ምህረት ሞገስ
‹‹በኢትዮጵያም ሆነ በየትኛውም አገር ቢገኙ ተሳደው ለፍርድ መቅረብ አለባቸው።›› በሚል በተደጋጋሚ ብዙዎች አስተያየት ሰጥተዋል። በትግራይ ክልል በአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ጥቃት የፈጸሙና የማይካድራውን ጭፍጨፋ የተሳተፉ ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ንጹሃን ሰዎችን የማጥቃት፣ የማሳደድና የመግደል ተግባርን የፈፀሙ ሰዎች እኔ ደግሞ ይጠየቁ ሳይሆን ‹‹ሰዎችን አሳደው ስለገደሉ ይሸለሙ›› እያልኩ ነው። መቼም ይሄ እብደት ነው ሊያስብል ይችላል፤ ነገር ግን እየተለመኑ፣ እየተያዙና ለፍርድ እየቀረቡ ከድርጊታቸው ካልታቀቡና ካልተፀፀቱ ለምን በተቃራኒው ‹‹እንሸልማችሁ›› አንላቸውም? ምናልባት ያው ሁሉ ነገራቸው የሰው ተቃራኒ ስለሆነና መሸለም ስለማይፈልጉ ድርጊቱን መፈፀም ያቆሙ ይሆናል በሚል ነው። ታዲያ ምን ላድርግ?
ሰው ፈርቶ እጁን ካልሰጠ፤ ከመታሰርና ከመገደል ይልቅ ‹‹በሰላም እጄን ልስጥ›› ብሎ ካላመዛዘነ ለምን በሽልማት ስም አንሰበስባቸውም? ከዚያ ችግር የለም ሸልመን ከሰበሰብናቸው በኋላ እንዳይበተኑና እንዳይበታትኑን ለመጠበቅም፤ ለመጠንቀቅም ምቹ ይሆናል። ‹‹ይቅርታ መጠየቅ ትልቅነት ነው፤ ይቅርባይነትም መሸነፍ ሳይሆን ታላቅነት ነው›› በሚል ሰው አሳደው የወገሩና የገደሉ ይቅር ይታለፉ ተባለ። ነገር ግን እነርሱ በጎ ብሎ ነገር አይታያቸውም። ለዚያውም እነርሱ በአደባባይ ይቅርታ ሳይጠይቁ በተለይ በየእስር ቤቱ ዘግናኝ ድርጊት የተፈፀመባቸው ተበዳይ ግለሰቦች፣ ቤተሰባቸው የተገደሉባቸው ዜጎች፤ ልጇ የተገደለባት እናት ሳትቀር፤ የበደለኝን በፍርድ አደባባይ ማየት እፈልጋለሁ ሳትል ለውጥ ይመጣል በሚል ተስፋ በይቅርታ ማለፏን ባፏ ባትገልፅም የፍትህ ጥያቄ ሳታቀርብ በዝምታ አልፋ ስለጥፋታቸው ቢታለፉም ከሰይጣናዊ ድርጊታቸው ሊቆጠቡ አልቻሉም።
ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድ ኢትዮጵያ ትፈጠራለች ብላ ጓጉታ ሁሉን ለፈጣሪ ሰጥታና ትታ ላለፈች አገር፤ ይቅር ላለ ሕዝብ፣ ፀፀት የማያውቁ ከጥላቸው የተጣሉ መንፈሶች ይቅርታና ሰላም እንደማይገባው የሚፈጸሟቸው እኩይ ተግባሮች አስረጂ ናቸው። ምረናችኋል ቢባሉ ምን ዋጋ አለው? ሁሌም የሚሄዱት በራሳቸው መንገድ ነው። በአንድ እጅ ማጨብጨብ ደግሞ አይቻልም። ነገር ግን እኔ ደግሞ አሁንም ‹‹ፅድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም›› ይባል አይደል። አገሩን የሚታትርና ለአገሩ ዘብ የሆነ ቢሾም ቢሸለም ደስ ይላል። አገሩን የበደለ ‹‹ምህረት ተደርጎልሃል›› ተብሎ ከስህተቱ ቢማርና ከጥፋቱ ተፀፅቶ ቢመለስም እንደዚያው ደስ ይላል። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች (ቡድኖች) ለሁለቱም ሃሳብ የሚመቹ ባለመሆናቸው በተቃራኒው ሽልማት አስቤላቸዋለሁ።
ሽልማቱ ምንም ዓይነት ነገር ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የግድ እነርሱን የሚያጓጓ መሆን አለበት። የሥልጣን ጥማት ያናወዛቸው በመሆናቸው ብቻ ሥልጣን ይሠጣቸው የሚል የሥልጣን ሽልማት ተቀባይነት የለውም። ምክንያቱም በብዙ መልኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመንግሥታት ቢጠቀምም፤ መበደሉም አይታበልም። በትህነግ የመንግሥትነት (የሥልጣን ዘመን) እርግጥ ነው ተወደደም ተጠላ የተሰራ መልካም ሥራ ቢኖርም ሚዛን ላይ እናስቀምጠው ከተባለ ደግሞ አባታቸውንና እናታቸውን ያጡ፤ ቤተሰባቸውን የተነጠቁ ቢናገሩት ይሻላል። ምን እርሱ ብቻ? ለአገሪቷ በዘመናት ተከፍሎ የማያልቅ የብድር ዕዳ ብቻ ሳይሆን ለመፍታት የሚያስቸግር የተተበተበ ውስብስብ የፖለቲካ ነቀርሳ ተክለዋል።
እነዚሁ ፖለቲከኞች የተከሉትን ነቀርሳ እንደመሣሪያ በመጠቀም ትናንት ሲያሳድዱና ሲገድሉ ቢኖሩም ዛሬም በየአካባቢው የሞት ድግስ እየደገሱ የሰው ሕይወት እያስገበሩ አገር እየፈተኑ ነው። ቅሌታም ፖለቲከኞች ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሰሩት ጥፋት ለታሪክ በምን መልኩ እንደሚቀመጥ ቢያስጨንቅም አሁንም በነጋ በጠባ ቁጥር ከሙሉነት ይልቅ ዘላለማቸውን የበታችነት ስሜት እየተሰማቸው፤ ለአንድ ወገን (ወገን ማለት ይከብዳል ለአንድ ቡድን) ብቻ የመቆም አባዜ የተጠናወታቸውን ፖለቲከኞች በውጭም በአገር ውስጥም ፈልፍለዋል። ነገሮችን ከውስጥም ከውጭም አስፍተው ከማየት ይልቅ ዓይናቸውን አጥብበው ጉድጓድ ውስጥ እንዳለች አይጥ አጥብበው እያዩ ኖረው ዓለምን ለማየት የተሳናቸው ትውልድን ፈጥረውና ይህንን ስሜታዊ ትውልድ በመጠቀም የኢትዮጵያን መበተን ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር ተባብረው የሞት ድግስ መደገሳቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። ለዚህ ማሳያው የቅርብ ጊዜ የሰሜን ሸዋ አጣዬ፣ ሸዋሮቢትና መሰል አካባቢዎች ጥቃት እና ወለጋ የሰው ሕይወት መጥፋትን መጥቀስ በቂ ነው።
ከለውጡ ተቃራኒ በጥፋት ሥራ ላይ ተሰማርተው ሌት ከቀን ከሚሰሩት መካከል የህወሓት ተላላኪ የሆነው ኦነግ ሸኔ አንዱ ነው።
ይህ ኃይል የመንግሥትን መዋቅር በኃይል ለመናድ የጥፋት ሰንሰለት እና እልቂት በየደረጃው ለማደራጀት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የትህነግን ተልዕኮ በመቀበል በመስራት ያለው ይህ ኃይል በገጠር እና በከተማ ባለሥልጣናት እና ዜጎችን የሚገድል ቡድን በማሰማራት በርካታ የሽብር ጥቃቶችን አድርሷል። ከዚህ ባለፈም በርካታ የመንግሥት እና የዜጎችን ንብረት አውድሟል።
የኦነግ ሸኔ ኃይል በተስፋ መቁረጥ ስሜት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚወስደው የሽብር ጥቃት አሁንም ቀጥሏል።
ከትናትና በስቲያ በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ ቦኔ ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ የሽብር ጥቃት በመፈጸም ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ተገድለዋል።
ትህነግ የቀበረው የሴራ ፖለቲካ ተከታዮች አገርን በሰንሰለት አስረው፤ እንዳታድግ ቀብረው፣ ሕዝቡን ከፋፍለው እርስ በእርሱ እንዲጫረስ ስላደረጉ በእርግጥም በፍርድ አደባባይ ሊጠየቁ እና ሊቀጡ ይገባል። ነገር ግን ፍርድ፣ እስርና ቅጣት ለሚያመዛዝን ተፀፅቶ ለሚመለስ ሰው ብቻ ነው። ምንም እንኳ ኢትዮጵያውያን ፈጣሪን የምንፈራ መልካም ባህላዊ እሴቶች ያሉን ቢሆንም፤ ቅጣት ለሚገባው ቅጣት ተገቢ ነው የሚል የፀና እምነት አለን። በመላው አገሪቷ የተፈፀሙ ዘግናኝ ድርጊቶች ደግሞ ተገቢውን ፍርድ ማግኘት እንዳለባቸውም ያለጥርጥር በሙሉ ድምፅ አፅድቀን፤ ድርጊቱን የፈፀሙ በፍርድ አደባባይ ይቀጡ እንላለን። ነገር ግን ምን ዋጋ አለው? ከዛስ እነርሱ ተቀጥተው ምን ይፈጠራል? ከእነርሱ ጋር ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያላቸውን እየኮተኮቱ ያሳደጓቸው ሰዎች ልክ እንደነሱ ተግባሩን ይቀጥሉታል? ወይስ ቅጣቱን ፈርተው ከድርጊታቸው ይታቀባሉ? የሚል ጥያቄ ከቀረበ በበኩሌ እነግፍ አይፈሬ ቅጣት ፈርተው ዘግናኝ ድርጊት ከመፈፀምና ከማስፈፀም ወደ ኋላ ይላሉ የሚል እምነት የለኝም።
በእርግጥ በበፊት መንግሥታት ተደረጉ የሚባሉ ዘግናኝ ድርጊቶች አሁን መፈፀም እንደሌለባቸው ቢያስማማም፤ የተዛባ ታሪክ እየተረተሩ፤ በዚህ ተረታቸው ሰው ያጫረሱና ለአገሪቷ የ100 ዓመት የቤት ሥራ የሰጡ አካላት፤ የማይነቀል ነቀርሳ በመትከላቸው እንዳለፉት መንግሥታት ከመወደስና ከመወቀስ ይልቅ ሸልመንና አስደስተን ከድርጊታቸው እንዲመለሱ ብናደርግ ሳይሻል አይቀርም። ምክንያቱም እነርሱን ይዞ ማሰርና መቅጣት ከባድ ነው። ምክንያቱም እነርሱ የተከሉት አሜኬላ በብዙ የሥልጣንና የገንዘብ ጥመኞችና ሥራ አጥ ወጣቶች ልብ ውስጥ ታትሟል። ስለዚህ የያዙትን ይዘዋልና ዘግናኝ ድርጊት መፈፀማቸውን እንዲያቆሙ የሽልማት ጥሪ ይካሄድላቸው።
ካልሆነም ለፍርድ ማቅረብ ብሎ ነገር ይቅር። መሣሪያ ስለተያዘ ማሸነፍ የሚቻል መስሏቸው የገቡበት ጦርነት በሽንፈት ቢጠናቀቅም፤ ዛሬም አላረፉም። ነገር ግን ‹‹ግፍ አድራጊን ግፉ ይገፋዋል።›› እንደሚሉት ከሚንደላቀቁበት ባለኮከብ ሆቴል ወጥተው አንዳንዶቹ በጫካ በጉድጓድ ውስጥ ተደብቀው ሲንገላቱ የቀይ ጥቁር ሆነው ያ የድሎት ፊታቸው ተጎሳቁሎ ተመልክተናል። ታዲያ ለምን መልካቸው ወደ በፊቱ እንዲመለስ አናግዛቸውም? መቼም የሚሉትን ስላልሰማን እንጂ አሁን ላይ የሚፈልጉት የድሎት ኑሮ ብቻ ሊሆን ይችላል። መቼም ከአሁን በኋላም በየቦታው በሚረጩት መርዝ ወገኖቻችን ከሚያልቁ በሽልማት ሰበብ እንሰብስባቸውና ድሎታቸው ይመለስ እኛም የሞት ዜናን ከመስማት እንረፍ።
ስለዚህ ትልልቅ የሥልጣን ቦታ ላይ ያሉት በሙሉ ይህን ጉዳይ ቢያስቡበት አይሻልም? ሌላ ሦስተኛ አማራጭ ያለው ካለ ይቅረብ በእኔ በኩል ማሸነፍ የሚቻለው ኑ እንሸልማችሁ በሚል አማራጭ ብቻ ነው የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም እነርሱ አሁን ላይ እየፈፀሙት ላለው ጥፋትና ግፍ የሚሸልማቸው ስላለላቸው እንሸልማችሁ ብንላቸው ምናልባት የተሻለ ሳይሆን አይቀርም።
‹‹በቋንቋ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አደረጃጀት ሥርዓት ይበጅለት። ለኢትዮጵያ አይጠቅምም›› ብሎ ደጋግሞ መናገር አይጠቅምም። እንደዚህ ዓይነት እምነት ያላቸውን ሰዎች ሰብስቦ ‹‹እንነጋገር እንወያይ ትውልድ አንጨርስ!›› መባባል ሚዛኑን ለመጠበቅ መጣር የሚበጅ ነው። ነገር ግን ያው መቼም ሁሉንም ማርካት አይቻልም። ሁሉም የራሱን ብሔር እንደእንብርት፤ አንዳንዱ እንደምሰሶ፣ አንዳንዱ እንደውሃ ልክ እየቆጠሩ ሌሎችን አሳንሶ ለማሳየት እየሞከረ የፖለቲካ ትርፉን ቢያጋብስም ለሥልጣን ጥመኞች መቼም እኛ መሸለም የማይታክተን በመሆኑ ሸልመን እንዲያው ትንሽ እያሰቡ ትንፋሽ እየሰበሰቡ እንዲመለሱ እንፍቀድላቸው።
ለአገርና ለሕዝብ አንድነት ሳይሆን ለመበታተን ጊዜ የሚያጠፉትን ከአሁን በኋላ ቀልባቸውን ሰብሰብ እንዲያደርጉ ይቅርታ አድርገንላችኋል ከማለት አልፈን እንሸልማቸው። ከአሁን በኋላ ሰላም ሰፍኖ፤ ትግል በሚል የዳቦ ስም ሞት የሚቆምበት ሁኔታ እንዲፈጠር እናድርግ። የማናሸንፍበት ጦርነት ውስጥ መግባት አንፈልግም። ስለዚህ ኢትዮጵያ ሁሉንም የምትጠቅም እንድትሆን ወጣቱና አዛውንቱ ጎልማሳና ሕፃኑ ሁሉም በአገራቸው ተከብረው ይኑሩ።
መንግሥት ሥራው ግብር መሰብሰብ ብቻ አይደለም። መንግሥት ፀጥታን የማስጠበቅ ሥራ መስራት አለበት፡፣ ባንኮችንና የሰዎችን ንብረት መዝረፉ መቆም አለበት። በከተሞች በተለያየ መልኩ የሚፈፀሙ ዝርፊያዎች መላ ሊበጅላቸው ይገባል። አዎ የፀጥታ ኃይሎችና የመንግሥት አመራሮች ለአገራቸው 24 ሰዓት ይሰራሉ። እያንዳንዱ ዜጋም በአገራችን ሰላም፣ ፍትህና እኩልነት እንዲሰፍን የበኩሉን ድርሻ ማበርከት አለበት።
የኢትዮጵያን ችግር በኢትዮጵያ መፍታት ይችላል ብሎ ማመን ያስፈልጋል። አዎ ‹‹መግደል ጀግንነት አይደለም። አዎ ጀግንነት ሰላምን ማምጣት ነው።›› ነገር ግን ሰላምን ለማምጣት የጥፋት ኃይሎቹን በሆነ መንገድ ማስቆም ያስፈልጋል፤ በሽልማትም … ቢሆንም ጥፋቱ መቆም አለበት።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በጦርነት ድል ማድረግን አይታማም። ግዛቱና ሃይማኖቱ እንዲነካበትም አይፈልግም። አዎ መነካትም የለባቸውም። ነገር ግን በተለያየ መልኩ ሉዓላዊ ግዛቱንና እምነቱን የሚሸረሽሩበት ነገሮች መጥተውበታል። ለዚህ ደግሞ ሁኔታውን ተረድቶ የፈተና ጊዜውን ማሻገር የሚችል ትውልድ፣ አመራርና መንግሥት ያስፈልጋል። የትናንቱን ጥፋት ይቅር በማለት የዛሬን ዕድል በመጠቀም፣ የነገው ተስፋ ለመጨበጥ የጥፋት ኃይሎቹን ከእኩይ ድርጊታቸው ለማስቆምና ተጸጸተው እንዲመለሱ ለማድረግ እነዚህ የጥፋት ኃይሎችን ይቅር የሚል ይቅር ከማለት አልፎ ሸልመናቸው ከጥፋታቸው የሚመለሱ ከሆነ ምን አልባት የሚሸልም ትውልድና መንግሥት ያስፈልገናል እንበል። ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2013