አዲስ አበባ፦ ኢትዮጵያ የሁለተኛውን ዙር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት በማካሄድ ኤሌክትሪክ ማመንጨት ስትጀምር የአካባቢውን ጂኦፖለቲካዊ ተጽእኖ ፈጣሪነቷ ከፍ ማለቱ እንደማይቀር በግድቡ ጉዳይ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ስለኢትዮጵያ የሚሟገቱት መምህር መካ አደም አስታወቁ ።
በግድቡ ጉዳይ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ስለኢትዮጵያ የሚሟገቱት መምህር መካ አደም በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር ውሃ ሙሌቱን አከናውና ኤሌክትሪክ ካመነጨት የአካባቢው ጂኦፖለቲካዊ እይታ ይቀየራል። ኢትዮጵያም በቀጣናዋ እና በአባይ ተፋሰስ የሚኖራት ተጽእኖ ፈጣሪነት ያይላል።
የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ግብጽ እና ሱዳን ኢትዮጵያ ሙሌት አከናውና ቀጣይ የኃይል ማመንጨት ሥራ ውስጥ እንደምትገባ በመገንዘባቸው ባለፉት ወራት ሱዳንና ግብጽ ጩኸታቸው ተበራክቶ እንደነበር አስታውቀዋል።
ሀገራቱ ቀጣዩ የኢትዮጵያ ሂደት እና የፖለቲካ አዝማሚያው ስላሳሰባቸው በየጊዜው የተዘበራረቀ መግለጫ ቢያወጡም ኢትዮጵያ ግን ወጥ አቋም በመያዝ ለኃይል ማመንጨት ሥራው የሚያግዘውን ውሃ ሙሌት እንደምታከናውን መግለጿ በአባይ ጉዳይ ወደተጽእኖ ፈጣሪነት መሸጋገሯን ያሳያል ብለዋል።
ግብጾች ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ውሃ ሙሌት አከናውና ኤሌክትሪክ አላመነጨችም፤ አሁንም ሁለተኛውን ዙር ብትሞላም ኃይል አታመነጭም ወደማለት መሸጋገራቸውን የተናገሩት መምህር መካ፤ ኢትዮጵያ ግን ከሙሌቱ በኋላ ኤሌክትሪክ ማመንጨት እንደምትጀምር በተግባር ማሳየት እንዳለባት ገልጸዋል።
ያኔ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራትም ፉከራ ረገብ ይላል። ከዚያ በኋላ ነገሮችም እየቀዘቀዙ ኢትዮጵያ በእራሷ ሃብት የመጠቀም መብቷ ይበልጥ እየተከበረ ይሄዳል የሚል እምነት እንዳላቸውም አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ በኩል እየተከናወነ ካለው የዲፕሎማሲው ሥራ ጎን ለጎን የግንባታ ሥራዎችንም አጠናክራ መሄድ ያስፈልጋል የሚሉት መምህር መካ፤ በቀጣዮቹ ጊዜያት በተቻለ ፍጥነት የኤሌክትሪክ ማመንጨት ሥራውንም በማስጀመር የጂኦፖለቲካውን ሂደት በይበልጥ መቆጣጠር እንደሚቻል ገልጸዋል።
የግብጽንና ሱዳንን ከሙሌቱ በኋላ ኤሌክትሪክ በማመንጨት ተጽእን ፈጣሪ እንዳትሆን እና የኢትዮጵያ አላማ እንዳይሳካ እና የተለያየ ጥረት ማድረጋቸው አይቀርም። እነዚያን በዲፕሎማሲውም ሆነ በውስጥ ጉዳይ የሚፈጠሩ ጫናዎችን በመቋቋም ግድቡን ዳር ለማድረስ በጋራ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ኃይል አመንጭታ እንዳትጠቀም በማሰብ ምስቅልቅሏ እንዲወጣ ለተለያዩ ቡድኖች ድጋፍ ያደርጋሉ የሚሉት መምህር መካ፤ግብጾች በኢትዮጵያ የማያባራ ግጭት ፈጥረው የአባይን ወንዝ ለብቻቸው ለመጠቀም የትኛውንም ቀዳዳ ለመጠቀም ወደ ኋላ እንደማይሉ አመልክተዋል ። ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት እንደሚከናወን ሲገለጽ በተለያዩ ቦታዎች ግጭቶች መስፋፋታቸውን እንደ ማሳያ ጠቅሰዋል።
ግብጾች የውስጥ ችግራችን ተጠቅመው ሰላማችን ለማሳጣት ሲሞክሩ አንዳንድ ተባባሪዎች ቢኖራቸውም አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅመውን እና የሚጎዳውን ያውቃልና ደባቸው መጨረሻ ላይ ውጤት አያስገኝላቸውም ብለዋል ። ኢትዮጵያም በመጨረሻ በግድቡ ተጠቃሚ እና ተጽእኖ ፈጣሪ መሆኗ የማይቀር በመሆኑ ህዝቡ ለግድቡ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት አስታውቀዋል ።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2013