መርድ ክፍሉ
በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ‹‹ወጣትነት በፍልስፍና ቅኝት›› በሚል ፅሁፍ ላይ እንደተቀመጠው፤ የወደፊቱ ዓለምና የሰው ልጅ ዕጣ ፋንታ ያለው በአዋቂዎች እጅ ሳይሆን ባብዛኛው በወጣቶች አእምሮ ውስጥ ነው። ዛሬ ያልተኮተኮተና ያልታረመ ማሳ ነገ በአረምና በአራሙቻ ይወረራል። ከዚህ የሚጠበቀውን ፍሬ ማምረት አይቻልም። የወጣቶች አእምሮም በዚሁ መልክ መታየት የሚችል ነው።
አዕምሮአቸው መልካምነት የሚዘራበት፤ ዕውቀትና ጥበብ የሚተከልበት፤ ሰላምና ፍቅር የሚታነፁበት መሆን አለበት። በእውን እየሆነ ያለው ግን ይኸ አይደለም። ማንኛውም ሐሳብና እምነት ጠቃሚነቱና ጎጂነቱ ሳይለይ ወደ ወጣቱ አእምሮ ይወረወራል። አይደለም ሌላ እናትና አባት ራሳቸው በልጆቻቸው ፊት ለሚያስቡትና ለሚናገሩት፤ ለሚሰሩትና ለሚፈጥሩት ነገር አስፈላጊውን ጥንቃቄ አያደርጉም።
ዓለም የወጣቶቿን አእምሮ ከቆሻሻ ነገሮች መጠበቅ አልቻለችም። ይልቁንም ይበልጥ የሚያቆሽሹና የሚያበላሹ ነገሮችን አምርታ ያለምንም የኃላፊነት ስሜት ለገበያ ታቀርባለች። ዛሬ ወጣቱንም ሆነ ዓለምን በሚፈለገው መንገድ ከጥፋት የሚታደግ ኃይል ወይም ሥርዓት የለም።
ወጣትነት በራሱ ማንነት ነው። ማንነቱ የሶስት ጊዜያት ክንውኖች ጠቅላላ ድምር ነው። ውጤቱ ቀደም ሲል የሆነው፤ አሁን በመሆን ያለውና ለወደፊት መሆን የሚፈልገው ነው። ስለዚህ የወጣትነት ማንነት በዛሬ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በትናንት እና በነገ ውስጥ ይገኛል። ይህ ማለት ወጣትነት የሚለማ፤ የሚገነባ ወይም የሚታነፅ ማንነት ነው። ያለቀለት ሳይሆን በመሆን ሂደት ውስጥ ያለ ማንነት ነው።
የሚታነፀው በራሱና በሌሎች ነው። ሌሎች ሲባል ወላጅን ወይም ቤተሰብን፤ ጎረቤትን፤ ሕብረተሰብን፤ መንግሥትን፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትንና የመሳሰሉትን ለማለት ነው። ይህ ማንነት በእውን ያለው በሆነና መሆን በሚፈልገው፤ በያዘውና ማግኘት በሚመኘው መካከል ነው። የመጀመሪያው ከመድረሻው አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ያለ ማንነት ነው።
ሁለተኛው ገና የሚደርስበት ወይም ከርቀት የሚታይ ማንነት ነው። ሽግግሩን ለማሳካት ያለውን አቀበትና ቁልቁለት መውጣትና መውረድ፤ መውደቅና መነሳት የግድ ይላል። ዛሬ የምናስቃኛችሁ በአሜሪካ በተካሄደው ምርጫ በሚንሶታ ግዛት የኦስቲን ከተማ ምክር ቤት አባል ሆኖ ስለተመረጠው ወጣት ኦባላ ኦባላ ነው።
በአገረ አሜሪካ በፈረንጆቹ ህዳር ወር መጨረሻ በተካሄደው ምርጫ የዴሞክራት ፓርቲን ወክለው የተወዳሩት ጆን ባይደን ከፍተኛ ድምፅ አግኝተው በፕሬዚዳንትነት ተመርጠዋል።በተጨማሪም በሁሉም ስቴቶች በሚገኙ ግዛቶችም በተደረጉ ምርጫዎች የከተማ ምክር ቤት አባላት ተመርጠዋል።
በዚህም በሚኒሶታ ግዛት ኦስቲን ከተማ በታሪኳ ጥቁር፣ አፍሪካዊ፣ ኢትዮጵያዊ እንዲሁም ስደተኛ በከተማ ምክር ቤት አባልነት መርጣለች። የ27 አመቱ ኦባላ ኦባላ ትውልዱ ኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል ነው። በስደት ወዳቀናባት አሜሪካ ዜግነቱን ያገኘው ከአንድ አመት በፊት ነበር።
ኦባላ በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት በዩኒቨርሲቲ ካምፓሶች ላይ ያለው የምግብ ደህንነትና የኤሌክትሮኒክስ መፅሃፎችን አቅርቦት በተመለከተ ከፍተኛ ቅስቀሳ ማድረጉ የተነገረ ሲሆን በምርጫውም ተፎካካሪውን በ481 የድምፅ ብልጫ እንዳሸነፈ ተዘግቧል። ስለ ምርጫው፣ በምክር ቤት አባልነቱ ስለሚያከናውናቸው የወደፊት እቅዶች፣ የስደት ጉዞውና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከቢቢሲ አማርኛ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደምንጭነት ተጠቅመናል።
ኦባላ ኦባላ የተወለደው በኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል ውስጥ ነው። ታህሳስ 3 ቀን 1996 ዓ.ም በጋምቤላ ክልል በደረሰው የዘር እልቂት ከ420 በላይ የአኝዋክ ህዝቦች ተገድለዋል። በዚህ እልቂት ኦባላ ዘመዶቹን አጥቷል። የዘር እልቂቱን ለመሸሽ ሲል ለመሰደድ ተገደደ። እሱና ሌሎች ሰዎች ከጋምቤላ ተነስተው ኬንያ ስደተኞች ካምፕ ገቡ። ከዚያ በፊት የነበረው የልጅነት ጊዜው መልካም እንደነበር ያስታውሳል።
ከጋምቤላ ሸሽተው ለሁለት ሳምንት ያህል በእግራችው ተጉዘው የደቡብ ሱዳንን ድንበር ተሻገሩ። ደቡብ ሱዳን የተወሰነ ቀን ከቆዩ በኋላ ከዚያም ወደ ኬንያ አቀኑ። በኬንያ የስደተኞች ካምፕም ውስጥ ለአስር አመት ያህል ቆይቷል። በእአአ 2013 ወደ አሜሪካ አቀና::
አሜሪካ ከመጣ በኋላ በሳውዝ ዳኮታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቀቀ። ከዚያም እናቱ ሚኒሶታ ከተማ ኦስቲን ግዛት መኖር ጀምራ ስለነበር ወደዚያ ሄደ። ነዋሪነቱን በኦስቲን ካደረገ ከሶስት ወራትም በኋላ ከተማው ጥሩ እንደሆነ መረዳቱን ይጠቅሳል። እናም በኦስቲን የሚኖሩ የአኝዋክ ጓደኞቹን በሚያነጋግርበት ወቅት ‹‹የኦስቲንን ከንቲባ ታውቃላችሁ? እንዲሁም እነማን መሪዎቻችን እንደሆኑ ለምሳሌ የፖሊስ ኃላፊው ማን እንደሆነ ታውቃላችሁ›› ብሎ ሲጠይቅ ሁሉም አናውቅም የሚል መልስ ሰጡት። ጓደኞቹ ከንቲባ እንዳለ እንደሚያውቁና ግን አግኝተዋቸው እንደማያውቁ ነገሩት።
የከንቲባውን ፅህፈት ቤት አድራሻ በጉግል ፈልጎ ወደ ቢሮአቸው ሄድ። ከንቲባውንም እንዳያቸው ስሙ ኦባላ ኦባላ እንደሚባል፣ በቅርብ ከሶስት ወራት በፊት ወደ ኦስቲን ሚኒሶታ እንደመጣ፣ ተማሪ እንደሆነ እንዲሁም የኦስቲንን ከተማም ሆነ ነዋሪውን ለማገዝ ማድረግ የሚያስፈልግ ነገር ካለ ፈቃደኛ መሆኑን መናገሩን ያስታውሳል።
በተጨማሪም የኦስቲንን ከተማ ለማገዝ በየትኛውም መንገድ ዝግጁ መሆኑንና ኦስቲንን በጣም እንደሚወዳት ሲነግራቸው ከንቲባውም ማንነቱን በድጋሚ እንደጠየቁት ይናገራል። ከዚያም ያላቸውን ደግሞ ነገራቸው። ከንቲባውም ሳቁና ቢሯቸው መጥቶ በምን መንገድ አስተዋፅኦ ላድርግ? በማህበረሰቡስ ልሳተፍ ያለ የመጀመሪያው ስደተኛ መሆን እንደነገሩት ያመለክታል። ከዚያም በኋላ በከንቲባውና በኦባላ መካከል ያለውም ግንኙነት እየጠነከረ መጣ። ከዚያም ከአመት በኋላ እአአ 2016 የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ውስጥ ሾሙት። በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቦርድም ከእአአ 2016 ጀምሮ አገልግሏል።
በቀጣይ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት የሚፈልገው የመኖሪያ ቤቶችን ችግር ለመፍታት ነው። በኦስቲን በርካታ ቤቶችን፣ አፓርትመንቶችን ለመገንባት ሃሳብ አለው። ስደተኞች ወደ አሜሪካ በሚመጡበት ወቅት ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ቤት መከራየት አይችሉም ። ሁለተኛው ደግሞ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ የህፃናት ማቆያ ማዕከል ማግኘት ችግር አለ።
በኦስቲን ተመጣጣኝ ዋጋ ባይሆንም ማቆያ ባለመኖሩ ብዙዎች ይቸገራሉ። ከዚያም በተጨማሪ ከሁሉ ነገር በላይ በኦስቲን በርካታ የስራ እድልን መፍጠር ያስፈልጋል። ከሁሉ ነገር በላይ የሚፈልገው ጉዳይ በማህበረሰቡ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ነው። እንደ ወጣት መሪም መሳተፍ፤ ድምፁንም ለየት ባለ መንገድ በዚህች ከተማም ሆነ ነዋሪውን ለማገዝ መጠቀም እንደሚፈልግ ያመለክታል።
የወከለው (የተወዳደረበት) አካባቢ 99 በመቶ ነጮች ናቸው። አፍሪካውያንና ሌሎች አናሳ ህዝቦች በጣም ዝቅተኛውን ስፍራ ዜሮ ነጥብ 05 ይሆናሉ። በከተማዋ ሌሎች ክፍሎች ስደተኞች ቢኖሩም እሱ የወከለበትና ያሸነፈበት አካባቢ የነጮች ቦታ ነው። የምረጡኝ ቅስቀሳውን የጀመረው ባለፈው አመት ግንቦት ወር አካባቢ ሲሆን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ጋር ተያይዞ በጣም ፈታኝ ጊዜ እንደነበር ይገልፃል። ምክንያቱም በርካታ ዝግጅቶችን ማዘጋጀት ባለመቻሉ ነው። ሆኖም በመጨረሻ ሁሉ ነገር በሰላም ተጠናቀቀ። የአሜሪካዊ ዜግነቱን ያገኘው ታህሳስ 7 ቀን 2012 ዓ.ም ሲሆን ለመወዳደር የወሰነው በግንቦት ወር ከጥቂት ወራት በፊት ነበር።
ዋነኛ ተቀናቃኙ የነበረችው ሄለን ጃር የምትባልና የ66 አመት ግለሰብ ናት። ግለሰቧ እዛው ኦስቲን ከተማ የተወለደች ናት። ሙሉ ህይወቷንም በዛው ከተማ ኖራለች። በምርጫው ወቅት ከፍተኛ ተፎካካሪ የነበረች ቢሆንም የኦስቲን ህዝብ እሱን ለመምረጥ ወሰነ። በአሜሪካ ምክር ቤት አሸንፋለሁ የሚል ሃሳብም ሆነ ህልሙም አልነበረውም። ነገር ግን በዳዳብ ካምፕ ውስጥ ስደተኛ እያለሁ አንድ ቀን አሜሪካ ሄጄ የተሻለ ህይወት እኖራለሁ፤ እንዲሁም ጥሩ ትምህርትም አገኛለሁ የሚል እንጂ በአሜሪካ አገር ፖለቲከኛ እሆናለሁ ብሎ ህልም እንዳልነበረው ይናገራል።
ምርጫውን በማሸነፉ ከመጠን በላይ ደስታ እንደተሰማው ይናገራል።በ152 አመታት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሚኒሶታ በከተማው ምክር ቤት አባልነት ጥቁር ስትመርጥ እሱ የመጀመሪያው ነው። ከሱ በፊት የተመረጠ ጥቁር አልነበረም። የምረጡኝ ቅስቀሳ በሚያደርግበት ወቅት አሸንፋለሁ ብሎ አላሰበም ነበር። ምክንያቱም የሚወዳደርበትና የወከለው አካባቢ በሙሉ ነጭ ነዋሪዎች ስለሚበዙበት ነው። ነገር ግን ማሸነፉን ሲያውቅ ከመጠን በላይ ደስታ እንደተሰማው ይጠቅሳል። በከተማው ምክር ቤትም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሆኖ መመረጡ ከፍተኛ ደስታ እንደሰጠው ያስረዳል።
በኢትዮጵያም፣ በደቡብ ሱዳን፣ ታንዛንያ በየትኛውም የአፍሪካ አገራት የሚኖሩ ስደተኞች ይሁኑ ሌላ ህልማቸው ትክክለኛና ተገቢ ነው። በህፃንነታቸው አሜሪካ መጥተው ሆነ በትልቅነታቸው ጠንክረው ከሰሩ በአሜሪካ ህልማቸውን ማሳካት ይችላሉ። አሜሪካ ታላቅ ከሆኑ አገራት አንዷ ናት።
በርካታ እድሎችም አሉባት። እነዚህ እድሎችም በቀላሉ አይመጡም፤ መውጣትና መውረድ ያስፈልገዋል። የተሻለ ሰውነትም ይፈልጋል። ይሄንን መንገድ በቀጣይ ለሚመጡ ህፃናት እየከፈተላቸው መሆኑን ይናገራል።በተለይም ማድረግ አልችልም ብለው ለሚያስቡ ህፃናት፤ አሜሪካ መጥቼ ይሄንን መፈፀም አልችልም የሚሉትን እንደሚመለከት ይገልፃል። በአሜሪካ በህይወት መቆየት ከተቻለ ህልም ያላቸው በሙሉ ህልማቸውን ማሳካት እንደሚችሉ ይጠቅሳል።
‹‹ብዙም ሩቅ አላስብም። በአሁኑ ወቅት በሚቀጥሉት አራት አመታት ዋናው አትኩሮቴ የኦስቲንን ከተማ መቀየር እንዲሁም ማሸጋገር ነው። ኦስቲን ሁሉን ተቀባይ እንደትሆን ማድረግና ሁሉም የሚበለፅግባት ከተማ እንድትሆን መስራት ነው። ከዚያ በኋላ የወደፊቱ ምን እንደሚሆን አላውቅም፤ ይሄ በራሱ ትልቅ ሃላፊነት ነው።
በሚቀጥሉት አራት አመታት ለህዝቡ ቃል የገባሁትን በሙሉ መስራት አለብኝ። የአምላክ ፈቃድ ሆኖም ሌላ እድል ከመጣም እሱንም ለመቀበል ዝግጁ ነኝ። በሚቀጥሉት አመታት ኦስቲን ለህፃናትና ለነዋሪዎቿ የተሻለች ቦታ ማድረግ እፈልጋለሁ።›› ይላል።
በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የኦባላን መመረጥ አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፎ ነበር። የኦባላ መመረጥ ሌሎችን ሰዎች የሚያበረታታ መሆኑን በመግለፅ፤ ኦባላ ከስደት ተነስቶ አሁን እስካለበት ደረጃ ለመድረስ ጠንክሮ መስራቱ ውጤታማ እንዳደረገው ጠቅሷል።
በፈረንጆቹ ህዳር ወር 2020 በሚኒሶታ ኦስቲን ከተማ በተደረገው ምርጫ የከተማው ምክር ቤት አባል ሆኖ መመረጥ ችሏል። በአካባቢውም የመጀመሪው ስደተኛ ጥቁር ተመራጭ የሚያደርገው ሲሆን ውልደቱ ኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል ሲሆን ለአስር ዓመት በኬንያ ስደተኞች ካምፕ መቆየቱን አትቷል።
ኦባላ አሜሪካ በደረሰበት ወቅት ፖለቲከኛ እንደሚሆን ቀድሞ የወሰነ ሲሆን ለዚህም እንዲረዳው በተማረበት ኮሌጅ የተማሪዎች ሴኔት ፕሬዚዳንት ሆኖ ማገልገሉን ጠቅሷል። በተጨማሪም በተማረበት ኮሌጅ በምግብ እራስን አለመቻል ዙሪያ ንግግር ያደርግ እንደነበር ኤምባሲው ጠቁሟል።
በአካባቢው በሚያደርገው ተሳትፎ ምክንያት ለምርጫው ለመወዳደር በቀረበበት ወቅት ቅስቀሳ ለማድረግ ምንም አልከበደውም ነበር። ምርጫውን ካሸነፈ በኋላ ባደረገው ንግግር አሜሪካዊ በመሆኑ በጣም እንደሚኮራና አካባቢውን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ጠቅሷል። በተጨማሪም የአሜሪካውያንን ህልም ለማሳካት ጠንክሮ እንደሚሰራና እንደሚያሳካው በርግጠኝነት ተናግሯል።
አዲስ ዘመን ጥር 28/2013