ቤተሰብ የማህበረሰብ አንድ አካልና መሰረት እንደመሆኑ መጠን ደስተኛና ጤናማ ቤተሰብ በመመስረት ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት መሰረት ለመጣል ወሳኝ ነው። ለዚህ ደግሞ ነባራዊውን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ በእቅድ ላይ የሚመሰረትና የሚመራም ቤተሰብ ሊኖር ይገባል። ጥንዶች የሶስት ጉልቻን ጉዞ ʽሀʼ ብለው ሲጀምሩ ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸውና ለማህበራዊ ጉዳያቸው እቅድ እንደሚነድፉት ሁሉ የልጅ መውለድንም ጉዳይ በእቅድና በስምምነት ሊያደርጉት እንደሚገባ ይታመናል። ነገር ግን በአብዛኛው ከጋብቻ በፊትም ሆነ ከጋብቻ በኋላ ያልታሰበ እርግዝና እየተከሰተ የሚወለዱትንም ልጆች ሆነ ወላጆችን ላልተፈለገና ላልታሰበ ችግር ሲዳርግ ይስተዋላል። ያልታቀደ እርግዝና በትዳር ውስጥም ሆነ ከትዳር ውጪ በሚኖር የሁለት ጥንዶች ግንኙነት መካከል ሲከሰት የሚያስከትላቸውን ችግሮችና እንዴት መከላከል እንደሚገባ የስነ ልቦና ባለሙያ ከሆኑት ወይዘሪት ሀናን ሁሴን ጋር ቆይታ አድርገናል።
«ያልታቀደ እርግዝና በትዳር ውስጥም ሆነ ከት ዳር ውጪ ሆነው ለሚከሰትባቸው የራሱ ተጽእኖና የሚያስከትላቸው አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳቶች አሉ» የሚሉት ባለሙያዋ የችግሩን አሳሳቢነት በማንሳት እንዴት መከላከል እንደሚገባ እንደሚከተለው ያብ ራራሉ። ያልታቀደ እርግዝና በአሁኑ ወቅት ከዓለም የህዝብ የጤና አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል አንዱ እየሆነ በመምጣት ላይ ይገኛል። ይህም ሊሆን የቻለው ብዙውን ጊዜ ለዚህ ችግር የተዳረጉ ሴቶች ጤናማ ባልሆነ መንገድ ፅንሱን ለማስወረድ የሚሄዱበት ህገ ወጥ መንገድ በከፍተኛ ደረጃ ለበሽታ ተጋላጭ ስለሚያደርጋቸውና ጉዳዩ ጠንከር ሲልም ለሞት የሚያበቃቸው ይሆናል። ከዚህም ባለፈ ያልታቀደ እርግዝና ሴቶችን ከወሲብ ጋር ለተያያዙና ለሌሎች የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች የሚያጋልጥ ነው። ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎቶች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ውጤታማ እና ተደራሽ እየሆኑ ቢመጡም ዛሬም ድረስ ያልታሰበ እርግዝና እና ደህንነቱ ያልተጠበቀ የፅንስ ውርጃ ዋነኞቹ የህብረተሰብ ጤና ችግሮች እንደሆኑ በመቀጠል ላይ ይገኛሉ። በዚህም ያልታቀደ እርግዝና ሴቶችን በተለይ፣ ቤተሰቦቻቸውን እና ህብረተሰቡን የሚነካ ዓለም አቀፋዊ ችግር ነው።
ያልታሰበ እርግዝና ከሚከሰትባቸው ምክንያቶች መካከል የእርግዝና መከላከያ መክሸፍ፣ የእርግዝና መከላከያ አገልግሎቶችን አለመጠቀም፣ በአስገድዶ መደፈርና ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ ስጋ ግንኙነት በመፈጸም ከቀዳሚዎቹ መካከል የሚከሰቱ ናቸው። ለእነዚህ ምክንያቶች ተጋላጭ የሚሆኑት ደግሞ በዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ የሚገኙ፣ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ባልተሟላላት አካባቢ የሚኖሩ፤ ስል እርግዝና መከላከያ መንገዶችና አጠቃቀም በቂ ግንዛቤ የሌላቸው፣ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ፣ ለእኩያ ጫና ተጋላጭ የሆኑ አንዳንድ ጊዜም የአእምሮ ችግር ያለባቸው ሳይፈቅዱና ሳያስቡት ላልታቀደ እርግዝና የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ነው።
በተጨማሪም በአፍላ እድሜያቸው ወሲባዊ ግንኙነት የሚጀምሩ ሴቶች ከሌሎች የእድሜ ክልሎች ጋር የወሊድ መከላከያ የመጠቀም ዕድላቸው አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት ላልታሰበ እርግዝና የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ሆኖ ይገኛል። ባጠቃለይም ያላገቡ ሴቶች ባለ ትዳር ከሆኑት በበለጠ ላልታቀደ እርግዝና የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ሲሆን ከነዚህም መካከል ስነ ተዋልዶ ላይ በቂ እውቀት የሌላቸው፤ ያለ እድሜ ጋብቻ የፈጸሙ፥ እንዲሁም ከወሲብ ጓደኛቸው ጋር በግልፅ የማይወያዩ፥ የቤተሰብ ምጣኔ እቅድ በበቂ ሁኔታ አገልግሎቶች አለመኖር ተጠቃሽ ናቸው።
ከላይ በተጠቀሰው መንገድ የሚከሰተው ያልታቀደ እርግዝና በሴቶች ላይ የጤና፣ የኢኮኖሚያዊ እና የሥነ-ልቦናዊ ጫናዎችን የሚያስከትል ሲሆን በልጅቷ ቤተሰቦችና በማህበረሰቡም ላይ ከፍተኛ የስሜት ቀውስ (emotional distress) የሚያስከትል ይሆናል። ከእነዚህም መካከል በስፋት የሚስተዋሉት ለከፍተኛ ጭንቀት መዳረግና ያንን ተከትለው ለሚመጡ እንደ ስኳር ደም ግፊት ያሉ በሽታዎች መጋለጥ፣ ፍርሀት ወስጥ መግባት፣ የአእምሮ ዕረፍት በማጣት ለውጥረት መዳረግ፣ ተስፋ የመቁረጥ መሰማት፥ የሚደጋገምና ረጅም ጊዜ የሚቆይ ድብርት መከሰትና ከሰዎች የመገለልና የተሸናፊነት ስሜት ወስጥ መግባት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።
ያልታቀደ ወይም ያልተፈለገ እርግዝና ከትዳር ዉጪም ሆነ በትዳር ውስጥ የሚያጋጥም ሲሆን በትዳር ዉስጥ የሚከሰተውም ልጅ ለመውለድ ሳይታቀድ ወይም ተጨማሪ ልጆችን ለመውለድ ባልታሰበበት ጊዜ ሲፈጠር ነው። በዚህ ወቅትም በአንድ ወገን እንደ ማህበረሰብ ያልታቀደ እርግዝናን የመቆጣጠር ኃላፊነት የሴቶች ብቻ ተደርጎ ስለሚወሰድ በሌላ በኩል ደግሞ ተፈጥሯዊ በሆነውም ሂደት ችግሩን ሙሉ በሙሉ የሚቀበሉት ሴቶች ብቻ ይሆናሉ። ነገሮችን በመነጋገርና በመግባባት እንዲሁም በመደማመጥ የመፍታት ልምድ የሌላቸው ጥንዶች ከሆኑ ችግሩ ጭቅጭቅ ከመፍጠርና ሰላማቸውን ከመንሳት ባለፈ ለፍቺና ለግብግብ የሚዳረጉበትም አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንደ ባለትዳርም ሁለቱ ጥንዶች እርግዝና ይከሰታል ብለው ራሳቸውን በስነ ልቦናም ሆነ በፋይናንስ አዘጋጅተው ስለማይጠብቁ እያንዳንዷን እንቅስቃሴ የሚቀበሉትና የሚያስተናግዱት አንደ አዲስ ይሆናል። በመሆኑም የየእለት እንቅስቃሴያቸው ከተለመደው ሁኔታ በተለየ በእቅድ ከመመራት ይወጡና ሁኔታዎች ብቻ በሚመሩት መልኩ እየሆነ ይመጣል። በዚህም የተነሳ ልጅ ወልደው ወደ ቀደመው ሰላማዊ ሁኔታ እስኪመለሱ ድረስ ካሰቡት መስመር የወጣ ምን አልባትም ጤነኛ ባልሆነ ህይወት ውስጥ ለመቆየት ይገደዳሉ።
እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች በቤተሰብ ውስጥ እንዳይከሰቱ ለማድረግ በቅድሚያ ያልታቀደ እርግዝና እንዳይከሰት ወንዶች ከሴቶች እኩል ኃላፊነት እንዳለባቸው ሊገነዘቡና ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። በሁለተኛ ደረጃ በስህተት ያልታቀደ እርግዝና ቢከሰት እንኳን ከመወቃቀስና ከመነቃቀፍ ይልቅ የተከሰተውን ነገር ተቀብሎ ቀጥሎ መሆን ስላለበት ነገር በተረጋጋ መንፈስ በመከባበር ሊወያዩበትና የመፍትሄ ሀሳብ ሊያስቀምጡ ይገባል።
ያልታሰበ እርግዝና በአፍላ ዕድሜ ላይ ባሉና ትዳር ባለመሰረቱ ወጣቶች ላይ በሚከሰትበት ጊዜ ከሁሉም በበለጠ በሴቷ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚፈጥር ይሆናል። በዋናነትም ትምህርት ማቋረጥ፣ የቤተሰብ ግንኙነቶች መናጋት፣ ለኢኮኖሚያዊ ጫና መዳረግ፣ ከማህበረሰቡ ለሚሰነዘሩ ትችቶችና ላለመረጋጋት መዳረግ ይጠቀሳሉ። እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜ በወጣትነት ዕድሜ ከትዳር በፊት ያልታቀደ እርግዝና መከሰቱን ሲሰማ ወንዱ በስጋት ሊሸሽ ይችላል ወይም ከእኔ አይደለም ብሎ ልጁን እስከመካድ ሊደርስ ይችላል። እንደዚህ አይነት ሁኔታዎችም ሲፈጠሩ አባት ያልተቀበለውን ልጅ በማሰብ ከእርግዝናው ባልተናነሰ ተደራቢ ችግር ሆኖ የሚመጣው ሳይታቀድ ላረገዘችው ልጅ ነው።
በሌላ በኩል በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ከሚገኙና ለእርግዝና በቂ የአካል ዝግጅት ከሌላቸው ወጣቶች የተወለዱ ልጆች የወደፊት ሕይወታቸው ላይ የተለያዩ ችግሮች የመጋለጣቸው እድል ሰፊ ነው። ከእነዚህም መካከል የአካላዊ እድገት እክል (developmental disorder)፣ የባህርይ ችግሮች (behavioral problems) እንዲሁም የትምህርት ውጤታቸው ላይ ደካማ መሆን (low academic performance) ይጠቀሳሉ። በእርግዝና ወቅት በተለያየ መልኩ የማስወረድ ሙከራ ተደርጎ ሳይሳካ ቀርቶ ከነበረ ደግሞ በህጻናቱ ላይ ከዚህም የበለጠ የጤና ችግሮች የመከሰት እድላቸው በጣም የሰፋ ነው። በመሆኑም ሲያድጉ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለማስቀረት ወይንም ለመቀነስ ከተወለዱ በኋላ ከሌሎች ህጻናት በተለየ ትኩረት የህክምናና ክትትል ድጋፍ እንዲሁም በአስተዳደግ ወቅት ጥንቃቄ ሊደረግላቸው ይገባል።
በእዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ልጆች ያልታቀደ እርግዝና ሲገጥማቸው አብዛኛውን ጊዜ እንደ ብቸኛ ምርጫ አድርገው የሚወስዱት ፅንሱን ማቋረጥ ነው። ይህንንም የሚያደርጉት ከቤተሰቦቻቸውና ከማህበረሰቡ የሚደርስባቸውን ጫና ለመሸሽ፣ እድሜያቸው ገና እንደሆነ በማሰብ ወይም ከአላማቸው መስተጓጎልን በመፍራት እንዲሁም አባት የሌለው ልጅ ላለማሳደግ ሲሉ ነው። ጽንስን ማቋረጥ ደግሞ በህግም በሃይማኖትም እንደ ማህበረሰብም የማይደገፍ ብቻ ሳይሆን የሚነቀፍም ተግባር ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ጉዳዩ ቤተሰብና የአካባቢ ነዋሪ እንዳይሰማ ተደርጎ ስለሚፈጸምና እንደ ሀገርም ይህንን አገልግሎት የሚሰጡ በቂ የህክምና ተቋማት ባለመኖራቸው ተመራጭ አማራጭ የሚሆነው በየመንደሩ ወዳሉ የባህልና የልምድ ሀኪሞች ማምራት ይሆናል። እነዚህ የልምድ አዋላጆች ደግሞ እነሱም በሳይንሳዊ መንገድ ያልተማሩና በቂ የህክምና ቁሳቁስና ማከሚያ ቦታ ሳያዘጋጁ ከመንግሥት ተቆጣጣሪ አካላት ጋር ድብብቆሽ እየተጫወቱ የሚሰሩ ናቸው። በመሆኑም የሚሰሩት ጽንስን የማቋረጥ ሥራ ሁሌም ቢሆን ችግሮች ያሉበት ሲሆን ጽንስ የምታስወርደውን ልጅ ከከባድ ስቃይ ጀምሮ እስከ ሞት ለሚያደርሱ የተለያዩ የጤና ችግሮች እንዲጋለጡ ያደርጋል። በዚህ ረገድ ከተለመዱት ጉዳቶች መካከል ከመጠን በላይ ደም ስለሚፈሳቸው ራስ መሳት፣ ጽንሱን ለማስወረድ የሚጠቀሙባቸው መገልገያዎች ንጽህናቸው የተጠበቀ ባለመሆኑ ለኢንፌክሽንና ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች መዳረግ፣ እንዲሁም መካንነት ተጠቃሽ ናቸው።
በሌላ በኩል ያልታቀደ እርግዝና በሁለቱ ጥንዶች (በባልና በሚስት) እንዲሁም ከልጆች አንዳቸው ላይ ያልተፈለገ እርግዝና ቢከሰት የሚያስከትለው ተጽእኖና የሚፈጠረው ችግር ተካፋይ የሚሆኑት ሁሉም የቤተሰቡ አባል ናቸው። ያልተፈለገ እርግዝና ሲከሰት ሁሌም ቢሆን የችግሩ ቀዳሚ ገፈት ቀማሽ የሚሆኑት ሴቶቹ መሆናቸው ይታወቃል። በተለይ ያረገዘችው ወጣት በትምህርት ውስጥ እያለች ከቤተሰብ ፈቃድ ውጪ በተፈጠረ ግንኙነት ከሆነ አጠቃላይ ቤተሰቡ ላይ በሁለት መልኩ ተጽእኖ ሊፈጠር ይችላል። የመጀመሪያው ቤተሰቡ እናትና አባት ወይንም ወንድምና እህት እንዲህ አይነት ነገሮች መከናወን ያለባቸው ባህልን መሰረት ባደረገ መልኩ በስርዓት መሆን አለበት ብለው ስለሚያስቡ የተፈጠረውን ነገር በጸጋ ለመቀበል ይቸገራሉ። አንዳንድ ቤተሰቦችም ያረገዘችው ልጅ ላይ የተለያዩ ለከፍተኛ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ችግሮች የሚዳርጉ ውሳኔዎችን ሲወስኑ ይስተዋላል። በሁለተኛ ደረጃ የተፈጠረውን ያልተፈለገ እርግዝና ቤተሰቡ አምኖ ሊቀበል ቢፈልግ እንኳን ከማህበረሰቡ ልምድ ውጪ የተከሰተ በመሆኑ በአረገዘችውም ወጣት ላይ ሆነ በቤተሰቡ ላይ ከማህበረሰቡ የሚመጣ ከፍተኛ ስነልቦናዊ ተጽእኖ ይኖራል። በዚህም የተነሳ ብዙ ጊዜ ካለ እቅድ ያረገዙ ሴቶች ጽንስ ለማስወረድ መሞከር፤ ከቤት መጥፋትና አንዳንድ ጊዜም ራሳቸውን ለማጥፋት እስከ መሞከር ይደርሳሉ።
በመሆኑም በልጆች ላይ ያልተፈለገ እርግዝና እንዳይከሰትና ከተከሰተም ለተጨማሪ ችግሮች ምክንያት እንዳይሆን በተመለከተ ከቤተሰብ ሊኖር የሚገባው ምላሽ በሁለት አይነት መልኩ ሊሆን ይገባል። በቅድሚያ እንደዚህ አይነት ችግሮች እንዳይከሰቱ ሴት ልጆችን ገና ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሄዋን ከደረሱበት ጊዜ ጀምሮ ስለ ስነ ተዋልዶ በግልጽ ማነጋገር። ይህንን ለማድረግ ቤተሰቦች የግድ የህክምና ወይንም የስነ ልቦና እውቀት ሊኖራቸው አይገባም። ይልቁንም የራሳቸውን ያለፈ ህይወት መሰረት በማድረግና በአካባቢያቸው ያለውንም ነገር ከግምት በማስገባት መሰረታዊ የሆኑትን ትልልቅ ችግሮች ሊያስከስቱ የሚችሉ ሁኔታዎችን ማስተማር ያስፈልጋል።
እነዚህም እርግዝና እንዴት ሊከሰት እንደሚችል፤ ከወንድ ጓደኞቻቸው ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት እንዴት መሆን እንዳለበት፤ እንዲሁም የችግሩን አሳሳቢነት በመግለጽና ድንገት እንኳ ያልታቀደ እርግዝና ቢከሰት ከቤተሰብ ለአንድ ሰው፤ ለመምህር አልያም በመደበኛው መንገድ ለህክምና ባለሙያ ማሳወቅ እንደሚኖርባቸው ግንዛቤ ማስጨበጥም ተገቢ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአፍላ እድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ከሚመከሩትና ከሚነገራቸው ይልቅ ለስሜታቸውና ከእኩያ ግፊት ተጋላጭ የመሆናቸው እድል ሰፊ ነው። በመሆኑም በተቻለ መጠን ከመምህራኖችና ከአካባቢ ነዋሪ ጋር በመሆን ክትትል በማድረግ በእረፍት ጊዜ የሚውሉባቸው ቦታዎች ለአደጋ የሚያጋልጧቸው እንዳይሆኑ መከላከል ይገባል። ይህን አልፎ የሚፈጠር አጠራጣሪ ሁኔታ ካለ ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያዎችን ጨምሮ ለእድሜና ለጤና ተስማሚ የሆነ የስነ ተዋልዶ ጤና አጠባበቅ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ማድረግ ይመከራል።
በሁለተኛ ደረጃ ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ቤተሰብ ከልጁም ሆነ ከውጭ ሰው ችግሩ እንደተከሰተ ካወቀ ቅድሚያ ሰጥቶ ማድረግ ያለበት የልጅቷንም የህጻኑንም ደህንነትና ጤና መጠበቅ ነው። ብዙ ጊዜ እንደሚታየው ልጅን ማስፈራራት መደብደብና ከቤት ማስወጣት እሷንም ለተደራራቢ ችግር የሚያጋልጥ ሲሆን የቤተሰብንም ሰላም የሚያሳጣ ይሆናል። ስለዚህ አስፈላጊውን ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ የልጅቷን ጤናና ስነልቦና እንዲሁም የህጻኑን ጤንነት መጠበቅ ይገባል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27/2013