ሰላማዊት ውቤ
ከተሞች በነዋሪዎቻቸው የሚፈለገው ነገር ሁሉ በቅርብና በቀላሉ የሚገኝባቸው መሆናቸው ግድ ነው ።ለቴክኖሎጂ ቅርብ የሆኑና ሥልጣኔ የነገሰባቸው እንደመሆናቸው የዚህኑ ያህል ለነዋሪዎቻቸው ምቹና የተደላደሉ መኖሪያዎች እንዲሆኑም ይፈለጋል።
ይሁንና መዲናችን አዲስ አበባን ጨምሮ የብዙ ከተማ ነዋሪዎች ለዚህ ፀጋ የታደሉ አይመስሉም። በሚኖሩባቸው ከተሞች ምቾት በማጣታቸው አያሌ የከተማ ነዋሪዎች በረሀ ዘልቀው ፣ ባህር ጠልቀውና ሀገር ጥለው ከመሰደድ ጀምሮ ብዙ እንግልት ሲደርስባቸው ይታያል። ከስደት የተረፉትም የከተማ ነዋሪዎች የዕለት ከዕለት ኑሯቸውን በምሬት ሲገፉ ማየት እየተለመደ ነው።አሁን አሁን በተለይ ምሬታቸው ተባብሷል።
ለመሆኑ የከተሞች ነዋሪዎች ለምን የተደላደለ ኑሮ መኖር አልቻሉም ? የዩኒቨርሲቲ መምህሩንና የኢኮኖሚ ባለሙያውን ዶ/ር ተክሌ አለሙንና አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በዚሁ ዙሪያ አነጋግረናቸው ነበር። ከዶ/ር ተክሌ ሙያዊ ሀሳብ በፊት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን አስተያየት አስቀድመን እንይ።
የካዛንችሱ ነዋሪ ወጣት ዮናስ ተጠምቀ ለጥያቂያችን እንደሰጠን ምላሽ የከተማ ነዋሪዎች የተደላደለ ኑሮ እንዳይኖሩ ከሚያደርገው አንዱና ዋናው ምክንያት ከገጠር ወደ ከተሞች የሚደረግ የማያቋርጥ የህዝብ ፍልሰት ነው።
እንደ ወጣቱ ሀሳብ ፍልሰቱ ከተሞችን ያጨናንቃል።ከመጨናነቅ አልፎ በነዋሪዎች መካከል ከፍተኛ ሽሚያ ይፈጥራል።በዚህም በከተሞች ያሉ ውሱን ሀብቶችና ዕድሎች ለነዋሪዎች ተደራሽ እንዳይሆኑ ያደርጋል።ይሄ ሁኔታ በተለይ ነባር ነዋሪዎች ተጠቃሚ በመሆን የተደላደለ ኑሮ እንዳይኖሩ ተፅዕኖ የሚያሳድርበት ሁኔታ ሲፈጥር በግልጽ ይስተዋላል።
ሌላዋ የፒያሳ አካባቢ ነዋሪ ወይዘሮ ፍሬሰላም ለገሰ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት ለከተማ ነዋሪዎች የተደላደለ ኑሮ እንቅፋት የመሆኑን የወጣት ዮናስን ሀሳብ ይጋራሉ። ወይዘሮዋ ሀሳቡን ሲያጠናክሩ በከተሞች የተደላደለና ምቹ ኑሮ ለመኖር ጥሩ ገቢ አስፈላጊ መሆኑን ያነሳሉ።
ይሄ ገቢ ደግሞ ዝም ብሎ ሳይሆን በከተሞች በሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች የሚገኝ እንደሆነም ይጠቅሳሉ።ነገር ግን በአብዛኛው ፍልሰት ከፈጠረው መጨናነቅ የተነሳ እነዚህ የሥራ ዕድሎች ተደራሽ መሆን የሚችሉበት ሁኔታ እንደሌለ ይናገራሉ።ቢኖርም ጠባብ ነው ባይ ናቸው።ደግሞም በብልሹ አሠራር የተተበተበና አድሏዊ እንደሆነም ያሰምሩበታል።
ለአብነት የአካባቢያቸውንና የአዲስ አበባ ከተማን ነዋሪ ወጣቶች ታሪክ ያነሳሉ። እንደሚሉት ከምርጫ ጋር ተያይዞ በሹመት ከሚቀመጠው ውጪ ከቀበሌ ጀምሮ በወረዳና በክፍለ ከተሞች በርካታ የሥራ ዕድሎች አሉ። የከተማዋ ወጣቶች ደግሞ ለዚህ የሚመጥን የትምህርት ዝግጅት አላቸው። ሆኖም እነዚህ ወጣቶች እያሉ ዕድሉ በመሳሳብና በዘመድ አዝማድ ፣ቀደም ብሎም በብሄርተኝነት ከሌላ ክልል ለመጡት የሚሰጥበትና እነዚህ ወጣቶች አማራጭ ሲያጡ ሀገር ጥለው የሚሰደዱበት አጋጣሚ አለ።
መሰደድ ብቻ ሳይሆን ተስፋ በመቁረጥ አደገኛ ቦዘኔ የሚል ቅጽል እስኪወጣላቸው ደህይተውና ሥራ ፈትተው የሚቀመጡበት ይከሰታል።የተሰደዱትም ነዋሪዎች ወይ ያልፍላቸዋል ወይ በዛው በተሰደዱበት ቀልጠውም ሆነ ሞተው ይቀራሉ።አክለውም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ።
በመሆኑም ከዳያስፖራው ውጪ ሁሉም የሀገሪቱ ነዋሪዎች ህጋዊ በሆነ አካሄድ የነዚህ ቤቶች ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት በያሉበት አካባቢ መሆን እንደሚገባም ይናገራሉ።በሕግ ይሄ የተቀመጠ እንደሚመስላቸውም ይጠቅሳሉ።
ነገር ግን በግልፅ ከሚታየውና ከሚሰማው አንፃር አዲስ አበባ ከተማ ላይ በተተገበረው በ10/90፣ በ20/80 በተለይም በ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት የከተማዋ ነዋሪዎች በዚህ አግባብ ተጠቃሚ ሆነዋል ማለት እንደማይቻልም ይገልፃሉ።የቤት ፕሮጀክቶቹ በራሳቸው ከሂደታቸው ጀምሮ ለእንግልት የሚዳርጉና የተደላደለና ምቹ ኑሮ ለመኖር ሳንካ የሆኑ እንደሆኑም ይጠቁማሉ።
በአጠቃላይ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነዋሪው የተደላደለና ምቹ ኑሮ መኖር ላለመቻሉ በየስርዓቱ የሚነሱና መንበረ ስለልጣኑን የሚቆናጠጡ ፖለቲከኞች አዲስ አበባ ከተማ አንድም ጊዜ ችግሯን በሚገነዘቡና መፍትሄ በሚሰጡ በራሷ ተወላጆች እንድትተዳደር ዕድል ለመስጠት አለመቻላቸው መሆኑንም በማስመር ሀሳባቸውን ያሳርጋሉ።
ደግሞ የዩኒቨርሲቲ መምህሩና የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶ/ር ተክሌ ዓለሙ በዚሁ ዙሪያ ወደ አካፈሉን ሀሳብ እንሻገር።ባለሙያው እንደሚሉት እንደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የከተማ ነዋሪዎች ምቹና የተደላደለ ኑሮ መኖር እንዳይችሉ የሚያደርጉ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትንና ከአቅም በላይ መውለድን ጨምሮ ብዙ ምክንያቶች አሉ።ከአቅም በላይ መውለድ የከተማው ብቻ ሳይሆን የገጠሩም ችግር ነው።
የውሃና መብራት መቆራረጥ፣መንገድ ብልሽት መድረስና የመንገድ ዝርጋታ አለመኖር እንዲሁም ሌሎች የመሠረተ ልማቶች አለመሟላት በራሱ ምቹና የተደላደለ ኑሮ ለመኖር መሰናክል ነው።አለ በነዚህ ምክንያቶች የተነሳ የከተማው ብቻ ሳይሆን የገጠሩም ነዋሪ ምቹና የተደላደለ ኑሮ የማይኖርበት ሁኔታ እንዳለም ይጠቁማሉ።
እንዳከሉት የሕዝብ ብዛት የሚፈጥረው ጫና ቀላል አይደለም።ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ገጠሬው ያመረተውን ምርት ከተማ ወስዶ መሸጥ ከከተማም ልብስና የሚያስፈልገውን መግዛት አለበት።
ሆኖም በትራንስፖርትም ሆነ በሰላም እጦት ይሄ እየሆነ አይደለም።የተመረተው ምርት ገበያ መድረስ ባለመቻሉ ዋጋው የጨመረበት።ይታያል። የዋጋ ጭማሪው ደግሞ የኑሮ ውድነት አስከትሏል። በሀገራችን አብዛኞቹ አካባቢዎች በተለይ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነበት ሁኔታ የለም።እንደነገሩን ነዋሪው ጥሮ ግሮ ያፈራው ንብረት በጠራራ ፀሐይ የሚዘረፍበት፣ቤት፣ ንብረትና ወደ ውጪ ተልኮ ዶላር ማስገኘት የሚችል ሰሊጥና ሌላ የደረሰ ሰብል በቃጠሎ የሚወድምበት ሁኔታ ይታያል።ይባስ ተብሎ የእርስ በእርስ ስምምነት በማጣት ውዱ የሰው ሕይወትም ይቀጠፋል።ሁለተኛው የከተማ ነዋሪ ምቹና የተደላደለ ኑሮ መኖር ላለመቻሉ ምክንያት የሆነው ጉዳይ ደግሞ በሰላም እጦትም ሆነ በሌላ ዜጎች ሥራ መሥራት አለመቻላቸው ነው።
‹‹በእርግጥ ሰላም ከሌለ ምንም ሥራ መሥራት አይቻልም›› የሚሉት ባለሙያው አስረግጠው ሁሉም ነገር የስራ ውጤት እንደሆነም ይገልፃሉ።እንዳከሉት ወደ ውጪ ካላክን ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ የምናስገባው ነገር አይኖርም። ሆኖም ከሰራን ፣ካመረትን ቡናም ሆነ ወርቅና ሰሊጥ ወደ ውጪ እንልካለን።
ይሄኔም ነዳጅ መግዛት፣መድሃኒት ማስገባት፣ ምቹና የተደላደለ ኑሮ መኖር እንችላለን። ሕዝብ በበዛባቸው ከተሞች ምቹና የተደላደለ ኑሮ ለመኖር ደግሞ ዋናው ሥራ መሥራት መቻል ነው። ሆኖም በሰላም እጦት ብቻ ሳይሆን ሰላም ባለበት አካባቢ ከመስራትና ከመለወጥ ይልቅ ሥራ የሚያማርጡና ማውራት የሚቀናቸው ዜጎች አሉ።
ሌሎቹ የኢኮኖሚ ባለሙያው የከተማ ነዋሪዎች ምቹና የተደላደለ ኑሮ እንዳይኖሩ እንቅፋት ናቸው ብለው የሚያነሷቸው ለራስ የሚመጥን አኗኗር አለማወቅ፣ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖር፣ሙስና፣ብልሹ አሠራር፣አውቃለሁ ባይነት ናቸው።
በተጨማሪም የራስን ኑሮ አለመኖር ወይም በሰው ሕይወት ጣልቃ መግባትና ጥቅሙን መንጠቅ፣መጠላለፍ፣መጠቋቆር፣ስርቆት፣የተዛባ አመለካከት መያዝ፣ባህላዊ ተፅዕኖ፣ህገወጥነት ይጠቀሳሉ።
ዶ/ር ተክሌ እንደሚሉት ይሄን ሁኔታ ለመለወጥ መንግሥት ሕዝቡ እንዲሠራ ዕድል መስጠት አለበት።የሚሰጠው ዕድል ደግሞ በአቅም መሥራት የሚያስችል መሆን አለበት።ሕዝቡ እንዲሰራ ዕድል የሚሰጠው አካል ነው ያጣው።ሥራው ማስተባበር እንደመሆኑ እኔ አውቅልሀለሁ ማለት የለበትም።
እንዲሰራ ብቻ ሳይሆን የፈለገውን እንዲሰራም መተው አለበት።ፖሊሲ አያስፈልገውም።ፖሊሲው ሕዝቡ የሚፈልገውን ሳይሆን እራሱ ያቀደውን ይሄን፣ ቀይር ይሄን እንዲህ አድርግ በማለት የሚበጠብጠው በመሆኑ አስፈላጊ አይደለም።አንዱ ከመንግሥት የሚጠበቀው ይሄው ነው።
ሌላው ከመንግሥት የሚጠበቀው ሕግ በማስከበርም ሆነ በሌላ እርምጃ ሰላም ማስፈን፣ንግድ እንዳይካሄድ የሚያደርጉ ዘረፋዎችን፣ የማስቆም፣የሚዘጉ መንገዶችን መክፈት ፣ሙስናን መቀነስ፣ ብልሹ አሰራሮችን ማስወገድ ፣ሰርቶ ማሳየት ነው።ለምሳሌ፦ ዛሬ ያሉት አብዛኞቹ ባለሥልጣናት ዱሮ አባቶቻችን በሰሩት ቤት ነው የሚኖሩት የራሳቸውን ቤት እንኳን መሥራት አልቻሉም። ሆኖም ሕዝቡ የተደላደለና ምቹ ኑሮ ለመኖር የየራሱን ቤት እንዲሰራ አርአያ መሆን አለበት።
ሕዝቡ በበኩሉ መንግሥት ቤት ሰርቶ እንዲሰጠውና የተደላደለ ኑሮ መኖር እንዲያስችለው መጠበቅ የለበትም።የመንግሥት ሀብትና ንብረት የራሱ በጠቅላላው የሕዝብ መሆኑን መገንዘብና እጁን ከስርቆት መሰብሰብ አለበት።በአቅሙና እንደ ራሱ መኖር መልመድ ይገባዋል።እንደሌላው ለመኖር ሲል መስረቅ በሞራልም በህግም የሚደገፍ መሆኑን መረዳት አለበት።ዕድገት ደረጃ በደረጃ ሰርቶ የሚገኝ እንጂ በአንድ ጊዜ የሚመጣ እንዳልሆነ ተረድቶ በዚህ መንገድ መጓዝ ይገባዋል።
መንግሥት ወይም ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል የተቋቋሙ ተቋማት የእንዲህ ዓይነቱን ሀብት ምንጭ በተገቢው መንገድ መፈተሽና ማጥራት አለባቸው። እኔ ብቻ ልብላ የሚለውንም እሳቤ አውልቆ በመጣል ለሌላው በቤተሰብ ደረጃ ለእህትና ለወንድሙ ከማሰብ ጀምሮ ለሌሎችም መኖር አለበት።በሥራ ገበታውም ሆነ በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴው ያለውን ሂደት ሕግ ማክበርና በዚህ መሰረት ሕይወቱን መምራት መቻል አለበት።ልጆቹን ገና ከመሰረቱ በስነ ምግባር ቀርጾ ማሳደግና ማስተማርም ከህብረተሰቡ ይጠበቃል።
አሁን ላይ ያለንበት ተጨባጭ ሁኔታ እንደ ሀገር ሲቃኝ ብዙዎቻችንን ስሜታዊም ሆነናል። በግለሰብ ደረጃም እኔ ብቻ ነኝ የማውቀው የሚል ግለሰብ ተበራክቷል። ዶ/ርም ሆነ አራተኛ ክፍል የደረሰ እኔ አዋቂ ነኝ እኔ ያልኩት ይሁን ሲል ይታያል።በዕድሜም ሆነ በትምህርትና በሌሎች ደረጃ ሕብረተሰቡ ውስጥ ያለውን የመከባበርን ማህበራዊ መስተጋብርን ባህል ይሸረሽራል ።ለአለመግባባትና ለፀብ መነሻም ይሆናል።
በተጨማሪም ተምሪያለሁ የሚልና አንድ አርፍተ ነገር ተናግሮ ቀጥሎ የሚናገረው መጀመሪያ የተናገረውን የሚቃረን ብዙ ግለሰብ አለ። ይሄ በሕዝቦች መካከል ላለው አለመግባባት ምክንያት ነው። ከሰው ጋር መኖርም አያስችልም። እንዲህ ዓይነቱ ግለሰብ በእያንዳንዱ ሰው አእምሮ ሰው ሆኖ ከሰው ጋር መኖር የማይችል ከሆነ ምኑን ነው ተማረ የሚያስብለው የሚል ጥያቄም ያጭራል።
እንደባለሙያው እሳቸው ከነዚህ ዓይነት ግለሰቦች ይልቅ ከሕይወት የተማሩ ሰዎች የበለጠ ምሁራን ናቸው ብለው ያምናሉ።ነዋሪዎች በከተሞች ምቹና የተደላደለ ኑሮ መኖር እንዲችሉ እነዚህ ሁሉ ከአመለካከት፣ከአስተዳደግ ፣ከባህልም ሆነ ከልምድ ጋር የተያያዙ ችግሮች መቀረፍ አለባቸው። ለመቅረፍ ደግሞ ራሱ የችግሩ ባለቤት አስተዋጾ ማድረግ አለበት።ለመለወጥ ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2013