አቶ ሳሙኤል ሀላላ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብአቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ናቸው። በአገሪቱ የሲሚንቶ ምርት አጀማመር፣ ፋብሪካዎቹ ለሕዝቡ ያላቸው ተደራሽነት፣ እንዲሁም ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ወሳኝ ስለመሆናቸው እና በየጊዜው የሚከሰቱትን የሲሚንቶ እጥረቶችና መፍትሄዎቻቸውን አስመልክቶ ከአዲስ ዘመን ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ የሲሚንቶ አንዱስትሪ የተጀመረው መቼ ነው?
አቶ ሳሙኤል፡- በአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው ሙገር የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ፋብሪካ ነው። ይህን ፋብሪካ ደርግ አስፋፍቶታል። ሲሚንቶ የማምረት አቅሙ ከአጼ ኃይለስላሴ ጀምሮ በደርግም ሆነ በኢህአዴግ ዘመን በአገር ደረጃ ሲታይ እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቶን ብቻ ነበር። በመጀመሪያ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይና በመጨረሻው አካባቢ ይሄ የአገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በማደጉ የተነሳ የሲሚንቶ ምርት በ2007 ዓ.ም አካባቢ ወደ 17 ነጥብ 1 ሚሊዮን ቶን ደርሷል።
በ2002 ዓ.ም የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ጅማሮ አካባቢ ላይ መንግስት ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የተለየ ትኩረት በመስጠቱ ባለሀብቶች በስፋት እንዲገቡ ተደርጓል። በመሆኑም በ2005 ዓ.ም ላይ ወደ 15 ነጥብ 1 ሚሊዮን አድጎ ነበር። በዛ ሂደት ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ 17 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሲሚንቶ ምርት የማምረት አቅም በሀገር ደረጃ ተፈጥሮ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡- ኢንቨስትመንቱ በአሁኑ ወቅት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ሳሙኤል፡- ኢንቨስትመንቱ ከ2004 ዓ.ም እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ በነበሩት ጊዜያት ከታየ በኋላ ቀደም ብዬ በገለጽከት አግባብ የሀገሪቷን የሲሚንቶ ምርት ፍላጎት አሟልቶ ትርፍ ማምረት ደረጃ ላይ መድረስ ችለናል። መንግስት የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ከእቅዱ እድገት ጋር አብሮ እንዲያድግ በማሰብ ረገድም የተሻለ አቅጣጫን በመከተል ነው እየሰራ ያለው። ከዚህ የተነሳ በቅርቡ የጀመረው አባይ ሲሚንቶ ካልሆነ በስተቀር አዲስ ኢንቨስትመንት አልነበረንም።
አዲስ ዘመን፡- የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ የሚጠቀሙት ቴክኖሎጂ ምንድነው?
አቶ ሳሙኤል፡- በኢትዮጵያ ያሉት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ሁለት አይነት ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ ናቸው። በዋናነት አንደኛው ዝርያ ቨርቲካል ሻፍት ቴክኖሎጂ የሚባለውን የሚጠቀም ነው። የሲሚንቶ ማቀጣጠያ ዋናው መሳሪያ ቨርቲካል ሻፍት እና ሆሪዞንታል ሻፍት የምንለው ነው። ይህም ሲሚንቶን የምናቃጥልበት ሲሆን፣ ሁለቱም ቴክኖሎጂያቸው የተለያየ ነው። ቨርቲካል ሻፍት የሆኑትን በሚመለከት በዋናነት በጥራታቸውም ሆነ በዋጋ ደረጃቸው ከሆሪዞንታል ሻፍቱ ጋር ተወዳዳሪ አይደሉም። ከዚህ የተነሳ ያኔ የሲሚንቶ እጥረት በነበረን ጊዜ አብዛኞቹ የቨርቲካል ሻፍት ኪን (ማቀጣጠያ) ተጠቅመው ሲሚንቶ የሚያመርቱት ሆሪዞንታል ሻፍት የሆኑት በስፋት ሲገቡ ከገበያ የመውጣት ሁኔታ ታይቶባቸዋል። የሲሚንቶ ዋጋ በጣም እየናረ ካልመጣ እነሱን አያዋጣቸውም። ሆሪዞንታል ሻፍት ማለት ትላልቅና ከባድ እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ድረስ በአመት ማምረት የሚችሉ በጣም ዘመናዊ የሲሚንቶ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ ጥራት እና መጠናቸው ከፍተኛ የሆነ ምርት ማምረት የሚችሉ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሲሚንቶ የሚሰራው ከምንድን ነው?
አቶ ሳሙኤል፡- ሲሚንቶ በዋናነት በሀገራችን ካለ የኖራ ድንጋይ ወይም በኬሚካል ስሙ ካልሽየም ካርቦኔት ከምንለው እና ሌሎችም ታክለውበት ነው የሚሰራው። የኖራ ድንጋይ በአባይ ሸለቆ ውስጥ በጣም በስፋት ይገኛል። ለሲሚንቶ ምርት ዋናው ግብአት ደግሞ እሱ ነው። ይኸው ግብአት በመቀሌ ከተማ እና ዙሪያ በከፍተኛ ደረጃ ክምችቱ አለ። ድሬዳዋ ላይ ሰፊ ክምችት አለ። ኦሮሚያ ላይ ካልሽየም ካርቦኔት በብዛት የለም። አልፎ አልፎ ወለንጪቲ አካባቢ በተወሰነ ደረጃ አለ። ነገር ግን ሲሚንቶ በማምረት ደረጃ አቅም ያለው አይደለም። አዲስ አበባ ዙሪያ የለም። ዋናው የሲሚንቶ ግብአቱ ካልሽየም ካርቦኔት በአማርኛ የኖራ ድንጋይ የምንለው ነው። ከኖራው ድንጋይ ጋር አብረው ለሲሚንቶ ምርት ማምረቻ ግብአት የሚሆኑ ቀይ አፈር፣ የእሳተ ገሞራ አመድ (ቮልካኒክ አሽ) የሆነ አሸዋ፣ ፑሙቼ የምንለው ይገባበታል። ሌላው ለሀይል አቅርቦት በግብአትነት የሚጠቀሙበት የድንጋይ ከሰልም እንዲሁ አለ።
አዲስ ዘመን፡- የድንጋይ ከሰል በሀገሪቱ አለ?
አቶ ሳሙኤል፡- በስፋት አለን፤ ኃይል የመስጠት አቅሙ ዝቅተኛ ስለሆነ በአብዛኛው ከውጭ ስናስመጣ ነው የኖርነው። በአሁኑ ሰዓት በአብዛኛው በቤኒሻንጉል ጉምዝ በአባይ ወንዝ ረድፍ ላይ የተገኘው የድንጋይ ከሰል የጥራት ደረጃው በተወሰነ ደረጃ የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል። የሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች የመጀመሪያ ማድረቂያ እና እርጥበት (ሞይስቸር) መቀነሻ ፕሪ ካልሳይመር በምንለው ደረጃ መቶ በመቶ ለመጠቀም እንዲቻል እያጠኑት ይገኛሉ።
በዋናው ኪን (ማቀጣጠያ) ላይ በሂደት ሙሉ በሙሉ መጠቀም የሚያስችሉ ማዕድኑን የማዘጋጀት ቤኒፊሴሽን የምንለው የማጽዳት፣ የመፍጨት እንዲሁም የመመጠን ስራዎች ተሰርተው ጥራቱ ተፈትሾ አሁን ያለው ከ3 ሺህ 500 እስከ 4 ሺህ 500 ኪሎ ካሎሪ ፐር ኪሎ ግራም የምንለው የኃይል ምጣኔን ነው የሚሰጠው።
ይሄ ደግሞ በጣም አነስተኛ ‹ሊግናይት› የምንለው የድንጋይ ከሰል (ኮል) አይነት ነው። የሚሰጠው የኃይል መጠን አነስተኛ ነው። ከደቡብ አፍሪካ ቢቲሚነስ የምንለውንና ከሱም ደግሞ ትንሽ ከፍ የሚል አቅም የሚሰጠውን የድንጋይ ከሰል አይነት ነው የምናስመጣው።
አዲስ ዘመን፡- በአባይ ሸለቆ ውስጥ ያለው ከፍተኛ ክምችት ለዚህ አይሆንም? ከውጭ ማስመጣቱን አሁንም አልተውንም ማለት ነው?
አቶ ሳሙኤል፡- በአሁኑ ሰዓት የድንጋይ ከሰሉ ሙሉ በሙሉ ከውጭ ነው የሚመጣው። አሁን ግን ከባለሀብቶችም ጋር ተነጋግረን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተሻለ ሆኖ የተገኘው የድንጋይ ከሰል ከፍተኛ ክምችት ስላለ በኦሮሚያም ያለውን አድርገን ለስራው ምቹ በማድረግ መጠቀም ይቻላል። በሀገር ውስጥ ያለውን የድንጋይ ከሰል በስፋት ለመጠቀምም ነው እየሰራን ያለነው። የድንጋይ ከሰሉ በደቡብ ክልል ዳውሮ አካባቢም በስፋት ይገኛል። መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም በጎንደር ጭልጋ አካባቢም እንዲሁ የድንጋይ ከሰል ክምችቱ አለ። ኃይል የመስጠት አቅሙ እና የአመድ መጠኑ ትንሽ መሆን ለቴክኖሎጂው ስላስቸገረን ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በሀገር አቀፍ ደረጃ ስንት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች አሉን ?
አቶ ሳሙኤል፡- በሀገር ደረጃ ወደ 21 የሚሆኑ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ነበሩን። 14 የሚሆኑት በጥሩ ሁኔታ እያመረቱ ናቸው። ሌሎቹ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ቨርቲካል ሻፍት የሆኑት ፋብሪካዎች ኖራ ለማምረት ወደሚመች ስራ የመዞርና ሌላ ምርቶችን የማምረት ዝግጅት ላይ ናቸው። ምክንያቱም ከሆሪዞንታል ሻፍቱ ጋራ በጥራት እና በዋጋ ተወዳድረው መሸጥ አይችሉም።
አዲስ ዘመን፡- ሀገራዊው የሲሚንቶ ፍላጎት እንዴት ነው? ምን ያህልስ ይመረታል?
አቶ ሳሙኤል፡- በእኛ እምነት የሲሚንቶ ፍላጎቱን አንቆ የያዘው የሲሚንቶ ዋጋ መናር ነው። ዋጋው ባይኖር ኖሮ መካከለኛ ገቢ ያለው አሁን ባለው የመኖሪያ ቤት ችግር የተነሳ ብዙ ሰው ቤት ወደ መስራት ገብቶ ከፍተኛ የሲሚንቶ ፍላጎት ይኖረው ነበር የሚል ግምት አለን። ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሆሪዞንታል ሻፍት የሆኑት የሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች ወደ 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ማምረት ይችላሉ። ከዚህ የማምረት አቅማቸው ውስጥ አሁን ከ8 እስከ 9 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ ነው በየአመቱ እያመረቱ ያሉት። በዋናነት የማምረት አቅማቸውን ያወረደው የኃይል አቅርቦት መዋዠቅ እና መቆራረጥ ከመጥፋት ጋር ተያይዞ ነበር። ብዙውን ጊዜ ከሚሰሩበት የማይሰሩበት ጊዜ ይበዛም ነበር።
አዲስ ዘመን፡- የኃይል አቅርቦት ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር አልመከራችሁም? በእናንተ በኩል ምን አደረጋችሁ?
አቶ ሳሙኤል፡- የኃይል አቅርቦት ችግሩ ተፈጥሮ የነበረው በብሔራዊ ደረጃ ሲሆን፣ እንደሚታወቀውም ግድቦች ላይ የውሃ መቀነስ ሁኔታ አጋጥሞ ስለነበር ለማዳረስ ሲባል የፈረቃ ሁኔታ መፈጠሩን ተከትሎ ነው። ሌላው ደግሞ የኃይል ማስተላለፊያ እና ማከፋፈያ መስመሮች ብዙ ጊዜ የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ለምሳሌ ኋላ ላይ የመጡት ትልልቅ ኢንቨስተሮች ካልሆኑ ሙገርን ጨምሮ ከእነሱ ላይ ለሌሎች ለመኖሪያ ቤት አገልግሎት እንዲሁም ለገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ተሰጥቶ ነበር። እነዛን መስመሮች ቆርጦ ለሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች ብቸኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ከዋናው የኃይል ቋት (ግሪድ) ላይ የመስጠቱ ሁኔታ ለሁሉም አሟልተን ስላልሰጠን ያስቸግራል። ወርክሾፖች ወይንም መኖሪያ ቤቶች፣ ወፍጮ ቤቶች ላይ ኃይል ሲቋረጥ ወይንም ጣልቃ ገብነት በሚኖርበት ጊዜ ሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎቹም አብረው ይጠፋሉ።
አዲስ ዘመን፡- የደርባ እና ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ተጀምረዋል ?
አቶ ሳሙኤል፡- በሀገር ደረጃ በ2007 ዓ.ም ተፈጥሮ የነበረው የሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ያለ ችግር ያስኬዳል በሚል ብድር ከልማት ባንክ የማግኘትም ሆነ ሌላ የኮንስትራክሽን ስራ ታግዶ ቆይቶ ነበር። ማስፋፊያዎቹን በተመለከተ ደርባ ሲሚንቶ ከኋላ ያለውን ኢንቨስትመንት በሙሉ ለ5 ሚሊዮን ቶን ምርት የሚያበቃ ሰርቶ የተወሰነ ማሽነሪ ብቻ በመጨመር ወደዛ መውሰድ ይችል ነበር። ደርባ ይሄን ማድረግ አልቻለም። መሀል እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ላሉ የሲሚንቶ ኢንቨስትመንቶች መንግስት የሰጠውን ማበረታቻ ስላነሳ ከሌሎች ማበረታቻ ከሚያገኙት ጋር መወዳደር ስለሚያስቸግረው እንዲስተካከልለት ጠይቋል። ውሳኔ አልተሰጠም። በዋናነት የሲሚንቶ ኢንቨስትመንት በመንግስት ተከልክሎ የቆየበት ምክንያት በሀገሪቱ የተፈጠረው የማምረት አቅም ለጊዜው በቂ ነው በሚል ነበር።
አዲስ ዘመን፡- የኢንቨስትመንት መስኩ ለምን ያህል ዜጎች የስራ እድል ፈጠረ?
አቶ ሳሙኤል፡- በአጠቃላይ በሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ አሁን በፕሮጀክት ላይ እየሰራ ያለውን አባይ ሲሚንቶን ጨምሮ 12 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል።
አዲስ ዘመን፡- በሲሚንቶ መስክ የሚደረገው ኢንቨስትመንት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል ? ስኬታማ ነው ብለው ያምናሉ ?
አቶ ሳሙኤል፡- በጣም ስኬታማ ነው፤ የሲሚንቶ ኢንቨስትመንቱ በከፍተኛ ደረጃ ባይሰራ ኖሮ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን እድገት ይስተጓጎል ነበር። መንግስት ጉዳዩን በልዩ ሁኔታ አጥንቶ በኢንቨስትመንት ማሻሻያ አዋጅ ኢንቨስትመንቱ እንዲቀጥል ፈቅዷል። አሁን የምንጠብቀው ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የማስፈጸሚያ ደንቡን እስኪያወጣ ነው። ከዛ በኋላ ደርባም ተጨማሪ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ማስፋፊያ ይሰራል። ዳንጎቴም ወደ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ተጨማሪ የማስፋፊያ ስራቸውን ይቀጥላል። ሌሎችም እንደዚሁ።
አዲስ ዘመን፡- የሲሚንቶው ዘርፍ ኢንቨስትመንት ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ያደረገውን አስዋጽኦ እንዴት ያዩታል?
አቶ ሳሙኤል፡- የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዋና ግብአቶች ሲሚንቶ እና ብረት ናቸው። የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪያችን የሚፈልገውን መጠን ያህል በሁለቱም ግብአቶች ሲሚንቶ እና ብረት ሙሉ በሙሉ የማምረት አቅም ላይ ሀገራችን ደርሳለች። ኢንዱስትሪውን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል። በሀገር ውስጥ እነዚህ ዋነኛና ወሳኝ የሆኑ ግብአቶች እስከተመረቱ ድረስ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ከፍተኛ እድል ይሰጣል፤ እየሰጠም ነው።
የሲሚንቶ ኢንዱስትሪውን በተመለከተ ጥራቱ ከፍተኛ የሆነ ሲሚንቶ ነው በሀገራችን የሚመረተው። ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ማደግና መስፋፋት እንዲሁም ለኢኮኖሚውም እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በአመት ከ22 በመቶ በላይ እያደገ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡- የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው ለማምረት ያልቻሉት ለምንድነው ?
አቶ ሳሙኤል፡- የኃይል አቅርቦት ችግር አይደለም። ችግሩ ሙሉ በሙሉ ባይጠፋም መቆራረጡም ሆነ መዋዠቁ በብዙ መልኩ ተሻሽሏል። ዋናው ችግር የመለዋወጫ እቃዎች ለሲሚንቶ እንዱስትሪዎቹ በተሟላ መልኩ በጊዜው ለማቅረብ አለመቻሉ ነው። የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እና አፈጻጸሙ ችግር አለው።
መንግስት ከማንኛውም ሴክተር በላይ በሚባል ደረጃ ለዚህ ሴክተር በአመት ከ220 ሚሊዮን ዶላር በላይ መድቦ ይገዛል። እንደገና ደግሞ ምርቱን ለማሸግ የሚያስችሉ ከረጢቶች በአብዛኛው ከውጭ ስለሚገቡ ከ130 እስከ 137 ሚሊዮን ዶላር ለዚህ ብቻ መድቦ ከውጭ በግዢ ያስገባል።
ኢንዱስትሪው ሰፊ እንደመሆኑ መጠን በየጊዜው ለመለዋወጫ እንዲሁም ለማሽነሪ ለተለያዩ እቃዎች (ለኢኩፕመንት) ኢንቨስትመንት ላይ የሚፈለገውም ሆነ የሚጠየቀው የውጭ ምንዛሪ ሰፊ ነው። ከዚህ የተነሳ መንግስት እንደማንኛውም ሴክተር ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ትኩረት ሰጥቶ በራስ አቅም ሲታይ በቂ የሆነ በጀት የሚመድብ ቢሆንም የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ችግር ያጋጥማል።
አዲስ ዘመን፡- የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ የት የት ነው ያሉት ?
አቶ ሳሙኤል፡- የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ ስርጭት በዋነኛነት አስፈላጊው ጥሬ እቃ ያለበትን አካባቢ መሰረት አድርገው የተገነቡ ናቸው። ከአባይ ሸለቆ ቀጥሎ ከፍተኛው ክምችት ያለው መቀሌ እና አካባቢው ላይ ነው። እዛ ደግሞ መሶቦ ሲሚንቶ አለን።
ከአባይ ሸለቆ ጋር ተያይዞ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች አሉ። ሙገር፣ ደርባ፣ ኢስት ሲመንት ኮዬ ሲመንት፣ ሀበሻ ሲሚንቶ እጅግ ከፍተኛ በሆነ መልኩ ሰሜን ሸዋ እና በኦሮሚያ ክልል አሉ። በጣም ሰፋፊ ናቸው።
በአባይ ሸለቆ ውስጥ ሆኖ ወደ ኦሮሚያ በኩል ነው አብዛኛው የኖራ ድንጋይ ክምችት ያለው። ስለዚህ አባይ ከወንዙ ማዶ አማራ ክልል ከወንዙ ወዲህ ደግሞ ኦሮሚያ ክልል እንደመሆኑ መጠን ሙገርና ሙገርን ይዞ ባሉት የአባይ ገባሮች ጭምር ነው ይሄ ክምችት ያለው። ከፍተኛ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች ያሉት በዚሁ አካባቢ ነው። ከአጠቃላዩ የሲሚንቶ ኢንቨስትመንት ወደ 72 በመቶ የሚሆነው ያለው ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተሻሽሏል ብለዋል፤ አቅርቦቱ እና አገልግሎቱ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ ብቻ ስላልሆነ በሌላውም የኢንቨስትመንት መስክ ላይ ከፍተኛ ችግር ይታይበታልና ይህን እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ሳሙኤል፡- የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ላይ ያጋጠመው ችግር ሚያዝያ 2011 ዓ.ም አካባቢ ግድቦች በበቂ ሁኔታ ውሃ ባለመሙላታቸው የተነሳ የተፈጠረ ችግር ነበር። አሁን በሀገር ደረጃ መሰረታዊ የኃይል አቅርቦት ችግር የለም። ኃይል በበቂ መልኩ የመስጠት አቅም አለ። የኃይል መዋዠቅ እና መቆራረጥ ችግር አልፎ አልፎ ይከሰታል። ከማከፋፈያ መረቡ ላይ ለሌሎች ወርክሾፖች፣ ለመኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ወፍጮ ቤቶች ከዋናው መስመር ለሲሚንቶ ከሚሄደው ላይ ኃይል እየተሰጣቸው ስለሆነ ሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎቹ ላይ ጫና አለው። የሚበይደው ሰው ለምሳሌ ከመብራት ጋር ተያይዞ ችግር ቢፈጠርበት በአካባቢ ያለው ሲሚንቶ ፋብሪካ ይቆማል።
አዲስ ዘመን፡- ይሄን ችግር ለመፍታት ሌላ አማራጭ አልፈለጋችሁም?
አቶ ሳሙኤል፡- እንደሚታወቀው የሲሚንቶ ኢንዱስትሪው በጣም ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት ተጠቃሚ ነው። አንዳንዱ እስከ 40 ሜጋ ዋት ይጠቀማል። በሀገራችን ያሉት ወደ 14 የሚሆኑ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች አንዱ ፋብሪካ ከ30 እስከ 40 ሜጋ ዋት ከተጠቀመ፤ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል በመጠቀም ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ማለት ነው። ያኔ በዝናብ እጥረት ውሃ ግድቦቹን ባለመሙላቱ ካጋጠመን ችግር አልፈን ዛሬ ኃይል ማመንጨት ላይ በሀገር ደረጃ ከፍተኛ አቅም ተፈጥሯል። ምንም ችግር የለብንም።
አዲስ ዘመን፡- ሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ ከአቅማቸው በታች 30 በመቶ ብቻ ነው የሚያመርቱት የሚሉ አሉ። ስኬታማ ናቸው ማለት ይቻላል?
አቶ ሳሙኤል፡- አይደለም፤ ሀበሻ ሲሚንቶ ማድረቂያው ላይ ያጋጠመውን ችግር ለማስተካከል እየሠራ ነው። ለምሳሌ መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ 90 በመቶ ያህል የአቅሙን ይሰራል። የዳንጎቴ፣ የደርባ፣ የፎዬ ሲመንትና ሌሎቹ ከ65 እስከ 70 በመቶ የአቅማቸውን እየሠሩ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፡- የግንባታ ባለሙያዎች መንገዶችን ከሬንጅ ይልቅ በሲሚንቶ ኮንክሪት መገንባት የተሻለ ነው ይላሉ። የአውሮፕላን ማረፊያዎችን በማሳያነት ያነሳሉ። በዚህ ረገድ ምን ለመስራት ታስቧል?
አቶ ሳሙኤል፡- መንገዶችን እና አውሮፕላን ማረፊያዎችን በሲሚንቶ ኮንክሪት መስራት የቆይታ ዘመኑን እና ጥንካሬውን ለረዥም ጊዜ እንዲያገለግል ያደርገዋል። ነገር ግን ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት የሲሚንቶ የማምረቻ ወጪ እኛ ሀገር ትንሽ ከፍ ብሎ ነው ያለው።
ዋናው የኃይል ግብአት የሆነው የከሰል ድንጋይ ምርት ላይ ከ70 እስከ 75 በመቶ ኃይል እንዲሰጥ ወይንም ሲሚንቶ ማቃጠል የሚደረገው የፔትሮ ኬሚካል ውጤቶች በሆኑ ነገሮች ነው። የድንጋይ ከሰሉ የፔትሮ ኬሚካል ስሪት ነው። ሌላው ደግሞ የውጪዎቹ ፔትኮክ የሚባለውን የተወሰነ የሶስተኛው ትውልድ (ሰርድ ጀነሬሽን) የምንላቸውን ኬሚካል ሻፍቶች እየሰሩ በፔትኮክ ነው የሚጠቀሙት።
ስለዚህ አሁን ከሰሉን በሀገራችን በተሟላ ሁኔታ ተጠቅመን ወደ ሜታል ለመሄድ ነው ዝግጅት እያደረግን ያለነው። ይሄ ከተሳካ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ሲቻል የዛን ጊዜ የተሻለ ዋጋ ይኖረዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን፡- ወደፊት የውጭ ግብአት ሳንጠቀም በራሳችን አቅም መንገዶችን እና አውሮፕላን ማረፊያዎችን በሲሚንቶ ኮንክሪት መስራት እንችላለን ማለት ነው?
አቶ ሳሙኤል፡- ይሄንን በእርግጠኝነት ለማድረግ የሚያስችል ከፍተኛ የሆነ የሲሚንቶ ግብአት ክምችት አለን። ከሰሎችን እዚሁ በሀገራችን ውስጥ የማምረት እድሎች እየመጡልን ነው። ይሄ ሁኔታ ሲሳካ ወደፊት በአነስተኛ ወጪ ሲሚንቶ በጥራት ማምረት ስንጀምር መንገዶቻችንን እንዲሁም አውሮፕላን ማረፊያዎቻችንን በሲሚንቶ ኮንክሪት ብንሰራቸው በሁለት እና ሶስት አመት መጠገን አያስፈልገንም። ለብዙ አመታት ያገለግላሉ።
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን የሲሚንቶ ዋጋ ጨምሮአል። ምክንያቱ ምን ይሆን?
አቶ ሳሙኤል፡- በእኛ እምነት የሰሞኑ የሲሚንቶ ዋጋ መጨመር ሰው ሰራሽ ችግር ነው። አንደኛ ዳንጎቴ ሲሚንቶ ለተወሰነ ቀናት ለጥገና ቆመ። ደርባ ለአንድ 45 ቀናት በጥገና ምክንያት እሱም ቆመ። እነዚህ ሁለቱ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ለጥገና በሚቆሙበት ጊዜ አከፋፋይ ነጋዴዎች በየሱቁም የሚሸጡት ጭምር ከኋላ ያለው እደላ ሊቀንስ ይችላል የሚለውን የራሳቸውን ፍላጎት ተከትለው ዋጋ በመጨመር የፈጠሩት ችግር ነው። ሁለተኛው ጉዳይ ማዳበሪያ እና ለሕብረተሰቡ ፍጆታ የሚሆኑ ተፈላጊ ሸቀጦችን ወደ መሀል ሀገር ለማምጣት አብዛኛዎቹ ተሽከርካሪዎች ወደ ወደብ ይሄዳሉ። በዚህ ጊዜ እዚህ ያሉት ያንን በማየት አርቲፊሻል የትራንስፖርት ዋጋ ይጨምሩበታል ።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በመንግስት ደረጃ ሲሸጥ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋው ምን ያህል ነው ?
አቶ ሳሙኤል፡- በፋብሪካዎች የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ከፍተኛ ዋጋ 258 ብር ነው። ዋጋውን እንዳሻቸው የሚጨምሩት ጅምላ ሻጮች እና ቸርቻሪዎች ናቸው። ከላይ የጠቀስኳቸው የተለያዩ ምክንያቶችና በተጨማሪም የፋብሪካዎቹ ጥገና ላይ መሆን አለ። ደርባ እና ሙገር በቀጥታ ለማንኛውም አካል ሲሚንቶ በቀጥታ ይሸጣሉ። ከነጻ ገበያ አንጻር አምራቹ እስከ ችርቻሮ አይገባም በሚል የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ይከለክላል። አምራቹ ለጅምላ ሻጩ እንዲሰጥ እነሱ ደግሞ ለቸርቻሪዎች እንዲሸጡ ነው የሕግ ስርዓቱ የሚፈቅደው።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ በጣም እናመሰግናለን።
አቶ ሳሙኤል፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2012
ወንድወሰን መኮንን