የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ዘርፍ በኢትዮጵያ ከተጀመረ ከ19ዎቹ አጋማሽ አንስቶ ላለፉት ዓመታት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የገቢ አቅም በማሳደግና ድህነትን በማስወገድ ሰፊ ድርሻ አበርክቷል ። ዘርፉ በርካታ ባለሃብቶች የተፈለፈሉበት ፣ለመካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች መሰረት የጣለበት ነው ። አገሪቱ ላስመዘገበችው ኢኮኖሚያዊ እድገት ሁነኛ ድርሻም ተወጥቷል። በመወጣትም ላይ ይገኛል ።
የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ማደግ፣የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት መስፋፋት እንዲሁም የዩኒቨርስቲዎቻችን ቁጥር ማሻቀብ የፈጠሩትን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ወደ ኢንዱስትሪ ልማት የሚደርገውን ሽግግር ለማሳካት የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ታሳቢ ያደረገ ፖሊሲ ተቀርፆ እሱን ለማስፈፀም ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው።
የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት አገሪቱ ያላትን ውሱን ካፒታልና ሰፊ የሰው ኃይል በአግባቡ ለመጠቀም እያስቻለ ሲሆን በከተሞች ያለውን የሥራ አጥነት ችግር በመቅረፍም ከግብርና ቀጥሎ ሰፊ የሰው ኃይልን የሚያቅፍ መስክ ሆኗል።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማት መሰረታዊ ማጠንጠኛ የሥራ እድል መፍጠር መሆኑ አጠያያቂ አይደለም ። የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችም በኢኮኖሚው ውስጥ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርትና ስራ ዕድል ፈጠራ አንጻር ከፍተኛ ድርሻ አላቸው::
ኢንተርፕራይዞቹ ዋነኛ የስራ እድል ፈጣሪ ኃይሎች የሚሆኑት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ብቻ አይደለም ። በአፍሪካ ሆነ በሩቅ ምስራቅ አገራትም አበርክቷቸው ከፍተኛ ነው። ምስራቅ አፍሪካዊቷን ኬንያን ብንመለከት እንኳን ኢንተርፕራይዞች ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ሶስት በመቶ ድርሻን ሲወስዱ ከሥራ እድል ፈጠራ አንፃር 30 በመቶውን ሚና ተረክበዋል።
ኢንተርፕራይዞች ለህንድ ኢኮኖሚ እድገት ዋነኛ መዘውር ናቸው።መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በተለይ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት እስከ 30 በመቶ የሚሆነውንም ድርሻ እንዲሁም በውጭ ከሚላኩ ጠቅላላ ምርቶች ውስጥ 40 በመቶ የሚሆነውን ይወስዳሉ ። በሥራ እድል ፈጠራም ከ 110 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በኢንተርፕራይዙ ስር ይንቀሳቀሳል።
ለአብነት እነዚህን አነሳን እንጂ የተለያዩ አገራት መንግስትም ኢንተርፕራይዙ የሚያበረክቱት ሁለንተናዊ ፋይዳ ጠንቅቀው በመረዳት እነርሱን ለማብቃት የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋሉ ። የተለያዩ እድሎችን ይመቻቻሉ ። በኢትዮጵያም የዘርፉ ልማትና የስራ እድል የመፍጠር አቅም ለማሳደግ እንዲቻልም በመንግስት በኩል ከፍተኛ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል ። የመስሪያ እና መሸጫ ቦታ አቅርቦት ጨምሮም ለኢንተርፕራይዞቹ እድገት ወሳኝ የሆኑ የስልጠና እና ብድር የማቅረብ እና የማመቻቸት ስራ ሲሰራ ቆይታል፡
ከመንግሥት ድጋፍ እና ክትትል ጥረት ባሻገርም የሶስተኛ ወገን ወይንም ባለድርሻ አካላት ኢንተርፕራይዞችን የመደገፍ እና ማብቃት አስተዋፅኦ ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ በአሁን ወደ ተሻለ ደረጃ በመጠጋት ላይ እንደሚገኝ በርካቶች ሲገለፅ ይሰማል።
ከቀናት በፊት የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የግብይትና የማምረት አቅም ያሳድጋል ውጤታማ እንዲሆኑም ያግዛል የተባለ ፕሮግራም ይፋ መሆኑም ለዚህ አብይ ምስክር ይሆናል ። ይሕ ፕሮግራም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ያንግ አፍሪካ ዎርክስ ብሪጅ ደጋፊነት እና በፈርስት ኮንሰልት ተግባሪነት በጋራ ያሰናዱት ነው።
በዚህ ፕሮግራም ለተመረጡ 525 የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የንግድ ክህሎት እና ሌሎችም ተጓዳኝ ስልጠና እና ድጋፎች የሚሰጡ ይሆናል። በመርሐ-ግብር ማስጀመሪያ ላይ የፈርስት ኮንሰልት ብሪጅ ፕሮግራም መሪ አቶ ሚካኤል አዲሱ እንደገለጹትም፤ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ እስከ 2030 ዓ.ም ድረስ ከ10 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች አመቺን እና ተስማሚ ሥራ እድሎችን የመፍጠር አላማ ይዞ ተነስቷል ። ብሪጅስ ፕሮግራምን የአምስት ዓመት ፕሮግራም ሲሆን የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና የሌሎች ድርጅቶችን እንዲሁም የጥቃቅን፣አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ትስስርን በመፍጠር ለወጣቶች የስራ እድል ለማመቻቸት እየሰራ ይገኛል።
በዚህም ከስድስት መቶ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ እድል የመፍጠር እቅድ አለው ። ከዚህም ሰማንያ በመቶው የሴቶች ድርሻ እንዲሆን አቅዶ እየሰራ ይገኛል።ከ15 ሺህ በላይ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተደግፈው ለወጣቶች የስራ እድል እንዲፈጥሩ እየተጋ ይገኛል ። ከሶስት መቶ ሺ በላይ ሥራ አጥ ወጣቶችን ስልጠና በመስጠት በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች መካከል የገበያ ትስስር እንዲፈጠር እየሰራ ነው።
ፕሮግራሙ አራት የትኩረት አቅጣጫዎች ያሉት ሲሆን የሥራ ቅጥር ትስስር፣ የኢንተርፕራይዝ ልማት እና እድገት፣ የኢንተርፕራይዞችን ተወዳዳሪነት ማሳደግ እና የፋይናንስ ተደራሽነትን ማጎልበት ናቸው ። ፕሮግራሙ በአሁን ወቅት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ 25 ሺ ለሚሆኑ የከተማዋ ስራ አጥ ወጣቶች የሕይወት ክህልቶች እና ሥራ ፈጠራ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገቡ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ። በከተማዋ ከሚገኙ ባንኮች እና የብድር ተቋማት ጋር በመተባበር ለሥራ ፈላጊ ወጣቶች የፋይናንስ ድጋፍ እና የግንዛቤ ሰልጠና በመስጠት ፍላጎትን ያማከለ የብድር አገልግሎቶች እንዲሰጡ እገዛ በማድረግ ላይ ይገኛል።
‹‹በኢንተርፕራይዝ ልማት ትኩረት አቅጣጫ ስር እየሰራን ካለናቸው ተግባራት አንዱ ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በተለያየ መልኩ መደገፍ ነው››ያሉት አቶ ሚካኤል፣አሁኑ የድጋፍ የፕሮግራም ዋና ዓላማም፣ኢንተርፕራይዞቹን ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ የንግድ ክህሎት እና የቢዝነስ ልማት ድጋፋ በመስጠት አቅማቸው ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርሱ፣የገበያ ትስስር በማጎልበት ሽያጭ እና ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ፣የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲሁም የሥራ እድል እንዲፈጥሩ ማገዝ ነው።
ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ዋነኛ የኢኮኖሚ ዘዋሪዎች በመሆናቸው ፍላጎት እና ተሳትፏቸው እጅግ ወሳኝ ስለመሆኑ አፅእኖት የሠጡት አቶ ሚካኤል፣ይሕን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ድጋፍ ከኢንተርፕራይዞቹ አልፎ ለአገሪቱ እድገት በተለይም በስራ እድል ፈጠራ ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር ስለመሆኑም ያስገነዝባሉ ።
በአዲስ አበባ ከተማ ከ36 ሺ በላይ ጥቃቅን አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ስለመሆናቸው የሚጠቁሙት ደግሞ የከተማ አስተዳደር የሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ይመር ከበደ ናቸው ። እንደ አቶ ይመር ገለፃም፣ባለፉት ዓመታት ኢንተርፕራይዞች ሁለንተናዊ ተሳትፎ አመርቂ ተብሎ የሚወሰድ ነው ። ይሁንና ጥረት እና የመጡበት መንገድ አልጋ በአልጋ አይደለም። ይልቅስ በበርካታ ፈተና እና ችግሮች የተተበተበ ነው ።
‹‹ጥቃቅን አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ወሳኝ የአገር የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች ናቸው›› የሚሉት አቶ ይመር፣ያሉባቸውን መሰረታዊ ችግሮች በመንግሥትም ሆነ በባለድርሻ አካላት ተጠንቶ መለየቱን እና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ማረጋገጥ መቻሉንም ነው ያስገነዘቡት ። ይሁንና ችግሮቹ በአንድ ወገን በተለይ በመንግሥት ተሳትፎ ብቻ ሊቃለሉ እና መፍትሄ ሊሰጣቸው የማይችሉ ስለመሆናቸውን ያሰምሩበታል ።
የብሪጅ ፕሮግራም ሁሉን አቀፍ የድጋፍ መርሐ ግብር የመንግሥት ኢንተርፕራይዞቹን ለማብቃት ብሎም ውጤታማ ለማድረግ እና ያሉባቸውን ችግሮች ለማቃለል እያደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ ረገድ ጉልህ ሚና የሚጫወተው ስለመሆኑ ያወሱት አቶ ይመር፣በፕሮግራሙም ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ በተለይም ፍላጎት ያላቸው እና ቢዝነሳቸው ጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች የተለዩ ስለመሆናቸው ነው የገለጹት።
ይሑንና በኢንተርፕራይዞቹ ላይ መሰረታዊ የሚባል ለውጥ ማምጣት እንዲሁም በሂደት የማስተዋሉ ልምዶች ለመውሰድ ግማሽ ያህሉን ቅድሚያ እንዲሳተፉ መደረጉን ያስገነዘቡት የቢሮ ኃላፊው፣‹‹በተለይም ወጣቶች እና ሴቶች ልዩ ትኩረት አግኝተዋል ነው››ያሉት ።
ኢንተርፕራይዞቹ በሁሉ ረገድ ውጤታማ ለመሆን መሰል ድጋፎችን በተለየ መንገድ ሊጠቀሙባቸው እንደሚገባ አፅእኖት የሠጡት የቢሮ ኃላፊው፣ፕሮግራሙም ኢንተርፕራይዞች ቢዝነሳቸውን እንዴት መምራት እና ማስተዳደር እንዳለባችሁ፣ ምርታቸውን እንዴት ለገበያ ማቅረብ እንደሚችሉ በቂ እውቀት ብሎም ክህሎት እንዲጨብጡ ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።
ከመንግሥት ድጋፎች ባሻገር መሰል በሶስተኛ ወገን ወይንም በባለድርሻ አካላት የሚመቻቹ እድሎችን በመጠቀም አቅማቸውን ይበልጥ ማጎልበት እና ውጤታማ ሆነ በተለይም የሥራ እድል በመፍጠር ራሳቸውንም አገራቸውንም ስለ መጥቀም ታሳቢ ማድረግ እንዳለባቸው አፅእኖት ሰጥተውታል ።
ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት መንግስት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶት ክትትልና ድጋፍ የሚያደርግበት ዘርፍ ስለመሆኑ አፅንዖት ሰጥተው ያስገነዘቡት ደግሞ በአዲስ አበባ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር አባይ ናቸው።
እንደ እርሳቸው ገለፃም፣ በኢትዮጵያ ጥቃቅን እና አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን የማስፋፋት እና የማሳደግ ስራ በተለያየ መልኩ ሲሰራበት የቆየ እና ውጤትም ያስገኘ ተግባር ነው ። በርካታ ኢንተርፕራይዞች ከጥቃቅን ወደ መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንተርፕራይዝነት ተሸጋግረዋል። በዚህም የበርካቶች አባላት ሕይወት መለወጥ ተችሏል። ከሥራ እድል ፈጠራም ሆነ እንደ አገራዊ ለተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገትም ከፍተኛ አቅም መፍጠር ተችሏል።
ጥቃቅን ፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር እንዲሁም ለአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ እጅጉን የጎላ መሆኑን ከተማ አስተዳደሩ ጠንቅቆ እንደሚገነዘብ ያስረዱት አቶ ዣንጥራር፣‹‹በአስር ዓመቱ የልማት እቅድ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን የማምረት አቅም በማሳደግ በዘርፉ ተወዳዳሪና የምርት አቅርቦትን ማሳደግ ነው››ብለዋል ።
ከተማ አስተዳደሩ በራሱ ተቋማት ከሚያደርጋቸው ክትትል እና ድጋፍ በተጨማሪ ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን ኢንተርፕራይዞችን አቅም ለማሳደግ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ዣንጥራር፤ የማስተር ካርድ ድጋፍ ኢንተርፕራይዞች በሚፈልጉት ዘርፍ ውጤታማ ተወዳዳሪ እና በገበያ ውስጥ ተፈላጊ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነ ነው ያስረዱት።
የኢንተርፕራይዞቹ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አቅም ከማሳደግ አንጻር ካለው የጎላ ሚና በተጨማሪ የመንግሥትን እና የከተማ አስተዳደሩን ጥረት የሚያግዝ እንዲሁም የመንግሥትና የግል ተቋማት ትብብር ውጤት የሚያሳይ ነው ።
የአገሪቱ ጥቃቅን እና አነስተኛ መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የእድገት ደረጃቸው ገና የሚባል እና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ተዋናይ ናቸው በሚል የሚወሰድ አለመሆኑ ያመላከቱት አቶ ዣንጥራር፣በዚህ ረገድ የተከናወኑ ተግባራትም ከጅምር የዘለሉ ባለመሆናቸው ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት ይበልጥ መጎልበት እንዳለበት አፅንዖት ሰጥተውታል ። ለዚህም‹‹የግልም ሆነ መንግሥታዊን አቅም አሟጦ መጠቀም የግድ ይላል ነው ››ያሉት።
የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ያሉባቸውን ችግሮች በመቅረፍ ውጤታማ እንዲሆኑ ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እንደሚሰራና የከተማ አስተዳደሩ የትኛውም ድጋፍ ያለ ኢንተርፕራይዞቹ ውጤታማ መሆን ስለማይችል በሁሉ ረገድ ንቁ እና ተሳታፊ እንዲሆኑም ጥሪ ሳያቀርቡ አላለፉም።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013