ጉዲፈቻ የሚለው ቃል ከኦሮምኛ ቋንቋ በቀጥታ ወደ አማርኛ የተወሰደ ሲሆን፤ ትርጓሜውም ተፈጥሮዓዊ ወላጅነትና የልጁ የሥጋ ዝምድ በተለያዩ ምክንያት ሳይኖር ሲቀር ከሌላ ሰው አብራክ የተወለደን ልጅ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ጥቅሙን ጠብቆ እንደ አብራክ ክፋይ ልጅ ማሳደግ ማለት ነው።
ጉዲፈቻ አድራጊው በነጻ ፈቃዱ ከሌላ አብራክ የተገኘን ልጅ ለማሳደግና ለመጠበቅ እንዲሁም ልጁ እድገቱ አስፈላጊ የሆኑትን ማናቸውም እንክብካቤዎች ለማድረግ ወስኖ የሚወስደው ሃላፊነት ነው። ይኼም ልጁ የጉዲፈቻ አድራጊውን ቤተሰብ ስም፣ ንብረትና ሌሎች ጉዳዮችን እንዲካፈል የሚያደርግ መብት ያጐናጽፈዋል። በጉዲፈቻ የሚያሳድገው ልጅ ከአብራኩ ክፋይ የተገኘው ልጅ ያለው ማንኛውም መብት ይኖረዋል።
በአጠቃላይ ጉዲፈቻ አንድ ሰው ቀደም ሲል የነበረውን ቤተሰባዊ የደም ትስስር በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ በአዲስ ቤተሰባዊ ትስስር የሚተካ ወይም የሚለውጥ ማህበራዊ ተቋም ነው ሊባል ይችላል።
በአገራችን የጉዲፈቻ ታሪክን ስንመለከት በኢትዮጵያ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በባህላዊ መንገድ ሲደረግ እንደነበረ ቢነገርም በእርግጠኝነት መቼ እንደተጀመረ የሚጠቁም ጥናት አልተገኘም። ሆኖም ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በኦሮሞ ማህበረሰብ ሲተገበር እንደነበረ ይነገራል።
ነገር ግን ጉዲፈቻ ለመጀመሪያ ጊዜ የህግ ማዕቀፍ የተበጀለት በ1952 ዓ.ም በወጣው የፍትሐብሄር ህግ ነው። በዚህ ህግ ስለ ድንበር ተሻጋሪ ጉዲፈቻ በግልፅ የተቀመጠ ነገር አልነበረውም። ለዚህም ነው በፍትሐብሄር ህግ ውስጥ ያለውን የቤተሰብ ህግ ክፍል ከልጆች ደህንነት፣ አስተዳደግና አጠባበቅን አስመልክቶ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስትና ኢትዮጵያ ካጸደቀቻቸው አለማቀፍ ስምምነቶች ጋር አጣጥሞ ማሻሻል በማስፈለጉ የተሻሻለ የቤተሰብ ህግ በአዋጅ ቁጥር 213/92 ፀድቆ እየተሰራበት ነው።
በፌዴራል ደረጃ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግም በምዕራፍ አሥር ስለ ጉዲፈቻ በዝርዝር ይደነግጋል። በአንድ ሰውና በአንድ ልጅ መካከል በሚደረግ ስምምነት የጉዲፈቻ ዝምድና ሊፈጠር እንደሚችል በአንቀጽ 180 ስር ሰፍሯል። በዚህም ሕጉ የጉዲፈቻ ሥርዓት አፈጻጸም መሠረታውያንን ማለትም የዕድሜ ገደብ፣ የስምምነት አሰጣጥ፣ የባለድርሻ አካላትን (ዕጓለማውታ ድርጅቶችን፣ የሕፃናትን ጉዳይ የሚመለከተውን የመንግሥት አካልንና የፍርድ ቤቶችን) ሚና በዝርዝር አስቀምጧል።
በዚህ ህግ ሕፃናት / ልጆች ኢትዮጵያዊም ሆነ የውጭ ዜግነት ባላቸው የጉዲፈቻ አድራጊዎች በስምምነት ሊሰጡ እንደሚችሉ ተመላክቷል። በአዋጁ አንቀፅ 193 እና 194 ላይ የውጭ ጉዲፈቻ እንደ አማራጭ መቀመጡ በህፃናቱ ላይ የተለያየ የማንነት ጥያቄዎችና ችግሮችን ከመፍጠሩ በሻገር በህፃናት ላይ ለሚፈፀሙ የተለያዩ ወንጀሎች በር እየከፈተ በመምጣቱ በ2010 ዓ.ም የወጣው አዋጅ ቁጥር 1070/2010 የቤተሰብ ህጉን በማሻሻል አገራችን የውጭ ጉዲፈቻ ስርዓትን እንድታስቀር / እንድትከለክል አድርጓል።
ኢትዮጵያ ህፃናትን ለውጭ አገራት ዜጎች በማደጎነት በመስጠት ከሚታወቁ አስር የዓለም አገሮች አንዷ እንደነበረችም መረጃዎች ያሰያሉ፡ አሁን ላይ ከዚህ አዋጅ መውጣት በኋላ በውጭ አገራት ዜጎች የሚደረግ የጉዲፈቻ ስርዓት ሙሉ ለሙሉ በህግ እንዲቆም ተደርጓል።
በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ መሰረት የጉዲፈቻ ዝምድና በጉዲፈቻ አድራጊውና በጉዲፈቻ ልጁ ማለትም በአሳዳሪው በኩል በሚደረግ ስምምነት የሚፈጸም ነው። ይህ ስምምነት ውጤት እንዲኖረው በአዋጁ በአንቀጽ 180፣190 እና በአንቀጸ 194 ንኡስ አንቀጸ 1 መሰረት በፍርድ ቤት ቀርቦ መጽደቅ ይኖርበታል። ስለዚህ አንድ ልጅ በባልና ሚስት ጉዲፈቻ ከሚደረግበት ሁኔታ በስተቀር በአንድ ጊዜ ለብዙ ሰዎች የጉዲፈቻ ልጅ ሊሆን አይችልም።
የጉዲፈቻ ውጤትን ስንመለከት ጉዲፈቻ የተደረገ ልጅ ከጉዲፈቻ አድራጊው ልጅ ጋር ተመሳሳይ መብት ያለው ሆኖ እንደ ልጅ ይቆጠራል። ይህ ማለት የጉዲፈቻ ልጅ እንደማንኛውም የተፈጥሮ ልጅ ከጉዲፈቻ ቤተሰቦቹ ጋር ህጋዊ ትስስር የሚኖረው ሆኖ ውርስን ጨምሮ ሌሎች ህጋዊ መብቶች ይኖረዋል።
ምንም እንኳን የጉዲፈቻ ልጁ የጉዲፈቻ አድራጊው ልጅ እንደሆነ የሚቆጠር ቢሆንም ከተፈጥሮ ወላጆቹ ጋር የነበረውን ዝምድናና ትስስር ይዞ የሚቀጥል ይሆናል። ሆኖም አስገዳጅ ሁኔታ ተፈጥሮ ከሁለት አንዱን መምረጥ ካለበት ከተፈጥሮ ቤተሰቦቹ ይልቅ የጉዲፈቻ ቤተሰቦቹ ሊመረጡ እንደሚገባ ህጉ በአንቀጽ 183 ደንግጓል።
ወደ ላይ የሚቆጠሩ ወላጆችን ወይም ወደ ጎን የሚቆጠሩ ዘመዶችን በሚመለከት ጉዲፈቻውን በግልጽ የተቃወሙና ይህንን ተቃውሟቸውን የጉዲፈቻ ስምምነቱ በፍርድ ቤት መጽደቁን ባወቁ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ በፍርድ ቤት መዝገብ ካስመዘገቡ የጉዲፈቻው ስምምነት ወይም ዝምድና በእነሱ ላይ ውጤት ወይም ተቀባይነት አይኖረውም።
አንድ ሰው በጉዲፈቻ አድራጊነት ልጅ ወስዶ ለማሳደግ በእድሜ መብሰል አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት በቀድሞ ህግ ላይ 18 አመት የነበረውን ዝቅተኛ እድሜ ከፍ በማድረግ የቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 184 ንኡስ አንቀጽ 1 የጉዲፈቻ አድራጊው ዝቅተኛው እድሜ 25 አመት እንዲሆን ደንግጓል።
ጉዲፈቻ አድራጊዎቹ ባልና ሚስት ከሆኑ የአንዳቸው እድሜ 25 አመት የሞላ ከሆነ በቂ ነው። በባልና ሚስት አማካኝነት የሚደረግ ጉዲፈቻ ልጁ ከሁለት የአንዳቸው ልጅ ካልሆነ በስተቀር ሁሌም ቢሆን የሁለቱ ስምምነት መኖር ያስፈልጋል።
የጉዲፈቻ ተደራጊ ልጅ የእድሜ ጣሪያን በተመለከተ ከጉዲፈቻ ስርአት አላማና ግብ ማለትም አካለ መጠን ያልደረሱ ሰዎች ጥቅምና ደህንነትን መጠበቅ ከሚለው አንጻር እድሜው ከ18 አመት በታች የሆነና ከሞግዚት አስተዳደር ነጻ ያልወጣ ማንኛውም ሰው የጉዲፈቻ ልጅ መሆን ይችላል።
ሌላው ጉዲፈቻ በዋናነት የህጻኑን ጥቅም ከማስጠበቅ ረገድ የሚደረግ እንደመሆኑ ህጉ በአንቀጽ 187 ንኡስ 1 ስር የተፀነሰ ልጅ የጉዲፈቻ ልጅ መሆን እንደሚችል ተደንግጓል። ሆኖም በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት እናትዬው ልጁን ከወለደች በኋላ እስከ ስድስት ወር ባለው ጊዜ ድረስ ሃሳቧን ለመቀየርና ስምምነቱን ለማፍረስ ትችላለች።
አንድ ልጅ የጉዲፈቻ ልጅ ለመሆን ወላጆቹ በህይወት ያሉና የሚታወቁ ከሆነ የወላጆቹ ወይም አንዱ ከሌለ የሌላኛው ፈቃድ ያስፈልጋል። በተመሳሳይ ሁኔታ የመንግስት ወይም የግል ዕጓለማውታን አሳዳጊ ተቋሞች እያሳደጉ ያሉትን ማንኛውንም ልጅ ለጉዲፈቻ አድራጊዎች በስምምነት መስጠት እንደሚችሉ ህጉ በአንቀጽ 192 ያስቀምጣል።
የጉዲፈቻ አድራጊው በጉዲፈቻ የተቀበለውን ልጅ እንደ ልጁ በማሳደግ ፋንታ በባሪያነት ወይም በመሰል ሁኔታ ወይም ከግብረ ገብ ውጭ ባሉ ተግባሮች እንዲሰማራ በማድረግ መጠቀሚያ ያደረገው እንደሆነ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ የልጁን የወደፊት ሕይወት ክፉኛ በሚጎዳ አኳኋን የያዘው ከሆነ ልጁ በራሱ፣ ጉዳዩን ለመከታተል ስልጣን በተሰጠው የመንግስት አካል ወይም ጉዳዩ ያገባኛል በሚል ማንኛውም ሰው አቤቱታ አቅራቢነት የጉዲፈቻ ስምምነቱ በፍርድ ቤት ሊሰረዝ ይችላል።
ምንጭ:- ኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013