ከገብረክርስቶስ
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
እኔ ለዛሬ የምጠይቀው ጉዳይ ሰሞኑን የትህነግ ቡድን በመቀሌ የሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ሰነድ ሙሉ ለሙሉ ማውደሙን ሰምተናል። በዚህም በጣም አዝነናል። መቼም የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ (ትህነግ) ቡድን ከተወለደበት ጎደሎ ቀን ጀምሮ ላለፈው ግማሽ ምዕተ-ዓመት በዚህ አገር ላይ ያልፈፀመው የወንጀል ዓይነት የለም ቢባል ግነት አይሆንም።
ከተራ ግድያ እስከ ዘር ማጥፋት፤ ከሌብነት እስከተደራጀ ዘረፋ፤ ከውንብድና እስከ መንግሥታዊ ሽብርተኝነት፤ ከውሸት እስከ መሰረተ-ልማት ውድመት ድረስ በትህነግ የተፈፀሙ ወንጀሎች ናቸው።
ወደ መቃብሩ አፋፍ በደረሰባቸው ባሳለፍነው ጥቅምት የመጨረሻዎቹ ቀናት የፈፀመው ድርጊት ደግሞ የወንጀሎቹን ክምር ተራራ አሳክሎታል። በዓለም ታሪክ ያልተመዘገበና በራስ መከላከያ ላይ የተፈፀመ የክህደት ተግባር በመፈፀም ዓለምን ጉድ ያሰኘ ቡድን ሆኗል።
ቡድኑ በባዶ ፉከራው ሲያደነቁራት ከሰነበተባት ከመቀሌ እና ከሌሎችም ከተሞች ተጠራርጎ ሲፈረጥጥ የሰነድ ውድመትና ዝርፊያ ፈጽሟል። ከዚህ አንፃር ቡድኑ የፈፀመው አሰፋሪ ድርጊት ከሕግ አኳያ እንዴት ይታያል፡፡ እባካችሁ በጉዳዩ ዙሪያ ባለሙያ አነጋግራችሁ ምላሽ ብትሰጡን።
እኛም ከአንባቢያችን የደረሰንን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የሕግ ባለሙ ጠይቀን ምላሽ ይዘን ቀርበናል።ለጥያቄው ምላሽ የሰጡን የሕግ ባለሙያው አቶ አብርሃም አያሌው ናቸው። መልካም ንባብ የትህነግ ቡድን የሰነድ ዝርፊያና ውድመት ከሰሞኑ ተደጋግሞ ሲነገር እንዳደመጥነው የትህነግ ቡድን በተለይም የመቀሌ ከተማ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ድርጅቶችን ሰነዶች ገሚሱን አውድሞ፣ እኩሌታውን ደግሞ ዘርፎ ነው የሸሸው።
በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የመቀሌ ከተማ ከንቲባ ሲገልፁ እንደሰማነውም ማዘጋጃ ቤት፣ የገቢዎችና የንግድ ጽሕፈት ቤቶችን የመሳሰሉ የመንግሥት አስተዳደር ተቋማት በተለየ ኢላማ ተደርገዋል። ዩኒቨርሲቲዎችን ሳይቀር መዝረፉና ማውደሙ ደግሞ የቡድኑን አሜኬላነት ገሃድ ያወጣ ሆኗል።
ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ደግሞ የተፈፀሙት ድርጊቶች ተራ የሰነድ ማጥፋትና የዝርፊያ ወንጀሎች ሳይሆኑ ሆነ ተብሎ በተቀነባበረ መንገድ የቡድኑንና በውስጡ የተሰገሰጉትን ስግብግብ ዘራፊዎች የዓመታት ወንጀል ደብዛ ለማጥፋት የተፈፀሙ እኩይ ተግባራት መሆናቸውን ነው።
በአሁኑ ወቅት በመቀሌ የተፈፀመው ድርጊት ከሁለት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባና በመላ አገሪቱ የተፈፀሙትን ተመሳሳይ አድራጎቶች ያስታውሳል።
በወቅቱ የትህነግ ቡድን ከአዲስ አበባና በመላ አገሪቱ ከዘረጋው የይስሙላ ፌደራሊዝም ተጠራርጎ መቀሌ ላይ ሲመሽግ የፈፀመው ድርጊት ተመሳሳይ ነው።
ያኔም ቡድኑ በኢኮኖሚ አሻጥር፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በተደራጀ ዝርፊያ፣ በዶላር ማሸሽና በመሰል ወንጀሎች የፈፀመው ሴራ እንዳይጋለጥበት ከበርካታ የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማት ሰነዶችን አጥፍቷል፣ አስጠፍቷል። ዘርፏልም።
የትህነግ የሰነድ ማጥፋትና ዘረፋ በሕጉ ዓይንበመሰረቱ የመንግሥትና የሕዝባዊ ተቋማት ሰነዶች ከሌሎች የግል ወይም የሌሎች ድርጅቶች ሰነዶች በሕግ የተለየ ጥበቃ ነው የሚደረግላቸው። ምክንያቱም ሰነዶቹ ከግልና ከቡድንም በላይ በአገርና በጠቅላላው ሕዝብ መብትና ጥቅም ላይ የጎላ አንድምታ ያላቸው በመሆናቸው ነው።
በ2007 ዓ.ም. የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ እንደሚገልፀው ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በመንግሥት በጀት የሚተዳደር እና የፌደራል ወይም የክልል መንግሥት ሥራዎች የሚከናወኑበት ማናቸውም መስሪያ ቤት ወይም የልማት ድርጅት ውስጥ የሚገኝ ሰነድ መንግሥታዊ ሰነድ ነው።
በሌላ በኩል በማንኛውም አግባብ ከአባላት ወይም ከሕዝብ የተሰበሰበ ወይም ለሕዝባዊ አገልግሎት ታስቦ የተሰበሰበ ገንዘብ፣ ንብረት ወይም ሌላ ሀብት የሚያስተዳድር አካል ሕዝባዊ ድርጅት በመሆኑ በእንዲህ ያለ ተቋም ውስጥ የሚገኝ ሰነድ ሕዝባዊ ሰነድ ነው።
በዚሁ መነሻ መንግሥታዊ ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰነዶችን ማጥፋት ወይም ጉዳት እንዲደርስባቸው ማድረግ ከባድ የሙስና ወንጀል ሆኖ ተደንጓል።
በአዋጁ በግልጽ ሰፍሮ እንደምናነበው ማንኛውም ሰው የሌላውን ሰው መብት ወይም ጥቅም ለመጉዳት ወይም ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ተገቢ ያልሆነ ማናቸውንም መብት ወይም ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብ በመንግስት ወይም በሕዝባዊ ድርጅት ሰነድ ላይ ጉዳት እንዲደርስበት ያደረገ በጽኑ እስራትና በመቀጮ ይቀጣል።
በሰነድ ላይ የሚፈፀሙት ድርጊቶች የሚባሉት ደግሞ መቅደድ፣ ማጥፋት፣ ጥቅም ላይ እንዳይውል ማድረግ ወይም መውሰድ ናቸው።
እነዚህ ሰነድ የማጥፋት ወይም በሰነድ ላይ ጉዳት የማድረስ ወንጀሎች የተፈፀሙት ሰነዶቹን እንዲያዘጋጅ፣ እንዲመዘግብ፣ እንዲጠብቅ ወይም ለጠያቂ አካላት እንዲሰጥ ኃላፊነት በተጣለበት የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ ከሆነ ደግሞ የእስራትም ሆነ የገንዘብ ቅጣቱ እንደሚከብድ ሕጉ ይገልፃል።
በትህነግ እንደተደረገው የሰነድ ማጥፋት ወንጀሉ በመደራጀት፣ በጦር መሣሪያ በመታገዝ፣ ወንጀልን ለመደበቅና ወዘተ ተፈጽሞ ከሆነ ደግሞ በፈፃሚዎቹ ላይ የሚጣለው ቅጣት እስከ እድሜ ልክ ይደርሳል።
በአጠቃላይ በመላው ትግራይ በትህነግ ቡድን የተፈፀመው የሰነድ ማውደምና መዝረፍ ተግባር በማን፣ እንዴትና ለምን እንደተፈፀመ ዝርዝር ምርመራ የሚካሄድበት መሆኑ እንደተጠቀ ሆኖ ድርጊቶቹ አደገኛ ዓላማን አንግበው በከባድ ሁኔታ የተፈፀሙ ወንጀሎች ስለመሆናቸው መናገር ይቻላል።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2013