ገና ልጅ ሆኖ አባቱ የባንክ ቤት ሰራተኛ መሆኑን እጅግ ይጓጉ ነበርና ተምሮ የባንክ ሰራተኛ እንዲሆን አብዝተው ይወተውቱት ነበር። ተደጋግሞ የተነገረው የባንክ ቤት ሰራተኝነት እሱም ወደደውና ባንከር ለመሆን አለመ። በእርግጥ በሂሳብ ስራ (አካውንቲንግ) ትምህርቱን አጠናቆም ስራ ተቀጥሮ ነበር። የሚወደው የሙዚቃ ሙያ ከስራ ለመሰናበቱ ምክንያት ሆነው እንጂ። ከአሰሪው ጋር ያጋጨው ሙዚቃ የዝናን እርካብ ያስረገጠው በኢትዮጵያዊያን እውቅናንና ስኬትን ያጎናፀፈው ሙያ ሆነው – አስገኘው አሽኮ (አስጌ ዴንዴሾ)።
ባህላዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ በዘመናዊ የሙዚቃ ጥበብ አድምቆ የሚያቀርባቸው የሙዚቃ ስራዎቹ ለተከታታይ አመታት በተለያዩ የሽልማት መድረኮች የአመቱ ምርጥ ሙዚቃ ተብለው ለውድድር ቀርበውለታል። በተላይ በ2010 ዓ፣ም “ባሌ ሮቤ” የተሰኘው ነጠላ ዜማው የዓመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ በሚል በአዲስ ሚዩዚክ አሸልሞታል። በራሱ ተገጥመው በሚያምር ቅላፄ የሚንቆረቆሩ የሙዚቃ ስራዎቹ በመላው ሀገሪቱ ከፍ ያለ ተቀባይነትና ዝናን አጎናፅፈውታል።
ወላይታ ሶዶ ከተማ ውስጥ ባሳለፈው የትምህርት ቤት ህይወቱ በተለያዩ የስነፅሁፍ ክበባት በመሳተፍና ስሜቱን የሚገልፁለት ግጥሞችን በመፃፍ ውስጣዊ ፍላጎቱ ባገኘው አጋጣሚ የመግለፅ ብርቱ እንደነበር ያስረዳል። ወደሙያው ከመግባቱ በፊት ሙዚቃ ስሰማ አንዳች የሚያክለፈልፍ ስሜት ውስጤ ይገባ እንደነበር ያስታውሳል። የሰዎችን ሙዚቃ ማዜም የራሱን ስንኖች እየሞከረ መዝፈን ያዘወትር እንደነበር ይናገራል።
በዛሬው የዝነኞች የዕረፍት ውሎ አምዳችን ይሄንን ፍልቅልቅና ዝነኛ የሙዚቃ ባለሙያ አነጋግረን እነሆ የዕረፍት ጊዜ መቆያዎ ብለናል። መልካም ንባብ።
የእረፍት ጊዜና መዝናኛዎቹ
ስራዬም እረፍቴም ሙዚቃና ከሙዚቃ ጋር የተያያዙ ናቸው። ያለዜማ ቆይታ፣ ያለ ሙዚቃ መዝናናት ለእርሱ የማይታሰብ መሆኑን ይናገራል። ስራዬን እንደ እረፍት ቆጥሬው የምዝናናው በሙዚቃ ነው በማለት ለሙያው ያለው ጥልቅ ፍቅር ይገልፃል። ያለውን የእረፍት ሰዓቱን በአብዛኛው ከቤተሰቦቹ ጋር ማሳለፍና ከስራ ባልደረቦቹ ጋር መጨዋወትን ልምዱ ነው።
ነገር ግን ከከተማ ወጥቶ መዝናናት፣ ሲኒማ እየገቡ ፊልም ማየት፣ መዝናኛ ቦታዎች ላይ ተገኝቶ የማይረሱ ጊዜያትን ማሳለፍ አስጌ ሞክሮት አያውቅም። ከቤተሰቡ በተለይም ከባለቤቱ ተደጋጋሚ መሰል የመዝናኛ ቦታና ሁኔታዎች እንተግብር ጥያቄ አሁን ላይ እየተነሳ ስለሆነ የዚህ አይነት መዝናኛዎች መሞከሩ በቅርቡ እንደማይቀር ይገልፃል።
ቤተሰብ ጥየቃና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ ነው። በስራ አጋጣሚ ከተገናኛቸው ሰዎች ጋር በቀላሉ የመላመድና የመግባባት ችሎታን የታደለ ጨዋታ አዋቂም ነው። ሰዎችን በቀላሉ ቀርቦ እራሳቸውን መስሎ መልካም የሆነን ድባብ በመፍጠር ለሰዎች ምቾትን ይፈጥራል። በአጋጣሚ ቀርበውት እጅግ የተዛመዳቸው ብዙዎች መሆናቸውንም ይናገራል።
የባህል ምግብ ፍቅር
ጥሎብኝ ዘመናዊ ምግቦችን አማራጭ ካጣሁ እንጂ ፈፅሞ አልመርጥም የሚለው ዝነኛ የሙዚቃ ባለሙያ ከምግቦች መሀል መርጬ ቀድሜ የሚነሳው የቦቆሎ ቂጣ ነው ብሎ ፈገግ አድርጎናል። ጎመንና ቆጮም ከማዕዱ ላይ ባይጠፋ ይመርጣል። አስጌ ድግስ ተጠርቶ ማዕድ ሲቀርብ አይኖቹ የሚፈልጉት ባህላዊ ምግቦች መኖር አለመኖራቸውን ነው።
የልብስ ምርጫ
የለበሰው ሁሉ እራሱ ላይ እንደሚያምርበት ለመግለፅ ሰዎች ጆንያ ብትለብስም ያምርብሀል ይሉታል። ያለምርጫ ከመልበሻ ሳጥኑ ውስጥ ያገኘውን ልብስ ተጎናፅፎ መገኘትን ይመርጣል። አዘውትሮ ቁምጣና ቀለል ያሉ ልብሶች ይለብሳል። በባህላዊ ሙዚቃው ዘርፍ ጎልቶ የወጣው አስጌ ለስራው የሚገጥም በባህላዊ አለባበስ ሲታይም ባህሉን እጅጉን አጉልቶ የሚያሳይ የሚገጥምም ልዩ ውበት ደርቦ ይገኛል። “እራስ በመሆን ውስጥ የስኬትን ደጃፍ መርገጥ ይቀላል፤ ስኬትም እራስን በመሆን የሚጎናፀፉት ድል ነው።” የሚለው አስጌ ባህል ወዳድና ስለ ባህል ያለው እይታ ጥልቅ ነው።
የሙዚቃ ባለሙያው
መልዕክት
“ሁሉን ገታ አድርገን ወደ ራሳችን እንመለስ። እዚያ ውስጥ አንድነትና ህብረታችን፤ መረዳዳትና አብሮ መቆማችን ከፍ ብሎ ይገኛል። አንዳችን ለሌላችን በመኖር ወደ ዋናውና እውነተኛ ማንነታችን እንመለስ” የዝነኛው የሙዚቃ ባለሙያ ለእኛ የቀረበ ታላቅ መልዕክት ነው። አበቃሁ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2012
ተገኝ ብሩ