“አባይ ማለት ታላቅ ማለት ነው። ከወንዞች ሁሉ አቢይ ነው። የበኩር ልጅን አባይነህ ይሉታል – ታላቅ ነህ ማለታቸው ነው። አባይ ከወንዞች ሁሉ ታላቅ ነው።” የጥቁር አባይ ወንዝ “ግዮን” ከእንግሊዝኛው” ብሉ ናይል”) ከጣና ሐይቅ ይመነጫል። ካርቱም፥ ሱዳን ሲደርስ ከነጭ አባይ ጋር ተገናኝቶ ከዚያ አባይ ወንዝ (ናይል)፤ ከዛ በግብጽ በኩል ወደ ሜድትራኒያን ባሕር ይፈሳል። ለዝርዝሩ የስለሺ ደምሴን “አባይ” ዜማ መኮምኮም ጥሩ ነው።
እጅግ የተከበሩ የአለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፍወርቅ ተክሌ “ስለ ኢትዮጵያ ክፉ አታውራ፤ ክፉ አትይ፤ ክፉ አትስማ።” ያሉትን በማስታወስ እኛም ከክፉ ክፉው ተቆጥበን ስለ አባይ አንዳንድ ደግ ደግ ነገሮችን ማንሳት ፈለግን። ምንም እንኳን ባሁኑ ጊዜ ስለኢትዮጵያ ክፉ አለማየትም ሆነ አለመስማት ባይቻልም፤ ክፉ አለማድረግና አለመናገር ግን ይቻላል። በመሆኑም ነው “ስለ አባይ ዝም አንልም፤ አባይ የኔ/የኛ ነው፤ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባንዲራችን ነው” ወዘተ አባባሎች ዛሬ ላይ የእለት ተእለት ንግግር እስከ መሆን የደረሱት- ደግ ደጉን መናገር በሚፈልጉ ሰዎች አማካኝነት።
ወደ ኋላ ለመሄድ በምናደርገው ጥረት ምክንያት ከቅርቡ፤ “የኢትዮጵያ ልጆች መጡ እንደገና …” ከሚለውና “አባይ”ን ከ-–እስከ ከሚያብራራው የስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) ዜማ ጀመርን እንጂ እቅዳችን ስለ አባይ ምን ተባለ፣ በማን ተባለ፣ ለምን ተባለ ወዘተ የሚሉትን በጥቂት ወካይ ምሳሌዎች አማካኝነት መግለፅ ነው።
አባይ ጉደል ብለው አለኝ በትሳስ፣
የማንሆድ ይችላል እስከዚያው ድረስ።
እንዳልተባለ ሁሉ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ የህዳሴው ግድብ መቼ አልቆ ባየነው እያለ ጉጉቱ ጣራ በነካበት በዚህ ወቅት ከዛው ከተለመደው ግብፅ አካባቢ
“የአባይን ውሃ ትሞሉና ዋ!” የሚል ቀረርቶ መሰማቱን ተከትሎ “ታዲያ ምን እንሙላው? የግብፅን አፈር?” በማለት አበሻ ማሾፍ መጀመሩን ተከትሎ ከዛው ከተለመደው ግብፅ አካባቢ ሌላ ተጨማሪ ራስ ምታት እየተምቦገቦገ ነው እየተባለ ነው። ብቻ “ይህ ጽሑፍ ስለ’ዛ ማዶ ራስ ምታት ምን አገባውና ነው እዚህ የሚያነሳው?” ቢባል ትክክል ነውና ሁሉንም “ስራው ያውጣው” በሚል አልፈነው ወደ ጉዳያችን እንዝለቅ። ጉዳያችን ደግሞ “አባይን በጥበብ” ይሉ አይነት ነው።
ስለ አባይ ብዙ ተብሏል። በየተለይ በስነቃል ያልተገለፀ የአባይ ማንነት አለ ለማለት የሚደፍር ያለ አይመስልም። ምናልባት ዲ/ን ተረፈ ወርቁ በ”አዲስ ጉዳይ” (ጥር 24/2006) ግብፅ አባይን የሚያሞግሱ ከ10ሺህ በላይ ስነቃሎች አላት ያሉንን ወስደን የእኛውን ስንመዝን ምን እንደሚሰማን ባይታወቅም ለጊዜው እንበልጣለን/ይበልጡናል ማለቱን ትተን በአንድ ጥናት ወደ ተገለፀ ጉዳይ እንሂድ።
ከሥነ ቃል እሴታችን ስንወጣ የምናገኘው ዘመናዊውን ትምህርት ሲሆን እሱም የጽሑፍ – በተለይም የሥነ ጽሑፍ አለምን ነው። ይህ ደግሞ በበኩሉ ወደ ዘመናዊው የሥነ ጽሑፍ ስራዎች ይወስደናልና “አባይ በዘመናዊው ሥነ ጽሑፍ፤ ባጠቃላይም ኪ(ሥ)ነ ጥበብ ምን ተባለ?” ስንል የምናገኘው በአ.አ ዩኒቨርሲቲው ዶ/ተፈሪ መኮንን የተደረገው የፒ.ኤች.ዲ መመረቂያ ጥናት የሚሰጠንን መልስ ይሆናል።
ከተወሰኑ አመታት በፊት በኢዮጵያ ደራሲያን ማህበር ጋባዥነት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ዶ/ር ተፈሪ መኮንን በኤፍኤም 97.1 “የጥበብ እልፍኝ” ፕሮግራም ላይ ቀርበው የኢትዮጵያ ደራሲያን ስራዎችና እይታ ላይ ያተኮረና ለሶስተኛ ዲግሪያቸው ማሟያ ይሆን ዘንድ ባካሄዱት ጥናት አማካኝነት ያገኙትን “ስለ አባይ ለማወቅ ስለ አባይ የተባሉትን የተፃፉትን በሚገባ መመርመር፤ መረዳት ይገባል። ስለ አባይ ከ60ዎቹ በፊትና በኋላ ያሉት ትረካዎች የተለያዩ ናቸው።
በፊት የነበሩት ትኩረታቸው የአባይ አስቸጋሪ ባህርያት ላይ ያተኮረ፤ በክረምት እየሞላ የግንኙነት መሰናክል በመሆን ሰዎች እንዳይገናኙ ማድረጉ ላይ ያተኮሩ ነበረ። ከ60ዎቹ በኋላ ግን ይህ ሁሉ ተቀይሮ የደራሲዎቻችን፤ ባጠቃላይ የኪነጥበብ ባለሙያዎቻችን ትኩረት ቁጭት ላይ ሆነ። እንዴት አንገድበውና አንጠቀምበትም የሚል ቁጭት። ለዚህ ደግሞ ግንባር ቀደሙ ፀጋዬ ገብረመድህን ነው። ፀጋዬ “አባይ”ን በመግጠም ቁጭቱን ገለፀ። በቃ ከዛ በኋላ ነው የኪነጥበቡ አለም የአባይን ጥቅም ላይ አለመዋል በመገንዘብ መቆጨት የጀመረው። ከዛ የፅጌረዳ ብዕር የግጥም መድበል መታተም ጀመሩ። ከዛ አያልነህ ሙላት “አባይ ጥቁር አፈር”ን ይዘው መጡ። ሀይሉ ገብረ ዮሀንስ (ጎመራው) ደግሞ ጭራሽ ብስጭቱን ከፍ አደረገውና አባይን በስድብ መጎንተል ሁሉ ጀመረ – በ”እነትክን” ግጥሙ። እያለ እያለ ዛሬ የበርካታ አርቲስቶች የትኩረት ማዕከል ሆኗል።
ዶክተር ተፈሪ እንደተናገሩት ከሆነ አባይ በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ ይከበራል፤ ይመለካል፤ ልሰት ይገባለታል፤ ፀበል ነው። ጉዳያችንን እናጥበውና በሙዚቃው ዘርፍ ስለተወደሰው አባይ እንምጣ።
“ሙዚቃ ፈዋሴ ነፍስ” የሚለውን ይዘን፤ አባይን አንተርሰን “በሙዚቃስ ምን ተባለ?” ካልን የምናገኘው ምላሽ “ብዙም ባይሆን ጥቂት፤ ግን ደግሞ ምርጥ ስራዎችን ነው።” የሚል ስለመሆኑ ጥርጥር የለም። ከሚጠቀሱት መካከልም (ሁላችንም እንደምናውቀው) እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ነች። ወደ ኋላም እንሂድ፣ የሷ ዘመንም ላይ እናተኩር “የእጅጋየሁን ግጥሞች፥ ተማሪዎች ክፍል ውስጥ ቁጭ ብለው ይጫወቱበታል፣ ይወያዩበታል። የመመረቂያ ጽሁፍ ማሟያ ለመስራት በርዕስነት ይመርጡታል። ጥበብ የጠራቻቸው በየማዕዘኑ እያነሱ ይጥሉታል። ምሁራን ይወያዩበታል። በጥልቅ የሚረዱት ይበረብሩታል። እንጂ እንዲሁ በአንድ ሰሞን ተሰምተው የሚተዉ” አይደሉም የተባለላትን ጂጂን የሚያስከነዳ አለ ለማለት እጅግ ይቸግራል። ጂጂ ከዜማዋ
አስቀድማ በግጥሟ አባይን (ኢትዮጵያም አለችበት) እንዲህ ትገልፃቸዋለች፤
የማያረጅ ውብት የማያልቅ ቁንጅና
የማይደርቅ የማይነጥፍ ለዘመን የጸና
ከጥንት ከጽንስ አዳም
ገና ከፍጥረት
የፈሰሰ ውሃ ፈልቆ ከገነት
ግርማ ሞገስ
የአገር ጸጋ የአገር ልብስ
ግርማ ሞገስ
የዚህ የአጭር አጭር ፅሁፍ አላማ ስለ አባይ ማን ምን አለ የሚለውን ለማሳየት እንጅ የግጥሙን የይዘትም ሆነ ቅርፅ፤ ወይም ዜማም ሆነ ቅንብር ለመፈተሽ አይደለም። በመሆኑም ከጂጂ ጎላና ከፍ አድርገን ለማሳያነት እንውስደና ስለ አባይ ያለችውን እናጉላው።
አባይ የወንዝ ውሃ አትሆን እንደሰው (?)
ተራብን ተጠማን ብለው
አንተን ወራጅ ውሃ ቢጠሩህ አትሰማ
ምን አስቀምጠሃል ከግብጾች ከተማ?
አባይ—— አባይ— አባይ—- አባይ
አባይ ወንዛወንዙ
ብዙ ነው መዘዙ
የበረሃው ሲሳይ (4)
ወደ ሌላ መሄዱ ብዙም የተነሳንበትን ጉዳይ የተለየ አያደርገውም ፅሁፋችንን በዚሁ ከጂጂ “ጉራማይሌ” አልበም፤ “አባይ” ዜማ ውስጥ በሚገኙ ስንኞች እናጠቃለው (በነገራችን ላይ ግድቡ የተጀመረው ይህ ዜማ በወጣ በአስር አመቱ እንደሆነ ልብ ይሏል)።
“አባይ ለጋሲ ነው በዚያ በበረሀ
የሚበሉት ውሃ የሚጠጡት ውሃ
*******
ስነካው ተነኩ አንቀጠቀጣቸው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2012
ግርማ መንግሥቴ