ሶሎሞን በየነ
የዛሬን አያድርገውና ድሮ ድሮ እንዲህ እየተባለ ይዜም እንደነበር አውቃለሁ።
ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ
አገርም እንደሰው ይናፈቃል ወይ?
ተብሎ የተዘፈነላት አዱ ገነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ በመጣው የኑሮ ውድነት ወዟ ተመጧል። ነዋሪዎቿ በልቶ ለማደር፣ የቤት ኪራይ ከፍሎ ለመኖር በሰላም ወጥቶና ሰርቶ ወደ ቤት ለመግባት አዳጋች የሆነባት ከተማ እየሆነች ነው። እንዲህ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አዲስ አበባ እንደስሟ ሳይሆን አዳዲስ መከራ የሚታጨድባት ከተማ ሆናለች ቢባል ማጋነን አይሆንብኝም።
አሁን ላይ በእናትና አባቶቻቸው የቤት ኪራይ ገንዘብ የሚንፈላሰሱ፣በርካቶች አይታጡም። ከነዚህ ባሻገር ደግሞ ሙሰኛ ባለሥልጣናት የሆኑና በህዝብ እንባ የከብሩ የስግብግብ ነጋዴ ልጆች የበረከቱ ናቸው። እኔ እያልኩት ያለው ከእንዲህ አይነቱ ቤተሰብ ስለተገኙና ቦሌ፣ ካሳንችስ፣ ጀሞ፣ ጉርድ ሾላ፣ ፒያሳ፣ መርካቶ ላይ በዓይናቸው ያዩትን ለብሰው፣ ያማራቸውን በልተው ሽርብትን ስለሚሉት የሸገር ቀበጤዎች አይደለም።
ይልቁንስ እንደሰው አርሰው የላባቸውን ምርት ያላገኙ፣ ተምረው ሥራ ያጡ፣ ጫጭረው የሚያድሩበት መሬት የሌላቸው፣ የኔ ቢጤዎች፣ ሰርቼ ያልፍልኛል ሲሉ ከአራቱም መአዘን በመዲናዋ የከተሙ ሰዎች ኑሮው የምርጊት ያህል የከበዳቸው መሆኑን ነው።
በተለይ በያዝነው ወር ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በመዲናዋ ብሎም በመላ አገሪቱ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት የሚያውቅ ያውቀዋል። ምንአልባትም ከመርካቶ ሱቅ፣ አልያም ከአሜሪካ ዘመድ ያለው ካልሆነ በቀር በመንግሥትና በግል ድርጅት ተቀጥሮ የሚሰራ ሠራተኛ፣ ጡረተኛ፣ ጉልት ቸርቻሪ እናት፣ በላቡ ወዝ የሚያድር የቀን ሠራተኛና በጉልበቱ ደክሞ የሚኖር ወጣት አከራረሙን እንጃ።
‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ የተፈጠረውን የኑሮ ውድነት አሳበው የኅብረተሰቡን ለቅሶ ሰርጋቸው ያደረጉ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች አልታጡም። እነዚህ አካላት በህገወጥ መንገድ ምርትን በመደበቅና በማከማቸት የነዋሪውን ህይወት ከድጡ ወደማጡ አድርገውታል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአገሪቱ በተፈጠረው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ዝርፊያና ውንብድና በመዲናዋ በእጅጉ ተስፋፍቷል።
ይቅርታ አድርጉልኝና በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ኅብረተሰቡን እርስ በእርስ ለማጋጨት የሚተላለፉ ሃሰተኛ መረጃዎች ተበራክተዋል። ይህ እውነታ ሁሉንም የሚያስማማ ሃቅ ቢሆንም በሌላ መልኩ ገለባውን ከምርቱ ከለየን ዳግሞ ከህዝብ የተደበቁ እውነተኛ መረጃዎች የሚተላለፍባቸው አይነተኛ የወሬ ምንጮች ናቸው ቢባል የሚያስማማ ይመስለኛል።
ውድ አንባቢያን ከሰሞኑ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን የሰማሁትንና ያነበብሁትን ላካፍላችሁ ወደድሁ። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ተከትሎ በመዲናዋ ዝርፊያና ውንብድና በእጅጉ ተባብሷል። ጉዳዩም በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተራገበ ነው። ለአብነት ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ተፈጸመ የተባለው ዝርፊያና ውንብድና እረፍት ይነሳል፤ ያሳዝናልም።
እንደ ወሬ ምንጩ ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ በአንድ ሳምንት ስድስት ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። ከነዚህ መሀል ለፍቶ በዕለት ጉርሱ የሚኖር ፣ የባጃጅ ሾፌር እና ቁርጥራጭ ብረታ ብረት እየለቀመ በተለምዶ ‹‹ቁሪያለሽ፣ ሰባራ ዕቃ ያለሽ››እያለ የሚዞር ለፍቶ አዳሪ ይገኝበታል።
ይህን ክፉ ዜና በማህበራዊ ሚዲያ ስሰማ ሰው ሌትና ቀን ሰርቶ በሰላም ወደ ቤቱ ካልገባ እንዴት ይሄንን የኑሮ ውድነት ይቋቋመው ይሆን ስል ራሴን ጠየቅሁ ። መለስኩናም ‹‹እሱ ይወቅው ስል ለፈጣሪ ተውኩት።
በአካባቢው ህጻናት እንደሚጠፉና፣ ጫኝ አውራጆችም ደብዛቸው እንደማይገኝ ሰማሁ። ኅብረተሰቡ ለአካባቢው ፖሊስ እና የሰፈር ጥበቃዎች አቤት ቢልም አጥጋቢ ምላሽ አላገኘም። ፤ ይባስ ብሎ የዛሬ ሳምንት በዕለተ ዓርብ እዛው አካባቢ ላይ አስገራሚ ጉድ ተነገረ።
ምሽት 11:00 ሰዓት ገደማ ቦሌ ወረዳ 12 በተለምዶ 93 ማዞሪያ በሚባል አካባቢ አንድ ሰው በመኪና ህጻን ልጅ ነጥቆ አመለጠ ተባለ። ቦታው ላይ ፖሊስ ቢደርስም ሰውዬውን መያዝ አልቻለም።
እንዲሁም ከሰሞኑ ሌቦች ከአንድ ጎረቤታችን ቤት በውሃ መፋሰሻ ቱቦ ሾልከው ገቡ። ሀሳባቸው ዝርፊያ ለመፈጸም ነው። ባለቤቶቹ ሰምተው ኖሮ በእሪታ ‹‹ድረሱልን አሉ›› የሰፈሩ ሰው ወጥቶ ህይወታቸውና ንብረታቸው አዳነ ። ለዚህ እውነት ደግሞ እኔ ምስክር ነኝ።
በጥቅሉ በከተማይቱ በሚገኙ አስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች ዝርፊያና ስርቆቱ ከመቼውም በላይ ተጧጡፏል። ህጻናት ከትምህርት ቤት ወደ ቤት በነጻነት ለመንቀሳቀስ፣ህብረተሰቡ ጠዋት ከቤቱ በሰላም ወጥቶ ማታ በቸር ለመግባት ተቸግሯል ። ለዚህም በማህበራዊ ሚዲያው የምናያቸው መረጃዎች ምስክር ናቸው።
ሁሌም እንደምንለው እኛ ኢትዮጵያውያን መደጋገፍና መረዳዳት ከጥንት አያቶቻችን የወረስነው መልካም ባህላችን ነው። የሚታየውን የኑሮ ውድነት ተደጋግፎ ለማለፍ አቅመ ደካሞችን በአቅማቸው የሚደጉሙና የሥራ እድል የሚፈጥሩ የህብረተሰብ ክፍል እንዳሉ ይታወቃል። ከዚህ በተቃራኒም ደፋ ቀና ሲል የዋለውን ምስኪን ጠብቆ ከመዝረፍ ባለፈ ክቡሩን የሰው ልጅ ህይወት በመቅጠፍ የሚተዳደሩ አያሌ ሰው በላዎችን ሳስብ እኔም እንደ ገጣሚ አያልሰው መኮንን ‹‹ሴጣን ሰው፣ እግዜር ሰው›› እንድል አስገድዶኛል።
ህዝቡን ነፃ ያወጣ … ጋንዲን ተመስሎ፥
ወይ እንደ ማንዴላ … አፓርታይድን ታግሎ፥
እንደ ማርቲን ሉተር … ዘረኝነትን ገድሎ፥
ለሰው ልጅ ነፃነት … ታግሎ የወደቀው፥
አምላክ እኮ አይደለም … ይህው የሰው ልጅ ነው።
መልከዓ ሞት ሒትለር … ሕዝብ ያስጨፈጨፈው፥
ፋሺስት መሶሎኒ … አብሮ የዘፈነው፥
የሰው ዘር ለማጥፋት … ፈንጂ ያዘነበው፥
ሳጥናኤል አይደለም … ይኸው የሰው ልጅ ነው።
እኔም ሰው ነኝ ልበል … ሰው ማለት እንዲህ ነው፥
እግዜርም ሰይጣንም … መሆን ያልተሳነው።
ሰው እግዜር … ሰይጣን ሰው፥
ሰው ሰይጣን … እግዜር ሰው።
የተላበሰ … ክፋት ደግነት፥
የተጀቦነ … ንፍገት ቸርነት።
በተቃርኖ ሕግ … የተዋቀረው፥
ሰው ሰይጣን … ሰይጣን ሰው፥
ሰው እግዜር … እግዜር ሰው።
የፌዴራል ፖሊስ፣ ልዩ ኃይል፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ደንብ አስከባሪ ወዘተ የመሳሰሉ የሰላም አስከባሪ አካላት በሚርመሰመሱባት ከተማ ለዜጎች በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት አስጊ መሆኑ ጥያቄ ያጭርብኛል። ከበላይ አካል ትዕዛዝ አልተሰጣቸው ይሆን እንዴ? ስልም መልስ የለሽ ጥያቄ በአዕምሮዬ ያቃጭላል።
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ህልፈተ ህይወትን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ሁከት እኩይ አላማ ያነገቡ ሰዎች በተለይ በኦሮሚያ ክልል በንጽኋን ዜጎች ላይ ግፍና በደል ሲፈጽሙ አይተናል።
እንደ ሻሸመኔ የመሳሰሉ ውብ ከተሞች የዶጋ አመድ ሲሆኑ አንዳንድ የጸጥታ አካላት ከበላይ ትዕዛዝ አልተሰጠንም በሚል የቆሙለትን ዓላማና የተረከቡትን አገራዊ ኃላፊነት ወደ ጎን ብለዋል። የአለቆችን ይሁንታ አላገኘንም በሚል ሰበብ እጃቸውን አጣጥፈው መቀመጣቸውም ለስንቱ ህይወት መጥፋትና ለበርካቶች ንብረት መውደም ምክንያት መሆኑ የቅርብ ቀን ትዝታችን ነው። በቀላሉ የማንዘነጋውና አንገት ያስደፋን ጠባሳችንም ነው።
በከተማይቱ ለተስፋፋው ውንብድናና ዝርፊያ ስነምግባር የጎደላቸው አንዳንድ ፖሊሶች ከወንጀለኞች ተመሳጥረው የሚፈጽሙት የጥቅም ተካፋይነት መሆኑ ይነገራል። ወንጀለኞች ተይዘው በህግ ፊት እንዳይቀርቡም መረጃዎችን የሚያስጠፉ መኖራቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው።
የመርካቶና የፒያሳ ጩልሌን አድነው ሊይዙ ቀርቶ አስፓልት አቋርጠው ለማለፍ ግራ የሚጋቡ አንዳንድ ፖሊሶች ባሉበት ከተማ የህብረተሰቡን በሰላም ወጥቶ የመግባት ዋስትና ማረጋገጥ አይቻልም። በእኔ ዕምነት የከተማዋን ፖሊሶች ከከተማዋ የእድገት ደረጃ ጋር ለማመጣጠን በንቃተ ህሊናም ሆነ በአካል ማብቃት ግድ ይል ይመስለኛል።
ወንጀል የሚፈጸምበት መንገድ እየረቀቀ መምጣቱን ተከትሎ መንግሥት የፖሊስ አባላት ወንጀልን ቀድመው ለመከላከልና የረቀቁ ድርጊቶችን ለመመርመር የሚያስችል የአቅም ደረጃ ላይ እንዲደርሱ የሚመለከተው አካል የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። የፖሊስ አካላት በክህሎትና በእውቀት በልጽገው በኢኮኖሚ የተሻሉ እንዲሆኑ ማድረግም ይጠበቅበታል።
አንባቢዎቼ ከኔ ጋር ናችሁ? አላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።እስቲ አንድ ትውስ ያለኝን ጉዳይ ላካፍላችሁ። አንድ የዘመኑ ልጅ የታሪክ መጽሐፉን ከሚያነቡት ቀና ብሎ አባዬ ‹‹ገና ጦርነቱን አልጀመርንም ያለው ማን ነው?›› ሲል ይጠይቃል አባትም ‹‹በጫጉላ ቤት ያሉ ሙሽሮች ሳይሆኑ አይቀሩም›› ሲል ይመልሳል።
አባትዬው ለካ ትዳሩ ያስመረረው አባወራ ኖሯል፤ እንዳለ መታደል ሆኖ በአፍሪካ ምድር ምርጫ የችግር መፍቻ መሆኑ ቀርቶ የችግር መፍለቂያ መሆኑ ተለምዷል። በአገራችን የሚካሄደው መጪው አገራዊ ምርጫም ምን ችግር ይዞብን ይመጣ ይሆን የሚለው ስጋት አይሏል። በአብዛኛው በህብረተሰብ ዘንድ ይህ ጭንቀት ቢመላለስ አያስገርምም፤ ለምን ካሉ ደግሞ ባለፉት 27 ዓመታት በተደረጉ ምርጫዎች ይበልጡን የጥቃት ሰለባ የሆነው የመዲናዋ ነዋሪ ነውና።
መቼም ለሁሉም ነገር መንግሥትን ብቻ መጠበቅ አይሁንብኝና የተፈጠረውን የገበያ አለመረጋጋት ሰበብ አድርገው ምርትን በህገ ወጥ መንገድ በማከማቸት የኑሮ ውድነቱን የሚያቀጣጥሉ ነጋዴዎችን መንግሥት አደብ ሊያስገዛቸው ይገባል። የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዶ ለኑሮ ውድነቱ እልባት ይሰጣል ብሎ ለሚያምነው ህብረተሰብም ተስፋ ሊያስጨብጠው ግድ ነው።
ከሰሞኑ አንድ የመንግሥት ባለስልጣን ነዳጅ ላይ የተደረገውን የዋጋ ጭማሪ አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጥያቄ ቀርቦላቸው፤ ባለስልጣኑ ቢያንስ እንደፖለቲከኛ አሁን ላይ መንግሥት ካለበት የተለያዩ ጫና አኳያ የነዳጅ ታሪፍ ቢጨምርም በቅርቡ የማስተካከል ሥራ ተሰርቶ ወደነበረበት ዋጋ ይመለሳል በሚል ህብረተሰቡን ማረጋጋት ይጠበቅባቸው ነበር። ባለስልጣኑ ግን ምን አሉ መሰላችሁ ? ህዝቡ ጭማሪውን ያውቀዋል እኮ! ብለው እርፍ ።
እናንተዬ ! ህብረተሰቡማ አይደለም በመንግሥት ድጎማ ከውጭ የሚገባውን ምርት ይቅርና በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ዋጋ መጨመራቸውን የጋለ ብረት ምጣድ ላይ እንደተቀመጠ ሆኖ ተቃጥሎ ያውቀዋል። የህብረተሰቡ ስሜት አይደለም ሦስቴ አንዴ በልቶ ለማደር አዳግቶናል የሚል ነው።
በመሆኑም መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ ወስዶ ገበያውን ያረጋጋልን እያለ ነው። አዎ! መንግሥት በአስቸኳይ ለጉዳዩ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ የዋጋ ንረቱንና የኑሮ ውድነቱን የማረጋጋት ሥራ ይጠበቅበታል።
ገዢው ፓርቲ በህዝብ ዘንድ ተመርጦ የቀጣይ የአገሪቱ መሪ ለመሆን የሚያበቃውን የህዝብ ድምጽ በመጪው ምርጫ ለማግኘት ‹‹በምረጡኝ›› ዘመቻው ያስተዋወቀውን አምፖል ከወዲሁ በተቸገሩና በልተው ማደር በተሳናቸው ጎዳናዎች ሊያበራ ይገባል። የህብረተሰቡን በሰላም ወጥቶ የመግባት ደህንነቱንም ሊያረጋግጥ ግድ ይለዋል።
አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በልቶ ማደር የተሳነውን ወጣት በጋለ ስሜቱ ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ ይልቅ ወደ ግጭትና አመጽ እንዳይጓዝ ሊያደርጉ ይገባል። መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወደዳድረው መንግሥት መሆን የሚችሉት ሀገር ስትኖር ነውና በሰላማዊ መንገድ የህብረተሰቡን ሃሳብ ሽጠው በማትረፍም የኑሮና ሰላም ማጣት ችግሩን መፍታት ይጠበቅባቸዋል ስል አምናለሁ።አበቃሁ!
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2013