መልካምስራ አፈወርቅ
‹‹ድሮ ድሮ ! ›› ብዬ ነገሬን አልጀምርም።የዛሬን አያድርገውና እያልኩም ጉዳዩን ማራቅ አልሻም።ላነሳው የፈለጉት እውነት አሁን እየሆነ ያለውን ሀቅ ነውና የታዘብኩትን እናገራለሁ።መናገሬ ለውጥ ካመጣ አሰዬው ነው።ካላመጣም አይገርመኝም።አዎ ! መናገሬን እቀጥላለሁ።ደሞ ለመናገር፡፡
‹‹ሁሉንም ቢያወሩት ሆድ ባዶ ይቀራል›› አሉ አበው።ወዳጆቼ መናገርን የመሰለ እፎይታ ግን የለም።የሚጎረብጥ፣ የሚያስጨንቅ የሚያናድደውን ሁሉ ዝርግፍ አድርጎ እፎይ … ማለት፡፡
ባዶ ቤት በክረምት፣
አንቺ የሌለሽበት፡፡
ባዶ ቤት ለብቻ፣
ባዶ ቤት ለብቻ ፡፡
ምነዋ! ይህ ድንቅ ዝማሬ በአይምሮዬ አቃጨለሳ? አንዳንዴ አንዳች ጉዳይ ባያችሁና በሰማችሁ ጊዜ ሁኔታውን የሚያጠናክር ነጥብ ትውስ ብሏችሁ ያውቃል ? እኔ ግን በዚህ አይነቱ አጋጣሚ በሀሳቤ ብቅ ጥልቅ የሚል ቅጭልታ አላጣም።ልክ እንደ ባዶ ቤት በክረምት አይነት ማጠናከሪያ ማገር ።
ወዳጆቼ! የተነሳሁበትን ጉዳይ አልዘነጋሁም። ላወሳው የፈለጉት እውነት የብዙዎች ትኩሳት እንደሚሆን አውቃለሁና ሀሳቤ ይቀጥላል።እናንተም የባዶ ቤቷን በክረምት መነሻ ይዛችሁ ተከተሉኝ።ባዶ ቤት ለብቻ… ባዶ ቤት በክረምት፡፡
በነገራችን ላይ አንዳንድ ሰዎች ‹‹አይ ዘመን ! እያሉ የሚያማርሩት ልማድ ይገርማኛል።እንዲሀ ባዮቹ የቆሙበትን ጊዜ እየተራገሙ እሱን ተከትሎ የመጣውን አጋጣሚ ማጣመር ልማዳቸው ነው።እኔ ግን ይህ ከጊዜና ዘመን ጋር ተያይዞ የሚሳበበው ጉዳይ መቼም ቢሆን ተመችቶኝ አያውቅም፡፡
እንዲህ አይነቶቹ ሰበበኞች የሚታየውን እውነት ሸፋፍነው የአንዳንዶችን ጉድ በዘመን ያላክካሉ።እውነታውን በጆሮ ዳባ ከልለውም ዶሮ ማታን ይጫወታሉ።እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ግን በሁኔታዎች ላይ ሊወቀሱ የሚገባቸው አጥፊዎቹ እንጂ ዘመኑ አልነበረም።እስቲ ዘመኑ ምን አጠፋ? ምንም።ዑደቱን አቋርጦ አያውቅም፤ ያው ይመሻል፤ይነጋል፡፡
ወዳጆቼ! ዘመንና ዘመነኞችን ካነሳን አይቀር አጋጣሚዎችን ተጠቅመው አይን ያወጣ ተግባር ስለሚፈጽሙ ስግብግቦች ማውሳት ግድ ይለናል።መቼም ስልጣን ይሉት እርካብ መልከ ብዙ ነው።በቦታው ፊጥ ያሉ አንዳንዶች አጋጣሚውን ተጠቅመው የማይታሰብ ድርጊት ይፈጽሙበታል።እንዲህ በሆነ ጊዜ ጉዳዩ ከግርምት አልፎ ብዙሃንን ከችግር ይጥላል።ለጥቂቶች ደምቃ የወጣች የምትመስለው ጸሀይ የበርካቶችን ዓለም ያጨለመች ያህል ድቅድቅ ትሆናለች፡፡
ስልጣንና ለቦታው ያልተገቡት ሲገናኙ የበርካቶች ዕንባ ሳይታበስ የጥቂቶች ከርስ ይሞላል።እንዲህ አይነት ስግብግቦች በበረከቱ ጊዜም የድሆች መቀነት ይራቆታል፣ የምስኪኖች ጓዳ ይበዘበዛል፣ ከምንም በላይ አገር መለመላ እርቃኗን ትቀራለች።ለልጇቿ የምታወርሰው ሳታጣ ሀብት ንብረቷ ይነጠቃል።ወርቅና አልማዝ ላይ ተቀምጣም እጆቿን ለዕዳና ብድር ትዘረጋለች፡፡
አዎ ስልጣንን በወጉ ካልያዙትና በአግባቡ ካልመሩት ውጤቱ ያልታሰበ ይሆናል፡፡‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› ብሂልን ለመተግበር የሚሮጡ ጥቅም ፈላጊዎችም ያሻቸውን ለመፈጸም አጋጣሚው ያመቻቸዋል፡፡
አሁን ላይ እየሰማናቸው ያሉ አንዳንድ እውነታዎችም ስልጣንን አለአግባብ ከመጠቀም ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ታሪኮች ናቸው፡፡‹‹ጉድና ጅራት ወደኋላ ነው›› እንዲሉ ሆነና እኛም ጉድ የተባለውን ጉድ እየሰማን ዛሬም ‹‹ጉድ ጉድ ማለታችንን ቀጥለናል።ለዚህማ! ማን ብሎን።እናንተ ግን የባዶ ቤት ለብቻ ጉዳይን እንዳትዘነጉብኝ ፡፡
ወዳጆቼ! አገር ስትለማ፣ ከተማ ሲዋብ አካባቢ ሲለወጥ ያስደስታል።በእኔ ግምትም ማንም ሰው ይህ አይነቱን ለውጥ ከራሱ ዕድገትና ከሀገር ስልጣኔ ጋር የሚያያዘው ይመስለኛል፡፡
እንዲህ የመሰለውን ፈጣን ሂደት በተመለከትን ጊዜም አብዛኞቻችን እኛነታችንን ከሌሎች አገራት ጋር አወዳድረን ሚዛናችንን እንለካለን፣ የዛሬውን ጅማሬ ከወደፊቱ በጎነት ጋር ደምረንም የነገዋን ታላቅ አገር በምናብ እንስላለን።እንዲህ ማድረጋችን አንድም ለሀገራችን ሌላም ለራሳችን ብለን ነው።
ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ከተሞች የምናስተውለው ዕድገት በእጅጉ ያስገርማል።በተለይ ደግሞ በአፍሪካዋ መዲና በአዲስ አበባችን ያለው ለውጥ እንዲህ ነው ብሎ ለመግለጽ ይቸግራል፡፡
ዛሬ አዲስ አበባ የፎቆች ጫካ እስክትባል በህንጻዎች መጠለቅጠቅ ጀምራለች፤ ትናንት ምልክት ያደረግናቸው ቦታዎች ከጊዚያት በኋላ ታሪካቸው አይኖርም።ከወራት በፊት ሜዳና ሰንሰል እንደነበር የምናውቀው ስፍራ የታላላቅ ህንጻዎች መናኸሪያ ሆኖ ልናገኘው እንችላለን።ይህ አጋጣሚ ታሪካዊ ቅርሶችን ጭምር እያፈረሰ በሌሎች ሲተካ አስተውለናል፡፡
ለአዳዲስ ለውጦች ሲባል በከተሞች የሚደረገው ሂደት እኩል ስሜት አይኖረውም፤ ተጠቃሚውን ሲያስደስት ተጎጂውን ያስከፋል።ለደግ ዓላማ ከሆነ ግን አብዛኞቻችን ይህን ታላቅ ዕድገት በበጎነት እንቀበላለን። እኛም ብንሆን እኮ ባለሀብቶቻችን ቢበዙልን ደስ ይለናል። ባለሙያዎች ቢበረክቱ፣ ስራ አጦችም እንጀራ ቢበሉ አንጠላም።
እንዲህ ማሰባችን ደግሞ ሸጋ የሚባል ነው። በጎ እሳቤ በጎ ነውና እሰዬው ማለቱ አይከፋም። መቼም ቢሆን ግን የማንተወውን አንድ ሀቅ ማንሳቱ ግድ ይላል። ግዙፎችን ህንጻዎች ለማቆም ብዙዎች ለዓመታት ከቆዩበት አካባቢ ተነስተውና ተፈናቅለው ይሆናል። ከእነዚህ ወገኖች አብዛኞቹ የኖሩበትን ማንነት ከአዲስ አካባቢ ለማላመድ ሁኔታዎች ቀላል አልሆነላቸውም፡፡
በርካቶች ለዓመታት የኖሩበትን ይዞታ ‹‹ይፈ ለጋል›› በተባሉ ጊዜ እንዲለቁ ተገደዋል።የተሰጣቸው ካሳና የኑሮ መልካቸው አልጣመር ሲላቸውም በችግር ማቀዋል።ቀሪ ህይወታቸውንም በሀዘንና ትካዜ ሲገፉ ታይተዋል፡፡
ለአንዳንዶቹ የከተማችን የፎቅ ጫካዎች ግንባታ ሲባል በርካቶች ጉቦና ምልጃን ባህል አድርገውት ኖረዋል። በስፍራው የሚገኙና ይመለከታቸዋል የሚባሉ ኃላፊ ነን ባዮችም በ‹‹ቢዝነስ ሰራን›› ቋንቋቸው በህዝቡ ትከሻ እንደመዥገር ተጣብቀው ሲመጡት ቆይተዋል።
ይህ ብቻ አይደለም፣ ህጋዊ ባልሆነ ሰነድና የተጭበረበረ ውል ጉዳዩን አወሳስበው ለጥያቄ እንዳይመች ሲያደርጉም ነበር።እንዲህ አይነቱ አይን ያወጣ አሰራር በርካቶችን የደም ዕንባ ሲያስለቅስ ቆይቷል ።
ይህ ተንኮልና ደባ ሲፈጸም ደግሞ ማንም ‹‹ያገባኛል፣ ይመለከተኛል›› ባይ ቢመጣ ጥግ እንዲይዝ የሚያደርግ ሲስተም መዘርጋቱ ግድ ነበር።ሲስተሙ በሲስተመኞቹ ኔትወርክ የተጠላለፈ ጥብቅ ሽቦ አለው።ይህ ሽቦ ሚስጥርን ጥቅምንና ተላላኪነትን በአንድ ያጣመረ ነው።ጥምረቱ ሁሉም እንደ ድርሻው ከጥቅሙ ተካፋይ እንዲሆን ያስችላል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ሌላው ወገን በዚህ ምክንያት ቢጎዳ፣ ቢንከራተት፣ ቢያለቅስና ቢሞት እነአጅሬ ደንታ የላቸውም። አንዱን ፋይል እንዳይሆን ዘግተው የሚቀጥለውን ጮማ ቢዝነስ ለመቁረጥ ቢላቸውን ይስላሉ፡፡
ወዳጆቼ! እያወራን ያለው ስለግዙፎቹ የከተማችን ህንጻዎች ነው።እነዚህ መልከ መልካም መለሎዎች ድንገት የበቀሉ ይመስል ለአካባቢዎች ውበት ሆነው አድናቆትን ሲያተርፉ ቆይተዋል።ለከተማዋ ዕድገትና ድምቀትም አንድ ርምጃን አክለዋል፡፡
ህንጻዎቹ ካላቸው ድንቅ ቁመና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እንደሰለቀጡ ማወቅ ቀላል ነው።የሚታይባቸው ጥበብና የቦታቸው ዓይን መሆንም እያነሳነው ያለውን እውነት ያጠናክራል።ምንአልባትም ከያኔው ‹‹ ቁመትሽ ሎጋ ነው ሰንደቅ ያሰቅላል›› እንዳላት መለሎ ሴት አይነት ልናደንቀናቸው ከጅሎንም ይሆናል፡፡
ድንቄም ! አድናቆት አለች ሴትዬዋ።ጉድና ጅራቱ ከተደበቀበት እሰኪወጣ በርካታው ምራቁን ቢውጥ፣ ሽቅብ አንጋጦ አጀብ ቢል አይገርምም፤ የባለሀብቱን ጥንካሬና ብርታት እያጋነነም መልካም ስም ቢቸረው አያስደንቅም።ይህ ልማድ ነገሩ ሳይገባን ከዳር ሆነን ለምናዳንቅ የሰማነውን ለምናጋንን ሁሉ ብርቃችን አይደለም፡፡
እስከዛሬ እነዚህ ባለሀብት ተብዬዎች የሚነገርላቸው ገብስ ገብሱ ብቻ ነበር። ጉድና ድብቅ ማንነታቸው ጊዜው ደርሶ እስኪጋለጥም ያልተገባውን ክብርና ዝና ተጎናጽፈው ቆይተዋል፡፡
ወዳጆቼ ! አሁንም የባዶ ቤት ለብቻን ጉዳይ እንዳትረሱብኝ። አዎ! ቤት ያለሰው ሕይወት የለውም። ቤት ያ እሴቱ ትርጉም የለሽ ነው።ሁሌም ቢሆን ሰው አልባ ማጀት በረከቱን ለአይጦች ከማሳለፍ ሌላ ምርጫ ላይኖረው ይችላል፡፡
ይህን ጉዳይ ሳነሳ ደራሲው ‹‹ኗሪ አልባ ጎጆዎች›› ሲል የከተበው ቁም ነገር ትውስ ብሎኛል፤ እውነት ነው፣ ህንጻ አምሮ ቢገነባ፣ አጥርና ግንቡ ቢማርክ፣ ከአላፊ አግዳሚው አድናቆትና ዝና ቢቸረው ያለሰው ትንፋሽ ምንም ማለት ነው፡፡
ባለቤት የለሽ ቤት፣ ቤተሰብ አልቦ እልፍኝ ትርጉም አለው እንዴ? በእኔ ዕምነት በር ተንኳኩቶ ማነህ? ባይ ካልከፈተ ፈጽሞ ቤት ነው ሊባል አይችልም።አድናቆት ተችሮት የእከሌ፣ የእከሊት ቤት ካልተባለም እሱ ቤት የሚለውን ስያሜ አያሟለም፡፡
ወዳጆቼ ! እንዲህ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ባዶ ቤት ለብቻ፣ ባዶ ቤት በክረምትን ማንጎራጎሩ አይከፋም።እስቲ ባዶ ቤትን ያለሰው ለዛውም በክረምት አስቡት።በእጅጉ ይከብዳል። ቁመተ ረጅም፣ ሆደ ሰፊ፣ ሚሊዮን ብሮችን የሰለቀጠ፣ ይዞታው የበረከተን ግዙፍ ህንጻ ያለባለቤቱ ማሰብ ለማንም ቢሆን ይከብዳል፡፡
ዘንድሮ እየተሰማ ያለው ግን እንዲህ መሰል ዘመናይ ህንጻዎች ባለቤት አልባ የመሆናቸው እውነት ነው።‹‹ ወቸጉድ! ›› አሉ ሴትዬዋ።አይፈረድባቸውም። እስከዛሬ እኛ የምናውቀው ባለቤት አልባ ውሾች መኖራቸውን ነበር፡፡
እነዚህ ውሾች ባሻቸው አዳሪና ተልከስካሾች ናቸው።ከየት ይምጡ የት ይድረሱ አይታወቅም።በድንገት የሚያገኛቸው ቢኖር በክፉ ዓይን ያያቸዋል፤ የእኔ የሚል ባለቤት ኖሯቸው አያውቅም።በቤት ስርአት ያደጉ አይደሉምና፤ በየስፍራው ሲሮጡ ይታያሉ፤ እነዚህ ባለቤት አልባ ውሾች ቤት እንዳገደጉት ዘመዶቻቸው ክብር ይሉት የላቸውም፡፡
ውሾቹ ለአንገታቸው ሰንሰለት ለእግራቸው ገደብን አያውቁም።ሲንከራተቱ ውለው ሲንከራተቱ ያድራሉ።ብዘዎቹ ደግሞ የመኪና እራት ከመሆን አያልፉም።ተገጭተው በጎዳና በወደቁ ጊዜ ማንም ስለነሱ ግድ አይለውም፤ ባለቤት አልባ ናቸውና መጨረሻቸውን የሚያውቅ፣ ጠፉብን ብሎ የሚጨነቅ አይገኝም፡፡
ባለቤት አልባዎቹ ውሾች እንደሌሎቹ ከአሳዳጊዎቻቸው የሚቸር ስም የላቸውም።ማንም በወል ስማቸው ‹‹ውሾች›› እያለ ይጠራቸዋል።እነዚህ ውሾች የዕለት ጉርሳቸውን የሚለቅሙት ፈርተውና ተሳቀው ነው፤ በመንገዳቸው አንዳንድ ዋልጌ የመንደር ልጆች ካገኟዋቸው በድንጋይ እያባረሩ መድረሻ ያሳጧቸዋል፡፡
ወደቀደመው ነገሬ ልመለስ፣ ወደ ባለቤት አልባ ህንጻዎቹ ጉዳይ።በእኔ እሳቤ እነዚህ ባለቤት የለሽ ህንጻዎች እንደ ባለቤት አልባዎቹ ውሾች መሆናቸው ላይቀር ነው።በየቦታው በርክተው እንደመገኘታቸው፣ የእኔ ነው ባይ ባለቤትን አላገኙም።
ህንጻዎቹ ገዥ ቦታ ላይ እንደ መቆማቸው እሰከዛሬ ዓይነገብ ሆነው ቆይተዋል።በ‹‹ስማ በለው›› በነበረው ግምትም ባለቤትነታቸው የታዋቂ ሰዎች፣ የድርጅቶችና አለፍ ሲልም የመንግስት ናቸው ሲባል ነበር፡፡
ጉዳዩ ሁሉ እንደዛሬ በነበር ሳይቋጭ በፊት በህንጻዎቹ የኪራይ ገቢ እነ እንቶኔና እንቶኒት ከበረከቱ ሲዝቁ ኖረዋል።ስውር ተጠቃሚዎቹ ማንነታቸው ሳይታወቅ፣ ስማቸውን በህጋዊ የካርታ ይዞታ ሳያስመዘግቡና እኛ ነን ብለው ሳያውጁ ለዓመታት የብር ጆንያ ሲሰፉና የባንኮችን ካዝና ሲያጨናንቁ ኖረዋል፡፡
ወዳጆቼ! ጉድ የሚያስብለው እንዲህ መደረጉ ብቻ አይደለም።ትናንት የብር ዛፍ የሆኑላቸው ድንቅዬ ህንጻዎች፣ ዛሬ እንቀድሞው ሰፊ ቋት አልሞሉም ።እንደ ወተት ላማቸው ሲያልቡት የቆዩት የገንዘብ በረከት ከምንጩ ሊደርቅ ጊዜው ደርሷልና ቤቶቹ ያለባለቤት ሊጠሩ ግድ ብሏል።
‹‹አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ›› እንዲሉ ዘራፊና አዘራፊ ተባብረው በሰሩት ሸፍጥ የእጃቸውን ሊያገኙ ግድ ብሏል።ወትሮ ያዙባቸው የነበሩ ሀብቶቻቸው ዛሬ ቢጠሯቸው አይሰሙም።ኢትዮጵያን ታህል ታላቅ ሀገር፣ ህዝብን ያህል ክቡርነት አዋርደዋልና ዛሬ በተራቸው ሊዋረዱ ጊዜው አሁን ሆኗል።
አሁንም ከተማችን በታላላቅ ህንጻዎች መዋቧን ትቀጥላለች። ለውበቷ ማገር የሆኗት የነስም አይጠሬ መሰል ህንጻዎችም ስም አልባነታቸውን እንደያዙ ከሌሎች ጋር ይደመራሉ። ለህዝብ ጥቅም የሚውሉበት ጊዜም ቅርብ ይሆናል፡፡
እኔ ግን ደግሜ እንዲህ እላለሁ።እነ እንቶኔ ሆይ! አሁን የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሄርን ለእግዜር ልትሰጡ ግድ ይላችኋል።እስካሁን የዚህን ድሀ ህዝብ ዓይን ሸፍናችሁ ለከርሳችሁ የሰለቀጣችሁትን በህግ አግባብ የምትተፉበት ጊዜም በአይናችሁ ታዩታላችሁ፡፡
አዎ! እውነትና ንጋት እያደር መንጋቱ አይቀሬ ነው።ትናንት የደም ዕንባ ያስለቀሳችሁት ህዝብ የእናንትን ስም የለሽ ንብረት በስሙ የሚያዞርበት ጊዜ ቀርቧል። ቀድሞ የሙቀት ጊዚያችሁን ባላፈራችሁት ቤት ተከልላችሁ አሳልፋችኋል፤ አሁን ደግሞ የቆፈኑን ስሜት ለይታችሁ እወቁት።እግረ መንገዳችሁን ባዶ ቤት ለብቻ፣ ባዶቤት… በክረምትን ማንጎራጎር ተራችሁ እንደሆነ ተረዱ።
አዲስ ዘመን የካቲተር 04/2013