አዲስ አበባ፡- በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ጨዋነት የተሞላበትና ኢትዮጵያዊ ለዛ የተላበሰ አካሄድ ሊኖር እንደሚገባ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አስታወቁ፡፡
በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በግል የሚወዳደሩት ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ‹‹ ኢትዮጵያዊነት በርቱአዊነት›› በሚል መሪ ሃሳብ የጎዳና ላይ ቋሚና ተንቀሳቃሽ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ፤ ‹‹ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ጨዋነት የተሞላበትና ኢትዮጵያዊ ለዛ የተላበሰ አካሄድ ሊኖር ይገባል›› ብለዋል፡፡
በቅስቀሳቸው፤ ‹‹ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአንድ ሀገር ልጆች መሆናቸውን ማወቅ አለባቸው፡፡ መፎካከር ብቻ ሳይሆን መተባበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ መገፋፋት አይጠቅምም›› በማለትም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያሸንፉት መጀመሪያ ኢትዮጵያ ማሸነፍ ስትችል ነው›› ያሉት ዲያቆን ዳንኤል፤ እኛ ወይም እኔ ብቻዬን ባሸንፍ ጥቅም የለውም፡፡ ስለዚህ ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን ከሆነችው በላይ እንዳትሆን መፍቀድ አያስፈልግም፡፡ እየሰማነው ያለውን አሰቃቂ ነገር እንድንሰማ መፈለግ የለብንም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
መንገዶች ብዙ ጊዜ እነ እገሌ ዘጉት እየተባለ ለመንቀሳቀስ አልተቻለም፡፡ ከዚህ ችግር መላቀቅ የምንችለውና ለውጥ የሚመጣው ደግም ስንሰራ እንጂ፤ ቁጭ ብሎ በማልቀስና ለሰዎች በመተው አይደለም ብለዋል፡፡
ከአምስት ዓመት በኋላ የሚወለዱ ልጆቻችን እኛ የምንሰማውን አሰቃቂ ነገር ሳይሆን መልካም ዜና የሚሰሙባት፣ መልካም ነገር የሚያዩባት አገር ማድረግ አለብን፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻልን ሀገር የለንም ሲሉም ገልጸዋል፡፡
‹‹ከዚህ በላይ ችግር እንዲደርስባት ስለማልፈልግ፣ ያለባትን ሸክም ለመሸከምና ያሉን ፖሊሲዎቻችን፣ ህጎቻችን፣ አሰራሮቻችን፣ ጸባያችንና የትምህርት አካሄዳችንን እንደገና መታየት አለበት ብዬ ስለማስብ እንጂ የተሻለ ሹመት የማገኝበት ሆኖ አይደለም›› ሲሉም በምርጫ ለመወዳደር ምክንያት የሆናቸውን ጉዳይ ጠቁመዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር፣ የዕምነት፣ የአስተሳሰብና የፖለቲካ አጥር በደንብ ሆኖ ተገንብቷል›› ያሉት ዲያቆን ዳንኤል፤ አንዱ ከሌላው ጋር እንዳይገናኝ ታጥሯል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የእኔ አላማ አሁን እየተገነቡ ያሉ ግንቦችን አፍርሶ ድልድይ መስራት ነው›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የክርስቲያን ህይወት ውስጥ የሙስሊም ህይወት አለ፤ በሙስሊም ህይወት ውስጥ የክርስቲያን ህይወት አለ፤ አንተ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ወላይታ ብቻ ነህ ብሎ ከመለያየት ይልቅም ሰርገኛ ጤፍን ቆጥሮ ጥቁሩን መለየት ይቀላል ብለዋል፡፡ ‹‹እርስ በርሳችን የሚያገናኙንን ድልድዮች መስራት ካልቻልን ለልጆቻችን የምናስረክባት ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ናት›› በማለትም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ የዳር ተመልካች መኖር የለበትም፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ ልክ እንደ ኳስ አስራ አንድ ሰው ሲጫዎት ሌላው የሚያጨበጭብበት ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡ ሁላችንም ተጫውተን ሁላችንም ዋንጫ የምናመጣበት እንጂ፤ የዳር ተመልካች መሆን አይኖርብንም፡፡
ኢትዮጵያ የሁላችንም እንጂ የእነከሌ ብቻ ወይም የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ አይደለችም፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሁላችንም አባቶች አስተዋጽኦ አድርገዋል ለዚህም ነው የሁላችንም ናት የምንለው፡፡
ለአድዋ ጦርነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከባሌ፣ ከዳውሮ፣ ከወላይታ፣ ከጋሞ፣ ከጎፋ፣ ከሀመር፣ ከጂግጂጋ፣ ከኦጋዴን ተነስተው ሀገሬ ብለው ዘምተዋል፡፡ ሁሉም ዜጋ በመምረጥ ለሀገሩ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪ ያቀረቡት ዲያቆን ዳንኤል የህዝብ ተውካዮች ምክር ቤት አባል በመሆኔ የማገኘው ጥቅም የለም፤ ነገር ግን ለዚች ሀገር እኔ ካልሰራሁ ማን ሊሰራላት ይችላል ብዬ በማሰብ ነው ብለዋል፡፡
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2013