
ከግብርና ሚኒስቴር በተገኘው መረጃ መሠረት፤አብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል በተለይም ምዕራብ ኢትዮጵያ ሩዝ ለማምረት ምቹ ሥነ ምህዳር እንዳለው የዘርፉን ባለሙያዎች ዋቢ አድርጎ ያስቀምጣል። በጣና ዙሪያ ብቻ ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ ለሩዝ ተስማሚ የሆነ መሬት ያለ ቢሆንም እስካሁን በሩዝ የተሸፈነው መሬት ግን ከ40ሺ ሄክታር አይበልጥም። 70 በመቶ የሚሆነው የሀገራችን ሩዝ የሚመረተው በአማራ ክልል ነው። የሀገሪቱ የሩዝ ፍላጎት ከ500ሺ ሜትሪክ ቶን በላይ ሲሆን በሀገሪቱ ተመርቶ እየቀረበ ያለው ከ150 ሜትሪክ ቶን አይበልጥም።
በ2005 ዓ.ም የተቋቋመው የፎገራ ብሔራዊ የሩዝ ምርምርና ስልጠና ማዕከል የሩዝ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት አድርጎ የተለያዩ ምርምሮችን ይሰራል። አዳዲስና ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ሰባት የሩዝ ዝርያዎችንና የአሰራር ዘዴዎችን በምርምር በማውጣት የሩዝ እሴት ሰንሰለቶችን ለተጠቃሚው እያቀረበ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅትም በሀገሪቱ ሁለት ዓይነት ሩዝ አለ፤ ውሃ ውስጥ የሚበቅል እና ብዙ ውሃ ሳያስፈልገው የሚበቅል። ፎገራ አካባቢ በክረምት ከፍተኛ ጎርፍ ስለሚሸፈንና ምንም አማራጭ ሰብል ስላልነበረው አርሶአደሩ በእርዳታና ከብት በማርባት ነበር የሚተዳደረው። ነገር ግን በ1980ዎቹ ከሰሜን ኮሪያ በመጡ የልማት አጋሮች ሩዝ ተሞክሮ ምርታማ መሆኑ ታየ። ለረዥም ዘመናት እህል ሳይመረትበት ፆሙን ያድር የነበረውን መሬት አርሶ አደሮች በሩዝ በመሸፈን ከድህነት በመላቀቃቸው ‹‹ከውሃ በላኝ ወደ ውሃ አበላኝ›› የሚል ሀገራዊ ብሂል መሸጋገራቸው ይነገራል።
ዛሬ የሩዝ ምርታማነት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለበትን ደረጃ እና ቀጣይ ስለሚደረጉ ጥረቶች በዛሬው የምጣኔ ሀብት እንግዳ አምዳችን በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የብሔራዊ ሩዝ ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ ከሆኑት ዶክተር ሙሉጌታ አጥናፍ ጋር ያደረግነውን ቆይታ በዚህ መንገድ አቅርበናል።
አዲስ ዘመን፡- የሩዝ የምርምር ማዕከል አሁን ያለበትን ደረጃ እንዴት መግለፅ ይቻላል?
ዶክተር ሙሉጌታ፡- ይህ ማዕከል በ2005 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በስፋት የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ ነው። ሥራዎቹ ሩዝ ላይ ያተኮሩ ናቸው። በሰባት የምርምር ክፍሎች ሁሉም የምርምር የሥራ ክፍሎች የሩዝ ክብካቤ፣ የግብርና ምርምር ኤክስቴንሽን፣ የቴክኖሎጂ እና ዘር ብዜት ምርምር ተብለው የተከፋፈሉ ናቸው። የሩዝ በሽታና ተባይ፣ የሩዝ ዝርያ ማሻሻል፣ የሃብት አያያዝ፣ በቅድመ እና ድህረ ምርት ማሽነሪዎች ላይ በስፋት እየተሰራ ነው። ለተጠቃሚ ማድረስና ማስተዋወቅ ላይም እየተሰራ ነው።
ባለፉት የምርምር ስራዎች ስምንት የሩዝ ዝርያዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ተለቀዋል። እነዚህም ለቆላማው እና ደጋማው የሚሆኑ ናቸው። እነዚህ ዝርያዎችም በስፋት እየተሰራጩ ነው። ባለፈው ዓመት 160 ሄክታር በሰርቶ ማሳያ ተሸፍኖ ብዙ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል። በዚህ ዓመት ደግሞ 1ሺ200 ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሲሆን 4000 አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል።
አዲስ ዘመን፡- የፎገራ ምርምር ማዕከል ሥራ የተገደበው በኢትዮጵያ ብቻ ነው?
ዶክተር ሙሉጌታ፡- አሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተገደበ ነው። ወደፊት ተጠናክሮ ሲሄድ የምርምር እና የስልጠና ማዕከል በመሆኑ ለሌሎች ይተርፋል። ከሀገርም አልፎ ወደ ሌሎች ወጣ ብሎ ለመሄድ ያስችላል። ማዕከሉ በሰራው ሥራ አሁን ለውጥ እያመጣ ነው። በሄክታር ይመረት የነበረው 2 ነጥብ 8 ወደ አምስት ቶን አድጓል። የአካባቢው ማህበረሰብም ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ ነው። ብዙ አምርተው ለገበያ እያወጡ ነው። ከዚህ በፊት ማህበረሰቡ ተረጂ ነበር። በክረምት ወቅት ውሃ ስለሚተኛ ብዙ ይቸገሩ ነበር። አሁን ግን ክረምት እና በጋ እያመረቱ ብሎም መስኖ ላይ አተኩረው እየሰሩ ነው። እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ በሴፍትኔት ይረዱ የነበሩ አርሶ አደሮች አሁን ትርፍ አምራች ሆነዋል። በአሁኑ ወቅት ከሀገሪቱ 70 ከመቶ የሚሆነው ሩዝ እያመረቱ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አርሶ አደሮች ምርጥ ዘር መጠቀም ፍላጎታቸውስ ምን ይመስላል?
ዶክተር ሙሉጌታ፡- ፎገራ አካባቢ ለየት የሚያደርገው ወንድ አባወራ የልማት አጋሮችም በዚህ ላይ እየሰሩ ነው። በየዓመቱ ስድስት ሺህ አርሶ አደሮች ቀጥታ በቴክኖሎጂ እየተጠቀሙ ነው። አዲስ ምርት ቢሆንም የመጠቀም ፍላጎት ከፍተኛ ነው። አርሶ አደሮችም በኑሯቸው ላይ ለውጥ በመመልከታቸው ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው። አንዳንዴ ደግሞ የሚጠቅማቸው ብቻ ላይ ያተኩራሉ። ለምሳሌ በ2009 ዓ.ም አራት ዝርያዎች ወጥተው ነበር። ግን አርሶ አደሩ የወሰደው ሁለት ብቻ ነው። አርሶ አደሩ አዲስ የሩዝ ምርት ሲመለከት ደስተኛ ነው። ገለባውን ደግሞ ለእንስሳት እያሰበ ነው አዲስ ዘር የሚወስደው።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ለሩዝ ምርት ምን ያክል ምቹ ቦታ አለ?
ዶክተር ሙሉጌታ፡- የኢትዮጵያን የሩዝ የማምረት ፀጋ ስናይ የተለያዩ መረጃዎች ወጥተዋል። በመረጃዎቹ መሰረት በ2010 ዓ.ም የግብርና ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ 30 ሚሊዮን ሄክታር ማምረት ይቻላል። ከዚህ ውስጥ አምስት ሚሊዮን ሄክታር በጣም ተስማሚ የሚባለው ነው። ከዚህ በኋላ መረጃዎች እየተሻሻሉ ወጥተዋል። ይህ በጣም ተስማሚ የተባለው ብቻ ሲወጣ 14 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆን በጣም ተስማሚ መሬት አለ። በሀገር ውስጥ ይህ ሁሉ ፀጋ አለ። በዋናነት ሩዝ የቆላ ሰብል ሲሆን ከፍተኛ ውሃ ይፈልጋል። በተጨማሪም ውሃ እና ሙቀት ይፈልጋል። ከሁለት አንዱ ከጎደለ የተሟላ ሩዝ ምርት ላናገኝ እንችላለን።
እነዚህ ነገሮች በአንድነት አሟልተው የያዙ አካባቢዎች ደግሞ በጣም ሰፋፊ ቦታዎች አሉ። ቤንሻንጉል፣ ጋምቤላ፣ ምዕራብ ጎንደር፣ ምስራቅ አካባቢ ሱማሌ አካባቢ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጉራ ፈርዳ እነዚህ አካባቢዎች በጣም ተስማሚ ናቸው፤ በምርምር ተረጋግጧል። የተሻሻሉ ዝርያዎችም በዚህ አካባቢ ምርታማ የሆኑባቸው አካባቢዎች ናቸው። ከዚህ መረዳት የሚቻለው ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ሰፊ ፀጋ አለ።
ከዚህ ውስጥ እየለማ ያለው 60ሺ ሄክታር ነው። ይህ በጣም አሳዛኝ ነው። ከዚህ ውስጥ አብዛኛው የለማው መሬት ያለው ፎገራ አካባቢ ነው። ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ ከፍጆታዋ ስንት እየሸፈነች ነው ስንል በእጅጉ አነስተኛ ነው። ሩዝ ስናመርት ዋነኛ ዓላማችን ምንድን ነው ብለን ማሰብ አለብን። ኢትዮጵያ በ2000 ዓ.ም የሚሊኒየሙ ሰብል ተብሎ በኢትዮጵያ መንግስት ተሰይሟል። ይህ የተሰየመው የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ካለው አቅምና ከሚሰጠው ዋስትና የተነሳ ነው። ግን ይህን ስያሜ መስጠት ብቻ በቂ አይደለም። ለዚህ የሚመጥን አጠቃላይ እንቅስቃሴ፣ ተጨባጭ ሥራ እና ኢንቨስትመንት ይፈልጋል። አሁን ያለውን ስናይ የእኛ የሀገር ውስጥ ፍጆታ አልሸፈነም፤ ትልቅ ፍላጎት አለ። የምርት አቅርቦት ደግሞ በጣም አነስተኛ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሀገሪቷ የምታመርተው ምርት የፍጆታዋ ምን ያህል ይሸፍናል?
ዶክተር ሙሉጌታ፡- አሁን ባለው ሁኔታ በሀገራችን 20 ከመቶ ብቻ ነው የምንሸፍነው። 80 ከመቶ የሚሆነው የሩዝ ፍጆታ የምናስገባው ከውጭ ሀገር ነው። ለዚህም ኢትዮጵያ በአማካይ በዓመት 300 ሚሊዮን ዶላር እያወጣች ነው። ይህ በጣም አሳዛኝ ነው። ፀጋ ብቻ ሳይሆን መሆን የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች እያሉ ወደ ኋላ ቀርተናል። ይህ ወጪ ሀገሪቱ ካለባት የውጭ ምንዛሪ እጥረት አኳያ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› የሆነ ነገር ውስጥ ነው የገባነው። ሩዝ በዋናነት ለቀጣናው ሀገራት መላክ ሲገባን እኛ እየገዛን ነው። በቀጣናው ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሩዝ የመጠቀም ፍላጎት አለ። በጣም እየጨመረ ነው።
በእርግጥ ሩዝ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በቅርብ ጊዜ ነው። ግን ፍላጎቱ በየጊዜው እየጨመረ ነው። የከተሜነት መስፋፋት እና ወቅታዊ ሁኔታዎች እንድንጠቀም እያደረጉን ነው። አሁን ያለንበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነው። አሁን የኮሮና ቫይረስ እየተስፋፋ ባለበት ሁኔታ ብር ቢኖርም ሩዝ መግዛት ሊከብድ ይችላል። ኢትዮጵያ 95 ከመቶ ሩዝ ከህንድ ነው የምትገዛው። ህንድ ደግሞ ምርቶቿን እየያዘች ነው።
የምግብ ዘይት፣ ስንዴ እና ሩዝ በጣም ትልቅ ፍጆታችን መሆኑን በማመን መንግስት በሰፊ እየሰራበት ነው። ከዚህ ሁሉ የላቀው ደግሞ ግን በሩዝ ምርት ራሳችንን መቻል አለብን የሚል ብሔራዊ ፕሮፖዛል ተቀርፆ ለፕላን ኮሚሽን ቀርቧል። ምናልባትም በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ ራሳችንን መቻል አለብን። በእርግጥ ይህ በትጋት ከተሰራበት ማሳካት ይቻላል። ይህን የሚመጥን እንቅስቃሴ እና ኢንቨስትመንት ከተደረገ ማሳካት አይከብድም። ሩዝ ከሌሎች ሰብሎች መወዳደር ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ምርቶች የማይሆን ለሩዝ ብቻ የሚሆነው ምርታማ ያልሆነው መሬት ወደ ምርት ማስገባት ይቻላል። ይህ በሀገር ደረጃ ያለውን ሁኔታ ወደ ጥሩ አጋጣሚ የሚቀይር እንቅስቃሴ ማድረግ እንችላለን። በአጠቃላይ እቅዱን ለማሳካት በሁሉም ረገድ በቂ ሃብት አለ። ትልቁ ነገር አስፈላጊውን ትኩረት መስጠትና ብሔራዊ ንቅናቄ መፍጠር ነው። እነዚህ ነገሮች ተናበው ከሄዱ ሃሳባችንን ለማሳካት የሚያግደን የለም።
አዲስ ዘመን፡- በርካታ ምርምር ሥራዎች እንደሚከናወኑ ነግረውናል። እነዚህ ስራዎች የሚከናወኑት ከማን ጋር ነው ?
ዶክተር ሙሉጌታ፡- የምርምር ሥራዎች በባህሪያቸው በአንድ አካል ብቻ የሚከናወኑ አይደሉም። ትብብርና መተጋገዝ ይፈልጋል። ከአቅምና ከሃብት አኳያም ትብብር ይፈልጋሉ። ብሄራዊ ሩዝ ምርምር ማዕከል ላይም በምርምር ሥርዓት ካሉ የምርምር
ማዕከላት ጋር ይሰራል። የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ማዕከል፣ የክልል ምርምር ማዕከላት፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የምርምር ሥራዎችና ቴክኖሎጂዎች ከተገኙ በኋላ ደግሞ ወደ አርሶ አደሩ ከማድረስ አኳያ ብሎም በማስተዋወቅ ረገድ መንግሥታዊ ካልሆነ ተቋማትና ድርጅቶች ጋር እንሠራለን። ለአብነት የፓዌ፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ ቴፒ፣ ቦንጋ፣ ወረር፣ ጂንካ፣ ባኮ፣ አሶሳ፣ የግብርና ምርምር ማዕከላት ጋር በሰፊው እየተሰራ ነው። ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ደብረታቦር እና አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር እየተሰራ ነው።
በማስተዋወቅ ደግሞ የግብርና ማዕከል አለ። ሜዳ የሚባል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅትም ሰፊ ሁለንተናዊ እገዛ ያደርጋል። ጃይካ የተሰኘ የጃፓን ሀገር ግብረ ሰናይ ድርጅት አብረን እንሰራለን። ዘረመል ቴክኖሎጂ ላይ እገዛ የሚያደርጉ ሁለት ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም አብረውን ይሰራሉ። እስካሁን በምርምር 38 የሚሆኑ የሩዝ ዝርያዎች ተለቀዋል። እነዚህ በአንድም በሌላ ከእነዚህ ተቋማት ጋር በመስራት የተገኙ ናቸው።
በምርምር ማዕከሉ በሰባት ክፍሎች ሰባት ዋና ዋና ሥራዎች ይከናወናሉ። ምርምር ማዕከሉ ውስጥ በዋናነት ሩዝ ላይ ይሰራል። ዝርያው ይሻሻላል። ሩዝ ክብካቤ አለ። አትክልትና ፍራፍሬ ይሰራል። ፎገራ አካባቢ ሩዝ ከተነሳ በኋላ አትክልትና ፍራፍሬ ይመርታል። በዚህ ላይ ድጋፍ ይደረጋል። ሌላው ተፈጥሮ ሃብት አያያዝ ደግሞ በአፈር ለምነትና ጤንነት ላይ በስፋት ይሰራል። ተፋሰስ እና መስኖ፣ በግብርና ምሕንድስና በድረ እና ቅድመ ምርት ላይ፣ እፅዋት፣ የቴክኖሎጂ ብዜትና ምርምር ስራዎች በስፋት እየተሰሩ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፡- በምርምር ማዕከሉ እና በዘርፉ ላይ በቂ የሰው ኃይል አለ?
ዶክተር ሙሉጌታ፡- በዚህ ላይ አቅም እየጨመረ ሲሄድ ሰዎች እየተቀጠሩ ነው። ግን በትምህርት እድል የማሳደግ ሁኔታዎች አሉ። በሀገር ደረጃ ያለው ተጨባጭ ችግር በማዕከሉ ላይም መንፀባረቁ አይቀርም። ሩዝ ወደ ማህበረሰቡ እንዲገባ ያደረገውን በቀላሉ ባህላዊ ምግባችን ጋር እንዲጠቀም በማድረግ ነው። ፡ በተለይ ፎገራ አካባቢ ለመጠጥ፣ ዳቦ እና እንጀራ ጋር እየተጠቀሙ ነው። በምርምር ግን ከዚህ በዘለለ ሌላ ጥቅም እንደሚሰጥም ማሳየት ይገባል። ለዚህም ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው። በሥነ ምግብ ላይ በሰፊው መስራት እንደሚገባም አመላካች ነው።
ምርታማነትን የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎች ያስፈልጋሉ። ወደ ውጭ ከመላካችን በፊት ጥራት በሚለው ላይ መስራት ይገባል። እኛ የሀገራችን ምርት ሱፐር ማርኬት አይገኝም። ይህ የሆነው የጥራት ችግር ስላለበት ነው። ለዚህ ደግሞ ከቅድመ እስከ ድረ ምርት ያለውን ሁኔታ በሚገባ መስራት ይገባል። አርሶ አደሩ ዘንድ መሠራት ያለባቸው በርከት ያሉ ሥራዎችም አሉ። እነዚህ ነገሮች ትኩረት ካልተሰጣቸው የሚፈለገውን ዓላማ ማሳካት አስቸጋሪ ነው። ሩዝ አቀናባሪዎችም የሚጠቀሙበት ማሽን መታወቅ አለበት። ይህ ከሆነ ወደ ውጭ ከመላክ የሚያግድ ነገር የለም።
አዲስ ዘመን፡- የምርምር ማዕከሉ የአምስት ዓመቱ እቅድ ዋነኛ ተልዕኮ ምንድን ነው?
ዶክተር ሙሉጌታ፡- በዋናነት ከውጭ የሚገባው ምርት መተካት ነው። ለዚህ ደግሞ በርካታ አስቻይ ሁኔታዎች አሉ። ከበቆሎ ቀጥሎ በአንድ ሄክታር ከፍተኛ ምርት የሚገኘው ከሩዝ ነው። በሄክታር 30 ኩንታል ነው። በምርምር ያገኘነው በሄክታር 50 ኩንታል ሩዝ ማምረት እንደሚቻል ነው። በአንድ ሄክታር 20 ኩንታል ልዩነት አለ። ይህ በሀገር ደረጃ ኩታ ገጠም ሲጠናከር የሚመጣውን ለውጥ ማየት ይገባል። ይህ ካለን ሃብትና የመሬት ስፋት አኳያ ሲታይ ለውጡ ትልቅ ነው። በምርምር መሥራት ከተጀመረ ወዲህ አርሶ አደሮች በሄክታር በአማካይ 40 ኩንታል እያገኙ ነው። ይህ ቀላል ነገር አይደለም። አርሶ አደሩ ዘንድም ትልቅ ለውጥ እየታየ ነው። እንግዲህ በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ በሚገባ ከተሰራ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካት ይቻላል። አንዱ ጥሩ ነገር ደግሞ ሩዝ የሌሎችን ሰብሎች ቦታ የሚጋፋ አይደለም። ሌሎችን ቦታ አይሻማም። በሀገሪቱ በጣም ሰፊ እርጥበት አዘል መሬት አለ። በተጨማሪም አርሶ አደሮች በቀላሉ እየተላመዱት ነው። እነዚህ ዕድሎችን በመጠቀም የታሰበውን ማሳካት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- የአምስት ዓመቱን ግብ ለማሳካት በአዲሱ እቅድ የተለዩ ቦታዎች አሉ?
ዶክተር ሙሉጌታ፡- በዓመቱ ከውጭ ሀገር የሚገባውን ሩዝ ለመተካት በርካታ አማራጮች አሉ። ከእነዚህ እይታዎች ውስጥ ያለውን ፀጋ በአግባቡ መጠቀም ነው። ዝናብን መሰረት ያደረገ አመራረት አለ። በመስኖ የሚደገፍ አለ። በዝናብ ፎገራ አለ። በኢትዮጵያ ሩዝ ምርት ለማምረት የታሰበው 95 ከመቶ በዝናብ መሰረት ያደረገ ነው። በመስኖ በጣም ትንሽ ነው። ግን ከተሰራበት በዚህም አቅም አለ። በዚህ ውስጥ የአምስት ዓመታት እቅዳችን ማሳካት ይቻላል።
በዚህ ውስጥ የሀገር ውስጥ ፍላጎት በመጠን ብቻ ማሳካት ሳይሆን ጥራትም መታሰብ አለበት። ይህንንም ታሳቢ ያደረገ ሥራ መሰራት አለበት። ለዚህም የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ እና የፕሮሰሲንግ ማሽን ከሌለ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። ቴክኖሎጂ መጠቀም ግዴታ ነው። የጥራት መጓደል በራሱ ጫና ስለሚፈጥርም መታሰብ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ሩዝ በስፋት ብታመርት የገበያ መዳረሻዎቿ የትኞቹ አካባቢዎች ሊሆኑ ይችላሉ?
ዶክተር ሙሉጌታ፡- ሩዝ ዓለም አቀፋዊ ምግብ ነው። በዓለም 75 ከመቶ የሚሆነው ሕዝብ ሩዝ ይመገባል። የእኛ የምርምር ማዕከል ዝርያዎችም ይህን ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው። ከመጠን አንፃር ሲታይ ብዙ ችግር የለብንም። ግን ጥራት ላይ ብዙ መሠራት አለበት። አርሶ አደሮችም በዚህ ላይ ግንዛቤ ሊኖራቸው ብሎም ቴክኖሎጂ ሊያገኙ ይገባል።
አብዛኛው ሰሃራ አካባቢ ሀገራት ብዙ ቢሊዮን ዶላር ለሩዝ ግዥ ያወጣሉ። አብዛኞቹ ይህን ምርት የሚገዙት ከኤዥያ ሀገራት ነው። ኢትዮጵያ ይህንን ምርት በአግባቡ ብታመርት ሰፊ ገበያ ዕድል አላት። ሱዳንን ጨምሮ ከፍተኛ የሩዝ ምርት የሚጠቀሙት በመልክዓ ምድር ቅርብ የሆኑ በርካታ ሀገራት አሉ። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በርካታ ሀገራት ሩዝን በብዙ መንገድ ስለሚጠቀሙ ተፈላጊነቱ ከፍ ያለ ነው። ከዚህ አኳያ ተጠቃሚነቷ የጎላ ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ካላት የሩዝ ሃብት ፍላጎትና ምቹ ቦታ አኳያ ዓመታዊ የግለሰብ ፍጆታ ስንት ነው?
ዶክተር ሙሉጌታ፡- እኛ ሀገር በጣም ትንሽ ነው። ዓመታዊ አማካይ የሩዝ ፍጆታ ስድስት ኪሎ ግራም ነው። በአፍሪካ ከፍተኛው 26 ኪሎ ግራም ሲሆን ይህን በመጠንም ቀዳሚዋ ሀገር ማዳጋስካር ናት። ሆኖም የኢትዮጵያ ፍጆታ ሁኔታ እየጨመረ ነው። ይህን በማሰብም ነው የአምስት እና 10 ዓመታት እቅዶችን ያወጣነው። ለዚህ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ለእቅዶቹ መሳካት የፕላን ኮሚሽን ይሁንታ ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ለሩዝ ምቹ የሚባሉ አካባቢዎች እና የአየር ሁኔታ የትኞቹ ናቸው?
ዶክተር ሙሉጌታ፡- በሀሳብ ደረጃ ጋምቤላ አቦቦ፣ መተማ፣ ቋራ፣ አርማጭሆ፣ ፓዊ፣ ውሃ እና ሙቀቱ ተጣምረው ከፍተኛ ከሆነ ምርቱ ከፍ ያለ ነው። ከውሃ አኳያ ፎገራ ቀዳሚው ነው፤ ግን ሙቀቱ ያን ያክል አመቺ አይደለም። ለሩዝ ምቹ ሁኔታ አማካይ ሙቀት 23 ዲግሪ ሴልሺየስ ቢሆን ጥሩ ነው። በመሆኑም ነገሮችን በአንዴ መደምደም አይቻልም። በምርምር በፎገራ አካባቢ የቅዝቃዜ አቅምን የሚቋቋሙ ዝርያዎች እየተሻሻሉ ነው። አንዳንድ ዝርያዎች ደግሞ በሁሉም ረገድ ጥሩ ምርት የሚሰጡ አሉ። አሁን በርካታ ዝርያዎች እየተላመዱ እና ምርታማ እየሆኑ ነው። አርሶ አደሮችም እየተጠቀሙት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ በዘላቂነት ሩዝ ለማምረት ምን መልካም አጋጣሚዎች አሉ?
ዶክተር ሙሉጌታ፡- አሁን ያለው አሃዝ እንደሚያመለክተው ፍላጎት እየጨመረ ነው። በሌላ በኩል 80 ከመቶ ከውጭ ሀገር እየገባ ነው። ስለዚህ ሩዝ በስፋት ለማምረት ይገፋፋል። ሁለተኛ ሰፊ የሆነ ለሩዝ ምርት የሚሆነ ስፍራ አለ። የትውልዱ የአመጋጋብ ስርዓትም እየተቀየረ ሲሆን ሩዝን በየጊዜው የመፈለግ ዝንባሌ አለ። የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎችም ቀላል ግምት የሚሰጣቸው አይደለም። እኔ የሚያሰጋኝ መንግስት ምን ያክል ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል የሚለው ነው። ዓለም አቀፍ ምርት በመሆኑ ዓለም ላይ ያለውን ቴክኖሎጂ ከተፈለገው ቦታ ማግኘት ይቻላል። የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችንም በተፈለገው ፍጥነት ማግኘት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– የመንግስት እና የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ግንኙነት ለቀጣይ ሥራዎች ምን ምልክት ይሰጣል?
ዶክተር ሙሉጌታ፡– ሩዝ ላለፉት 10 ዓመታት ስትራቴጂ ተነድፎለት ነበር። የሚሊኒየም ሰብል ሲባል ለዚያ የሚመጥን እንቅስቃሴ ለማድረግ ብዙ ሥራ ተሰርቷል። የምርምር ማዕከሉ መገንባቱ ትልቅ ነገር ነው፤ ግን በቂ አይደለም። የሰው ኃይል ማደራጀት አስፈላጊ ነው። ይህ ተደርጓል፤ ግን በቂ አይደለም። ሆኖም በሀገር ደረጃ ሩዝ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የተሰጠው ትኩረት በጣም አነስተኛ ነው፤ በጣም ብዙ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል። ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ ሥራ ይፈልጋል።
ነገር ግን አንድ ማወቅ የሚገባን ነገር በተፈለገው ቦታ ለመድረስ ትልቅ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን ነው። በመስኖም እና ሆነ በክረምት እርሻ ሩዝ ለማምረት ትልቅ ተስፋ አለ። ከፍተኛ ውሃ ትነትና በረሃማነት የሚስተዋልበት ግብፅ በመስኖ ልማት ከአንድ ሄክታር 100 ኩንታል ማምረት ችለዋል። እኛ ገና 4ነጥብ5 ላይ ነን። ግን ደግሞ በመስኖ እና በዝናብ ከእነርሱ የተሻለ ማምረት እንችላለን። ለዚህ መንግስት ትልቅ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡኝ ማብራሪያ በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ሙሉጌታ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013