
ቦጋለ አበበ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የውል ስምምነት ሰነድ ተፈራረመ። ስምምነቱ በየደረጃው የሚገኙ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኖች፣ የተለያዩ ሊጎችንና የፌዴሬሽኑ ሰራተኞችን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚያስችል ሁለቱ አካላት የውል ስምምነቱን በፈረሙበት ወቅት ተገልጿል።
ፌዴሬሽኑ ከውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ጋር ሕክምናን በተመለከተ በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የስምምነት ሰነድ ባለፈው አርብ ከሰዓት ወሎ ሰፈር በሚገኘው ጽሕፈት ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ የተፈራረመ ሲሆን፣ በኘሮግራሙ መክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ተገኝተው ‹‹ይህ ስምምነት የስፖርቱን አቅም ለመገንባት የሚያስችል ዝግጅት በመሆኑ ደስተኛ ነኝ›› በማለት አስተያየታቸውን እንደሰጡ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።
እንደ አቶ ኢሳያስ ገለፃ፣ ስምምነቱ በቀላሉ የተገኘ ሳይሆን ሰፊ ስራ የተሰራበት ሲሆን የሕክምና ባለሙያ ቅጥር በማከናወን በፌዴሬሽኑ የሚዘጋጁ ወደ ሰባት የሚጠጉ ውድድሮች(በዋናው ቡድኖች በወንዶችና በሴቶች ፣ በከፍተኛ ሊግ ፣ በአንደኛ ሊግ፣ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ውድድሮች) እንዲሁም ከ100 በላይ ለሚሆኑ የፌዴሬሽኑ ሠራተኞች የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እድሉን ይፈጥራል። በተመሳሳይ የውዳሴ ዲያግኖስቲግ ማዕከል በብሔራዊ ቡድኖች ትጥቆችና በተለያዩ የስታዲየሞች ዝግጅትና የተለያዩ ስፖርታዊ ክንውኖች ላይ ማዕከሉን የሚያስተዋውቅበት እድል ማግኘት ይችላል። ከገንዘብ አኳያ ሲታይ ፌዴሬሽኑ የተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርግ እድል ይፈጥራል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ሳሙኤል የሺዋስ በበኩላቸው፣ እስከ አሁን ድረስ የፌዴሬሽኑ የሕክምና እንቅስቃሴ በሕክምና ኮሚቴ እየተመራ የቆየ መሆኑን በመግለፅ አሁን ፌዴሬሽኑ የሕክምና ዲፖርትመንት ለማቋቋም ጅማሮ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል። በቀጣይም ስምምነቱ ምን መሆን አለበት? ምንስ ላይ መሰራት ይኖርበታል በሚል ብሔራዊ ቡድኖችን መሠረት አድርጎ ሌሎችንም የውድድሮች አካላት ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል። ከስምምነቱ በፊት የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል በቅርቡ በተለያዩ ደረጃዎች ለሚገኙ በርካታ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኖችና እንዲሁም ለፌዴሬሽኑ ባለሙያዎች በነፃ የኮቪድ-19 ምርመራ በማድረግ አጋርነቱን እንዳሳየ ዶክተር ሳሙኤል አስታውሰዋል።
የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ባለቤት እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ኃይሉ ከስምምነቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት ‹‹እንዲህ አይነት የኢትዮጵያን ባንዲራ በያዘ ሥራ ላይ አጋር መሆን ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው ብለን እናምናለን። ውዳሴ ብቻውን የአገሪቱ የህክምና ክፍተት ለመሙላት አይችልም ። ጉልበት ያለው በጉልበቱ ፣ እውቀት ያለው በእውቀቱ ማገዝ አለበት›› በማለት ተናግረዋል።
በቅርቡ ዋሊያዎቹ ወደ ካሜሩን 2021 አፍሪካ ዋንጫ ከስምንት ዓመት በኋላ በማለፍ ያሳዩት ተስፋ መልካም መሆኑን በማስታወስም ‹‹እንኳን ደስ ያላችሁ፣ እንኳን ደስ ያለን›› በማለት የደስታ መልዕክታቸውን አስተላፈዋል። ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል በሕክምናው ዘርፍ ከአስራ ሁለት ዓመታት በፊት አንስቶ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝና ከእንደ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አይነት ተቋማት ጋር በአጋርነት መስራት አንዱ የማዕከሉ አላማ መሆኑን ተናግረዋል።
የሁለቱ አካላት ስምምነት መልካም ጅምርና ለሌሎችም መነሳሳትን እንደሚፈጥር የተናገሩት አቶ ዳዊት፣ ስምምነቱ በእግር ኳሱ ዙሪያ ያሉ ሰዎች ጤናቸው ሲታወክ ብቻ ሳይሆን ጤናማም ሆነው ክትትል የሚያደርጉበት፣ ከእዛም ባለፈ ምክክር እና ጥምረት የሚፈጠርበት ትልቅ ርምጃ መሆኑን አስረድተዋል። ‹‹በቀጣይም ማዕከሉ በሚከፍታቸው የጤና አገልግሎቶች ፌዴሬሽኑ ተጠቃሚነቱ የሚቀጥል ይሆናል። በዚህም ትልቅ ኩራት የተሰማኝ በመሆኑ በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ ነን›› በማለት አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 18/2013