ጥር 22 ቀን በዚሁ አምድ ላይ “አገር በቀል እውቀት፤ ባህላዊ ህክምናን በቃል ግጥም” በሚል ርዕስ ባህላዊ ህክምናን እንደ አንድ አገር በቀል እውቀት ዘርፍ በመውሰድ በስነ ቃል (“Folk medicine”ን ያስቧል) አማካኝነት እንዴት እንደተገለፀ ለማሳየት ሞክረን ነበር።
ባህላዊ መድኃኒት (“Naturopathic medicine” ማለትም ይቻላል) ወይም ህክምና ምንነትና የፈዋሽነት ጠቀሜታው በተለያዩ መንገዶችና ዘዴዎች የሚገለፅ ሲሆን አንዱም የስነቃል ዘርፍ የሆነው ቃል ግጥም ነው። ለምሳሌ:-
ግዛዋ ካለ ደጅሽ፤
ለምን ሞተብሽ ልጅሽ።?
ይህ ቃል ግጥም “ግዛዋ” ስለሚባለው ተክልና ወደር የለሽ የፈዋሽነት ድንበሩ የት ድረስ እንደሆነ የሚናገር ሲሆን፤ እፁ ዝም ተብሎ የትም የሚበቅል፣ ወፍ ዘራሽ ብቻ ሳይሆን ታስቦበት፤ ይሁነኝ ተብሎ ካለበት ተፈልጎ መጥቶ በቅርብ እጓሮ የሚተከል መሆኑን ሁሉ በግልፅ እንረዳለን። (ዛሬስ? ፈረስ የሚያስጋልብ ግቢ የያዘው ሁሉ የሚያውቀውንና የሚፈውሰውን ዳማ ከሴ፣ ነጭ ሽንኩርት … ከመትከል ይልቅ የማያውቀውንና የማይጠቅመውን የፈረንጅ ዛፍ ቢተክል ይመርጣል።)
አንድ ቆየት ያለና ከወደ ቻይና የተለቀቀ መረጃ እንደሚያመለክተው ከተለያዩ አፍሪካ አገራት ምርቱን በማስገባት የምትታወቀው ቻይና በአሁኑ ጊዜ ነጭ ሽንኩርት ከ800 በላይ ለሆኑ የበሽታ አይነቶችን እንዲፈውስ አድርጋ ስራ ላይ አውላዋለች። “እኛስ?” “የት ነህ?” ያላልነው ነጭ ሽንኩርትና ህክምናዊ ፋይዳው ዛሬ በእግር በፈረስ ስንፈልገው ከዋጋው ጀምሮ እየገላመጠን ማለፉን ስናስብ ምን ታዝቦን ይሆን??
ፕሮፌሰር ሪቻርድ እንዳጠኑት ዘመናዊ ህክምና ከመምጣቱ በፊት ባህላዊ 100 በ100፤ ዘመናዊ ህክምና ከመጣ በኋላ 80 በመቶ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቀምው ባህላዊ የህክምና ዘዴን ነው። “በመሆኑም” ይላሉ ሪቻርድ “ይህንን አገር በቀል እውቀት ወደ ዘመናዊ እውቀት አሳድጎ መጠቀም እጅግ አስፈላጊ ሲሆን ለዚህም የሚመለከተው አካል አስፈላጊው ጥረት ሁሉ ሊደረግ ይገባል።”
ከግማሽ በላይ ዕድሜያቸውን በባህል መድኃኒት ጥናት ላይ ያሳለፉትና “የኢትዮጵያ ባህላዊ መድኃኒትና ሕክምና የምዕተ-ዓመት ጉዞ” (‘A century of Magico-Religious Healing: The African, Ethiopian case (1900-1980)) በሚል ርዕስ ለንባብ ያበቁት በደሴ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አሰፋ ባልቻ እንደሚሉት ኢትዮጵያውያን “በባህል ህክምና ዘርፍ በጽሁፍ የሰፈሩ ጥንቅሮችን፣ የቁጥርና የፊደላት ማስላት፣ ለመናፍስት፣ ዕፅዋትን፣ ማዕድናትን እንዲሁም የእንስሳት ተዋፅኦ ፈውስን ማግኘት ኢትዮጵያውያን እንዴት” ተክነንበትና ልቀንበት እንደነበር ይነግሩናል። አሁን ላይ መዘናጋታችንን የሚነግሩን ዶ/ር አሰፋ “አሁንም ቢሆን ለራስ ህመም ጠንከር አድርጎ ማሰር፣ ለጉንፋን ዝንጅብል ማር፣ ለሆድ ድርቀት ተልባን በጥብጦ መጠጣት ብዙ ኢትዮጵያውያን ለራሳቸውም ሆነ ለወዳጆቻቸው ፈውስ” እንደሚመክሩ ይነግሩናል።
“ቃር እና የልብ ማቃጠል፤ ቶንሲል፤ ከፍተኛ የደም ግፊት፤ ስኳር በሽታ፤ ተቅማጥ፤ የደም ማነስ፤ ከፍተኛ ኮሌስትሮል ችግር፤ አስም፤ የጀርባ ህመም፤ የኩላሊት ጠጠር፤ እና ሌሎች በርካታ ህመሞች በአገራችን ባህላዊ ህክምና እንደሚፈወሱ እና፤ “እነዚህ መድኃኒቶች አብዛኞቻቸው ከምንመገበው የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የቅመማ ቅመም አይነቶች እና አስፈላጊ በቤት ውስጥ የሚዘጋጁ ተፈጥሯዊ የሆኑ ቁሶች” መዘጋጀት እንደሚችሉ የሚናገሩት ተመራማሪው አሁንም የሚመለከታቸው አካላት ቆም ብለው ማሰብ እንደሚገባቸው ይመክራሉ።
“ጣልያን የሀገረ-ሰብ መድኃኒትና ህክምና አዋቂዎች ናቸው ባለቻቸውና በተለይም ደግሞ የቤተ-ክህነት ትምህርት በቀሰሙ የመስኩ ባለሙያዎች ላይ በሰነዘረችው ጥቃትና የዘመናዊ ህክምናን ለማስፋፋት ባደረገችው ጥረት የተነሳ በቀደሙት ዘመናት የበላይነት የነበረው የባህል ህክምና መዳከም ጀመረ” የሚሉት ዶ/ር አሰፋ “ባህላዊ መድኃኒት ትልቅ ስፍራ ነበረው፤ አሁንም እየተሰራበት ነው። የዘመናዊ ህክምና አቅርቦት ዝቅተኛ መሆን እንዲሁም መወደድ አማራጩን ወደ ባህል መድኃኒት እንዲያዞር አድርጓል” ሲሉም በአሁኑ ወቅትም የባህላዊ ህክምናን አስፈላጊነት ከጤና ባለፈም ከኢኮኖሚ አኳያ ያስረዳሉ።
“እኛ የምናውቀው የእፅዋት ስብስቡን ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለመድኃኒትነትም ይጠቀሙባቸው የነበሩ የማዕድኖች ስብስብ ነበራቸው” የሚሉት ዶክተር አሰፋ “ኢትዮጵያውያን ከነበሩባቸው ተፈጥሯዊ ችግሮችና ጦርነቶች ጋር ረዥም እድሜ በመኖራቸው ምክንያት የተለያዩ ችግሮች ገጥመዋቸዋል፤ እነዚህን ችግሮች ለመቋቋምም በርካታ [አገር በቀል እውቀትን እና] ባህላዊ መድኃኒቶችን ተጠቅመዋል። ይህም በመድኃኒት ምን ያህል የላቁ እንደነበር ማሳያ ነው” የሚሉት ዶክተሩ “ከቀላል ስብራት ጀምሮ ውስብስብ ተውሳክና እንደ ካንሰር ወይም በተለምዶ መጠሪያው ነቀርሳ የመሳሰሉ የውስጥ በሽታዎችን ማከም ይሞክሩ የነበሩበት አገር ሰዎች መኖሪያ ለመሆኗ፤ በአረብኛ፣ በግዕዝ፣ የማጣቀሻ ፅሁፎችም” መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ “ይህን ያህል ዓመት ተጉዘን አንድ የባህል መድኃኒትን የሚመለከት ተቋም” እንኳን የሌለን መሆናችንን በቁጭት ይናገራሉ።
ከአራት አመት በፊት የአዲስ አድማስ ጋዜጣ እንግዳ የነበሩትና ከ25 አመታት በላይ በባህላዊ ህክምና ላይ ጥናትና ምርምር ያደረጉት “ለ11 ዓይነት በሽታዎች ፍቱን መድኃኒት አለኝ” የሚሉት ዶ/ር ኢያሱ ኃ/ሥላሴ “ኢትዮጵያ ውስጥ ከ80ሺ በላይ የባህል መድኃኒት አዋቂዎች ያሉ ቢሆንም በማህበር ተደራጅተው ያሉት ግን ከዘጠኝ ሺህ የሚበልጡ አይደሉም፡፡” ይላሉ፡፡
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በዚሁ ገዳይ ላይ ሰፋ አድርገው ካጠኑት አንዱ ናቸው። በጥናቶቻቸውም ቱባ አገር በቀል እውቀት እንዳለን፣ ከእነዚህ መካከልም አንዱ ይሄው ባህላዊ መድኃኒት/ ህክምና መሆኑን፤ በመሆኑም ከመካከለኛው ዘመን (ከ1066–1485፤ በእኔ የተጨመረ) ጀምሮ የውጪ ሰዎች አይናቸውን እንደጣሉበትና ተደጋጋሚ ጥናቶችን ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል። መፍትሄውንም “ኢትዮጵያ በፍጥነት ወደዚህ ዘርፍ ጥናት እንድትገባ”፣ ለጥናቱም የተለያዩ ዘዴዎችን እንድትጠቀም፣ ለጥናቱ “መረጃ ምንጭነት ከሚያገለግሉት አንዱ ቃላዊ ሥነ ጽሁፍ (ሥነ-ቃል)” እንዲሆን፤ በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በተለይም በግዕዝ የተፃፉና የተነገሩ ሀሳቦች በአግባቡ እንዲመረመሩ፣ ከሁሉም በላይ በባህላዊ መድኃኒት/ህክምናና አገር በቀል እውቀት ላይ ብቻ ያተኮረ ሙያዊ ህትመት “Journal of traditional Ethiopian Medicine” እንዲዘጋጅ አበክረው አሳስበዋል። እንደ ፕሮፌሰሩ ጥናት ከሆነ ስንዘረፍ ኖረናል፤ አገር በቀል እውቀታችን ከስሩ ተመንግሎ እየጠፋ ነው፤ ስለዚህ ፈጥነን ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብቶቻችንን ለራሳችን ጥቅም ልናውለው ይገባል።
ሀሳባችንን በዶክተር አሰፋ አስተያየት እንዝጋው፤ “ይህን የዕውቀት ሀብት እንደማይረባና እንደማይጠቅም አድርገን ነው የምናየው። የእኛን ሀገር የባህል ህክምና ለምን ትኩረት እንደነፈግነው አላውቅም፤ ትውልድ ባለፈ ቁጥር ትልቅ ሀብት እያጣን ነው። በጣም የሚከበሩ አዋቂ ሰዎችን እያጣን ነው። የአንድ በሽታ መድኃኒት ማወቅ ማለት እኮ በአንድ ዩኒቨርሲቲ 20 ዓመት የሰለጠነ ሰው ከአንድ አካል በላይ የሚያውቀው የለም።’’
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2012
ግርማ መንግሥቴ