ምህረት ሞገስ
ህግ በትክክል ፍትህን የሚያሰፍን የማያዳላ አንዱን ጠቅሞ ሌላውን የማይጎዳ መሆን ይጠበቅበታል። እንደዚህ ዓይነት ህግ የሁሉም ነገር መሰረት እና በእኩልነት የመኖር ውሃ ልክ መሆኑን አስመልክቶ ብዙዎች ይስማማሉ። በአገሪቱ ህግ መከበሩን ማረጋገጥ የግድ ነው። ህግ አክባሪ መሆን የግድ ነው ሲባል፤ በኢትዮጵያ ህግ በትክክል ምን ያህል ይረጋገጣል? የሚለው ጉዳይ ደግሞ ያጠያይቃል።
በተለይ ባለፉት ጊዜያት ህግ ከግለሰቦች ስልጣን በታች ወርዶ፤ በመዋረዱ አገርን የህግ አለማክበር ውጤቶች ሲያዳክማት፤ አንዳንዴም ገደል አፋፍ ላይ ወስዶ በአፍጢሟ ሊተክላት ጫፍ አድርሶ ሲመልሳት ተስተውሏል።
በአንድ አገር ውስጥ ህግ ሲከበር የነጠረ ትውልድ ይገነባል፤ ነፃነትና ሀብት በልካቸው እንደወንዝ ውሃ ይፈሳሉ። በኢትዮጵያ ግን ነፃነትና ሀብት ሊፈሱ ቀርቶ በተለያዩ አጋጣሚዎችም የጠብታ ውሃን ያህል ሲገኙ አቅጣጫቸው እየተጣመመ፤ መሰረታዊና ፍትሐዊ ጥቅም ሳይሰጡ ደርቀው ቀርተዋል።
ለእዚህ መንስኤው የፖለቲከኞች አመለካከትና ድርጊት ከህግ በታች መሆን ሲገባ፤ በተቃራኒው ስልጣን ከህግ በላይ ሲመለክ ዕድገት፣ ነፃነት፣ ዴሞክራሲ እና ሰላም የቁልቁለት ጉዞ የኋሊት በመንሸራተት አገሪቷን ለከፋ ጉዳት በመዳረጋቸው ነው።
አንድ ሰው ከሰው ጋር ህግ አክብሮ በሰላም መኖር እያለበት፤ ያለምንም የህግ መሰረት የሰውን የልፋት ውጤት ሊዘርፍ ከዳዳ፤ መዳዳት ብቻ አይደለም ከዘረፈ፣ በህግ ሊጠየቅ ሲገባው ከታለፈ፤ ፍትህ ተጓደለ አገር ፈረሰ።
ይህ ሲሆን ሰምተናል፤ ዓይተናል። ህግ አክባሪ ትውልድ በመጥፋቱ በአደባባይ ንብረት ሲወድም የሰው ህይወት ሲጠፋ፤ ሰዎች ያለሃጢያታቸው ለስደት ሲጋለጡ ታዝበናል። ይህንን ህግ ማክበርን የመጠየፍ ጥግ በአስቸኳይ መላ ካልተበጀለት ምንም ቢለፋ ፤ ምንም ቢሠራ ውጤቱ አያምርም።
አንዲት እናት ወደ አንድ የአውሮፓ አገር አመሩ፤ ልጃቸው ዘንድ ሊያርፉና ሊዝናኑ። እዚያ አገር ካዩት እና ከተዝናኑበት ጉዳይ ሁሉ ተለይቶ እጅግ የተደሰቱት በህዝቡ ህግ አክባሪነት ነው። መኪና የሚነዳው በስርዓት በተመጣጣኝ ርቀት ነው። ትራፊክ ‹‹አየ አላየ›› በሚል በፍፁም የህግ ጥሰት አይፈፀምም። እግረኛ ዜብራ መንገድ ለመሻገር ቆሞ በፍፁም መኪና ቅድሚያ የማይሰጥበት አጋጣሚ የለም።
እና አገር ጎብኚዋ ኢትዮጵያዊት እናት በአገራቸው ‹‹በህግ አምላክ›› ሲባል ሁሉ በነበረበት የሚቆመው ነገር ትውስ አላቸው። በህግ አምላክ ከተባለ ለመሮጥ ያሰበ ይቆማል። ለመቆም የተዘጋጀ ይቀመጣል፤ ሁሉም ተጠንቀቅ እንደተባለ ባለበት ይደርቃል።
ዘንድሮ ደግሞ በህግ አምላክ ሲባል፤ (የህግን የበላይነት የማያውቅ ትውልድ ተፈጥሯልና) አያዳምጥም። እርሱ ጉልበት አለውና በጉልበቱ ያገኘውን ይሰብራል። ይህ ድርጊት በአንድ ጀምበር በተገኘ ሃሳብ በስሜታዊነት የሚፈፀም ቢመስልም፤ የህግ አክባሪነት መንፈስ አለመገንባቱ፤ ይባስ ብሎ ቀድሞ የተገነባውም በመፈራረሱ የመጣ ውጤት ነው።
በትዝታ ውስጥ ሰምጠው በሰመመን ያለፈውን ጊዜ የናፈቁትን እናት አደራ ‹‹የድሮ ስርዓት ናፋቂ›› እንዳትሉብኝ። እርሳቸው የናፈቃቸው ስርዓቱ ሳይሆን በጊዜው የነበረው ህዝብ ህግ ለማክበር የነበረው ታዛዥነትና ፅናት ብቻ ነው። እንደአንዳንድ የመሳፍንት ዘመን ደጋፊዎች መሬት ላራሹ በሚል በ1960ዎቹ ንጉሱን ሲቃወሙ የነበሩ ወጣቶች ‹‹ ለህግ የማይገዙ ነውረኞች›› ብለው ለመዝለፍ አስበው አይደለም።
በእርግጥ ግን እኚህ እናት በዚያ ጊዜ የነበረው ወጣት ያቀረበው ጥያቄ ተገቢነቱን ቢያምኑም፤ ተያይዞ ከህግ የመውጣት አባዜ ሳያስቀይማቸው አልቀረም። ያው የንጉሱን አገዛዝ ከመቃወም ጋር ተያይዞ የመጣው መዘዝ ዙፋን ነቅንቆ ስልጣን ቢያስለቅቅም የህግ የበላይነት ብሎ ነገር አፈር ድሜ እንዲግጥ መነሻ ሆኗል።
ቀይ ሽብር ነጭ ሽብር በሚል ያለ ፍርድ ቤት ክርክር በአደባባይ መሳሪያን ጉልበት ያደረጉ ጨካኞች ከህግ በላይ ሆነው ፍርድ ሳይሰጥ ብዙዎችን ጨርሰዋል። እናቱ ጉያ የተደበቀ ሳይቀር እየተጎተተ ወጥቶ፤ ተንበርክኮና እጁ ወደኋላ ታስሮ ግንባሩ ላይ እየተተኮሰ በግንባሩ ተደፍቷል።
ተደፊው ቢያጠፋ በህግ ፊት ቀርቦ ቅጣት ሲገባው፤ ጉልበተኛው ባለጠመንጃ ፖሊስ ሆኖ እራሱ አስሮ፤ ራሱ መርምሮ፤ ችሎት ፊት ሳይቀርብ ዳኛ ሳይሰየም ለሞት ፍርድ አደባባይ በማቅረብ ግድያ ሲፈፀም ባለጉልበት ባለስልጣን ከህግ በላይ ሆኖ ሲገል ጎብኚዋ እናት ታዝበዋል።
ያ ህግ የማይተገበርበት በግፍ ብዙዎች የተገደሉበት የደርግ ዘመን ህግ አለማክበሩ ጠልፎት ቢሸኝም፤ በአደባባይ ይፈፀም የነበረ ግፍ በድብቅ ሲፈፀም የወጣ እንደወጣ ሲቀር፤ ሰዎች ሲዘርፉ ህግ እንደአፈር ተረግጦ ሲንፈራፈር ከልካይ ሲጠፋም አገር ጎብኚዋ እናት ታዝበዋል።
በሥራ አጋጣሚ አለቃቸው ከህግ ውጪ ሰዎችን ሲቀጥር ሲያባርር ታዝበዋል። እስር ቤት ያለፍርድ ብዙ ሰዎች ከህግ ውጪ የሚንገላቱ መሆናቸውን አይተው ባያረጋግጡም፤ በዘመዳቸው ላይ ‹‹ግብር አጭበርብርሃል›› በሚል ሰበብ ታስሮ ያለፍርድ ለዓመታት እስር ቤት መንገላታቱና ልጆቹ ያለአሳዳጊ መሰቃየታቸው ሲታወሳቸው መንግሥት ሳይቀር ህግ እንደማያከብር እና እንደማያስከብር ራሱ ከህግ ውጪ መሆኑ ትውስ ብሏቸው፤ ዘግንኗቸዋል። ያው ህግ የሚጥስ ባለስልጣን መስፋፋቱን ተከትሎ ተያይዞ የመጣው የ1960ዎቹን መሳይ አመፅና እምቢተኝነት ያስከፈለውን የወጣት ህይወት ህልፈት እያሰቡ አንገሽግሹዋቸዋል።
አሁን አሁን ደግሞ ትውልዱ በህግ አለመመራት አጥለቅልቆት የሰውን ንብረት ከመዝረፍ አልፎ መንግሥትን ሳይቀር እስከመዝለፍ የመንግሥትን የሥራ ድርሻ ለመንጠቅ እስከ መንደርደር የደረሰ ጥፋትን አይተው አንጀታቸው እርር ብሏል። እና እኚህ እናት ሰሞኑን ደግሞ አንድ ነገር አጋጥሟቸዋል።
እርሳቸው እንደሚገልጹት ህግ ከሚከበርበት አገር ከመጡ ከራርመዋል። በአንዲት ለአዲስ አበባ ቅርብ በሆነች አካባቢ ለአንድ ዓላማ ቦታ ሲታጠር ያያሉ። ወዲያው የአካባቢው ወጣቶች ቦታው ላይ ተገኝተው ትርምስ ይፈጠራል።
ወጣቶቹ ጥያቄ ያቀርባሉ። የታጠረው በማን ነው? ፈቃጁስ ማን ነው? ብለው ይጠይቃሉ። ቦታው የታጠረው በመንግሥት ፈቃድ ተሰጥቶ በመንግሥት አካል ነው። የሚል ምላሽ ሲሰጣቸው ‹‹መንግሥት ማን ነው? እኛ ሳንፈቅድ መንግሥት ማጠር አይችልም፤›› የሚል አምባጓሮ ያነሳሉ።
በአጥር ሠሪዎቹና ወጣቶቹ መካከል የተፈጠረው ትርምስ የአካባቢውን ሰው ያስጨንቃል። የፀጥታ ኃይል ይመጣል። ህግ የሚከበረው ሁልጊዜ በአስገዳጅ ፀጥታ አስከባሪዎች ብቻ መሆን ባይኖርበትም፤ የአካባቢው ወጣቶች ግን ፀጥታ አስከባሪዎችንም ለመስማት ፈቃደኛ አልሆኑም። በማግስቱ ሰዎች የሚሳፈሩባቸውን ተሽከርካሪዎች አዝዘው እስከማስቆም ደረሱ። አሁን በተወሰነ መልኩ በፀጥታ ኃይሉ አማካኝነት የተወሰነ መሻሻል ቢኖርም ወጣቶቹ ህግ ለማክበር የፈለጉ አይመስልም።
እንደእዚህ የመሰሉ ጥፋቶች በየቦታው እየታዩ ነው። አሁንም ህግ አለማክበር የኋላ ቀርነት ጭራ ቢሆንም እንደዘመናዊነት እየታየ እንደጀብድ ሲገለጽ መስማት ያሳምማል። ሰው ገድሎ በአደባባይ መፎከር ጥንትም የሚታወቅ አጉል ባህል ቢሆንም፤ ድሮ አንድ ሰውን የመግደል ድርጊት ከጀርባው ቢያንስ በትንሹ ሊጠቀስ የሚችል ቤተሰቤን ቤተሰቡ ገድሎብኛል የሚል የበቀል ምክንያት ነበረ።
ያም ቢሆን ህግ አለማክበር ነው። የአሁኑ ግን ያለምንም በቂና አሳማኝ ምክንያት አንድን ሰው ሳይሆን ራስን ከህግ በላይ አስቀምጦ ህዝብ ማሳደድና ማሰደድ ነገን ብቻ ሳይሆን ዛሬንም ጭምር ለመፍራት ያስገድዳል። ለዚህ ነው አገር ጎብኚዋ እናት ነገን ብቻ ሳይሆን ዛሬንም የፈሩት።
በቤንሻንጉል ጉምዝ መተከል፤ በደቡብ ክልል ማረቆና መስቃን አካባቢ፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተፈፀሙ ድርጊቶች ምንጫቸው አንድ ነው። ምንጫቸው አንድ ቢሆንም ብዙ ጥፋት የተከሰተበት ምክንያት ደግሞ ህግ አክባሪነት ሙሉ ለሙሉ በመጥፋቱ ነው።
የአሳዳጁ ህግ አለማክበር ብቻ አይደለም። ተራ ዜጋው ብቻ ሳይሆን ለስልጣንና ለክብሩ ሲጨነቅ ህጉን የዘነጋው ግለሰብም አደጋ ላይ መውደቁ የማይቀር መሆኑን ዘንግቶ ህግ ማክበር እና ማስከበሩን ትቶታል። ይሄ ድርጊት እየዳበረ ሲመጣ በነፃነት መኖር የማይችሉ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ባለስልጣኖችም በጉልበተኞች ሥራቸውንና ነፃነታቸውን ያጣሉ። ህግ ቦታውን ለጉልበት ካስለቀቀ ሁሉም ነገር ያበቃለታል።
እንዳየነውና እስከአሁንም እያየን እንዳለነው ጉልበተኝነት የህግን ቦታ ሲያስለቅቅ የሚፈርሰው የተገነባ ሕንፃ፣ መንገድና ድልድይ ብቻ ሳይሆን ሰውም እንደቀልድ እየፈረሰ ያልቃል። የጉልበተኞች ቀንበር ስር የወደቀ ህዝብ ተረግጦ ይኖራል። ነፃነት፣ ዴሞክራሲና ሰላም ብሎ ነገር አይታሰብም። የሚተገበረው ነገር ሁሉ በህግ የተመራ ሳይሆን በጉልበተኞች ፍላጎት ላይ ብቻ የተመሰረተ ይሆናል። አዳዲስ ሃሳቦች እየቀረቡ አገርንና ህዝብን ተጠቃሚ የማድረጊያው በር ይዘጋል። አገር ክፉኛ ትደቃለች።
ስልጣን ጥቅምና ክብር ህግ ካልተከበረ አይዘልቁም። የሰዎች የእርስ በእርስ ግንኙነት ህግ የማይገዛው ከሆነ በግጭት መታመስ ይበረክታል። ጉልበት እስካለው ድረስ ልጅ ወላጁን፣ ተማሪ አስተማሪውን፣ ቄስ ጳጳስን ፣ ተቀጣሪ አሠሪውን በተገላቢጦሽ እንደፈለገ የሚያደርግበት ሁኔታ ከተፈጠረ ሙሉ ለሙሉ ፍቅር ይጠፋል።
ፍቅር ብቻ አይደለም የዕልቂት ማዕበል ይነሳል። ማንም ወደ የትኛውም ቢሮጥ የሚጋጥመው ገደል ነው። ማምለጥ አይቻልም። የህግ አክባሪነት አስተሳሰብ አሁንም የሚያንሰራራበት ዕድል ካልተፈጠረ አደገኛ ነው። ውድመት ይከተላል። የህግ አክባሪነት አስተሳሰብን ለማስረፅ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ግድ ይላል።
በጥቂት ሥራ የተገነባን ማፍረስ ቢቻልም ለውጥ ለማምጣት ብዙ መጣር ያስፈልጋል። መምህራን እና ወላጆች ልጆች ህግ አክባሪ እንዲሆኑ ተግተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ያለፈው አልፏል። ነገር ግን አሁንም ቢሆን የተጣመመው ሳይሰበር እንዲቃና እያረጠቡ ማስተካከል ያስፈልጋል። ወጣቱ መብቱን ብቻ ሳይሆን ግዴታውንም እንዲያውቅ። ከጉልበቱ ይልቅ በህግ ላይ እንዲተማመን መገሰፅ የግድ ነው።
ያለበለዚያ የነገዋ ኢትዮጵያ ታሰጋለች። አሁንም በትክክል ትልቅ ለውጥ ለማምጣት በህዝቡ ውስጥ የህግ አክባሪነት አስተሳሰብ ከነበረበት ተነስቶ እንዲያንሰራራ መልፋትን ይጠይቃል። በዚህ ላይ በተለይ መንግሥት ግዴታውን መወጣት አለበት። ያለበለዚያ ከህግ ውጪ ለመሆን የጣረ ጎርፍ የትኛውንም አካል ጠራርጎ ከመውሰድ ወደ ኋላ የማይል በመሆኑ ከወዲሁ ጎርፉን ለመከላከል ይታሰብ። ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2013