ጌትነት ምህረቴ
ዛሬ በዓለማችን መረጃዎች እንደ ብርሃን ፍጥነት ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ እየተሰራጩ ይገኛሉ።ዕድሜ ለቴክኖሎጂ ምዕራብ ዳርቻ የዓለማችን ክፍል የተፈጸመ ጉዳይ በሰከንድ ምስራቅ ዳርቻ የዓለም ጫፍ የሚደርስበት ሁኔታ ተፈጥሯል።የመገናኛ ብዙኃን መረጃዎችን ለብዙኃኑ በማድረስ ባህላዊ፣ታሪካዊና አገራዊ አንድነትን ከማዳበርና ከማጠናከር አኳያ እንዲሁም ሁለንተናዊ ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ከማፋጠን ረገድ አወንታዊ ሚና ቢኖራቸውም ማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃዎች ለአገራትም ራስ ምታት እየሆኑ ነው።
በተለይ ብሄርን ከብሄር ጋር የሚያጋጩ፤የአገር አንድነትን የሚፈታተኑና የዜጎች በየትኛውም ቦታና አካባቢ ተቀሳቅሶ የመስራት መብቶች የሚገድቡ የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ።የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ለማህበራዊ ትስስር፣ ለፖለቲካ መረጋጋት፣ለአገራዊ አንድነት፣ ለሰብዓዊ ክብር፣ ለብዝሃነትና ለእኩልነት ጠንቅ ናቸው።
የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት የህዝቦችን የአብሮነት ቋጠሮ ይበጥሳሉ።በሰዎች ዘንድ ውዥንብር ይፈጥራል።ህዝብ ተረጋግቶ የዕለት ተግባሩን እንዳይከውን ያደርጋሉ።አገራዊ አንድነትን ይፈታተናሉ።የሰዎችን የመኖር ህልውና ይፈታተናሉ።የህዝቦች ራሳቸውንና አካባቢያቸውን ለልማት የሚያደርጉትን ሁለንተናዊ ጥረት እና ሥራ ዋጋ የሚያሳጡና የሚያደናቅፉ ናቸው።
ሀሰተኛ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ሰዎች ባልሰሩት ተግባር የሚያጠለሽ፣ በጥላቻ፣ በአድሏዊነት፣በተዛባ፣በዘረኝነት እና በመሳሰሉት እኩይ ምግባሮች የህዝብን ህልውናና አብሮ መኖር ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው።በእነዚህ ክፉ ስራዎች የተሰማራ ሰው ጠንክረው ለአገር ልማትና ለህዝቦች አንድነት የሚሰሩትን ሰዎች ስም ያጠፋል፣ ያጠለሻል።ህዝቦችን እርስ በእርሳቸው ለማጋጨት ይዋሻል፣ ያጭበረብራል።በሚሰራው እኩይ ድርጊትም በአገራችን ረጅም ጊዜ ያስቆጠረውን የህዝብን አብሮ የመኖር መልካም እሴት ይሸረሽራል።
በአገራችን ኢትዮጵያም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት በተለያዩ ማህበረሰቦች ላይ ጥቃት የሚያነሳሱ፣ ግድያንና መፈናቀልን የሚቀሰቅሱ መልዕክቶች በተለያዩ ጊዜያት ይሰራጫሉ።ይህን ተከትሎ በርካታ የአገራችን ዜጎች እየተፈናቀሉ ነው፤ በርካታ ንብረት ወድሟል፤ ህይወትም ጠፍቷል።ሰዎች በስጋት እንዲኖሩ አድርጓል።መንግስትም በልማት ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ የህዝብን ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ብዙ ጊዜ፣ሀብትና ጉልበት እንዲያጠፋ ይገደዳል።
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያችን እየተስፋፋ የመጣውን የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ለመከላከልም የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ዓመት የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ አዋጅን አጽድቋል።ይህ አዋጅ በዜጎች እኩልነት፣ አንድነት፣ ሰላምና አብሮ መኖር ላይ አደጋ እያመጣ ያለውን የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ለመከላከል የሚያስችል አቅም ያለው ነው ተብሏል።
“የጥላቻ ንግግር” ማለት በአንድ ሰው ወይም የተወሰነ ቡድን ላይ ያነጣጠረ፣ ብሄርን፡ ብሄረሰብንና ህዝብን፣ ሀይማኖትን፣ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ ጥላቻን፣ መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያበረታታ ንግግር መሆኑን የጥላቻ ንግግርን እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1185/2012 ያስቀምጣል።
እንዲሁም “ሀሰተኛ መረጃ” ውሸት የሆነና የመረጃውን ውሸት መሆኑን በሚያውቅ፣ ወይም መረጃውን የሚያሰራጨው ሰው ካለበት አጠቃላይ ሁኔታ አንጻር የመረጃውን ሀሰተኝነት ሊያውቅ ይገባ ነበር የሚያስብል በቂ ምክንያት እያለ የሚሰራጭ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ከፍ ያለ ንግግር መሆኑንም በአዋጅ ውስጥ ተጠቅሷል።
በአዋጁ መሰረት እነዚህን የጥላቻ ንግግሮችና የሀሰተኛ መረጃዎች ሆን ብሎ በሬዲዮ ፣ በቴሌቪዥን ፣በማህበራዊ ሚዲያ (ፌስ ቡክ፣ቲውተር፣ዩቲዩብ) እና የህትመት ሚዲያ ማሰራጨት ተጠያቂ ያደርጋል።
የአዋጁ ዋነኛ ዓላማዎችም ሰዎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ሲጠቀሙ ግጭት ወይም ሁከትን የሚቀሰቅስ ወይም ብሄርን፤ ሀይማኖትን፤ ዘርን፤ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ በግለሰብ ወይም በተለየ ቡድን ላይ ጥላቻ ወይም መድልዎ የሚያስፋፋ ንግግር ከማድረግ እንዲቆጠቡ ማድረግ ነው።
ሌላው መቻቻልን፣ የዜጎች ውይይትና ምክክርን፣ መከባበርና መግባባትን ማበረታታትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ማጎልበት፤የጥላቻ ንግግርን፣ የሀሰተኛ መረጃና ተያያዥነት ያላቸውን ሌሎች የውሸትና አሳሳች መረጃዎችን ስርጭትና መበራከትን ለመቆጣጠርና መግታት ያለመ ነው።
በዚህ አዋጅ የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ የተከለከሉ ተግባራት መሆናቸውን ይገልጻል።ስለዚህ የጥላቻ ንግግርንና የሀሰተኛ መረጃን በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚዲያ በጽሁፍ፣በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪዲዮ ማሰራጨት የተከለከለ መሆኑን በግልጽ አስፍሯል።እናም ህጋዊ ክልከላ ተላልፎ በተገኘ ሰው ላይ የወንጀል ተጠያቂነትን ያስከትላል።
ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ አንቀፅ 4 መሰረት የተከለከለውን የጥላቻ ንግግር ያደረገ እንደሆነ እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከብር መቶ ሺህ ያልበለጠ መቀጮ ይቀጣል፤በጥላቻ ንግግሩ ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ እንደሆነ ቅጣቱ እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ይሆናል።ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ አንቀፅ 5 መሰረት ክልከላ የተደረገበትን ተግባር የፈጸመ እንደሆነ እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ በቀላል እስራት ወይም ከብር 50ሺህ ባልበለጠ መቀጮ ይቀጣል።
እንዲሁም የጥላቻ ንግግር ወይም የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ወንጀሉ የተፈጸመው ከአምስት ሺ በላይ ተከታይ ባለው የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ከሆነ ወይም በብሮድካስት አገልግሎት ወይም በየጊዜው በሚወጣ የህትመት ውጤት ከሆነ ቅጣቱ እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከብር 100 ሺህ ያልበለጠ መቀጮ የሚጠብቀው ይሆናል።ሀሰተኛ መረጃ በመሰራጨቱ ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ ወይም የተሞከረ ከሆነ፣ ሁከት ወይም ግጭት የተከሰተ እንደሆነ ቅጣቱ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይሆናል።
በጥላቻ ንግግር ውይም በሀሰተኛ መረጃ ወንጀል መፈጸም ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት ያልተፈጸመ ወይም ያልተሞከረ ከሆነ፣ ሁከት ወይም ግጭት ያልተከሰተ እንደሆነ እና ጥፋተኛውን ለማረም የተሻለ ነው ብሎ ሲያምን ፍርድ ቤቱ በእስራት ምትክ የግዴታ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራን በአማራጭ ቅጣትነት ሊወስን ይችላል። በዚህ አዋጅ የተከለከሉት ተግባራት የተፈጸሙት በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ከሆነ በወንጀል ሕጉ ጠቅላላ ክፍል የተካተቱት በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት የሚደረጉ ወንጀሎችን የተመለከቱ ድንጋጌዎች( አንቀጽ 42-47) ተግባራዊ ይሆናሉ።
በተለይ በምርጫ ወቅትና እዚህም እዚያ ግጭቶች መከሰታቸውን ተከትሎ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ሊጨምር ይችላል።በዚህ ተግባር የምትሳተፉ ሰዎች ህጋዊ ተጠያቂነት የሚያስከትል መሆኑን ከወዲሁ መገንዘብ ይኖርባቸዋል።ስለዚህ የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ የመረጃ ስርጭት አዋጅ ከተቀመጡ ህጋዊ ተጠያቂነቶች ራስን ለመጠበቅ ከጥላቻ ንግግርና ከሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ተግባር ተቆጠቡ እንላለን።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2013