(ክፍል አንድ)
እነሆ የመጀመሪያዋን ወደ ሕዋ የመጠቀች ኢትዮጵያዊት ሳተላይት ስናይ ግሩም እምግሩማን ቦ ግዜ ለኩሉ !! አልን እንደ አባቶቻችን። ዘመን ደጉ። ኢትዮጵያ የእነ አንድሮይድ፤ የነካሶፒያ በስማቸው ጠፈር የተሰየመላቸው ጥንታውያን ሀገር ነች። ሳይንስ ፤ቴክኖሎጂ የሚባል በማይታሰብበት ሩቅ ዘመን ሀገርህ ኢትዮጵያ ጠፈርና ሕዋን ምድርን የሚመራመሩ ታላላቅ ሊቃውንቶች ነበሯት፤ አሉ ሊቁ አዝመራይ ዙሪያቸውን ለተሰበሰቡት ተማሪዎቻቸው።
ለጠቁና የስነፈለግ፤ የስነጥበብ፤ የህክምና፤ የሥነምድር፤ የኪነ ሕንጻ ፤ የስነመለኮት፤ የብዙ እውቀት ባለቤቶች የነበሩት ቀደምት አባቶቻችሁ ነበሩ ብለው በዝምታ ተዋጡ። ወደኋላ ሩቅ ዘመን በሀሳብና በታሪክ እሳቤ ተመው። ከጎናቸው የተቀመጡት የቀለም ቀንድ የሚባሉት ምርምር ወዳዱ አባ ዘማርያም ይበሉ ይበሉ የሚያሰኙ በሞት የተነጠቁ ስንት ድንቅ ሊቃውንት ነበሩን።
ሀገር ጉድ ያሰኙ አሉና ስለ አሰፋ ሳይንቲስት የሰሙትን ያወጉ ጀመር። ግዜው ሩቅ መሆኑን አሰታውሰው። የሰሞኗ ሳተላይት ስትመጥቅ ሀገር ጉድ በማለቱ ተደመመዋል። ፕሮፌሰር አሰፋ ኃይለመስቀል (አሰፋ ሳይንቲስት) ፈረንሳይ ሀገር የተማሩ ኬሚስት ነበሩ። ድንቅ ኬሚስት። በቤተክህነትም አድገዋል። የያኔው ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ኬሚስትሪ አስተማሪ ነበሩ፤ አሰፋ ሳይንቲስት።
በቀዳሚው ኃይለስላሴ ዘመን ሀገር ያስደመሙ፤ ቀሳውስቱን ያንጫጩ፤ ቤተመንግስቱን ጉድ ያሰኙ፤ ለእስር የተዳረጉ፤ ከንጉሱ ፊት የቀረቡ ሰው ነበሩ አሰፋ ሳይንቲስት ሲሉ አባ ዘማርያም ተናገሩ። የእኛው ዘመን ሰው ነበሩ አሉ ሊቁ አዝመራይ። ምርምር አድናቂ ናቸው። ደርሰው አይተቹም። እንደው ባንገጣጠም ነው እንጂ ታሪካቸውን ከተለያዩ ሰዎች ሰምቼአለሁ አሉ በአሰፋ ሳይንቲስት ስራና ሙከራ በእጅጉ ተደምመው።
ሆሆይ !! ነፍሳቸውን ይማርና የማይሞከር ነገር ሞክረው ሀገሩን አንጫጭተውት ነበር እኮ። እንዴት እንዴት አሉና ጠየቁ አባ ዘማርያም። በአህያ አድርገው ሮኬት ወደ ሰማይ አስወንጭፈው ሀገር ተንጫጫ እኮ ትዝ አይልዎትም እንዴ። እስቲ አውጉኝ። ግዜውም ራቀ እኮ አሉ። ከሊቁ አዝመራይ የድሮ ተማሪዎች አንዱ የሣይንስ ተማሪ ነበረና ተመርቆ በምርምር ስራ ላይ ይገኛል። የድሮ ተማሪዎቻቸው አልፎ አገደም የቀለም አባታቸውን ለመጠየቅ ይመጣሉ።
እንደኔ አምላክ አብዝቶ የባረከው እስቲ ማን አለ ይላሉ ሊቁ አዝመራይ ተማሪዎቻቸው ሳይረሱ ስለሚጠይቁአቸው። ይኸው የሳይንስ ምሩቅና ተመራማሪ የሰማውን ታሪክ መናገር ጀመረ። አሰፋ ሳይንቲስት ከዘመናቸው ብዙ እጥፍ የቀደሙ ዛሬን በትላንት ውስጥ ያዩ፤ ዓለም የሳይንስ ትሆናለች ብለው በልባቸው የዘመሩ የምር ተመራማሪ ሳይንቲስት ነበሩ። ሮኬት የተባለውን ነገር ፈረንሳይ ሀገር ተማሪ ሆነው ሳያዩ እንዳልቀሩ ፤እንዴት እንደሚሰራም እውቀት ሳይገበዩ እንዳልቀሩ ይገመታል ።
የኬሚስትሪ ተማሪ ሆነው በላቦራቶሪ ምርምር አድርገዋል። ታላላቅ የዓለማችን ግኝቶች የሰው ልጅ የፈጠራና የምርምር ስራ ውጤቶች ናቸው። ሳይንስ ምርምር ሙከራን ደጋግሞ ሙከራን ይጠይቃል። ቀኖና አይደለም። አሰፋ ሳይንቲስት ሮኬት ለማምጠቅ የተጠቀሙበትን ጥበብና ሙከራ የሚመሰክሩላቸው በሕይወት የሚገኙ አዛውንቶች አሉ። የድሮው ተፈሪ መኮንን ት/ቤት የሀገሪቱን ታላላቅ ምሁራን ያፈራ ነው።
አሰፋ ሳይንቲስት በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ላቦራቶሪ ውስጥ ነበር እንዴት ሮኬት ሰርተው ወደ ሰማይ ማስወንጨፍ እንዳለባቸው ሲመራመሩ የቆዩት። ኬሚስቱ አሰፋ ኃይለመስቀል (አሰፋ ሳይንቲስት) እቅዳቸው በሰሩት ሮኬት አህያ ወደ ጨረቃ ማስወንጨፍ ነበር። አቡጀዲውን ጨርቅ ሰም አቅልጠው አድቦልቡለው ትልቅ ክብ ባሎን የኳስ ቅርጽ ይዞ እንዲያድግ አደረጉት።
ባሎኑ በሀይድሮጅን የሙቀት ኃይል ወደላይ ሲነሳ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲንሳፈፍ አስበው ይመስላል ለአህያዋ መቀመጫ የሚሆን ትልቁን ባሎን በሚዛናዊነት መሀል ሆኖ የሚሸከም ሳጥን ያሰሩት አለና የሰማውን ታሪክ ቀጠለ። ከመሬት በሀይደሮጅን የሙቀት ኃይል አህያዋን በተሰራላት መቀመጫ እንደያዘ ሽቅብ ወደሰማይ መሬትን ለቆ የጎነው ትልቁ ባሎን በሰማይ ላይ መንሳፈፍ ጀምረ።
ከተነሳበት ቦታ ከፍ እያለ በመራቅ በቀጥታ ወደ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አቅጣጫ አመራ ሲል በድንገት ነበርክን አሉት። በአተራረኩ ተመስጠው። እኔማ መች ተወልጄ አዛውንቶች ነገሩኝ እንጂ አላቸው። ቀጥልማ ቀጥልማ አሉት በጉጉት። ጎልማሳው የሠማውን ወግ መናገር ቀጠለ። ባሎኑ ወደሰማይ እየራቀ ሲሄድ የንፋሱን ኃይል(አየሩን) መቋቋም ባለመቻሉ እየተነፈሰ ሄደ።
እናም ያኔ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ በሚገኝ አንድ ቄስ ቤት ላይ ተምዘግዝጎ ወርዶ ቤቱን አፈራረሰው። አሰፋ ሳይንቲስት በራሳቸው ጥረትና ምርምር ያለማንም አጋዥ በዚያ ድቅድቅ ዘመን የመጀመሪያዋን ኢትዮጵያዊ ሮኬት በመስራት ወደ ሰማይ ማምጠቃቸው ሀገርን ጉድ አሰኘ። የቻለችውን ተጉዛ ፈነዳች። ይሄንን ሙከራ በዚያ ዘመን ማንም አስቦትም ሆነ ሞክሮት አያውቅም አለና ዝም አለ። ቀልባቸው በመሳቡ ደግመው ቀጥል ቀጥል አሉት። አሰፋ ሳይንቲስት አንድ አይና ስለነበሩ ትልቅ የአይን መነጽር ያደርጉ እንደነበረ ሰምቼአለሁ።
አሰፋ ሳይንቲስት ሮኬት ለማስወንጨፍ ባደረጉት ሙከራ ተከሰው ታሰሩ። ንጉሱ ፊትም ቀርበው ነበር። ምን እንደተነጋገሩ ባይታወቅም ኋላ ላይ ተለቀዋል። ፈረንሳይ ሀገር ተምረው የመጡትን የኬሚስትሪ እውቀትና የምርምር ችሎታ እንዳይሰሩበት ተከልክለው በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አማርኛ ትምህርት እንዲያስተምሩ ተገደዱ። ራሳቸውን ለአዲስ ተማሪዎች ሲያስተዋውቁ በኩራት አሰፋ ሳይንቲስት ይሉ እንደነበር ተማሪዎቻቸው በፍቅር ሲያወሩ ሰምቼአለሁ።
እንዴታ እንዴታ ይገባቸዋል እንጂ አሉ ሊቃውንቱ። ሮኬት ለማስወንጨፍ ያደረጉት ጥረት በዚያ ጨለማ ዘመን አስወነጀላቸው። እሳቸው ከግዜው የቀደሙ ታላቅ ሰው ነበሩ። ሮኬት የማስወንጨፍ ሙከራቸውን ይህ የአጋንንት ስራ ነው ብለው የወነጀሏቸውም ነበሩ። አሰፋ ሳይንቲስት ከኖሩበት ዘመን በእጅጉ የቀደሙ የሮኬት ሳይንስን በሙከራ ደረጃ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረጉ የመጀመሪያው ቀዳሚ ሰው ናቸው።
ግና ምን ያደርጋል የእኛ ሀገር ነገር ማስታወሻ እንኳን አልቆመላቸውም አለ ወጣቱ የሳይንስ ሰው። የሮኬት ሳይንስ ፈር ቀዳጅ ስለሆኑ ታሪካቸው ከቤተሰባቸው ተፈልጎ አሊያም ከሚያውቋቸው ሰዎች ተሰብስቦ ማስታወሻ ሀውልት ሊቆምላቸው ይገባል ሲል ሁሉም በአንድ ድምጽ ይገባቸዋል፤ ይገባቸዋል፤ ሲሉ አስተጋቡ። ለአሰፋ ሳይንቲስት!
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 16 / 2012
ወንድወሰን መኮንን