የኮሮና ቫይረስ በአገራችን ከተከሰተበት መጋቢት አራት ጀምሮ 84 ቀናት ተቆጥረዋል ። ከዚያን ጊዜ ወዲህም ያዝ ለቀቅ እያደረገ የነበረው የስርጭት ሁኔታ በተለይ ባለፈው አንድ ሳምንት በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩና በበሽታው ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥርም እያደገ በመምጣቱ ስጋቱን ከፍተኛ አድርጎታል ።
በአንፃሩ ግን ህብረተሰቡ ከቫይረሱ ራሱን ለመከላከል የሚደርጋቸው ጥንቃቄዎች ከመጀመርያዎቹ ቀናት አንጻር ሲታዩ እየቀነሱ መሄዳቸውን በየመንገዱ ካለው እንቅስቃሴ መታዘብ ይቻላል ። ይህን ታሳቢ በማድረግም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የበለጠ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ተጨማሪ የህግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው እየተተገበሩ ይገኛሉ ። ከእነዚህ መካከል አንዱ ከቤት ውጪ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስኮችን ማድረግ የሚያስገድደው ህግ አንዱ ነው ።
ባለሙያዎች እንደሚመክሩት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታትና ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ዋነኛው መፍትሔ የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ መለየትና ተግባራዊ ማድረግ ነው ። ነገር ግን ከመከላከያ መንገዶቹ ውስጥ ጥቂቱን አለመተግበር አጠቃላይ ውጤቱን በዜሮ የሚያባዛ በመሆኑ ጥንቃቄያችንን ሙሉ ማድረግ ላይ ትኩረት ልንሰጥ ይገባል ። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የሚደረጉ ጥንቃቄዎች አንዳንድ ጊዜ ለይስሙላ የሚከናወኑ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ጭራሹኑ ትኩረት ያልተሰጣቸው እንደሆነ አመላካች ናቸው ። ለአብነትም ጥቂቶቹን እናንሳ ።
የማስክ አጠቃቀም
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ በየጎዳናው ሲኬድ ማስክ የማያደርግ ሰው የለም ለማለት ያስደፍራል ። ለዚህ ተግባራዊነት የፖሊስ አስተዋጽኦም ቀላል አይደለም ። በየመንገዱ ፖሊሶች ማስክ የማያደርጉትን ሲያስገድዱ ይታያልና ። አጠቃቀሙ ላይ ግን ገና ያልተሻገርነው ችግር ይስተዋላል ። አንዳንድ ሰዎች ማስክ የሚያገለግለው ለምን እንደሆነ የገባቸው እስከማይመስል ድረስ ማስኩን አገጫቸው ላይ አድርገው ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል። በተለይ በገበያዎች አካባቢ ማስክ አድርጎ የመጣ ሰው ሲገበያይ ማስኩን ዝቅ አድርጎ አገጩ ላይ ሲያደርግና ሲያወራ ይታያል ። የማስኩ አስፈላጊነት ቫይረሱ በአፍና በአፍንጫ እንዳይገባ መከላከል ሆኖ እያለ ወደሰዎች ሲቀርቡ ማስኩን አገጫቸው ወይም አንገታቸው ላይ አድርገው የሚያወሩ ሰዎች ማስኩ ለምን እንዳስፈለገ እንኳ ተረድተዋል ለማለት አያስደፍርም ።
ከዚህም ባሻገር አንዳንዶቹ ደግሞ አፋቸውን ብቻ ሸፍነው አፍንጫቸውን አጋልጠውሲሄዱ ይስተዋላል።ይህም አንዱን ጥሎ፣ ሌላውን አንጠልጥሎ የሚለውን ብሂል የሚስታውስ ነው ። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ለቫይረሱ የተጋለጠ ሰው በምንም መልኩ ራሱን ሊከላከል አይችልም ።
ሌላው ደግሞ የማስክ ዓይነቱ መብዛት ነው ። በተለይ በየመንደሩ የሚሰፉ ማስኮች በመብዛታቸው በአሁኑ ወቅት የማስኩም ዓይነት እንደየሰው ሁኔታ የተለያየ ነው ። አንዳንዱ ማስኩን የሀብት ልዩነት ማሳያ አድርጎ የመውሰድ ሁኔታ ይስተዋላል ። አንዳዶቹ ደግሞ የሚደግፉት ክለብ ማስታወቂያ በማድረግ ይጠቀሙበታል ። ከ15 ብር እስከ 200 ብር ድረስ በገበያ ላይ የሚቸበቸቡት ማስኮች የጥራት ደረጃ ቢለያይም በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ ግን የዋጋው ልዩነት ለውጥ ላያመጣ ይችላል ።
የአትክልትና ፍራፍሬ ገበያ
የቫይረሱ መተላፊያ ከሆኑ መንገዶች ውስጥ አንዱ የተለያዩ ንክኪዎች እንደሆኑ በተደጋጋሚ ተነግሯል ። በተለይ ቫይረሱ ተለቅ ያለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሰዎች ሲያስነጥሱ ወይም ሲያስሉ በቀላሉ ከአፍና ከአፍንጫ በመውጣት በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኝ ቁስ ላይ ሊያርፍና ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፍ ይችላል ። እስከአሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ ቫይረሱ በዕቃዎች ላይ የመቆየት አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ማድረጉን ባለሙያዎች ይመክራሉ ።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች በተለይ በቀጥታ ወደአፍ የሚገቡ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እንዲሁም የምግብ ዓይነቶችን በእጃቸው ሲነካኩና ሲገበያዩ ይስተዋላል ።ለምሳሌ በመንገድ ላይ በጋሪ ሙዝ፣ ብርቱካን፣ ማንጎ፣ፓፓያና የመሳሰሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን የሚሸጡ ሰዎች ይህንን የንክኪ ሁኔታ በአግባቡ ስለመረዳታቸው አጠራጣሪነው። ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ ገዢዎች እነዚህን አትክልትና ፍራፍሬዎች እያነሱ መብሰል አለመብሰሉን በእጃቸው ጫን ብለው ሲፈትሹና ጥለው ሲሄዱ አስተውያለሁ ። ቀጣዩም ገዢ በተመሳሳይ መልኩ እየፈተሸ ይገዛል፤ ወይም ጥሎ ይሄዳል ። በዚህ ረገድ በቀን ውስጥ እነዚህ አትክልትና ፍራፍሬዎች ምን ያህል የእጅ ንክኪ እንደሚስተናግዱ መገንዘብ አያዳግትም ።
ይህ ብቻ አይደለም፤ በተለያዩ አነስተኛ የምግብ ቤቶችና የጀበና ቡና መሸጫዎች ውስጥ የቡና ስኒዎችን ጨምሮ የተለያዩ የመመገቢያና የመጠጫ ዕቃዎች ምን ያህል ከቫይረሱ ፀድተው ለደንበኛ እንደሚቀርቡ አይታወቅም ። በአብዛኛው ግን በቀላሉ ታጥበው ከመቅረብ የዘለለ ከቫይረሱ ነፃ ስለመሆናቸው የሚረጋገጥበት መንገድ አይታይም ። ይህ ደግሞ ለቫይረሱ የማጋለጥ ደረጃው ከፍ እንዲል ያደርጋል ።
የብር ኖትና ሳንቲሞች ግብይት
ሌላው የአገራችን በተለይ የአዲስ አበባ የቫይረሱ የማሰራጫ መንገድ ደግሞ የብር ኖትና የሳንቲም አጠቃቀም ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ አያዳግትም ። እነዚህ የመገልገያ ዕቃዎች በየዕለቱ ከሰው ወደ ሰው የሚዘዋወሩበት መንገድ ከፍተኛ ነው ። በተለይ በህዝብ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የእነዚህ ገንዘቦች ዝውውር ከፍተኛ በመሆኑ የተለያዩ ሰዎችን የማዳረስ አቅማቸው ከፍተኛ ነው ።
በሌላም በኩል እነዚህ የመገበያያ ገንዘቦች ቫይረሱን የመያዝ አቅማቸው ከፍተኛ ሊሆን ይችላል ። አንድ ቫይረሱ ያለበት የብር ኖት በቀን ውስጥ የተለያዩ ደንበኞች ጋር ሊዘዋወር ስለሚችል ቫይረሱን ለማሰራጨት ያለው አቅም ከፍተኛ ነው ። ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ የህዝብ ትራንስፖርት ውስጥ በምንገባበት ወቅት ከበር ጀምሮ ወንበሮችና መደገፊያዎችን የመንካት ዕድላችንም ከፍተኛ ነው ። ይህ ደግሞ አጋላጭ ሊያደርገን ይችላል ። በመሆኑም በሁሉም እቅስቃሴያችን አልኮሆል ወይም ሳኒታይዘርና የተለያዩ የመከላከያ ቅባቶችን ይዞ መዘዋወርና እጅን ከእነዚህ ተህዋስያን ማፅዳት መዘንጋ የለበትም ።
በየቦታው መትፋት
ከዚህ ቀደም በተለያዩ ቦታዎች ላይ ምራቅ መትፋት ያስነውራል የሚል ጽሑፍ ይታይ ነበር ። ይህ ከባህል አንፃር ሲታይ ትክክል ነው ። አሁን ግን ምራቅን በየቦታው መትፋት ከማስነወርም አልፎ ህይወትን የሚያሳጣ ሊሆን ስለሚችል በየቦታው ከመትፋት መቆጠብ ተገቢ ነው ። አንዳንድ ሰዎች ምራቃቸውን ወይም አክታቸውን በየመንገዱ ይተፋሉ ። በዚህ አጋጣሚ ታዲያ ቫይረሱ ያለበት ሰው ምራቁን በመንገድ ላይ ከተፋና ይህንን ምራቅ ሌላ ሰው ረግጦት ወደቤት ከገባ ቫይረሱ በቀላሉ ወደቤት ሊገባና በተገኘው ቀዳዳ ወደሰው ሊደርስ የሚችልበት ዕድል ሰፊ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ። እንዲህ ዓይነት ችግሮች ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ከሚገቡ ተግባራት አንዱ ነውና ይታሰብበት ።
እንግዲህ ከላይ የጠቃቀስኳቸው የኮሮና ቫይረስ ማስተላለፊ መንገዶች በአሁኑ ወቅት በአግባቡ ትኩረት የማንሰጣቸውና የምንዘናጋባቸው ጉዳዮች ናቸው ። ለዚህ ችግር ዋነኛው መፍትሔ የቫይረሱን የስርጭት መንገዶች በአግባቡ በመለየትና እያንዳንዱን ጉዳይ በጥንቃቄ በመተግበር በቫይረሱ ከመያዛችን በፊት ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል ። ይህ ሳይሆን ቀርቶ አንዳንዱን የመከላከያ መንገድ ብቻ ተግባራዊ በማድረግ ከፊሉን የምንዘነጋ ከሆነ ግን ታጥቦ ጭቃ ነውና ጥንቃቄያችን ይበልጥ ይጠናከር መልዕክቴ ነው ። ሳምንቱ ቸር ወሬ የምሰማበት እንዲሆን ተመኘሁ ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2012
ውቤ ከልደታ