አዲስ አበባ፦የቁም እንስሳት ማቆያ የዘርፉን የውጭ ንግድ ለማመቻቸት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ። 56 የቁም እንስሳት የገበያ ማዕከላትን ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል
በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የገበያ ጥራትና ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዴስነት በላይ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ የቁም እንስሳት ማቆያ የቁም እንስሳት ሀብት ጤናው ተጠብቆ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የተመቻቸ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ እንደ ሀገር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት ነው።
ሚሌ፣መተማ፣ሁመራ፣አልመሀና ጅግጅጋ ላይ አምስት የቁም እንስሳት ማቆያ ሲገነቡ መቆየታቸውን የጠቀሱት አቶ ዴስነት፣ ከተገነቡት ውስጥ አፋር ሚሌ ላይ ያለው የቁም እንስሳት ማቆያ በቅርቡ ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉንም ገልጸዋል።
ማቆያው ወደ ሥራ መግባቱ የቆይታ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን ጤናማ የቁም እንስሳት ወደ ውጭ ለመላክ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል። ለአብነትም በቅርቡ የቆይታቸውን ጊዜ ያጠናቀቁ የቁም እንስሳት ወደ ጅቡቲ የተላኩበትና የገበያ ትስስሩ እንዲሳለጥ የተደረገበት ሁኔታ መኖሩን አስታውቀዋል።
የቁም እንስሳት ማቆያ አገልግሎትን ዕቅድ ይዞና በጀት መድቦ የሚሠራው ግብርና ሚኒስቴር መሆኑን ያመለከቱት አቶ ዴስነት ፣ እንደ ሀገር 99 አንደኛ ደረጃ እንዲሁም 69 ሁለተኛ ደረጃ የቁም ከብት ገበያ ማዕከላት መኖራቸውን አመልክተዋል።
ግብይቱን ለማዘመንና መሰረተ ልማቱን ለማስፋፋት በስድስት ክልልና ሁለት ከተማ አስተዳደር 56 የቁም እንስሳት የገበያ ማዕከላት ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዳይሬክተሩ አያይዘውም ወቅቱ ኮቪድ19 እየተስፋፋና የበለጠ ለደህንነት አስጊ እየሆነ የመጣበት እንዲሁም የትንስኤ በዓል ቢያልፍም መጪው ወራት የረመዳንን በዓል ጨምሮ የሠርግ ድግስ የሚበዛበት በመሆኑ የሚፈጠረውን መጨናነቅ ተከትሎ ኮቪድ እንዳይስፋፋ በገበያ ስፍራዎቹ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2013