያረጋገጡበትን የአርበኞች ድል ወጣቱ መማርና ማስቀጠል እንደሚኖርበት አመልክተዋል::
የአሁኑ ትውልድ አገር ከብሔርም ከቋንቋም በላይ መሆኗን በመገንዘብ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚመጡ ልዩነቶችን በማስፋት ሀገርን አደጋ ላይ ለመጣል የሚቋምጡ ኃይሎችን በአንድነት ሊታገላቸው እንደሚገባ አስታውቀዋል::
“አባት አርበኞች ያስተማሩትንና ያስረከቡትን ትልቁ ሀብት አንድነት ነው:: በአሁኑ ወቅት የውስጥና የውጭ ኃይሎች አገራችን ላይ ጫና እየፈጠሩ የሚገኙበት ወቅት መሆኑን ወጣቱ በውል በመገንዘብ ልዩነቶችን በሰከነ መንገድ በውይይት መፍታት ይገባዋል” ብለዋል::
የአሁኑ ትውልድ አንድነትን የማጠናከር፣ አገርንም ከጠላት የመጠበቅ ኃላፊነት እንደተጣለበት ያብራሩት ዶክተር ሰይድ ፣ አርበኞች ለአገራቸው ሲሉ በዱር በተራራ ያደረጉትን ተጋድሎ የአሁኑ ትውልድ የጋራ ጠላት በሆነው ድህነትና አለመግባባትን መከላከልና ማስወገድ እንደሚገባው ገልጸዋል::
እንደ ዶክተር ሰይድ ገለጻ፣ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት ትግል በማድረግ ላይ ትገኛለች:: ነገር ግን አንዳንድ የውስጥና የውጭ መልዕክተኞች ልዩነትን በመፍጠር አገር እንዳይረጋጋ እየሠሩ ናቸው:: ሁሉም ዜጋ ይህንን በመረዳት ለሀገሩ ዘብ መቆም አለበት::
በተለይም ታላቁ የህዳሴ ግድብ የድህነት ድል መንሻ ዋናው መሳሪያ ነው ያሉት ዶክተር ሰይድ፣ የግድቡ ግንባታ እንዳይጠናቀቅ እየሠሩ ያሉ የውስጥና የውጭ ኃይሎችን አሳፍሮ መመለስ ያስፈልጋል ብለዋል::
“ሀገር ማለት ከብሔር፣ ከሃይማኖት፣ ከቋንቋና ከሁሉም በላይ የሆነች ነች:: ሁሉንም በአንድ ጥላ ስር አቅፋ የምትይዝ ናት:: አገር ሲኖር ሃይማኖትን በነፃነት ማራመድ፣ የራስን ማንነት ማንፀባረቅና ሀብት ማፍራት ይቻላል:: በመሆኑም ቅድሚያ ለአገር አንድነት መሥራት ወሳኝ ነው “ብለዋል::
ወጣቱ ወቅታዊ ትኩሳቶችን ለመንዛት ለሚሞክሩ ኃይሎች ቦታ መስጠት የለበትም:: ከዚህ ይልቅ ከታሪክ በመማር፣ የትናንት ጥፋትን ላለመድገም ልዩነቶችንና አለመግባባቶች በሰከነ መንገድ በውይይት ለመፍታት መሥራት እንደሚጠበቅበት አስታውቀዋል::
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2013