አስመረት ብስራት
አፍላ ወጣትነት ከ10 እስከ 19 አመት የእድሜ ክልል ነው። በዚህ ወቅት አፍላ ወጣቶች በተለይ የልጃገረዶችን የአመጋገብ ሁኔታ ማስተካከል፣ የትምህርት ተሳትፏቸውን ማረጋገጥ፣ የጤና እንክብካቤ ተጠቃሚነትን መጨመር፣ ያለእድሜ ጋብቻና ወሊድን በመከላከል ሙሉ አቅም ያላቸውን አገር ተረካቢ ወጣቶችና ቀጣይ ትውልድ ለማፍራት ይረዳል። በተቃራኒው በዚህ አፍላ እድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ባልጠበቁት አጋጣሚ ችግር ውስጥ ሊወድቁም ይችላሉ።
በአገሪቱ ለ33ኛ ጊዜ በተከበረው የዓለም ኤድስ ቀን የጤና ሚኒስቴር ከፌዴራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤትና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በዘውዲቱ ሆስፒታል የሚገኙ የኤች አይ ቪ ኤድስ ታማሚዎች ተጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ላይ በበሽታው የተጠቁት ህፃናትና ወጣቶች በሽታውን ተቀብለውት በጥንካሬ ቢኖሩም የበሽታው ስርጭት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ በግልፅ ይታያል። ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ሙሉ የወጣትነት ነፃነት ፊታቸው ላይ አይነበብም።
የቫይረሱ ሰለባ የሆኑት ወጣቶች ‹‹አብዛኞቹ በእኛ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ኤች አይ ቪ የለም ብለው ያስባሉ። እኛ ምስክር አለን። እኛ እየተሰቃየን ያለነውን አይነት ስቃይ ሌሎች ወጣቶች ላይ እንዲደርስባቸው አንፈልግም። የተወሰነው በእሳቱ እድሜ ምን እንደሚፈጠር ሳናስብ በስሜት ብቻ ተነድተን ችግር ውስጥ የገባን ሌሎቹ ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው የተቀበሉት ስቃይ አፍላውን የወጣትነት ዘመናችንን በአግባቡ እንዳንኖር አድርጎናልና ይህ ስቃይ በማንም አይደገም›› ይላሉ።
ወጣቶቹ እንደሚሉት፤ ሁሉም ነገር በጊዜው ይሆናል። በርካታ ህፃናትና ወጣቶች ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፊያ መንገድ የሚያዙ ናቸው። በተጨማሪም የወጣትነት እድሜ ካለመገንዘብ ለሁሉም ነገር ከልክ በላይ በመቸኮል በቫይረሱ መጠቃት ደግሞ እጅግ አደገኛ ነው።
ሆስፒታል የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ኃላፊ የሆኑት ዶክተር አስቴር ሸዋአማረ በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ። እንደሳቸው አባባል፤ ዛሬም በከፍተኛ ሁኔታ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መካከል ሴቶችና አፍላ ወጣቶች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ። በአዲስ አበባ የኤች አይቪ ቫይረስ ስርጭት መጠኑ ከሶስት በመቶ በላይ ሆኗል። ይህ ደግሞ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሆነ አመልካች ነው።
በከተማዋ ኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኙ ግለሰቦች 109 ሺህ በላይ መሆናቸውን ያስታወሱት ዶክተሯ፤ ከእነዚህ መካከል ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 24 የሚሆን ወጣቶች በከፍተኛ ቁጥር በቫይረሱ መያዛቸውን ጥናቶች እንደሚያሳዩ ይናገራሉ። በሀገሪቱ 76 በመቶ የሚሆኑ ወጣት ሴቶች ስለ ኤች አይ ቪ እውቀት የሌላቸው መሆኑንም ያስረዳሉ። ለኤች አይ ቪ ምርመራ ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል ከሚመጡት መካከል እድሜያቸው ከ15 እስከ 24 የሆነ አፍላ ወጣቶች የኤች አይ ቪ ተጠቂ ቁጥሩ ከፍ ብሎ እንደሚታይ ይጠቁማሉ።
በዝግጅቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስቴር ዲኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በበኩላቸው እንዳሉት፤ አዲስ አበባ ከተማ ከጋምቤላ ቀጥሎ በከፍተኛ ሁኔታ የኤች አይ ቪ ስርጭት የሚታይባት ከተማ ናት።
በጋምቤላ የኤች አይ ቪ የስርጭት መጠን ወደ አምስት በመቶ የሚጠጋ መሆኑን አስታውሰው አንዳንድ የሀገሪቱ ከተሞች ላይም የስርጭት መጠኑ ከፍ ብሏል።
ዶክተር ደረጀ እንደሚሉት፤ በከተማዋ በአፍላ ወጣቶች ያለው የኤች አይ ቪ የስርጭት መጠን ከፍ ማለት ምክንያቱ መዘናጋት ነው። የተለያዩ አካላት ኤች አይ ቪ ላይ የሚሰጡት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች መቀዛቀዛቸው በአዲሱ ትውልድ የስርጭት ምጣኔው ከፍ እንዲል በምክንያትነት ይጠቀሳል። ስራውም የአንድ ሰሞን ስራ ከመሆን በዘለለ ተከታታይነት ያለው መሆን አለበት።
የኤች አይ ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ እንደሚሉት፤ በከተማዋ ያለውን የኤች አይቪ የስርጭት መጠን አሳሳቢ የሚያደርገው በአፍላ ወጣቶች መካከል ያለው የስርጭት መጠን ከፍተኛ መሆኑ ነው። ለዚህም ደግሞ ከስራ አጥነት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች ናቸው።
“ስራ አጥነት ለኤች አይ ቪ የሚያጋልጡ ስፍራዎች እንዲውሉ ገፊ ምክንያት ነው” የሚሉት ዶክተሯ፤ በከተማዋ ያሉ የኢንዱስትሪና የሆቴሎች መስፋፋት ሌላው እንደ ምክንያት ያነሱት ነው። በከተማዋ የመጤ ባህሎች መስፋፋትም እንደሚታይና የራቁት ዳንስ ቤት፣ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት፣ ጫት፣ ሺሻና ቡና ቤቶች መበራከታቸው ለኤች አይ ቪ መስፋፋት አስተዋፅኦ ማድረጉንና በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየው የኮንስትራክሽን ስራዎች ላይ ለመሰማራት ከተለያዩ ከተሞች የሚመጡ ወጣቶች ቁጥር ከፍ ማለትም የስርጭቱ መጠን እንዲሰፋ ማድረጉን ያብራራሉ።
ጽሕፈት ቤቱ በከተማዋ ለኤች አይቪ ተጋላጭ ብሎ የለያቸው በትምህርት ቤትም ሆነ ውጭ ያሉ ወጣቶች፣ የቀን ሰራተኞች፣ የከባድ መኪና የረዥም ርቀት አሽከርካሪዎች፣ በወህኒ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች፣ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ግለሰቦች፣ እና በቅርቡ በተደረጉ ጥናቶች እንደታየው ደግሞ ባሎቻቸውን በፈቱ ሴቶች የስርጭት ምጣኔው ከፍ ያለ ነው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 5/2013