በኪነ ጥበብ ውስጥ የአንዲት አገር ምንነት ይታያል። ምክንያቱም ኪነ ጥበብ የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅ ነው። ሃያል የሚባሉ አገራት ገናናነትን ያገኙት በኪነ ጥበብ ነው። ለምሳሌ አሜሪካና ህንድን የምናደንቃቸው ሁላችንም አሜሪካም ሆነ ህንድ ሄደን አይደለም። የአገራቸውን ባህልና ታሪክ በመኖር አውቀነው ሳይሆን በኪነ ጥበብ ሥራዎቻቸው በተለይም በፊልሞቻቸው አማካኝነት በደረሱን መልዕክቶች ነው።
ወደ ኢትዮጵያ እንምጣ። በኢትዮጵያ ውስጥ ከአርሶ አደር እስከ ወታደር፣ ከዘፈን እስከ ለቅሶ…. ነገሮች ሁሉ በኪነ ጥበብ ይገለጻሉ። አርሶ አደሩ የሥራ እንቅስቃሴዎቹን ሁሉ የሚገልጸው በኪናዊ ለዛ ነው። ብሶትና ደስታውን የሚገልጸው በጥበባዊ እንጉርጉሮዎች ነው። ለዚህም ነው ኪነ ጥበብ የአንድን ማህበረሰብ ስነ ልቦናዊ ምንነት ይገልጻል የሚባለው።
ለዛሬው የምናወራው በጀግንነት ላይ ስለሚያተኩሩ የጥበብ ሥራዎች ነው። ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ የኖረች አገር መሆኗን ዓለም ያውቃል። ከእነዚህ የጀግንነት መገለጫዎቿ አንዱ ደግሞ የዓድዋ ድል ነው። ዓድዋን ምክንያት አድርገን የኢትዮጵያውያንን የጀግንነት ስነ ልቦና የኪነ ጥበብ ሥራዎች እናያለን።
የኢትዮጵያ ህዝቦችን ጀግንነትንና አይበገሬነትን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወርዱ ሲወራረዱ ከመጡ የስነ ቃል ትውፊቶች መረዳት እንችላለን። ይህ ከዓድዋ በፊትም ሆነ ከዓድዋ በኋላ የነበረና ያለ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነው። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ግን የምናተኩረው ዓድዋ ላይ ትኩረት አድርገው የተሰነኙ ስንኞች ላይ ነው።
የዓድዋን ድል የተመለከቱ በርካታ የኪነ ጥበብ ሥራዎች አሉ። የመድረክ ቴአትሮች፣ግጥሞች፣ ጭውውቶች፣ ስነጽሁፎች እና ፊልሞች ውስጥ የዓድዋ ታሪክ ይካተታል። በአብዛኛው ደግሞ የቃል ግጥሞችና የመድብል ግጥሞች ናቸው። ከሁሉም እናያለን። እነዚህ ዓድዋን የተመለከቱ የኪነ ጥበብ ሥራዎች በዓድዋ ጦርነት ወቅትና ከጦርነቱ በኋላ ኩራትን ለመግለጽ የተሰነኙ ናቸው። አንዳንዶቹ በጦርነቱ ወቅት የጦርነቱ ተሳታፊዎች የገጠሟቸው ናቸው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በዚያው በጦርነቱ ወቅት ህዝቡ አርበኞችን ለማበረታታትና የደስታ ስሜቱን ለመግለጽ የገጠማቸው ናቸው። ሌሎች ደግሞ ታዋቂ ድምጻውያን የዓድዋን ድል ለማወደስ የዘፈኗቸው ናቸው። በወቅቱ ከነበሩት እንጀምር።
አንዳንዶቹ በቅኔ የሚነገሩ ናቸው። ለምሳሌ አንዱ ቅኔ እንዲህ የሚል ነበር።
እስኪ ለጣሊያኖች መዲሃኒት ስጧቸው
የሚያስቀምጥ ሳይሆን የሚያስመልሳቸው
የዚህን ግጥም ትርጉም በወቅቱ ዓውድ እንረዳው። ዘመናዊ ህክምና ባልነበረበት በዚያ ዘመን ለመድሃኒትነት የሚያገለግሉት ከቅጠላቅጠልና ሥራሥር የሚዘጋጁት የባህል መዲሃኒቶች ናቸው። እነዚህ መዲሃኒቶች ህመምን የሚፈውሱት ወደታች (በዓይነ ምድር መልክ ማለት ነው) እና ወደላይ (በማስመለስ) ነው።
የዚህ ግጥም ሰም ጣሊያኖች ታመዋልና መዲሃኒት ስጧቸው ነው። መዲሃኒቱ ግን በመቀመጥ (በዓይነ ማድር ማለት ነው) መልክ ሳይሆን በማስመለስ የሚፈውስ መሆን አለበት የሚል ነው። ዋናው ትርጉም ያለው ወርቁ ላይ ነው።
ጣሊያኖች ታመዋል። ጤነኛ ቢሆኑ ኖሮ እንደ ኢትዮጵያውያን አይነት ጀግና ህዝብ እንወራለን ብለው አያስቡትም ነበር። የእነዚህ ሰዎች መድሃኒት ቅጠላቅጠልና ሥራሥር ሳይሆን፣ ጎራዴና ጥይት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲቀመጡ ሳይሆን በመጡበት እግራቸው ወደ አገራቸው የሚመልስ መሆን አለበት የሚል መልዕክት አለው።
ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር ሲያሻት በመኪና ሲያሻት በፈረስ እየሄደች ነበር። የጣሊያን ወታደሮችም ሰውነታቸው ከኢትዮጵያ ተዋጊዎች ጋር ሲነጻጸር የለሰለሰና ያማረባቸው ናቸው። ዳሩ ግን ምን ዋጋ አለው እንዲህ ሆነ!
የሞሶሎኒ አሽከሮች ሁሉም ሎጋ ሎጋ
ሲመጡ በፈረስ ሲመለሱ በአልጋ
እንግዲህ በፈረስ ሲንሸራሸር የነበረ ሸበላ የጣሊያን ጦረኛ ፈረሱን መቀማቱ ሳያንስ በእግሩ እንኳን እንዳይሄድ በጥይት አንካሳ አደረጉት ማለት ነው። የሞተው ሞቶ የቆሰለውም በአልጋ እንዲወሰድ ተደረገ የሚል መልዕክት አለው።
የዓድዋ ድል አስገራሚ ታሪክ የሆነው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ያላት ጣሊያን ‹‹ኋላ ቀር›› እያሉ በሚሳለቁባት ኢትዮጵያ መሸነፏ ነው። ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀ ወታደር ባህላዊ ጎራዴና ጋሻ በያዘ ወታደር መማረኩ እስከዛሬም ለብዙዎች ትንግርት ነው። ጣሊያን በራሱ መሳሪያ ተወጋ። ራሱ ይዞት በመጣው መሳሪያ ተገደለ። ለዚህም ነው የወቅቱ ከያኒያን እንዲህ ያሉት።
በሰራው ወጨፎ ባመጣው እርሳስ
ተፈፀመ ጣሊያን ሐበሻ እንዳይደርስ
በዓድዋ ጦርነት ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ጀግኖች ተወድሰዋል። እነዚህን ጀግኖች በማወደስ ለሌሎች ጀግኖች ተጨማሪ ሞራል መስጠት ተችሏል። ከእነዚህም አንዱ ራስ አሉላ አባ ነጋ ናቸው። ራስ አሉላ አባ ነጋ በርካታ የጦር ገድል ነው ያላቸው። በኩፊት፣ በዶጋሊ፣ በጉንደት፣ በጉርዓ፣ በሰሀጢ፣ በመተማ፣ በዓድዋ ከወራሪዎች ጋር ተፋልመው አንፀባራቂ ድሎችን ያስመዘገቡ ናቸው። በዚህ ጀግንነታቸው እንዲህ ተብሎላቸዋል።
ጣሊያን ሰሀጢ ላይ እግሩን ቢዘረጋ
እንደ ገብስ ቆላው አሉላ አባ ነጋ
ይቺኛዋ ስንኝ ዓድዋ በመጣ ቁጥር በየመድረኩና በየመገናኛ ብዙኃኑ ተደጋግማ ትነገር እንጂ ስለአሉላ አባ ነጋ ሌሎች የውዳሴ ግጥሞችም አሉ።
ዮሐንስ መብቱን ላሉላ ቢሰጠው
እንደ ቀትር እሳት ቱርክን ገላመጠው
ጣልያንም ወደቀ እያንቀጠቀጠው
አጭዶና ከምሮ እንደ ገብስ አሰጣው!
አሉላ አባነጋ የደጋ ላይ ኮሶ
በጥላው ያደክማል እንኳንስ ተኩሶ!
አሉላ አባነጋ ካስመራ ቢነሳ
ቢቸግረው ጣሊያን አለ ፎርሳ ፎርሳ።
ጣሊያን በሀገርህ አልሰማህም ወሬ?
የበዝብዞች አሽከር የነ ሞት አይፈሬ
ዘለው ጉብ ይላሉ እንደ ጎፈር አውሬ!
ሌላኛው ጀግና ደግሞ ፊት አውራሪ ገበየሁ ናቸው። ፊት አውራሪ ገበየሁ በጦርነት መሃል እየገቡ የሚፎክሩ ነበሩ። በዚህ ጀግንነታቸው ጣሊያንን ሲያርበደብዱ ነበርና እንዲህ ተባለላቸው።
የዓድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው
ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው!
ፊት አውራሪ ገበየሁ በተፋፋመ ጦርነት ውስጥ ገብተው ሲዋጉ በጣሊያን መድፍ ተገደሉ። ዳሩ ግን ጣሊያን ኢትዮጵያውያንን ማሸነፍ አልቻለም። ቆራጥ ጀግኖች እነ ባልቻ ሳፎ (ባልቻ አባ ነፍሶ) ሃይለኛ የመድፍ ተኳሽ ሆነው ጣሊያንን አጥረገረጉት። ወዲያውም እንዲህ ተባለ።
ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ!
የዓድዋ በዓል በመጣ ቁጥር የሚታወሱት ሌሎች ግጥሞች ደግሞ ራሳቸው ንጉሱን አጼ ምኒልክን የተመለከቱት ናቸው። ዳግማዊ አጼ ምኒልክ በብልህነታቸውና በጀግንነታቸው ኢትዮጵያን ከጣሊያን ወረራ ታድገዋል። እነሆ ብቸኛዋ በቅኝ ያልተገዛች የአፍሪካ ነፃ ሀገር እየተባለች እንዲትጠራ አደረጉ። ህዝቦቿ በራሳቸው ባህልና ወግ እንዲኮሩ አደረጉ። ለዚህም ነው እንዲህ የተባለው።
ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ
ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ ሐበሻ
እስኪ አሁን ደግሞ በቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወርዱ ሲወራረዱ ከመጡት እንውጣና ወደ ሌሎች ሥራዎች እንሂድ። እነዚህኞቹ ባለቤት ያላቸው ናቸው። በዓድዋ ታሪክ ውስጣቸው ሀሴት ያደረገ ከያኒያን የሰሯቸው ናቸው። ገጣሚያንና ድምጻውያን ማለት ነው። ከእነዚህም ውስጥ የዓድዋ በዓል በመጣ ቁጥር ሁላችንም የምናውቃት ድምጻዊት እጅግአየሁ ሽባባው (ጂጂ) አንዷ ናት።
የጂጂ የዓድዋ ዘፈን እያንዳንዷ ስንኝ የምትተነተን ናት። ጥልቅ መልዕክት ያለው ነው። ‹‹ምን ማለት ይሆን?›› ብለን ስናስብ እያደር እየተገለጠልን የሚሄድና የሚመስጥ መልዕክት ያለው ነው። እስኪ ከስንኞቹ ውስጥ ‹‹ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን›› የሚለውን ቃል እንውሰድ። አንድ ጀግና ወደ ጦር ሜዳ ሲሄድ አልሞትም ብሎ አይደለም። የሚሄደው ወገኑን ለማዳን ነው። ራሱ ሞቶ ሌላውን ማዳን ማለት ነው።
ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን
ሰውን ሲያከብር
በደህንነት በፍቅር በክብር ተጠርቶ
በክብር ይሄዳል ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ
የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነፃነት
ሰው ተከፍሎበታል ከደም እና ከአጥንት
አድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትላንት
መቼ ተነሱና የወዳደቁት።
‹‹ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት›› አዎ! ይህ የዓድዋ ድል የተገኘው በልመና ወይም በግዥ አይደለም። በሰው ሕይወት ነው የተገኘው፤ የብዙዎች አጥንት ተከስክሶበትና ደም ፈሶበት ነው። ይህ የድል ታሪክ ዛሬም ነገም ይወደሳል፤ የጀግኖቻችን ውለታ ነውና! መቼ ተነሱና ነው የምንተወው?
እነዚህ ተወዳጅ አርቲስቶች በዘመን ተሻጋሪ ሥራዎቻቸው ጀግኖቻችን እንዳይረሱ አድርገዋል። ሥራዎቻቸውን ለትውልድ አስተላልፈዋል። ከእነዚህ ዘመን ተሻጋሪ ድምጻውያን አንዱ ተሾመ አሰግድ ነው። ‹‹እንዲያው ዘራፌዋ›› በሚለው ዜማው ጀግኖችን እንዲህ ያስታውሳል።
መቅደላ አፋፉ ላይ ጎበዝ ወንድ ሆነበት
በመተማም ጎራ ጀግኖች አንድ ሆኑበት
እንዳይሞት ሆነ እንጂ ስሙን እንዳይቀብሩት
የመቅደላን መንደር የዶጋሊን ሜዳ
የማይጨው ዓድዋን የመተማን ሜዳ
ተዳኘበት እንጂ መች ዋኘበት ባንዳ
አፄ ቴዎድሮስ አባ ታጠቅ ካሳ
እምዬ ምኒልክ ጥራኝ የእኔ አንበሳ
በደም ታዋጋለህ በአካል ባትነሳ!
ተሾመ አሰግድ በዚህ ዜማው ኢትዮጵያ ጥንትም የጀግኖች አገር እንደሆነች ይናገራል። አጼ ቴዎድሮስ፣ አጼ ዮሐንስ፣ አጼ ምኒልክ እና የጦር አርበኞችን ያወድሳል። ድል ያደረጉባቸውን ቦታዎች ይጠቅሳል። ጠላት ከእነዚህ ድሎች መማር እንዳለበት ይነግረናል።
ሌላኛዋ ከያኒ ራሄል ዮሐንስ ናት። ‹‹ምኒልክ›› በሚለው ዜማዋ እንዲህ ትላለች።
ብወጣው በእግሬ እንጦጦን
አላገኝም ወይ ጣይቱን
ፍቅሩን አብዝቶ ያለ ልክ
ዛሬም ይባላል ምኒልክ
እስኪ ወደ አንኮበር ተነሱ እንዝለቀው
እኛ አናየውም ወይ ምኒልክ ቢለቀው
የጣይቱን ማጀት ቢፈልጉት እዛ
አይጠፋም እስከ አሁን የጥጃ መዓዛ
እስኪ አንተ ሰውየ እንደ አባትህ ሥራ
ከጓዳ እንድትቀዳው ወተቱን በእንስራ
ያገኘህ እንደሆን ግቢን ከአዲስ አባ
የደግ አደራሽ ነው ሰተት ብለህ ግባ
አይቆረቁረውም እንግዳ ደጁን
ገብቶ ይጥገብ እንጂ ሥጋና ጠጁን
ያ ሁሉ ደስታ ፊቴ ይደቀናል
ሰው እንዴት በሄደው ባለፈው ይቀናል
ያ የፍቅር ጊዜ ያ የደስታ ቀን
ደግሞ በአይኔ መጥቷል እፊቴ ሊደቀን
ይህ የራሄል ዮሐንስ ዘፈን የአጼ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱን ዘመን ያሳየናል። ደግነታቸውን ይነግረናል። ይሄን ደግነታቸውን ልናስታውስላቸው እንደሚገባ ይገልጻል።
‹‹አንኮበር›› በሚለው የገነት ማስረሻ ዜማ ውስጥ ደግሞ ይሄን እናገኛለን።
እሱማ መቼ ጠፋው ብልሃቱ
ከበስተግራው አለች ፀሐይቱ
ደግ ሰው ነበር አመለ ምቹ
ፍቅር መጋቢ ለወገኖቹ
ከእንጦጦ ጋራ ዓድዋ ድረስ
ሰራዊት ይዞ በእግር በፈረስ
ስንት ቀን ይሆን የፈጀበት
ስንት በጋና ስንት ክረምት
ቀና ነው ልበ ቀና
የወገን ቤት ያቀና
አዛኝ ነው አመዛዛኝ
ሃቀኛ ብርቱ መዛኝ
እምየ አባ ዳኘው
በፍቅር የተቃኘው
ቋንቋ ሃይማኖት ሳያግደው
መሃሉን ከዳር ያገናኘው
ህዝቡን አንድ አርጎ ሄደ ስምሪት
በአንድ ባንዲራ በአንድ ነጋሪት
እምየ ዳኘው ልበ ተራራው
በከዘራ ነው ጦሩን የመራው
ምን ቢባል ምን ቢወራ
ህያው ነው የሱ ሥራ
ያ ቢሄድ ያ ቢመጣ
እሱስ ከልቤ አይውጣ
የጎራዴው ብልጭታ
ጠላትን ድባቅ መታ
አንኮበር ላይ ደገሰው
ዓድዋ ላይ ለኮሰው!
‹‹እሱማ መቼ ጠፋው ብልሃቱ፤ ከበስተግራው አለች ፀሐይቱ›› ይላል የገነት ማስረሻ ዘፈን። ከበስተግራው ማለት እቴጌ ጣይቱ የአጼ ምኒልክ ሚስት መሆናቸውን ለመግለጽ ነው፤ ሚስት ደግሞ ግራ ጎን ተብላ ትጠራለች። ለአጼ ምኒልክ ስኬት ሁሉ የእቴጌ ጣይቱ ብልህነት እንዳለበት ይነገራል።
‹‹ቋንቋ ሃይማኖት ሳያግደው መሃሉን ከዳር ያገናኘው››፤ የዓድዋ ድል የተገኘው የኢትዮጵያ ህዝቦች ከጫፍ እስከ ጫፍ ተጠራርተው በመሄድ ነው። አንድ ልብ፣ አንድ ሀሳብ ሆነው፤ ለአንድ ዓላማ ከአራቱም አቅጣጫ እየተመሙ ሄደው ጠላትን ድባቅ አድርገው መጡ። አንኮበር ላይ የተደገሰው የዓድዋ ጦርነት ዓድዋ ላይ ተለኮሰ፤ ዓድዋ ላይ የተለኮሰው እሳት ጠላትን ለብልቦ መለሰ።
ሁለት መልዕክት ባለው ሀሳብ እንሰናበት። ከነገ ወዲያ የዓድዋ ድል በዓል ነው። የነገ ሳምንት ደግሞ ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን ነው። ስለሴቶች ሲነሳ ደግሞ እቴጌ ጣይቴን አለማስታወስ አይቻልም። የሴትን ብልህነትና ጀግንነት ያስመሰከሩ ጀግና ናቸዋ!
እቴጌ ጣይቱ ጀግንነትን ከብልህነት ጋር የያዙ ናቸው። በጦርነት ጊዜ ቁጣና ችኩልነት ብቻ እንደማያዋጣ፤ ይልቁንም ብልህነት መኖር እንዳለበት አሳይተዋል። ይህን የእቴጌ ጣይቱን ብልህነትና ጀግንነት የሚገልጸውን የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ስንኝ መሰናበቻ አድርገነዋል። ክብር ለጀግኖቻችን!
የቀፎው ንብ ሲቆጣ ስሜቱ
ከፊት ሆና መራችው ንግስቲቱ!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 21/2012
ዋለልኝ አየለ