ባለፈው ሳምንት በያዝነው ቀጠሮ መሰረት እነሆ ስለፊላ ሙዚቃ ምንነት ጊዜ ሰጥተን ልናወራ ነው። ደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ ነን። ስለዚህ የሙዚቃ አይነት ብዙም አልተባለም። ስለውጭው ዓለም እንጂ ስለራሳችን እንደማናጠና እና እንደማናውቅ አንዱ መገለጫችን ነው። ዓለም የሚያቆለጳጵሳቸው እነ ሞዛርትና ቤትሆቨን በ18ኛውና 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ብቅ ያሉ ናቸው። ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ግን ከእነርሱ ከሺህ ምናምን ዓመታት በፊት ዜማን ፈጥሯል። ዳሩ ግን እንኳን በዓለም በኢትዮጵያም የዚህ ጥበበኛ ስም ብዙም ሲነሳ አይደመጥም።
አንድ የታወቀ ነገር ካለ በዚያው ላይ ብቻ መረባረብ ነው። በተለይም ከባህር ማዶ የተገኘ ከሆነ ያለመታከት ስዘምርና ስናወድስ መኖር ጠባያችን ሆኗል። እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ መንግስት ባለን ላይ መኩራት አይሆንልንም። ያሉንን ሃብቶች እንኳን ለሌላው ልናስተዋውቅ ለራሳችንም በአግባቡ አናውቃቸውም። ለዚህም ነው የሙዚቃ ቅኝቶቻችን እንኳን ስንት እንደሆኑ አንድ ወጥ እይታ የሌለን። አንዳንዶቹ አምስት ናቸው ይላሉ፤ አብዛኞቹ ደግሞ አራት ናቸው ይላሉ። አንዳንዶቹም ከአራትም ከአምስትም በላይ ናቸው ይላሉ። ለዛሬው ይሄን ለዘርፉ ባለሙያዎች እንተወውና ስለፊላ የሙዚቃ ምንነትና ቅኝቶች ላይ ትኩረት እናድርግ። ዋቢ ያደረግነው በፍሬው ተስፋዬ የተጻፈውን ‹‹ፊላና ሌሎች ሙዚቃዊ ጥበባት በጋርዱላ ዲራሼ›› መጽሐፍን ነው።
በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ የተሰሩ ጥናቶችና ምርምሮች የአካታችነት ችግር እንዳለባቸው ፀሐፊው ጠቅሰዋል። የሙዚቃ ቅኝቶች በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በወሎ አካባቢ ብቻ የተወሰኑ ናቸው። ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ያሉትን የአገሪቱን የሙዚቃ ቅኝቶችና ስልቶች አልተጠኑም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደረጉ ጥናቶች ግን የጋምቤላና የደቡብ ኢትዮጵያ ሙዚቃዎች መጠነኛ ትኩረት አግኝተዋል።
በጋሞ ከፍታ ቦታዎች የሚገኙ ዶኮዎችና የጋርዱላ ዲራሼዎች የሚጫወቷቸው ሙዚቃዎች ‹‹ሆሞፎኒክ›› ምድብ ውስጥ የሚገኙ ናቸው። በተለይም የፊላ ሙዚቃ በኢትዮጵያ ብቸኛ ባለሰባት ኖታ የሙዚቃ መሳሪያ ነው። በመጀመሪያ ፊላ ምንድነው? የሚለውን እንመልከት።
ፊላ ሦስት ትርጓሜዎች አሉት። ፊላ ሙዚቃ ነው፤ ፊላ ውዝዋዜ (ዳንስ) ነው፤ ፊላ የሙዚቃ መሳሪያ ነው። ፊላ እንደ ሙዚቃ መሳሪያ ሲታይ ከአንድ ሜትር እስከ አምስት ሜትር ርዝመት ያለው የትንፋሽ መሳሪያ ነው። የሚዘጋጀው ከቀርቀሃና ከሸንበቆ ነው። እነዚህ ከሸንበቆና ከቀርቀሃ የሚዘጋጁ የሙዚቃ መሳሪያዎች በአንድ በኩል ክፍት፤ በሌላኛው በኩል ድፍን ናቸው። የፊላ የሙዚቃ መሳሪያ እንደ ዋሽንት አንድ (ነጠላ) ብቻውን አይሆንም፤ በስብስብ ነው፤ ስብስቡ ዝቅተኛው 24 ሲሆን እስከ 32 እና 48 ይደርሳል።
የመሳሪያዎቹ ብዛት ያስፈለገበት ምክንያት የተለያየ ድምጽ ለማውጣት ነው። አጨዋወቱ የራሱ ምትና ስልት አለው። ከትንሿ ቀጠን ያለች ድምጽ ይጀምርና እስከ 24ኛው ወፍራም ድምጽ ድረስ ይዘጋጃል። ለአቀማመጥ እንዲያመች በታችኛው በኩል የክር ማስገቢያ ቀዳዳ ይኖረዋል። ሁሉንም ፊላዎች በአንድ ክር በማስተሳሰር በጥንቃቄ ግድግዳ ላይ ይቀመጣል።
እነዚህ 24 የፊላ የሙዚቃ ድምጾች በሦስት ዋና ዋና ደረጃዎች (በባለሙያዎች ቋንቋ ቤዞች) ይመደባሉ። ይሄውም ካሳንታ (ወፍራም ድምጽ) ፣ ኦታንትያ (መካከለኛ ድምጽ) እና ፍት ፍታ (ቀጫጭን ድምጽ) በመባል ይመደባሉ። መሳሪያዎቹም በዚህ መልክ የተዘጋጁ ናቸው። በጨዋታ ጊዜ እያንዳንዱ መሳሪያ የሚያወጣው ድምጽ ቀዳሚና ተከታይ በመሆን ነው። መካከለኛና ወፍራም ድምጽ የሚያወጡት ከቀርቀሃ የሚዘጋጁት ፊላዎች ናቸው። ቀጭን ድምጽ የሚያወጡት ደግሞ ከሸምበቆ የሚዘጋጁት ናቸው። የፊላ ሙዚቃ በመሳሪያ ብቻ የተቀነባበረ ስለሆነ ከጃዝ ጋር እንደሚመሳሰል የአፍሪካ ጃዝ አባት የሚባሉት ሙላቱ አስታጥቄ ተናግረዋል።
ፊላ ውዝዋዜ (ዳንስ) ነው። የፊላ ውዝዋዜ ለየት የሚያደርገው ነገር ተወዛዋዡ ራሱ የመሳሪያው ተጫዋች ነው። ተወዛዋዥ ለብቻው አያስፈልገውም። ውዝዋዜውን የሚመሩት በፊላ ጨዋታ ውስጥ የሚገኙ ሦስት መሪዎች ናቸው። እነዚህ መሪዎች ራሳቸው ፊላ እየነፉ ከመሀል አቋርጠው በመውጣት ውዝዋዜውን ይመሩና እንደገና ፊላ ወደመንፋቱ ይመለሳሉ። ለፊላ ጨዋታ አዲስ የሆነ ሰው የአጨዋወት ስልታቸው ግራ ያጋባዋል።
የፊላ ጨዋታ በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች ይታያል። ከ1998 እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ በአርባ ምንጭ ይታይ በነበረው ‹‹ሺ ኮከቦች›› የሙዚቃ ፌስቲቫል፣ በብሄር ብሄረሰቦች ቀን እና የዓድዋ ድል በዓላት በሚከበሩባቸው ጊዜያት በአገር አቀፍ ደረጃ ይታያል፤ ሙዚቃዎቹም በቴሌቭዥን ጣቢያዎች ይታያሉ።
የሙዚቃ መሳሪያዎቹ የተለያዩ ናቸው። የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያዎች ሎላት፣ ማይራ፣ ኩሉታት፣ ታርባ፣ ሐናት፣ ሉላ፣ ካሳ፣ ካልጋ እና ሀምቡፓ የሚባሉት ናቸው።
ሎላት የሚባለው ከሳላ ቀንድ ወይም ከአጋም እንጨት ይዘጋጃል። ከተዘጋጀ በኋላ በቅቤ ታሽቶ ጭስ ባለበት ይቀመጣል፤ ይሄውም እንዲወዛ በማለት ነው። ከፍየል ጺም አካባቢ በሚገኝ ቆዳና ፀጉር ይዋባል። ቁመቱ እስከ 40 ሴንቲ ሜትር ይሆናል። ይህ መሳሪያ በሁለቱም ጫፍ ቀዳዳ ያለው ሲሆን አንደኛው ሰፊና ሌላኛው ቀጭን ነው። አነፋፉ በሰፊው በኩል ሲሆን በቀጭኑ በኩል ደግሞ በጣት ያዝ ለቀቅ በማድረግ የተለያየ ድምጽ እንዲያወጣ ይደረጋል።
ሎላት ለዲራሼ ማህበረሰብ የሙዚቃ መሳሪያ ብቻ አይደለም። መግባቢያም ነው። እያንዳንዱ ቤተሰብና መንደር የየራሱን ሎላት ያውቃል። ለሆነ ጉዳይ የሚጠራሩት በሎላት ነው። ማታ ከሥራ ሲገቡም መጥተናልና ተዘጋጁ የሚል መልዕክት የሚያስተላልፉት በሎላት ነው። አነፋፉም እንደየመልዕክቶቹ ይለያያል። አንድ ጊዜ ሲሆን ምን እንደሆነ፣ ሁለት ጊዜም ሦስት ጊዜም… ከሆነ መልዕክቱን የአካባቢው ማህበረሰብ ያውቀዋል።
ሌላው የትንፋሽ መሳሪያ ማይራ የሚባለው ነው። ከቀጫጭን ሸምበቆ ይዘጋጃል። እነዚህ ቀጫጭን ሸንበቆዎች ስድስት ሲሆኑ ከላይ ክፍት ከታች ድፍን ናቸው። ቁመታቸው የተለያየ ሲሆን ከትልቅ ወደ ትንሽ ይደረደራሉ። በቃጫ ገመድ ከታሰሩ በኋላ በቁልቋል ወይም በቅንጭብ ደም ይጣበቃሉ። ከቁልቋልና ቅንጭብ የሚወጣ ደም የማሟጨጭ ባህሪ ያለው ነው። የማይራ አደራደር በድምጹ አወራረድ መሰረት ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ ወይም ከከፍተኛ ወደ ዝቅተኛ ነው።
ማይራን የሚጫወቱት ወንዶች ሲሆኑ በጃንሜዳው ጥምቀት ላይ ከምናየው ሀርሞኒካ ጋር ይመሳሰላል። አጨዋወቱም ልክ እንደ ሀርሞኒካ ከንፈር ላይ በማድረግ ከግራ ወደ ቀኝ ወይም ከቀኝ ወደ ግራ በማመላለስ የሚጫወቱት የትንፋሽ መሳሪያ ነው። የማይራ ጨዋታ ለወጣቶች የፍቅር መገለጫ ሲሆን አዋቂዎችም ጀግንነትንና ማንነትን ለመግለጽ ይጫወቱታል።
ይሄኛው የትንፋሽ መሳሪያ ደግሞ ከዋሽንት ጋር ይመሳሰላል፤ ዲራሼዎች ኩሉታት ይሉታል። ኩሉታት የሚዘጋጀው አንድ ወጥ ከሆነ ሸምበቆ ወይም ቀርቀሃ ነው። ቁመቱ እስከ 50 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ ሲሆን በሁለቱም ጫፍ ክፍት ነው (እንደ ዋሽንት ማለት ነው)። በእኩል ርቀት የተበሱ አራት ቀዳዳዎች ይኖሩታል። አጨዋወቱም ልክ እንደ ዋሽንት በሁለት እጅ ተይዞ ቀዳዳዎችን በጣት በመያዝና በመልቀቅ ነው። ይህን ጨዋታ የሚጫወቱት በብዛት ሴቶች ናቸው። በነገራችን ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚዘወተረው ዋሽንት ሴቶች ሲጫወቱት አይስተዋልም።
ከዘመናዊው ሳክስፎን ጋር የሚመሳሰለው የሙዚቃ መሳሪያ ደግሞ ታርባ ይባላል። የሚሰራው የቀርቀሃ አንጓዎችን አንዱን በአንዱ ላይ በመሰካት ነው። ጥንት የነበረው አገልግሎት አደጋ መከሰቱን ለማሳወቅና ትልቅ ሰው ሲሞት ለመርዳት ነው። በሁሉም እጅ ላይ አይገኝም፤ ኃላፊነት ለተሰጣቸው ሰዎች ብቻ ነው። አሁን ላይ ግን ይህ መሳሪያ እምብዛም አይታይም።
ሐናት የሚባለው የሙዚቃ መሳሪያ ደግሞ ከረጅም የሳላ ቀንድ የሚዘጋጅ ነው። በአፉ በኩል የሚነፋ ሲሆን ዋና አገልግሎቱም ከለቅሶ ሥርዓት ጋር የተያያዘ ነው። ሐናት ሲነፋ ከተሰማ በአካባቢው ሰው እንደሞተ ይታወቃል። የለቅሶ ስነ ሥርዓቱና መጠናቀቁም በሐናት ይደረጋል። ይህን መሳሪያ አሁን ላይ ለማዘጋጀት ስለሚያስቸግር (የሳላ ቀንድ) ያለውን በጥንቃቄ መያዝ ነው።
ሌላው የመጥፋት ደረጃ ላይ የደረሰው መሳሪያ ሉላ የሚባለው ነው። የሚዘጋጀውም ከድኩላ ቀንድ ነው። እርሻ የሚውሉ አርሶ አደሮችና እረኞች ወደቤት ሲገቡ የሚጠራሩበት ነው።
የዲራሼ ማህበረሰብ ከሚጠቀማቸው የሙዚቃ መሳሪያዎች ለየት ያለው ደግሞ ሀምቡፓ የሚባለው ነው። የሚዘጋጀው ከዛፍ ፍሬ ነው። ፍሬው የሚገኘው ማህበረሰቡ ሺጫራ ብሎ ከሚጠራው ሐረግ መሰል እሾሃማ ተክል ነው። የፍሬውን ጠንካራ ቅርፊት በመተው በውስጡ የሚገኙ ትንንሽ ፍሬዎች በማጽዳት ሦስትና ከዚያ በላይ ቀዳዳዎች እንዲኖሩት ይደረጋል። አንደኛው ቀዳዳ የሚነፋበት ሲሆን የቀሩት በጣት እየተሸፈኑና እየተለቀቁ ድምጽ እንዲያወጡ ይደረጋል።
የጋርዱላ ማህበረሰብ የክር የሙዚቃ መሳሪያዎችም አሉት። አንደኛው ሾንቃ የሚባለው ሲሆን ከክራር ጋር ይመሳሰላል። ቀደም ሲል ከእንጨት፣ ከቃጫ ገመድ፣ ከቆዳና ከጅማት የሚዘጋጅ ቢሆንም አሁን ግን ከሲባጎና ሌሎች ዘመናዊ ክሮች እየተዘጋጀ ነው። ትምባ የሚባለው የምት የሙዚቃ መሳሪያ ደግሞ በአማርኛ ከበሮ ከሚባለው ጋር የሚመሳሰል ነው። አሰራሩም ሆነ አገልግሎቱም ከከበሮ ጋር ይመሳሰላል።
ይሄኛው ደግሞ የሙዚቃ መሳሪያ ብቻ ሳይሆን የእግር ጌጥም ነው። ሉሌት ይባላል። ከመዳብ የሚዘጋጁ ትንንሽ ቃጭሎች ናቸው። በቀጭን ጠንካራ ክር ከተሳሰሩ በኋላ የሴቶች ቁርጭምጭሚት ላይ ይታሰራሉ። ይህ ቁርጭምጭሚታቸው ላይ የታሰረ ቃጭል በተንቀሳቀሱ ቁጥር እያቃጨለ ሙዚቃ ይፈጥራል። ድምጹም እንደ አረማመዳቸው ይሆናል፤ በዚህም ማን እንደሆነች ለመለየት ያስችላል።
እንግዲህ በእነዚህ የሙዚቃ መሳሪያዎች (የትንፋሽ፣ የክር፣ የምት፣ ቃጭል) የሙጫወቱት ጨዋታ የተለያየ መልዕክት ያለው ነው። ለሀዘን፣ ለደስታ፣ ለፉከራ የሚውሉ ናቸው። አንዳንዶቹ መሳሪያዎችም የማህበረሰቡ መግባቢያና መጠራሪያ ናቸው። ጨዋታዎችም እንደየወቅቱ ይከናወናሉ። በዝናብ ወቅት፣ በበጋ ወቅት፣ በሰርግ ወቅት ይጫወቷቸዋል። ጨዋታዎችም የየራሳቸው መጠሪያዎች አሏቸው።
የፊላና ሌሎች የጋርዱላ ሙዚቃዊ ጥበባት አሁን አሁን ጥናት እየተደረገባቸው ነው፤ የባህል ቡድን ተዘጋጅቶላቸውም እየተሰራባቸው ነው። ይህ ጅምር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012
ዋለልኝ አየለ