እንኳን ለታላቁ የረመዳን ወር በሰላም አደረሳችሁ!
ታላቁ የረመዳን ወር በሂጅራ አቆጣጠር ዘጠነኛው ወር ነው። ረመዳን የተቀደሰ፣ የጾም፣ የጸሎት እና የመንፈሳዊነት ወር ነው። በእስልምና ሃይማኖት የረመዳን ጾም ከአምስቱ የእስልምና መሠረቶች ውስጥ ይመደባል። ይህንን ወር ከቢሊዮን የሚልቁ ሙስሊሞች በመላው ዓለም በጾም፥ በመልካም ተግባራትና በጸሎት ያሳልፋሉ። ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንደ ተናገሩት፣ በረመዳን ወር፣ የገነት በሮች ሁሉ ይከፈታሉ፣ የገሃነም በሮች ይዘጋሉ፣ ሰይጣናት ይታሠራሉ።
የረመዳን ወር ፈጣሪ ቅዱስ ቁርዐንን በቅዱስ ገብርኤል አማካኝነት ለነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ያወረደበት የተቀደሰው ወር ነው። በረመዳን ወር ውስጥ ቁርዐን የተወረደበት የተባረከች ሌሊት ‹ለይለተ አል-ቀድር› ወይም ‹የመወሰኛዪቱ ሌሊት› ትባላለች። በዚህች ሌሊት የሚተገበር መልካም ተግባር ከአንድ ሺህ ወራት መልካም ተግባራት የላቀ ምንዳ እንዳለው በቁርዐን ተጠቅሷል። ሙስሊሞች በረመዳን ወር ሙሉ ለመልካም ተግባራት ይሽቀዳደማሉ፤ ጊዜዋ ተለይታ ያልጠቀሰችውን ይህችን የ‹ለይለተል ቀድር›ን መልካም ተግባር ምንዳ ለማግኘት ግን በልዩ ሁኔታ ይትጋ።
እንደ ወትሮው ቢሆን፣ ይህ መልዕክት፣ የወራት ሁሉ አውራና ፊታውራሪ ለሆነው የረመዳን ወር እንኳን አደረሳችሁ በሚል በጎ ምኞት ዙሪያ ብቻ ያጠነጥን ነበር። የዚህ ዓመት የረመዳን ወር የሚውለው ግን ዓለም በኮሮና (ኮቪድ -19) በተጠቃችበትና ወረርሽኙን ለመከላከል አለመጨባበጥ፥ መራራቅና በቤት መወሰን ዋና የመከላከያ መንገዶች ሆነው በመላው ዓለም በሚተገበሩበት ጊዜ ነው። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል ሲባል በመላው ዓለም መስጊዶችን ጨምሮ ቤተ እምነቶች ሁሉ ተዘግተዋል። የእስልምና ሊቃውንት እንደሚያብራሩት አላህ በቸርነቱ ችግሩን አስወግዶ እርሱን በነፃነት እንድናመልከው ያስችለን ዘንድ በየቤታችን ሆነን ለፈጣሪያችን መጸለይና መማጸን እንችላለን። በኮሮና ምክንያት በየቤታችን ለመሆን የተገደድንበት ይህ ጊዜ ነቢዩ ሙሐመድ፣ ቲርሚዚ እንደዘገቡት «የትም ስፍራ ሆነህ አላህን ፍራው። ኃጢአት ከሠራህ በመልካም ተግባር አስከትል። ይጠርገዋልና። ከሰዎች ጋር በመልካም ሥነ ምግባር ተኗኗር::» በማለት ባልደረባቸውን ሙዓዝ ኢብኑ ጀበልን የመከሩበትን ምክር ያስታውሰናል።
በቀላሉ የሚተላለፉ የኮሮና ዓይነት ወረርሽኞች ሲከሠቱ መወሰድ ስላለባቸ ውና የጥንቃቄ ዕርምጃዎች ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ያስተማሩትን በዚህ ወቅት አበክረን ልንተገብረው ይገባል። ነቢዩ ሙሐመድ(ሰዐወ) የወረርሽኞችን መስፋፋት ለመከላከል ካስተማሩት አንዱ የሰዎችን እንቅስቃሴዎች መገደብ ነው። ቡካሪና ሙስሊም እንደዘገቡት እንዲህ ብለዋል፦ «በአንድ ስፍራ ወረርሽኝ መከሰቱን ከሰማችሁ ወደዚያ ስፍራ አትግቡ። ወረርሽኙ እናንተ ባላችሁበት ስፍራ ከተከሰተ ደግሞ ከስፍራው አትውጡ። » ብዙ ሰዎች ከሚሰበሰቡበት ቦታ፣ እንቅስቃሴዎች ከሚደምቁበት ሥፍራ መቆጠብ ራስንም ሆነ ሌሎችን ከዚህ ወረርሽኝ ለመጠበቅ ያስችላል።
የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል እየተተገ በረ ያለው ሌላኛው የጥንቃቄ ዕርምጃ በቫይረሱ የተያዙትን በልዩ ማቆያ ስፍራ ለይቶ ማስቀመጥ ነው። ይህ መከላከያ አቡ ዳውድ እንደዘገቡት «በተላላፊ በሸታ የተጠቁትን ከጤነኞቹ ለዩዋቸው።» በማለት ነቢዩ ሙሐመድ ካስተማሩት ትምህርት ጋር የተስማማ ነው። ሙስሊሞች በበሽታው የሚጠረጠሩትን ለመለየት ከጤና ባለሞያዎች ጋር ተባባሪ እንደምትሆኑ ሙሉ እምነቴ ነው። «ንጽሕና የእምነት ክፍል ነው» በማለት ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዳስተማሩት የራሳችንን፥ የቤተሰባችንንና የአካባቢያችንን ንጽሕና በመጠበቅ ኮሮናን በእምነትም በምግባርም እንከላከለው።
ከረመዳን ወር ዕሴቶች ዋናዎቹ ‹ዘካ›ና ‹ሰደቃ› ናቸው። ለሌሎች ማካፈል። ዘካ በታወቀ ተመን ከሀብት ላይ ለችግረኞች የሚሰጥ ሲሆን ሰደቃ ግን በብዙ መልኩ ሊደረግ ይችላል። ለሌሎች የሚሰጥ በጎ ነገር ለሰጭው ደስታን፣ ለተቀባዩ ደግሞ የኑሮ ድጋፍን የሚያስገኝ ነው። በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ኢኮኖሚው ተቀዛቅዟል፤ የዕለት ምግባቸውን ከዕለት ሥራቸው የሚያገኙ ሠራተኞች ኑሮ ከአቅማቸው በላይ ሊሆንባቸው ይችላል። በየመንደራችን ቤት የሸፈናቸው አያሌ ድሆች አሉ። ታድያ የዚህ ዓመት ዘካችንና ሰደቃችንን ለእነዚህ ወገኖች ካልደረሰ ለማን ሊሆን ነው? ነቢዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ‹‹ውኃ እሳትን እንደሚያጠፋ ሁሉ ልግስናም ክፋትን ከልብ መደምሰሻ ናት። » በማለት የነገሩንን ከዚህ ጊዜ በተሻለ መቼ በተግባር እናውለዋለን? ለሺ ዘመናት የቆዩ ዘካንና ሰደቃን የመሰሉ ዕሴቶች እያሉን አንድም ኢትዮጵዊ መቸገር የለበትም።
ዘካንና ሰደቃን የመሰሉ ለሌሎች ያለንን የማካፈል በረከት እያሉን አንድንም ወገን በኮሮና ምክንያት ችግር ጫንቃውን ሊሰብረው አይገባም። የዚህ ዓመት ዘካችንና ሰደቃችን ንግዳቸው የቀዘቀዘባቸውን፣ የቤት ኪራይ የሚከፍሉት ያጡትን፣ የትምህርት ቤት ክፍያ ለመክፈል ያቃታቸውን፣ ልጆቻቸውን ለመመገብ የከበዳቸውን እንዲያስባቸው ይሁን። ረመዳን የመጣው በሚያስፈልገን ጊዜ ነውና ለወቅታዊው ችግራችን መፍቻነት እንጠቀምበት። ‹‹ለመልካም ሥራ ተሽቀዳደሙ» (ቁርዐን 5፡48) በማለት ቁርዐን እንዳስተማረን እገዛችንን ከሚፈልጉት ወገኖቻችን ጎን ለመቆም እንሽቀዳደም። የገንዘብ ዐቅም የሌለን ሰዎች በመልካም ተግባራት ሁሉ እንሰማራ። እነዚህ መልካም ተግባራት በጉልበት፣ በዕውቀትና ለነፍስ አድን መመሪያዎች ተገዥ በመሆን ይገለጣሉ። ነቢዩ ሙሐመድ ‹‹መልካም ነገር ሁሉ ሰደቃ ነው» እንዳሉት።
ረመዳን የመሰባሰቢያ ወቅት መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን። ቤተሰቡ፣ ሠፈር መንደሩ፣ የቅርብ የሩቁ ሁሉ ለኢፍጣር ይሰባሰባል። ረመዳን ለብቻ ማፍጠር ሠርግን ለብቻ ከማድረግ በላይ ከባድ ነው። ግን ያለንበት ወቅት ይሄንን አልፈቀደልንም። በመስጊዶች እንደ ልባችን ተሰባስበን የተራዊን ሰላት(ጸሎት) ለማድረስ አልቻልንም። በየቤታችን ከሠፈር ጎረቤቱ ጋር ተሰባስበን በሰፊ ማዕድ ለማፍጠር አልቻልንም። ሆኖም ዐቅመ ደካማ የሆኑት ችግረኞችን በያሉበት ልናስፈጥራቸው እንችላለን።
የኮሮና ወረርሽኝ ለብዙ ነገሮቻችን ተቃራኒ ሆኖ የመጣ ነው። መሰባሰብን፣ መጨባበጥን፣ መቀራረብን፣ ለወረርሽኙ መስፋፊያ እየተጠቀመበት ነው። በዚህም ምክንያት እንዲህ ካሉ ነባር ልማዶቻችን ለጊዜው እንድንለይ ተገድደናል። የዘንድሮውን ረመዳን በየቤታችን ሆነን በቤተሰብ ደረጃ ብቻ አካላዊ ርቀታችንን ጠብቀን እንድናከብረው ሆነናል። ይሄንን የችግር ወቅት በፈጣሪ ዕርዳታና በጋራ ጥረታችን አልፈነው ረመዳንን እንደ ጥንቱ ዕሴቶቻችንን ጠብቀን እንደምናከብረው ተስፋ አደርጋለሁ።
በዚህ የተቀደሰ የረመዳን ዋዜማ ላይ ቆሜ፣ ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች፣ የነባር እምነቶች ተከታዮች፣ አማንያንና ኢአማንያን የሆንን ኢትዮጵያውያን ሁሉ፣ በዚህ ወረርሽኝ ላይ፣ በጋራ እንድንነሳ፣ ጥሪዬን አቀርባለሁ። የመላ ኢትዮጵያውያን ጸሎት፣ ከጋራ ጥረታችን ጋር አንድ ሆኖ የወረርሽኙን ጊዜ እንደሚያሳጥረው አምናለሁ። መንፈሳውያን አባቶችና የሕክምና ባለሞያዎች የሚነግሩንን በመተግበር፣ በዚህ ወቅት ለሀገራችን ልንሠራላት የሚገባንን እስከ መጨረሻዋ ጠብታ ድረስ በመሥራት፣ ኢትዮጵያን ከኮሮና ነፃ እናውጣት።
ረመዳን ከሪም!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር! ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ! ሚያዝያ 15 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2012