ሶማሊያ ከኬንያ ጋር ያቋረጠችውን ዲፕሎማሲ እንደገና መጀመሯን ይፋ አድርጋለች። በሶማሊያ እና በኬንያ መካከል ተፈጥሮ በነበረው “ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት እና የድንበር መሬት ይገባኛል” ውዝግብ የሶማሊያ መንግሥት ከስድስት ወር ገደማ በፊት ከኬንያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳቋረጠ ተገልጾ ነበር።
የሶማሊያ ኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩን ጠቅሶ አልጀዚራ እንደዘገበው ደግሞ ሰሞኑን “የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት መልካም ጎረቤት ሃገርነትን ለማስጠበቅ ከኬንያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን” እንደገና አስጀምሯል።
“ሁለት ሃገራት ያላቸውን የወዳጅነት ግንኙነት ሃገራዊ ሉዓላዊነትን እና የጋራ ጥቅምን ባስከበረ መርህ ለማስቀጠል ተስማምተዋል” ብሏል። ለዚህም ውጤት የሶማሊያ ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይ ደግሞ የካታር መንግሥት የሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲ እንዲቀጥል ከፍተኛ ሥራ መስራታቸውን በመግለፅ አመስግነዋል።
በኬንያ በኩል ደግሞ ባለፈው ሐሙስ ዕለት ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከኳታር ልዩ መልዕክት እንደተቀበሉ አልጀዚራ ዘግቧል።የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ መሐመድ ቢን አብዱራህማን አል ታኒ የሁለቱ ሀገር መልካም ግንኙነት እንደሚቀጥል ተስፋቸውን ገልፀው በመካከላቸው ያለውን ተግባቦት ለመጨመር ኳታር እንደምትሰራ ማስታወቃቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።
ኳታር ይህን መሻሻል እንደምትከታተል እና ጣልቃ ገብነት የሚያስፈልግ ከሆነም ሁለቱን ሃገራት ግንኙነታቸው እንዲቀጥል እንደምታግዝ አስታውቀዋል።አሁንም ቢሆን የሶማሊያ መንግሥት ከኬንያ ጋር የሚኖረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደገና ለመጀመር ፈቃደኝነቱን ሲገልፅ በሁለቱም ሃገራት ጣልቃ ገብነት በማይኖርበት ሁኔታ እንደሚሆን ገልጿል።
ከዚህ ቀደም አዲስ ዘመን ከአንድ የኢጋድ ደህንነት ቢሮ ባለሙያ ጋር ባደረገው የስልክ ቃለ መጠይቅ ኬንያ እና ሶማሊያ እርስ በርሳቸው እየተጠራጠሩ ስለመሆናቸው ተናግረው ነበር። የኬንያ ወታደሮች በድንበር አካባቢ የጦር ዝግጅት እያደረጉ እንደነበር እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኬንያ ወታደር በተጠንቀቅ ላይ እንዳለ ሶማሊያ ባቀረበችው ቅሬታ ላይ ተመርኩዞ የኢጋድ ልዑካን ቡድን ባደረገው ማጣራት
ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እንደወትሮው እንደነበረም ባለሙያው ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ከሶማሊያ ለመገንጠል የሚንቀሳቀሱትን የጁባ ላንድ ፖለቲከኞች በኬንያ መንግሥት እርዳታ ይደረግላቸዋል በሚልም ሲካሰሱ መቆየታቸው ይታወቃል። ባለፈው ታህሳስ ወር የሶማሊያ መንግሥት በኬንያ የሚገኙ ዲፕሎማቶች ወደ ሃገራቸው ሶማሊያ እንዲመለሱ በማዘዝ፤ በሶማሊያ የነበሩ የኬንያ ዲፕሎማቶች ደግሞ እንዲወጡ ተደርጎ ነበር። በወቅቱም የሶማሊያ መንግሥት ኬንያ አሁንም በውስጣዊ ፖለቲካችን ጣልቃ መግባቷን ቀጥላለች፤ ከዚህ ቀደም የተስማማንባቸው ጉዳዮችን ጥሰዋል የሚል ክስ አቅርቦ እንደነበር በስፋት ሲነገር ነበር።
ዓለም አቀፍ ተቋሟትን ጨምሮ ብዙ አካላት የሁለቱ ሃገራት ውዝግብ ምክንያት አንድ ጉዳይ ባለመሆኑ ችግሩ እየተስፋፋ ሊሄድ ይችላል፤ ይህም ለአሸባሪዎች ትልቅ አቅም ሊፈጠር እንደሚችል ስጋታቸውን ሲገልፁ ነበር። የተሻለ የዲፕሎማሲ ዜና በተሰማበት በአሁኑ ጊዜ እንኳ የሁለቱ ሀገር የድንበር መሬት ይገባኛል ውዝግብ ያልተፈታ መሆኑ ደግሞ ችግሩ አሁንም እንደገና ሊያገረሽ እንደሚችል ስጋት ፈጥሯል። የኳታሩ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግን የድንበሩ ጉዳይ አወዛጋቢ ሆኖ የቆየ ቢሆንም አሁንም ድረስ ሁለት ሃገሮች ችግሩን የመፍታት ዕድል እና አቅም እንዳላቸው አስታውሰዋል።
ይህ አወዛጋቢው የድንበር መሬት በሕንድ ውቅያኖስ ዳርቻ አካባቢ ሲሆን፤ ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ ክምችት እንዳለው ይነገርለታል።
በቅርቡ ከተበሰረው አዲስ ግንኙነት ጋር ተያይዞ የሶማሊያ እና የኬንያ የንግድ፣ የሕዝብ ለሕዝብ፣ እና ሌሎች ማህበራዊ ግንኙነቶች የሚቀጥሉ መሆኑ ቢነገርም የድንበር ጉዳይ በተመለከተ ግን እስካሁን ከሁለቱም በኩል የተሰጠ ነገር የለም።
የሶማሊያ እና የኬንያ ውዝግብ በኢጋድ እና በጎረቤት ሃገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እንደነበርም ሲገለፅ ቆይቷል። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ የሁለቱን ሃገራት መሪዎች በተለያዩ ጊዜያት የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን እንዲያሻሽሉ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውም እንዲሁ የሚታወስ ነው።
በሰኔ ወር 2011 ዓመተ ምህረት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሁለቱን ሃገራት በጎበኙበት ወቅት በኬንያ እና በሶማሊያ መካከል ምንም ዓይነት ውጥረት ሊኖር እንደማይገባ በመናገር ኢትዮጵያም ችግሩን ለመፍታት ከሁለቱም ሀገር ጎን እንደምትቆም አስታውቀው ነበር።
የሱፍ እንድሪስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2013