ጌትነት ምህረቴ
ዛሬ ዘመን ላይ ዝናው የገነነው ማህበራዊ ሚዲያ የተፈጠረው ሰዎች ለበጎ ተግባር ይጠቀሙበታል ተብሎ ነው ፡፡ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቁጥር መጨመርና የቴክኖሎጂውን ማደግ ተከትሎ እውነት ነው ብዙዎች በማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ምርቶቻቸውን አስተዋውቀዋል፣መልካምና አዲስ ሀሳባቸውን ለብዙዎች አካፍለዋል፡፡የፖለቲካ አቋማቸውን ገልጸውበታል፣ምክንያታዊ ትችት አካፍለውበታል፡፡እንዲሁም አዝናኝና አስተማሪ ጹሁፎችን አስነብበውናል።እንዲሁም ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ጥሩ ጓደኛ ያፈሩም በርካታ ናቸው፡፡
በአንጻሩ ማህበራዊ ሚዲያ የጥቅሙን ያህል ጉዳቱም ከፍተኛ ነው።በተለይ ሀላፊትነት የማይሰማቸውና ጥቅማቸውን ብቻ ታሳቢ አድርገው የሚጠቀሙ ሰዎች የሚያሰራቸው የሀሰት መረጃዎች ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ምክንያቱም ዛሬ ላይ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም መሬት ተሰነጠቀ፣ ሰማይ ዝቅ አለ፣ ዓለም ታመሰችና ጠፋች እያሉ ሟርት እየለፈፉ የሚውሉትም የትየሌሌ ናቸው።እንዲሁም የግለሰቦችንም መልካም ዝና ለማጉደፍ የሚጠቀሙበትም ብዙዎች ናቸው፡፡ከእነሱ ጋር የተለየ ሀሳብ ያላቸውን ሰዎች በምክንያት ከማስረዳት ይልቅ ስሜት የተቀላቀለባቸው ዘለፋዎችና ስድቦችን ማሽጎድጎድም ማህበራዊ ሚዲያ የክፉዎች ሰናይ ተግባር ማንጸባረቂያ ሆኖ ይታያል፡፡
ለአብነት ያህል በማህበራዊ ሚዲያ የተቀጣጠለው የአረቡ አገራት አመጽ ብዙዎችን ቀጥፎል፡፡እንደ የመን፣ሶሪያና ሊቢያ ያሉ አገራትን አፍርሷል፤ ዜጎቹን አገር አልባ አድርጓል፣ብዙዎችን ለአስከፊ ስደትና እንግልት ዳርጓል፡፡ይህ በማህበራዊ ሚዲያ የተቀጣጠለው የአረቡ ዓለም አመጽ ብዙ አገራት ላይ የኢኮኖሚ ኪሳራም አስከትሏል፡፡
አሁን አሁን ከእነዚህ አገራት ያልተማሩ የእኛ አገር እንደ አሸን እየፈሉ ያሉ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች ነን ባዮች ( ድንቄም ማህበራዊ አንቂ) ማህበራዊ ሚዲያን( ፌስ ቡክ፣ዩቲዩብና ቲውተር) ተጠቅመው ጥላቻን አስፋፍተዋል፣ወጣቱ ጭካኔን የተላበሰ ተግባር እንዲፈጸም ቀስቅሰዋል፡፡ጽንፍ ወጣ ዘረኝነትን ሰብከዋል።የሀሰት ዜና በማሰራጭትም ህዝቡን ውዥንብር ውስጥ እንዲገባ አድርገዋል።በዚህም በማህበራዊ ሚዲያዎች ጥላቻንና ሀሰትን በመንዛት የክፉዎች ሰናይ ተግባር መሆኑን አሳይተውናል፡፡
እነዚህ ማህበራዊ ሚዲያ “ቅንቅኖች“ ዛሬ ኢትዮጵያ ምጥ ላይ በሆነችበትም ጊዜ ከዚህ ተግባራቸው ሊቆጠቦ ቀርቶ እንዲያውም “በዕንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ “እንዲሉ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ፣ የአገርን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ፣ የግለሰቦችን መልካም ዝና የሚያጎድፍ የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ሰናይ ተግባራቸው ይህ መሆኑን እያረጋገጡልን ነው።
ኢትዮጵያ በመጪው ግንቦት አገራዊ ምርጫውንና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማካሄድ ዝግጅት ላይና በዚህ ምክንያትም እዚህም እዚያ የዲፕሎማሲ ጫና በበረታባትም ወቅት አገራዊ አንድነት እንዲጠናከር ህዝቡን ከማስተማር፣ ከማንቃት ይልቅ አገር አንድትበተንና ህዝብ ከህዝብ እንዲጋጭ በማህበራዊ ሚዲያ አበክረው የጥላቻ መርዛቸውን ይረጫሉ፡፡የሀሰት መረጃዎችን ያሰራጫሉ፡፡
በዚህ ወቅት አንድነታችንን ማጠናከሪያ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ምርጫ ማብሰሪያ ማድረግ ሲገባን ሀላፊነት የማይሰማቸው ክፉዎች ሰናይ ተግባር ምርጫው ለማስመሰል የሚካሄድ ነው፤ ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ነች፣ክልሎች ተጋጩ፣ህዝቡ እርስ በዕርስ እየተላለቀ፤ እከሌ የተባለ ብሄር የከሌን ብሄር የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጸመ፣እከሌ ተመረዘ፣እከሌ ተገደለ እያሉ የሀሰት መረጃ እያሰራጩ ይገኛሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው እንደ አሸን እየፈሉ ያሉት እነዚህ የእናት ጡት ነካሾችና ባንዳዎች አገር በውስጥና በውጭ ችግሮች ተወጥራ እያለች ችግሮች እንዲፈቱ በጎ ሚና ከመጫወት ይልቅ ችግሩ እንዲባባስ ዱላ ያቀብላሉ።በእነሱ ዘንድ ስነ ምግባር፣ህሊናና ለህዝብ መቆርቆርና ለአገር መጨነቅ ብሎ ነገር የለም፡፡ከዚህ ይልቅ የሚያሳስባቸው በፌስ ቡክ የሚያገኙት ዝናና በዩቲዩብ የሚከፍላቸው ገንዘብ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮ እንዳ አልተዋለደ፣ ለዘመናት አብሮ እንዳልኖረ፤ ክፉውንም ደጉንም አብሮ እንዳላሳለፈና የውጭ ወራሪ ሀይልን አብሮ ድል እንዳላደረገ እነዚህ ውስን እኩያን በሀሰት መረጃ አልያም ሀቁን በመጠምዘዝ ሊለያዩት፣ ልዩነቱን አጉልተው ሊያሳዩትና በብሄር ከፋፍለው ሊያጋድሉትና ለውጭ ጠላት አጋልጠው ሊሰጡት ሌት ተቀን ሙሾ ሲያወርዱ፣ሲያላዝኑና እየየ ሲሉ ይታያሉ።እነዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ቅንቅኖች በሚፈጸሙት እኩይ ተግባር በአገራችን ታይተው የማይታወቁ ዘግናኝ ጥቃቶችን አይተናል።
እነዚህ ክፉዎች ሰናይ ተግባራቸው የሀሰት መረጃ ማሰራጭት ነው።የታዋቂ ሰዎችን ስም፣ የተቋማትንና የመደበኛ መገናኛ ብዙሃንን ሎጎ አስመስሎ በመጠቀም የሀሰት መረጃውን የሚያሰራጩባው መንገዶች ናቸው ፡፡እንዲሁም ስማቸውን በመቀያየር በርካታ የፌስ ቡክ አካውንት በመክፈት የሀሰት መረጃው እንዲሰራጭም ያደርጋሉ፡፡ብሄር እየቀያየሩም በፌስ ቡክ እሰጣ ገባ የማስገባም ጉዳይም ሌላው የሀሰት መረጃ የማሰራጫ ስልታቸው ነው፡፡በኢትዮጵያ በተለይ በሀይማትና በብሄር ተኮር ግጭትና ረብሻ እንዲከሰት የሀሰት መረጃዎችን ያሰራጫሉ።ግጭቱ ከተከሰተ ደግሞ ክስተቱን ሀይማኖታዊና ብሄር ገጸታ በማላበስ በቃል አጋኖ አጅበው የሀሰት መረጃውን ይለቃሉ፡፡
ብዙ ሰው እንዚህ ክፉ ሰዎች የሚያሰራጩትን የሀሰት መረጃ ሳያጣራና ሳይረዳ እራሱ አምኖ ለሌሎች ሰዎች ያካፍላል፡፡ይህ ተገቢ አይደለም።ህዝቡ በእነዚህ የግጭት ነጋዴዎችና የሀሰት መረጃ አስራጮች ከደገሱለት እኩይ ድርጊት መንቃት አለበት።የእነሱን ተግባር ከማጋለጥ ባለፈ የእነሱን የሀሰት መረጃ ከማሰራጨትም ራሱን መቆጠብ አለበት።
የሀሰት መረጃ በህዝቡ ዘንድ ሲሰራጭ ይዞት የሚመጣው ጣጣ ከፍተኛ ነው፡፡የሀሰት መረጃን ለሌሎች ማጋራት ጥፋት ነው ። ስለዚህ ወገን በክፉ ሰዎች አማካኝነት በማህበራዊ ሚዲያ የሚለጠፉና ተቀናብረው የሚለቀቁ የሀሰት መረጃዎች ሳያጣሩ ለሌሎች ሰዎች መረጃውን ባለማጋራት( ሼር)ና ባለመወደድ(ላይክ) ባለማድረግ ፣የጥፋቱ ተጋሪ አለመሆን ያስፈልጋል፡፡ለአገር ሰላምና ደህነትም የበኩልን ድርሻ መወጣት ይገባል፡፡
ቁጭ ብለው የሰቀሉት ቆሞ ማውረድ ይከብዳል እንዲሉ ዛሬ በየካፌው፣በየቤቱ ቁጭ ብሎ በማህበራዊ ሚዲያ የዘሩት የጥላቻ ዘር ተመልሶ ራስን እንደ ሰደድ እሳት የማይለበልብበት ምክንያት የለም።ሀገርን የማያፈርስበት ምክንያት አይታየኝም፡፡እነዚህ እንኳ ባይፈጸሙ በወጣቶች ላይ የሚፈጥረው መጠራጠርና ጥላቻ ቀላል አይሆንም፡፡
የታዋቂ ሰዎችን፤ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና በተለያዩ ብሄሮችን የሀሰት የፌስ ቡክ አካውንት በመክፈት በፌስ ቡክ የሚገኘውን ዝና፣ በዩቲዩብ የሚገኘው ገንዘብ እያሰበ፣ በጥላቻ በመነሳሳትና በፖለቲካ ጥቅም እያሰሉ የሚለቀቀው የተሳሳተ መረጃ ግጭቶችንና ዘግናኝ ግድያዎች እንዲፈጸሙ ያደርጋል።
ለምሳሌ በኢትዮጵያ በተሰራጩ የሀሰተኛ መረጃዎች ምክንያት በሻሸመኔና ሰሞኑን በቻግኔ አሰቃቂ ግድያዎችን የተከሰቱበት ሁኔታ ተፈጥሯል።ስለዚህ ሆን ተብለው የህዝቡን ስሜት ይኮረኩራሉ፤ለግጭት ያነሳሳሉ ተብለው የተሳቡ አጀንዳዎች ተቀርጸው የሚሰራጩ የሀሰት መረጃዎች የሚያስከትሉት ችግር ቀላል አለመሆኑን ልንማርበት ይገባል።ለአብነትም በሻሸመኔና ሰሞኑን በቻግኒ በንጹሃን ሰዎች ላይ የደረሰውን የመንጋ ዘግናኝ ጥቃት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ፍቅር ስትሰጥ ፍቅር ፤ እውነት ስትሰጥ እውነት፣ ሰላምና መተባባር ስታዳብር ሰላምና በመተባበርን በትውልዱ ታሰርጻለህ መልካም ፍሬ እንደምትገኝ ሁሉ በአንጻሩ ጭካኔን ፣ዘረኝነት፣ ክፉ ሀሳብን፣ ራስ ወዳድነትንና ሌብነትን ስታሰርጽ ውጤቱ አገር ማፍረስ፣ ሰላም መደፍረስና ህዝብን ለሞትና ለእንግልት መዳርግ መሆኑን አስበህ የምታሰራጫቸው መረጃዎች እውነትነታቸው የተረጋገጠ መሆን አለባቸው።ምክንያቱም “ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ“እንዳይመጣ ከወዲሁ ለምናደረግው ነገር ምን ሊያመጣና ሊያስከትል እንደሚችል እያሰብን መረጃውን ማሰራጨትና መጻፍ ይኖርብናል፡፡
ሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት በመጪው ግንቦት ለሚካሄደው ምርጫ ፈተና እንደሚሆን መገመት አይከብድም።ምክንያቱም የክፉዎች ሰናይ ተግባር ግጭት የሚፈጠርበትና ሰላም የሚደፈርስበትን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ነው ፡፡
ምርጫው ነጻ፣ ፍትሀዊ፣ ዲሞክራሲያዊና በህዝብ ታዓማኔ ሆኖ እንዳይጠናቀቅ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የሚደረግ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት አንዱ ስጋት መሆኑ አይቀርም።ይህም ከወዲሁ መላ ካልተበጀለት፣ ህዝቡን ማንቃትና ማስተማር ካልተቻለ ሁከትና አለመረጋጋት ሊያስከትል ይችላል።በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን የሀሰት መረጃ ስርጭት ብዙ ጊዜ ሀይማኖትና ብሄር ላይ ያተኮሩ ናቸው።በተለይ በኢትዮጵያ ብሄርና ሀይማኖት ስስ ብልት ናቸው፡፡ በተለይ ምርጫውን ተከትሎ ሀይማኖትና ማንነትን መሰረት ያደረጉ የሀሰት መረጃዎች ስርጭት አደጋቸው ከፍተኛ ይሆናል ፡፡
ህብረተሰቡ መንቃትና ማስተማር እንደተጠበቀ ሆኖ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚውም መረጃው እውነተኛ መሆኑን ሳያረጋግጥ መረጃውን አለማጋራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች የሚለጠፍ የተሳሳተ መረጃ ከሆነ ደግሞ እውነትነቱን የፓርቲዎቹ ኦፊሻል ድረ ገጽ ሄዶ የመረጃውን ትክክለኛነት መረጋገጥና እውነተኛነት ማጣራት ያስፈልጋል፡፡
እነዚህ ክፉዎች የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች ሳይሆን ቅንቅኖች መጪው ምርጫንም እንደ መልካም አጋጣሚ ሊጠቀሙበት እንደሚችል ግምት ውስጥ በማስገባት በህዝቡም ሆነ በመንግስት በኩል ከወዲሁ ስራዎች መሰራት አለባቸው።በተለይ የሀሰት መረጃዎችን በመልቀቅ ግጭቶችን ለመቀስቀስ ህዝቡን ውዥንብር ውስጥ ለመክተትና ብሎም ግጭት ቢፈጠር “ግርግር ለሌባ ያመቻል“ እንዲሉ በግጭቱ ለተጎዱ ሰዎች ያዘኑ በመምሰል ይህን በማረጋብና ጥላቻና ስሜት ቀስቃሽ ቃላቶችን በመጠቀም እንዲባባስ ማድረጋቸው የዕለት ተግባራቸው መሆኑን ከዚህ በፊት በነበሩት ግጭቶች አይተናቸዋል፡፡
በሰው ሀዘን፣ ስቃይና ፣መከራ፣ሞት መደሰትና ገቢ ማግኘት የክፉዎች ሰናይ ተግባር ስለሆነ በመጪው ምርጫ የሀሰት መረጃዎችን በመልቀቅና የሚፈጠሩ አነስተኛ አለመግባባቶችና ግጭቶችን ካሉ እነዚህን አጋነው በማቅረብና አንዱን ብሄር ከሌላው ብሄር ጋር ግጭት እንዲፋፋም የሚያደርጉ የግጭት ነጋዴዎች ምርጫውን አቆብቁበው እየተጠባበቁ እንደሚጠብቁ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
በነገራችን ላይ እነዚህ ክፉዎች ሰናይ ተግባራችን የሚሉት ብሄራችን ተጎዳ፣ተፈናቀለ ፣ሞተና ተሰደደ እያሉ ያላዝናሉ።እነዚህ ክፉዎች ሰናይ ተግባር ክስተቶቹን የፖለቲካ መጠቀሚያቸውና የማህበራዊ ሚዲያ ላይክና ተመልካች ማግኛ ያደርጉታል እንጂ በግጭት የተፈናቀሉ ወገኖችን ስቃይ ከቃላት ባለፈ በተግባር ድጋፍ ሲያደርጉ አይስተዋልም፡፡
“ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም “እንዲሉ ለእነዚህ ሰዎች ከልብ እዝነት ቢኖራቸው ገንዘብ አዋጥተው በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ድጋፍ ያደርጉላቸው ነበር።ነገር ግን የእነሱ ዓላማ ችግሮቹ በውይይት እንዲፈቱ፤ የጥቃቱ ሰላባ የሆኑት ሰዎች እንዲቋቋሙ ከማድረግ ይልቅ “በሰው ቁስል ሽንቁር ጨምርበት“ እንደሚባለው በእነሱ ቁስል ትርፍ ማግኘትና ተቆርቋሪ ለመምሰል ነው ዓላማቸው፡፡
ህዝቡ የሚጠቀመው አገር ሰላም ሲሆንና ስትመነደግ እንጂ ሰላምና መረጋጋት ሲጠፋ እንዳልሆነ በውል ቢረዱትም በአንጻሩ አገር ለማፍረስና ግጭት ለማስፋፋት የሀሰት መረጃዎች በመሰራጨት ተግተው ሲሰሩ ይታያሉ።እነዚህ ክፉዎች ይህን ሀይላቸውን አገር ለመገንባት፣ሰዎችን ለማስተሳሳር፣ግጭቶችን ለማርገብና ሰላምን ለማስፈን ቢጠቀሙ ኖሮ ኢትዮጵያ ሰላም የሰፈነባት፣ ዜጎች በአገራቸው ያለ ስጋት የሚኖሩባት ለትውልድ የሚተርፍ ስራ የሚሰሩባትና ተባብረው ለማደግና ለመስራት ምቹ ሁኔታ ይፈጠር ነበር።ግጭቶች እንኳ ቢፈጠሩ በቆየው አገራዊ እሴት በእርቅ የሚፈታበት ሁኔታ ይፈጠራል።ምን ያደርጋል በክፉዎች ሰናይ ተግባር ምክንያት በሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨትና ጽንፍ የወጡ ዘረኝነትን የሚሰብኩ ጹሁፎችን በማህበራዊ ሚዲያ በመለጠፍ ወጣቶች በስሜት ነገን እንዳይመለከቱ አድርገዋቸል፡፡
እነዚህ ክፉ ሰዎች ተመክረው ፣አዝነውና ተጸጽተው ከሰናይ ምግባራቸው የሚመለሱ ከሆነ መልካም።ምክንያቱም የሚፈጠሩ ችግሮችን በማባባስና ተጨማሪ ቀውስ መፍጠር ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይጎዳል እንጂ አይጠቅማትም።ኢትዮጵያዊያንን በብሔርም ሆነ በሃይማኖት በማጋጨት ማጋደል፣ ማፈናቀልና ውድመት እንዲፈጸም መቀስቀስና የሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨት እንደ አገርና ህዝብ አዘቅት ውስጥ ይከተናል እንጂ ዕድገት አያመጣም፡፡ግን ከዚህ የጥፋት ተግባራቸው የማይመለሱ ከሆነ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የሀሰትን መረጃዎች ከማሰራጨትና ሀሳቡን ከመጋራት ራስን መጠበቅ ይገባል፡፡መንግስትም ሆን ብለው በሀሰት መረጃ ህዝቡን ወደ ግጭት የሚመሩትና የጥላቻ ዘርን የሚዘሩትን ወደ ህግ አቅርቦ ተጠያቂ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
በተከሰቱ ግጭቶች ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ምሬቱ ከማሰማቱና እና ከማልቀሱ በተጨማሪ ሁላችንም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት የበኩላችንን ሃላፊነታችንን ብንወጣ መልካም ነው ፡፡ ከምንም ነገር በላይ ለአገራቸው ማንኛውንም ዓይነት መስዋዕትነት ለመክፈል የማያንገራግሩት ኢትዮጵያዊያን ብዙዎች ቢሆኑም በአንጻሩ ለግልና ለቡድን ጥቅም የሰከሩ ኃይሎችና ለእነሱ መጠቀሚያ በሆኑ የማህበራዊ ሚዲያ የክፉዎች ሰናይ ተግባር ምክንያት የአገር ሰላም መደፍረስ የለበትም፡፡ስለዚህ ሁሉም የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መረጃዎችን ትክክለኛነትና ምንጭ ሳያረጋግጡ ለሌሎች ሰዎች መጋራት የለባቸውም፡፡የሀሰት መረጃዎችን ሁላችንም በጋራ በመከላከል የዜግነትና አገራዊ ግዴታችንን መወጣት ይጠበቅብናል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 7/2013