ተወልደው ያደጉት በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢ ነው። በቤተሰቦቻቸው የሥራ ሁኔታ ምክንያት የመጀመሪያ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዘጠኝ ትምህርት ቤቶች የተማሩ ሲሆን 11ኛ እና 12ኛ ክፍል ኩየራ በሚገኘው ኩየራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
በመቀጠል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስታትስቲክስ የትምህርት ክፍል ገብተው ለአንድ ዓመት ከተከታተሉ በኋላ በ1964ዓ.ም በነበረው የተማሪዎች አመፅ ላይ በመሳተፋቸው ለአንድ ዓመት ታገዱ። በዚህ ምክንያት ወደ አሜሪካ በመሄድ በኢኮኖሚክስ ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ማግኘት ችለዋል። እዚያው አሜሪካ እያሉም የማስተርስ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሜትሪክ ትምህርት ዘርፍ አግኝተዋል። በተጨማሪም አዲስ አበባ በሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የልማት ኢኮኖሚ ሳይንስ አጥንተውም ሌላኛውን የማስተርስ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል።
የ69ኛ ዓመቱ አምሃ ዳኘው ታዲያ በዕድሜያቸው ሦስት መንግሥታትን ማየት የቻሉ ሲሆን በሁሉም የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የነቃ ተሳትፎ አድርገዋል። በተለይም የአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥትን በመቃወም በነበረው ፖለተካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የጎላ ሚና ስለነበራቸው ለሰባት ወራት ታስረዋል። በደርግ ዘመነ መንግሥትም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ባደረጉት ጥናት እውቅና ሊቸራቸው ሲገባ በተቃራኒው ከርዕዮተ ዓለም አፈንግጥሃል በሚል ለአንድ ዓመት በሊቀመንበሩ ልዩ ትዕዛዝ ለእስር ተዳርገዋል።
ባለፉት 27 ዓመታትም ኢህአዴግ መራሹን መንግሥት በመቃወም በቅንጅትና በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ተሳትፈዋል። በአሁኑ ወቅትም በኢዜማ ፓርቲ የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ከፖለቲካው በተጨማሪም ላለፉት 26 ዓመታት ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ለሚገኙ ከ100 በላይ ኤምባሲዎች «the ethiopian weekly press digest» የተሰኘ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ እያዘጋጁም ይገኛሉ። ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት የሆኑት የዛሬው እንግዳችን አቶ አምሃ ዳኘው በቅርቡ ደግሞ የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታና መፍትሄ አማራጭን የሚጠቁም «ሀገራዊ ብሔርተኝነት እና ዘውጋዊ ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ» የተሰኘ መጽሐፍ ፅፈው ወደ ማተሚያ ቤት ልከዋል። ከእንግዳችን ጋር በወቅታዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነው ቃለምልልስ እንደሚከተለው ይቀርባል።
– አቶ አምሃ ዳኘው የኢዜማ ፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ኃላፊ
አዲስ ዘመን፡- እስቲ በደርግ ዘመን መንግሥት ለእስር የዳረገዎ ጉዳይ ምን እንደነበር ይንገሩንና ውይይታችን እንጀምር?
አቶ አምሃ፡- ከአሜሪካ ከተመለስኩ በኋላ በዋና አዘጋጅነት ከምሰራበት መስከረም ከሚባለው የኢሰፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ የርዕዮተ ዓለም መጽሔት ወደ በፓርቲው የኢኮኖሚ መምሪያ ምክትል ኃላፊ ሆኜ ተመደብኩ። በሙያዬ በኃላፊነት እያገለገልኩ ሳለም የአገሪቱ ኢኮኖሚ በፖለቲካው ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ጥናት እንዳካሂድ በሊቀመንበሩ ታዘዝኩ። እኔ በምመራው መምሪያ አስተባባሪነት ከሌሎች ተቋማት የተውጣጣ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ለአንድ ዓመት ያህል በቅይጥ ኢኮኖሚ ዙሪያ የፖሊሲ ጥናት አካሄድን።
ጥናቱ እንዳለቀ ለ9ኛው የኢሰፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለማቅረብ ታቅዶ ስለነበርም ከዚያ በፊትም ለሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም አራት ሰዓታት የፈጀ ገለፃ አደረኩ። ገለፃውን አድርጌ ከጨረስኩ በኋላ ግን ጥናቱ በሊቀመንበሩ ስላልተፈለገ በተጠናው መልክ ሳይሆን ድሮ በተለመደው ሁኔታ እንደገና ተስተካክሎ ይቅረብ ተባለ። እኔ ደግሞ ብዙ ጊዜ እና ጉልበት ወስዶ የተጠናው ጥናት እንዲቀየር መወሰኑ አሳማኝ ሆኖ ስላላገኘሁት መቀየር የለበትም ስል በድፍረት ከሊቀመንበሩ ጋር ተሟገትኩኝ።
አዲስ ዘመን፡- ጥናቱ ምን አዲስ ነገር ይዞ ነው የመጣው?
አቶ አምሃ፡- እንደምታውቂው እንግዲህ የደርግ ኢኮኖሚ የሶሻሊስት ኢኮኖሚ ነው። ርዕዮተ ዓለሙ ኢኮኖሚውን ብዙ አላሳደገውም። ለምርታማነትም ሆነ በአጠቃላይ ለኢኮኖሚ እድገት የሚያመች ስላልነበር በተጨባጭ ታይቶ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ሪፎርም ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ነበር። ይህም ማለት ለሶሻሊዝም ግንባታ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ከሚለው የቆየ ፖሊሲ ቅይጥ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መቀየርና ለግሉ ዘርፈ ሚና መስጠት የሚቻልበትን ሁኔታ በስፋት የሚያትት ጥናት ነው ።
የእኛ ጥናት ፖሊሲ አቅጣጫ መቀየር ጀምሮ አንዳንድ ተቋማዊ ለውጥም የሚጠይቁ ነገሮችን ያካትት ነበር። በመጀመሪያ ላይ ታምኖበት እንዲጠና ቢደረግም ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ግን ሊቀመንበሩ ሊቀበሉት አልቻሉም። እኔ ግን አንድ ዓመት ሙሉ ደክሜ ያጠናሁት ጥናት መቀየር የለበትም በሚል ከሊቀመንበር መንግሥቱ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገባን። ያን ጊዜ ደግሞ ሥርዓቱ ወታደራዊ እንደመሆኑና በሃሳብ ተለያይተሽ መኖር የማይቻል በመሆኑ በተለይ ደግሞ የፓርቲውን ሊቀመንበር ትዕዛዝ አለመቀበል ማለት ወታደራዊ እርምጃ ነው የሚያስከትለው። እናም ከሊቀመንበሩ ጋር ልንስማማ ባለመቻላችን ከቢሯቸው እንደወጣሁ ነው እንድታሰር የተደረኩት።
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ ሥርዓቱ ወታደራዊ እንደመሆኑ ይህ እንደሚገጥምዎት አያውቁም ነበር?
አቶ አምሃ፡- እንዳልኩሽ በመጀመሪያ ደረጃ እኮ በአመራር ደረጃ ባሉት አባላት ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር ጥናቱ የተካሄደው። ብዙኃኑ ያመነበት መሆኑን እኔም ይህንን ያህል ችግር ያመጣብኛል ብዬ አላሰብኩም ነበር። ለእስር የሚዳርግም ሥራ ሰርቻለሁ ብዬ አላሰብኩም። ነገር ግን ከእስር ከተፈታሁ በኋላ የነበሩ ሰዎች እንደነገሩኝ በወቅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም እየተዳከመ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እና በጎርባቾቭ የተጀመረ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመቀየር የሚደረግ እንቅስቃሴ ነበር። ፖለቲካውንም ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመቀየር ተሃድሶ በሚል የተለያዩ ሥራዎች ተጀምረው ነበር። እንደአጋጣሚ ሆኖ ይህ ጥናት ከቀረበ በኋላ የሶቪየት ኮሚኒስት ፓርቲ በድብቅ አንድ ልዑክ ይመጣና ሶሻሊዝም እንኳን ለእናንተ ለእኛም አላዋጣም፤ ስለዚህ በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው መስክ ለውጥ ማካሄድ አለባችሁ የሚል መልዕክት ይተላለፍላቸዋል።
እናም የልዑኩ ሃሳብ በወቅቱ እኔ ካቀረብኩት ጥናት ጋር እንደ አጋጣሚ ሆኖ ተገጣጠመ። እንግዲህ የሊቀመንበር መንግሥቱ አንዱ ችግር ሥልጣን አፍቃሪ መሆናቸው ነበርና ይህ ጥናት ምንአልባት ከራሺያዎች ጋር የተያያዘ ይሆናል የሚል ጥርጣሬ ያደረባቸው ይመስለኛል። ለነገሩ ሊቀመንበሩ በባህሪያቸው በጣም ተጠራጣሪ ስለነበሩ ከውጭ ኃይል ጋር የማገናኘት ሁኔታ ነበራቸው። እኔም በማላውቀው፤ ነገር ግን በማምንበት ነገር ገፋሁ። ይሄ ነው እንግዲህ ለአንድ ዓመት እስር የዳረገኝ።
አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ ታዲያ እንደሌሎች የፖለቲካ እስረኞች አካላዊ ጉዳት አልደረሰብዎትም?
አቶ አምሃ፡- አይ በፍፁም! እኛ ባለሥልጣኖች ስለነበርን እንደዚህ ዓይነት ድብደባ አልደረሰብንም። ለአንድ ወር ያህል አፄ ምኒልክ ቤተመንግሥት ውስጥ ነው የታሰርኩት። ከወር በኋላ ግን ማዕከላዊ ወሰዱኝ። በዚህ ጊዜ ውስጥም እንደሚባለው ምንም ዓይነት አካላዊ ጉዳት አላደረሱብኝም። በእርግጥ ከእስር ከተፈታሁ በኋላ በማንኛው መንግሥታዊ ድርጅት እንዳልሰራ ታግጄ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ከዚያ ከፖለቲካውና ከመንግሥታዊ አገልግሎት ራስዎን ሙሉ ለሙሉ አገለሉ ማለት ነው?
አቶ አምሃ፡- እንደነገርኩሽ ለሁለት ዓመታት ሥራ ፈትቼ ነበር የቆየሁት። ከዚያም ከ1982 ዓ.ም በኋላም አብዛኞቹ ጓደኞቻችን ታሰሩብን። ከእስር ከተፈቱ በኋላ ግን ከአንዳንዶቹ ጋር ተሰባስበን የግል ኩባንያ አቋቋምን። መድረክ የሚባልም በአገሪቱ አንኳር ችግሮች ላይ የሚያጠነጥን ጥናታዊ መጽሔት ማሳተም ጀመርን። ይሁንና በወቅቱ የንባብ ባህሉ ገና ባለማደጉ ምክንያት ያሳተምነውን ግማሽ ያህል እንኳ መሸጥ አልቻልንም ነበር። ሁለተኛውን ርዕሰ ጉዳይ ይዘን ብንወጣም ገዢ በማጣታችን ለከፍተኛ ኪሰራ ነው የተዳረግነው። እናም የታተመው መጽሔት ፈላጊ በማጣቱ ከእኔ ጋር አብሮ ሲንከራተት ለዓመታት ቆይቶ በኋላም ለሱቆች ችርቻሮ ሸቀጣሸቀጥ መሸጫነት በኪሎ ለመሸጥ ተገድጃለሁ። በዚህ ግን ተስፋ አልቆረጥኩም።
ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ለዲፕሎማቶች የሚቀርብ «the ethiopian weekly press digest» የሚባል ጋዜጣ ማዘጋጀት ጀመርኩ። ላለፉት 26 ዓመታት እዚህ አገር ላሉ የውጭ ማህበረሰብ አባላት ወሳኝ የሆኑ ዜናዎችን ከየመገናኛ ብዙኃኑ ለቅመን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተርጉመን እናቅርብላቸዋለን። እነሱም አንዳንድ የማማከር ሥራዎች ይሰጡናል። እንደዚህ ዓይነት ሥራ እየሰራን ይኸው እስካሁን አለን።
አዲስ ዘመን፡- የምትመርጧቸው ጽሑፎች የአገሪቱ ጥቅምና
ገፅታ ባስጠበቀ መልኩ መሆናቸው ታሳቢ ታደርጋላችሁ?
አቶ አምሃ፡- እኛ ለህትመት ከበቁ የመንግሥትና የግል ጋዜጦች ላይ ነው መረጃዎችን የምንወስደው። በዋናነትም የሳምንቱ ወሳኝ ፖለቲካዊ ክስተቶች ላይ የምናተኩር ሲሆን የመንግሥትና ፖለቲከኞችን ወቅታዊ አቋም ያለባቸውን ሥራዎች ነው የምንመርጠው። በምንተረጉምበትም ጊዜ በጋዜጣው ላይ የወጣውን ሃሳብ ሳንጨምር ሳንቀንስ ጨምቀን ነው የምናቀርበው። የእኛ አስተያየትና ሃሳብ አይካተትበትም። ለነገሩ እነሱም የእኛ ሃሳብና አስተያየት እንዲካተት አይፈልጉም። ይሁንና ምርጫ በሚኖርበት ጊዜ ቡድን አቋቁማችሁ አጠቃላይ እንቅስቃሴዎችን ሪፖርት አድርጉልን ይሉናል። አንዳንድ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጥናት ማካሄድ ሲፈልጉም የማማከር ኮንትራት እንፈራረምና የምንሰራበት ሁኔታም አለ።
አዲስ ዘመን፡- ግን ይሄ በአገር ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ ጣልቃ እንደመግባት አይቆጠርም? ለአገር ደህንነትስ ስጋት አይሆንም?
አቶ አምሃ፡- ምንም ምስጢር እኮ የለውም። የትኛውም አገር የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ፈጥሮ ኤምባሲ እስኪከፈት ድረስ ስለተመደበበት አገር አጠቃላይ ሁኔታ ለመደበው መንግሥት አጥንቶ ማቅረብ ነው ዋናው ሥራው። የዲፕሎማቱ መደበኛ ሥራም ስለዚህች አገር ሁኔታ መረጃ እያነፈነፈ ለአገሩ መንግሥት ሪፖርት ካላደረገ ይነሳል። ይህም ማለት በጥቃቅንና በጣም ውስጣዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሁሉ ይገባሉ ማለት አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ በተለይ በአሁኑ ወቅት ፖለቲካ ውስጥ እየተሳተፉ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለዲፕሎማቶች ተርጉማችሁ በምታስተላለፉት ዜና ላይ የግልዎ ፖለቲካ አመለካከት ተፅዕኖ እንዳያሳድር ምን ያህል ጥንቃቄ ያደርጋሉ?
አቶ አምሃ፡- ጥያቄሽ ትክክል ነው! ግን እኛ ሙያችንን አክብረን የምንሰራው። የጋዜጠኝነትንም ዲሲፕሊን እናውቃለን። እኛ የምንስራውን ሥራ ማንም ሰው ቢመለከተው ዜናውን ከወሰድንበት ጋዜጣ ላይ ያልተባለ ነገር አንጨምርም። ከዚህ ቀደምም በምንሰራበት መድረክ መጽሔት ላይ እኛ ጥልቀት ያለው ጽሑፍ እንጂ አሉባልታ አንፅፍም ነበር። የሚገርመው ነገር እኛ መድረክ መጽሔትን በምናዘጋጅበት ወቅት ሕዝቡ የሚፈልገው ወሬ እንጂ ጥልቅት ያለው ጽሑፍ ስላልነበር ብዙ ፈላጊ አልነበረውም።
አዲስ ዘመን፡- ከደርግ ውድቀት በኋላ የነበርዎ የፖለቲካ ተሳትፎ ውጤታማ ነበር ማለት ይቻላል?
አቶ አምሃ፡- አዎ! በቅንጅት ውስጥ አመራር ባልሆንም በፖለቲካው ውስጥ በመሳተፍ የበኩሌን አስተዋፅኦ ሳበረክት ቆይቻለሁ። ቅንጅት ከፈረሰ በኋላም አንድነት ፓርቲ ሲቋቋም የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የፖሊሲ ምርምርና ጥናት ዘርፍ ኃላፊ ነበርኩ። ጥቂት ጊዜ እንደሰራን በመካከላችን አለመስማማት ተከሰተ። እኔ፣ ዶክተር ሽመልስና ፕሮፌሰር መስፍን በኋላም ሰማያዊን የመሰረቱት ወጣቶች ፓርቲውን ለቀን ወጣን። በቅድሚያ እንዲያውም እኔን ነበር ያስወጡኝ።
አዲስ ዘመን፡- ቀድመው እንዲ ሰናበቱ ያደረግዎ የተለየ ምክንያት ነበር?
አቶ አምሃ፡- እነሱ እነ ስዬን ለማስገባት ፈልገው ነበር። እኔ ደግሞ ከእነሱ ጋር የፖለቲካ ልዩነት ስለነበረኝ በዚህና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ መስማማት አልቻልንም። በዚህ ምክንያት ክርክር ሲነሳ አስቀድመው እኔን አስወጡኝ። ሌሎቹ ጓደኞቼ ደግሞ ባለመስማማታቸው እኛም አንፈልግም ብለው ወጡ። በኋላም ከዚያ የወጡት አባሎቻችን ሰማያዊ ፓርቲን ሲመሰርቱ እንደ እኔ በዕድሜ የገፋነው ሰዎች ከፖለቲካው ራሳችንን አገለልን።
አዲስ ዘመን፡- የፖለቲካውን ነገር ለወጣቶች ትቻለሁ ብለው ከተዉ ከዓመታት በኋላ ዳግም ፖለቲካውን ተቀላቅለዋል። ምን የተለየ ምክንያት ኖርዎት ነው ፊትዎን ወደ ፖለቲካው የመለሱት?
አቶ አምሃ፡- በፊት የተለያዩ ድርጅቶች ቢኖሩም አብዛኞቹ በብሔር መልክ የተደራጁ ናቸው። እኔ የዜግነት ፖለቲካን የሚያራምድ የፓርቲ መስመር ነው የሚጥመኝ፤ በዚህ ምክንያት ራሴን ከፖለቲካ አግልዬ ነው የኖርኩት። በእርግጥ ከግንቦት ሰባት ሰዎች ጋር እሰራ ነበር። እናም በዚያው ግንኙነት መሠረት አሁን ከለውጡ በኋላ በዜግነት ላይ የተዋቀረ ፓርቲ ሲመሰረት ዓይኔን አላሸሁም። ደግሞም የኖርኩትም በፖለቲካ ውስጥ በመሆኑ ዳር ቆሞ ዝም ብሎ ከማማት ባለን አቅም ብናግዝ የራሳችንን አስተዋፅኦ ማበርከት እንችላለን በሚል መንፈስ ነው እንግዲህ ዳግም ወደ ፖለቲካው ለመመለስ የወሰንኩት።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያሉ ፓርቲዎች ወደ አንድ ከመምጣት ይልቅ ከቀን ወደ ቀን እየተበራከቱ ይገኛሉ። ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ? ኢዜማስ በስሩ ካቀፋቸው በተጨማሪ ሌሎችን ለመቀበል ምን ያህል ዝግጁ ነው?
አቶ አምሃ፡- ኢዜማ ውህደቱን አልጨረሰም፤ ሌሎችንም የማካተት እቅድ አለው። ዞሮ ዞሮ የፓርቲ መብዛት አገርን አይለውጥም። ቢያንስ ቢያንስ በዜግነት የሚያምኑ በአገር አቀፍ ፖለቲካ የሚያምኑ በዜግነት ዙሪያ የተደራጁ ፓርቲዎች ምን ልዩነት እንዳላቸው አይገባኝም። በእኛ አገር ያው እንደሚታወቀው የራሱን ዙፋን ማግኘት ስለሚፈልግ ሁሉም የራሱን ዘውድ በየኪሱ ይዞ ነው የሚዞረው። በእኔ እምነት ግን በዜግነት ፖለቲካ ላይ ከተስማማን በአገሪቱ ላይ ያለውን ችግር በሚመለከተት ልዩነት ሊኖር አይችልም። ብዙ የሚያጣላ ነገር እኮ የለም። በፖሊሲ ዙሪያ ያሉ ልዩነቶችም ቢሆኑንም እውነታውን መሠረት በማድረግና በመወያየት ሊፈቱ ይችላሉ።
በተረፈ ግን ምንም የአመለካከት ልዩነት ሳይኖረን ፓርቲዎችን ማብዛት ምንም ፋይዳ የለውም። ስለዚህ ኢዜማ ውስጥ እንዳሉት ፓርቲዎች ሁሉ ሌሎቹም ተዋህደው አንድ ትልቅና ጠንካራ ፓርቲ መፍጠር ነው የሚገባቸው። በእኔ እምነት ቢበዛ ሦስት ፓርቲ ቢሆኑ አገሪቱን ከብዙ ወጪና ውዥንብር ያድኗታል። አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ ግን በቀውስ ላይ ቀውስ መጨመር ካልሆነ በስተቀር አገሪቱን ወደ ትክክለኛ የእድገት አቅጣጫ እንድትሄድ አያደርጋትም።
አዲስ ዘመን፡- ኢዴፓን በመሳሰሉ ፓርቲዎች ውስጥ የነበሩ አመራሮች የግል ቁርሾ ያላቸው አካላትስ በምን መልኩ ነው ልዩነታቸውን ፈተው ወደ አንድ ሊመጡ የሚችሉት?
አቶ አምሃ፡- በኢዴፓ ውስጥ ያለው የተለየ ሁኔታ ነው። በመካከላቸው ሳይስማሙ ቀርተው የተፈጠረ ነገር ነው። የሌሎቹ ግን ምክንያታቸው በእውነቱ አይገባኝም። እንዲያው በፕሮግራም ደረጃ ልዩነታችን የቱ ጋር ነው ብለሽ ብትጠይቂያቸው አንድም ነገር ነቅሰው ሊያወጡልሽ አይችሉም። ስለዚህ ቅድም እንዳልኩሽ ያለው ችግር እንግዲህ ዘውድ ይዞ የመዞር ነው። የኢትዮጵያን ፖለቲካ እኮ ላለፉት 27 ዓመታት ሲጎዳ የኖረው ይህ ዓይነት ስሜት ነው። የአንድነት ኃይል ነኝ በሚለውም ውስጥም ሆነ በማንነት ዙሪያ በተደራጀው አካል ይህ ስሜት አለ። እናም ይህ ሁኔታ የአገሪቱን ፖለቲካ ከቀውስ ወደ ቀውስ ነው እየወሰደ ያለው።
እኔ የአመራርነቱን ቁልፍ ካልጨበጥኩ በስተቀር አልዋሃድም የሚለውን ፅንፍ የያዘ አቋም የትም አያደርሰንም። እንዲያውም ዋናውና ወሳኙ ችግር ይሄ ነው የሚመስለኝ። ዓላማው አገሪቱን ካለችበት ችግር ውስጥ ማውጣት እስከሆነ ድረስ በተራ አባልነትም ቢሆን ማገልገል ይገባናል። ደግሞም ችሎታ ካለ ሥርዓቱ ራሱ ቀስ እያለ ያወጣሻል። ግን ያልኩሽ ችግር ስላለ አፍ አወጥተው ባይነግሩሽም መዋሃድ የማይፈልጉት ሥልጣን ፍለጋ መሆኑ ግልፅ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለው ፖለቲካ ሥርዓት ለፓርቲዎች ምን ያህል ምቹ ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ አምሃ፡- ለውጡ መምጣቱን ተከትሎ ለፓርቲዎች ጥሩ ሁኔታዎች ተፈጥሮ ላቸዋል። ከአምባገን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመሸጋገር ሂደት ላይ ነው ያለነው። ለዚህ ደግሞ ሁለት ደረጃዎችን ማለፍ ይጠበቃል። የመጀመሪያው ፈረንጆቹ ሊበራላይዜሽን የሚሉት ሲሆን ሁለተኛው ዴሞክራታይዜሽን ነው። የመጀመሪያው ደረጃ ያው እንደሚታወቀው የታሰሩ እስረኞች ተፈተዋል፤ በጣም አፋኝ የነበሩ ሕጎች እንዲሻሻሉ እየተደረገ ነው፤ ለፕሬሱም ነፃነቱ ተሰጥቶታል። እነዚህ ጉዳዮች እንግዲህ ወደ ሚፈለገው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሄድ ጥርጊያ መንገዶች ናቸው።
ሁለተኛውና ዋናው ደረጃ ግን ነፃ ተቋማትን የመገንባት ጉዳይ ነው። ከምርጫ ቦርድ ጀምሮ እምባ ጠባቂ የሚባለው፣ ስታትስቲክስ መስሪያ ቤቱን ሳይቀር በአጠቃላይ ዋና ዋና የተባሉትን የፍትህ እና የዴሞክራሲ ተቋማትን ሙሉ ለሙሉ የመንግሥት ወገንተኝነት አላቆ በገለልተኝነት ማደራጀት ይገባል። ለፓርቲዎች በነፃነት እንዲደራጁ ከመፍቀድ በዘለለ የሚያሰራና ትክክለኛ የሆነ ሕግ ማውጣት ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን ነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተፈጠረ የምንለው። ይሄ ደረጃ ካልታለፈ በስተቀር እንደገና የመመለስ ሁኔታ ይፈጠራል።
ነፃ ተቋማት በሌሉበት ሁኔታ ምርጫ ይካሄዳል ማለት ዘበት ነው። እስከዛሬ ነፃ ተቋማት በሌሉበት ሁኔታ ነበር አምስት ምርጫ የተካሄደው። በዚህ ምክንያት የተፈጠረው ሁኔታ ይታወቃል። አሁንም እነዚህ ነፃ ተቋማት አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ካልተመሰረቱ በስተቀር የታሰበውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ልናመጣ አንችልም።
አዲስ ዘመን፡- እያሉኝ ያሉት እንደ ምርጫ ቦርድ ያሉ የዴሞክራሲ ተቋማት አሁንም የገለልተኝነት ችግር አለባቸው ነው?
አቶ አምሃ፡- አይደለም! ምርጫ ቦርድ በአመራር ደረጃ ገለልተኛ የሆኑ ሰዎች ተመድበዋል። ግን እኛ እያወራን ያለነው ስለተቋም ነው። ተቋም ማለት አምስትና ስድስት ሰዎች ለምርጫ ቦርድ የሚሰጡ ሰዎች ብቻ አይደሉም። ምርጫው ሲካሄድ እነሱ የበላይ አመራር ይሰጣሉ እንጂ ውጤቱን አይቆጥሩትም፤ በሺ የሚቆጠሩ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የሚሰሩ በርካታ ሠራተኞች ናቸው የሚሰሩት። እነዚህ ሠራተኞች ምን ያህል ገለልተኛ ናቸው? ብቃታቸውስ በምን ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው? የሚለው ነገር አሁንም አጠያያቂ ጉዳይ ነው።
እነዚያ ሠራተኞች ስለነፃና ፍትሃዊ ምርጫ የጠራ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል። ፓርቲዎችም የየራሳቸውን ተቆጣጣሪ መመልመል ይገባቸዋል። ራሱ ምርጫ ቦርድ በሁሉም የምርጫ ጣቢያ የራሱን ኃይል መመደብ አለበት። የምርጫ ተቆጣጣሪዎች ምልመላ በራሱ በገለልተኝነት እንዲደራጁ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ጉዳይ ሰፊና ከበድ ያለ ሥራ ነው። ስለዚህ መሪዎችን እና ተቋማን አንድ የማድረግ አዝማሚያ ትክክል አይደለም። በሁለተኛ ደረጃ በገለልተኝነት መደራጀት አለበት ብዬ የማምነው የፍትህ ሥርዓቱ ነው። ከምርጫ በኋላ በቆጠራው ላይ ቅሬታ ቢፈጠር ገለልተኛ ሆኖ የሚዳኝ የፍትህ አካል ያስፈል ጋል። ይህንንም መፈተሽ ወሳኝ ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ካለው አጭር ጊዜ አኳያ እርስዎ በሚሉት ደረጃ የተዋጣለት ተቋም መመስረት ይቻላል ብለው ያምናሉ?
አቶ አምሃ፡- እኔ ሕገመንግሥቱ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ መካሄድ አለበት ስላለ የግዴታ መካሄድ አለበት ብዬ አላምንም።አላማው ምንድን ነው? ደግሞስ በየቀኑ ሲጣስ የነበረ ሕገመንግሥት አይደለም እንዴ? አሁን ለዚህ ሲጣስ ለኖረ ሕገመንግሥት ሳይሆን ይህችን አገር ካለችበት ችግር ማላቀቅ ነው ትኩረት መስጠት ያለብን። ለእኔ ትልቁ ጉዳይ ብዬ የምለው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ወደ ዴሞክራሲያዊ ጎዳና ማሸጋገር ነው። ሁኔታዎቹ ካላመቹ የግዴታ ግንቦት መካሄድ የለበትም። ምርጫ ቦርድ በሚፈለገው ደረጃ አልተደራጀም፤ ፓርቲዎቹ ራሳቸው ዝግጁ አይደሉም፤ አሁን ደግሞ በወጣው የፓርቲ ሕግ ትልቅ አቤቱታ ቀርቧል።
በተለይም እያንዳንዱ ፓርቲ በአገር አቀፍ ደረጃ ከተደራጀ 10ሺ አባል በክልል ደረጃ ደግሞ አራት ሺ አምስት መቶ መሆን አለበት የሚለውን ሃሳብ ባለመቀበላቸው የረሃብ አድማ እናደርጋለን እያሉ ነው። እነዚህ ነገሮች ሁሉ ባልጠሩበት ሁኔታ ምርጫ መካሄድ አለበት ብዬ አላምንም። ምርጫ ለማካሄድ በምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ራሳቸው መስማማት አለባቸው።አለበለዚያ ግን ያለው አማራጭ እነዚያን ሁሉ ፓርቲዎች አራግፎ በሚችሉት ብቻ ውድድሩን ማካሄድ ነው። ይህም ደግሞ ብዙ ጩኸት የሚያስነሳ ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የምርጫው መራዘም ጥያቄ ኢዜማን ይመለከታል?
አቶ አምሃ፡- ኢዜማ በሕጉ የተጠየቀውን መስፈርት ለማሟላት ችግር የለበትም። አሁን ይካሄድ ቢባልም ለመወዳደር ዝግጁ ነው። በግሌ ግን ምርጫ ቢራዘም የተሻለ ነው ብዬ አምናለሁ። ነፃ ተቋማት በአግባቡ ከተደራጁ በኋላ ቢካሄድ ለሁሉም የሚበጅ ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡- ሌሎች ግን ምርጫውን አለማካሄድ በራሱ በአገሪቱ ላይ ተጨማሪ ፖለቲካዊ ጫና ይፈጥራል ብለው ይሰጋሉ። በተለይ ሕዝቡ ባልመረጠው አካል እንዲመራ መቀጠሉ
ከፍተኛ ቅሬታ ሊፈጥር እንደሚችል ያስባሉ?
አቶ አምሃ፡- እንግዲህ ይህ የእምነት ጉዳይ ነው። ለምሳሌ በአዲስ አበባ ምርጫ ሁለት ጊዜ ተራዘመ አይደለም እንዴ? የሥልጣን ጊዜያቸው እኮ አልፏል። በእኛ አገር መንግሥት ሲፈልግ ምርጫን ያራዝማል፤ እሱ ሲመቸው ደግሞ አላራዝምም ይላል። ይሄ ሃሳብ ለእኔ ምንም ውሃ የሚቋጥር አይደለም። ዋናው እኮ ተግባር ነው። የድሬዳዋም ተላልፏል። ታዲያ ለምን በጊዜው አልተካሄደም? በሕግ የሚታመን ከሆነ ሕጉ ለሁሉም መስራት ነው ያለበት። አለበለዚያ ሌላ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ነው የሚያስገባን።
ራሱ የምርጫ ቦርድ የድሬዳዋንና የአዲስ አበባን ምርጫ አልተዘጋጀሁም መተላለፍ አለበት ብሎ ጊዜው ተላልፏል። እናም በሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ጊዜያቸው አልፏል። ምንም የተናገረ ሰው እኮ የለም። ስለዚህ ሕጉ ለአንድ ወገን ብቻ በሚያደላ መልኩ እየታየ መሄዱ ነው እንጂ ችግር የሚፈጥረው መራዘሙ አይደለም ችግር የሚፈጥረው። ሁሉም ይዘጋጅ፣ አስፈላጊ ተቋማት ይገንቡ፣ ከዚያ በኋላ ምርጫ ይካሄድ ማለት ለአገር ይጠቅማል ባይ ነኝ። የምርጫው መራዘም ይህችን አገር አሁን ካለችበት ሁኔታ ለማውጣት ያግዛታል።
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን በተለያዩ ማህበራዊ ድረገፆች በኢህአዴግ ከመሠረቱት ዋነኛ የሆነው ህወሓት ራሱን ችሎ ሊወጣ መሆኑን ሰምተናል። ይህ ሁኔታ ፓርቲ አገርን የሚመራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ምን ዓይነት አሉታዊና አወንታዊ ጎን አለው ብለው ያምናሉ?
አቶ አምሃ፡- የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ አንድ ሆኖ ያለመቀጠልና የመቀጠል ጉዳይ ክብደት ልንሰጠው የምንችለው አገር የሚመራ ድርጅት በመሆኑ ነው። የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አንድ አለመሆን በአገር ሰላምና አንድነት ላይ አሉታዊ ተፅፅኖ ያሳድራል። በእኔ እምነት በመጀመሪያ የአመለካከት ውህደት ሊቀድም ይገባ ነበር። ቀደም ሲል ህወሓት በሚመራበት ጊዜ ያው ሁሉንም ደፍጥጦ አመለካከቱንም አንድ አድርጎት ነበር። አሁን ግን ከለውጡ ወዲህ የአመለካከት ልዩነት መጥቷል።
ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ፓርቲዎችም የራሳቸውን አመለካከት ማራመድ ይችላሉ። ህወሓት ጥጉን ይዞ ቁጭ ባለበት ሁኔታ በአዴፓና ኦዴፓ መካከል የአመለካከት አንድነት ባልመጣበት ሁኔታ ውህደት መፍጠሩ በራሱ ውጤታማ ያደርጋቸዋል ብዬ አላምንም። ሲዋሃዱ ደግሞ የሃሳብ ልዩነታቸውን ሁሉ መጣል ይጠበቅባቸዋል። የአመለካከት አንድነት ከሌለ ነው ግንባር ሆነው ሊቀጥሉ የሚችሉት። ግን አሁን በየቀኑ በተጨባጭ የምናየው የአመለካከት አንድነት የላቸውም። ስለዚህ ውህደቱ እውን ይሆናል የሚለው ነገር ጥያቄ ውስጥ ነው።
እንዳልኩሽ በአገር አቀፍ ደረጃ መዋቀር በራሱ በጣም መልካም ጎን አለው። ለእኔ እንዲያውም ትልቅ መሰረተ ድንጋይ እንደመጣል ነው። በማንነትና በብሔረሰብ ተደራጅቶ አገር ሲመራ የነበረ ድርጅት በአስተሳሰብ ደረጃ ይሄ አያዋጣምና በአገር አቀፍ ደረጃ አንድ እንሁን ሲል ይሄ ትልቅ ታሪካዊ ክንውን ነው። ለወደፊቱ የሚያዋጣው ይሄ መሆኑን ኢህአዴግ መገንዘቡን ነው የሚያሳየው። እስከዛሬ በማንነት ላይ ተመስርቶ የተዋቀረው የፖለቲካ ሥርዓት አዋጭ አለመሆኑን ተረድቷል ማለት ነው።
የማንነት ጉዳይ የፖለቲካ ጥያቄ ሊሆን አይገባም። ምክንያቱም በተፈጥሮ ያገኘነው ስጦታ በመሆኑ። አሁን የአገራችን አንገብጋቢ ችግር ይሄ አይደለም። ከሆኑ ቤተሰቦች መወለድ በማህበራዊ አስገዳጅነት የሚፈጠር እንጂ ከፖለቲካ ጋር የሚያይዘው ነገር የለም። ባለፉት 27 ዓመታት ማንነትና ፖለቲካ ተዋህዶ ነው አገራችንን ችግር ላይ የጣላት። ባህልንና ቋንቋን የማሳደግ ጉዳይ የግዴታ በማንነት ፖለቲካ መደራጀት አያስፈልግም። ሌሎች አገሮች ይህ እንደሚቻል አሳይተውናል።
አዲስ ዘመን፡- እንበልና ኢህአዴግ ውህደቱ ቢሰምርለት በቀጣዩ ምርጫ በተለይ ከዶክተር አብይ ሕዝባዊ ተቀባይነት አኳያ ለኢዜማ ፈተና አይሆንበትም?
አቶ አምሃ፡- ነፃና ፍትሃዊ ሥርዓት እስከተፈጠረ ድረስ ማንም ያሸንፍ ማንም ፈተና ይሆናል የሚል እምነት የለኝም። እኛ የታገልነውና እየታገልን ያለነው እኛ አሸንፈን ብቻ ሥልጣን ለመቆናጠጥ አይደለም፤ ማሸነፍ እንዳለ ሁሉ መሸነፍም እንዳለ አምነን ነው የገባንበት። ዋናው ነገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፈጠሩና በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት መቋቋሙ ነው። ደግሞም የጨዋታው ሜዳው ጤናማ እስከሆነ ድረስ የሚስፈራን ነገር የለም። የተሸነፍነው በትክክለኛ መንገድ ከሆነ አሜን ብሎ ተቀብሎ ለቀጣዩ ራሱን ማዘጋጀት ነው ከሁሉም የሚጠበቀው።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካ ሁኔታ ዙሪያ መጽሐፍ ጽፈው በቅርቡ ለህትመት እንደሚበቃ ሰምተናል፤ የእርስዎ መጽሐፍ አጠቃላይ ይዘት ምን ይመስላል? ለአገሪቱ የፖለቲካ ትኩሳት ምን አዲስ መፍትሄ ይዞ ይመጣል ብለን እንጠብቅ?
አቶ አምሃ፡- የመጽሐፉ ርዕስ «አገራዊ ብሔርተኝነት ዘውጋዊ ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ የሚል ነው» ይህ መጽሐፍ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር የቀረበ የመፍትሄ አማራጭ ነው ይዞ የመጣው። በዋናነትም ኢኮኖሚው እንዳያድግ ሰንጎ የያዘው ፖለቲካዊ ችግር መሆኑን ባደረኩት ጥናት በማረጋገጤ ፖለቲካዊ ችግር በምን መልኩ ሊፈታ እንደሚችል የችግሩን ምንጭ ከነታሪካዊ ዳራው ተንትኖ ነው በዚህ መጽሐፍ ለማስቀመጥ የተሞከረው። በተለይም ባለፉት 27 ዓመታት ፖለቲካችን ያለፈበትን ታሪክ እንደሌለ ቆጥሮ አዲስ ታሪክ ልስራ ብሎ መነሳቱ ያስከተለውን ቀውስ በስፋት ያብራራል።
አዲስ ዘመን፡- አዲስ ታሪክ ለመፍጠር ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
አቶ አምሃ፡- ለዚህ ማስረጃ ለማግኘት ብዙ ርቆ መሄድ አያስፈልገንም። ሕገመንግሥቱ ሲጀመር እኮ «እኛ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በስምምነት አዲስ አገር እንመሰርታለን» ይላል። ኢትዮጵያ አዲስ አገር ናት እንዴ? ከዚህ እኮ ነው ችግሩ የሚጀምረው። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ያልነበረች ህወሓትና አጋሮች በመልካም ፍቃዳቸው የፈጠሯት አድርጎ ነው የሚገልፀው። ያንን ሁሉ የዘመን ታሪክ ካዱ። ስለዚህ ይሄ መጽሐፍ ሊተነትን የሚሞክረው ከታሪካችን የተገነጠለው ፖለቲካችን ያስከተለብንን ቀውስ ነው። አንቺ ከታሪክሽ ተገንጥለሽ ሰው ልትሆኚ አትችዪም። እነ ጃፓንና ኮሪያ የሰለጠኑት ዝም ብለው የምዕራባውያንን አምጥተው ሕዝባቸው ላይ በመጫን አይደለም። ታሪካቸውን ሳይጥሉ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ማጣጠም በመቻላቸው ነው በአጭር ጊዜ ከማይታመን ደረጃ የደረሱት። እኛ ግን የሃሰት የታሪክ ትርክት አምጥተን ሳናበቃ በሃሰት የታሪክ ትርክት ላይ ፖለቲካ ገነባን። ይህ መሠረት የለውም፤ ሃሰት ነው። ይህንን በዝርዝር ለማሳየት የተነሳ መጽሐፍ ነው። እያንዳንዱን በማስረጃ ተደግፎ ነው ለመፃፍ የተሞከረው።
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ አሁን የገለፁትን ነገሮች ሌሎችም በራሳቸው መንገድ አስቀድመው ፅፈውታል፤ ይህ መጽሐፍ ምን የተለየ ሃሳብ ይዞ መጥቷል፤ በተለይ ለአገሪቱ ፖለቲካ መፍትሄ የሚሆነው እንዴት ነው?
አቶ አምሃ፡- እስከዛሬ የተለያዩ መጽሐፎች ተፅፈዋል፤ ይሁንና በተለይ የዘውጌ ወይም የብሔር ማንነትና የዜግነት ማንነት ዙሪያ ተቆራርጠው የተፃፉ እንጂ ታሪክንና ጥናት መሰረት ተደርገው የተፃፉ ጽሑፎች የሉም። ዝንፈቱን ከነባራዊ የታሪካዊ መረጃዎች ጋር በማመሳከር ነው የተፃፈው። የእኛ አገር መንግሥታዊ አወቃቀር በቋንቋ ማደራጀት ለምን ተፈለገ? ይባላል እንጂ በቋንቋ ተደራጅቷል በተግባር ተደራጅቷል? ኦሮሚያና ትግራይ ክልል የፈለጉትን ከወሰዱ በኋላ የተቀረውን እንደፈለክ ተደራጅ ብለው ለቀውታል። በቋንቋ ነው ከተባለ ደቡብም በቋንቋው መሠረት 56 መሆን አለበት። በዋነኝነት የተፈለገው ሁለት በጦር ኃይል አሸንፈው የገቡ ኃይሎችን ጥቅም ለማስከበር ነው። ይህ ከሆነ ዘንድ የእኛ አገር የመንግሥት አወቃቀር ምን መልክ ሊኖረው እንደሚገባ በዝርዝር ቀርቧል። የሚያስፈልጋት ፌዴራሊዝም በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ብቻ ሳይሆን ከመሰረቱ ጂኦግራፊያዊ ሆኖ ሌሎች መስፈርቶችም አሉት።
ለምሳሌ ታሪካዊ ምህዳሩ ከሚወሰዱት መስፈርቶች አንዱ ነው። አምስት ስድስት መመዘኛዎች አሉት። ከእነዚህ መመዘኛዎች ተነስተቶ እንደገና መደራጀት አለበት። ይህም በብሔረሰብ ሳይሆን በቀጣና ነው የሚከፈሉት። ስለዚህ ይህ መጽሐፍ ለየት የሚያደርገው ከነተጨባጭ መፍትሄው በዝርዝር ማስቀመጡ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እኮ አንድ ቋንቋ ብቻ የሚናገር ወረዳ ከአምስት በመቶ አይበልጥም። የዚህችን አገር አወቃቀር ከብዙ አገሮች ለየት የሚያደርገው ራሱን ችሎ የተቀመጠ ሕዝብ ያለመኖሩ ነው። ይሄ አገር በጦርነት፣ ቸነፈር እንዲሁም በሰላማዊ መንገድ ለሺ ዓመታት ሲጓዝ የኖረ እዚያው ቤተሰብ እየመሰረተ በከፍተኛ ደረጃ ተቀላቅሎ የኖረ ነው። ይህንን ሁሉ እውነታ ጥሶ ነው ሕገመንግሥቱ የተቀረፀው።
አዲስ ዘመን፡- ላለፉት 27 ዓመታት ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ሥርዓት የቆየ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ ሕዝብ አምኖበት ተቀብሎ የኖረ እንደመሆኑ አሁን ላይ ሌላ አወቃቀር ማምጣት በራሱ ተቀባይነት ያገኛል ብለው ያምናሉ?
አቶ አምሃ፡- ድሮ የነበረው አህዳዊነት አናመጣም ግን አዲስ አሠራር ነው የሚኖረው፤ እኔ የምልሽ ከ27 ዓመታት በላይ እኮ ለሺ ዓመታት የኖረውን ሥርዓት በአንድ ጊዜ እኮ መናድ ተችሏል። ስለዚህ ከብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም መውጣት ያን ያህል ይከብዳል ብዬ አላምንም። ይህን ያህል ውሃ የሚቋጥር መከራከሪያ የሚቀርብበትም አይደለም። ሰዎች ለሺ ዓመታት በሰላም በኖሩበት አካባቢ አንተ መጤ ነህ እየተባለ ነው እየተሰደደ ያለው። በአለፈው ዓመት በዓለም ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዓመት 3ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕዝብ በመፈናቀል ከነሶሪያ ሁሉ በልጠናል። እኛ መንግሥት አለ በሚባልበት አገር ያለው መፈናቀልና የፖለቲካ ቀውስ ከዚህ ሥርዓት የመነጨ ነው። እናም ይህንን ሥርዓት እንቀጥል ማለት ይህችን አገር እናፍርስ ማለት ነው።
አገር ከፈረሰ ደግሞ ሁላችንም እንተላለቃለን። ስለዚህ የሚያዋጣው ሥርዓት የቱ እንደሆነ ግልፅ ነው። ይህ አስተሳሰብ የጥቂት ሰዎች ነው፤ የሕዝቡ አይደለም። ይህ አስተሳሰብ ፖለቲካውን መርተን ከፖለቲካው እንጠቀማለን የሚሉ ወገኖች ነው። የኦሮሞ፣ የአማራም የትግራዩም ገበሬ እጅ የለበትም። በመጀመሪያ ደረጃ በዚህች አገር ውስጥ ሕዝቡ መቼ ነው በፖለቲካ ጉዳይ ላይ ወስኖ የሚያውቀው? እስቲ ዕድሉን ይስጡትና ሕዝበ ውሳኔ ያድርጉ። እስቲ ድፍረቱ ይኖራቸው። የእኛ አገር የፖለቲካ ችግር ሕዝቡን ከፖለቲካ ሙሉ ለሙሉ ማግለሉ ነው። የሕዝቡን ውሳኔ ሁሉም ፖለቲከኛ ሊቀበል ይገባል። እኛ አንወስንለት። ዘመናዊ ፖለቲካ በሕዝብ ውሳኔ የሚመራ ነው። ንጉሱ እኮ ተንከባክበው ያስተማሩት ተማሪ ነው ትምህርት አነቃውና በራሳቸው ላይ የተነሳባቸው። አሁንም ይህ ሥርዓት የሕዝብን የልብ ትርታ ማዳመጥ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት መንግሥት አገሪቱን ከገባችበት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለማውጣት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው የሚገኘው፤ እርሶ የኢኮኖሚ ምሁር እንደመሆንዎ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንዴት ይመለከቱታክል? ምንስ የተሻለ አማራጭ ሊከተል ይገባል ይላሉ?
አቶ አማሃ፡- በእኔ እምነት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ተባባሰ ሁኔታ ውስጥ ያስገባው ባለፉት 27 ዓመታት የተከተልነው የፖለቲካ መስመር ነው። መንግሥት ከራሱ ውጪ ፓርቲውም በኢኮኖሚ ተሳታፊ እንዲሆን በማድረጉ ነበር ሥርዓቱ በከፍተኛ ደረጃ በሙስና ውስጥ የተዘፈቀው። መንግሥት ሲከተለው የነበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በብዙ አንፃር ትክክል ያልሆነና የተዛባ ነው። እናም ለተወሰነ አካባቢ ብቻ እንዲጠቅም ተደርጎ የተቀረፀ ስለነበር ለአገር ሊጠቀም በሚችልበት ሁኔታ አልነበረም።
በእርግጥ መንግሥት በኢኮኖሚ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ መውጣት አለበት እያልኩ አይደለም፤ ነገር ግን ተቋሞችን ይዞ በሚያስተዳድርበት ጊዜ በንፅህና መሆን አለበት። አመራር የሚሰጠው ኃይል ከሙስና የፀዳ፣ ለአገር የሚያስብ መሆን አለበት። ለራሱ ብቻ የሚያስብ ኃይል የሚደራጁ የኢኮኖሚ ተቋማት የአገር ሳይሆን የግለሰብ መጠቀሚያ ነው የሚሆኑት። ይሄ ሁሉ ችግር የመጣበት ምክንያት መንግሥት ዝም ብሎ ብሔራዊ ባንክን እያዘዘ የበጀት እጥረት ባጋጠመው ቁጥር ገንዘብ እያተመ ነበር ወደ ገበያ የሚያስገባው። ምርቱ ባላደገበት ሁኔታ ገንዘብ እየታተመ ወደ ገበያ ሲለቀቅ አንዱን ምርት ለማዘዋወር ከሚያስፈልገው ገንዘብ በላይ የእያንዳንዱን ምርት ዋጋ እየጨመረ ነው የሚመጣው። ይህ ሁኔታ የዋጋ ንረት አሁን ልንቆጣጠረው በማንችልበት ደረጃ ላይ አድርሶታል። ሥራ አጥነትና የኑሮ ውድነት እየተባባሰ መጥቷል። ኢኮኖሚውን የፖለቲካ ፍላጎት ለማርኪያ እንደመሣሪያ ነው ሲጠቀምበት የቆየው። ኢኮኖሚው በኢኮኖሚ መርህ ነው መመራት ያለበት።
በሌላ በኩል በትላልቅ ኢንቨስትመንቶች ጣልቃ ሲገባ በምን መልኩ መግባት እንደነበረበት በውል ሳይጠየን ነው ዘው ብሎ የተገባበት። የቁጥጥር ሥርዓት ስላልተበጀለት ነበር የስኳር ኮርፖሬሽን ለምዝበራ የተዳረገው። እናም መንግሥት ራሱ ያልፀዳ መንግሥት ከሆነ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ አይችልም። እኛ አገር ግን በምርኮ የተያዘ መንግሥት ስለሆነ ኢኮኖሚውንና አገሪቱን ለመበዝበዝ ተጠቅሞበታል። ስለዚህ ፖለቲካው ለሕዝብ ተጠያቂ ቢሆን ይህ ሁኔታ አይፈጠርም ነበር። ተሯርጦ የፖለቲካውን ሥልጣን የጨበጠ ኢኮኖሚውን መጫወቻ ያደርገዋል። አሁንም ከዚህ ሁኔታ አልወጣንም። ሌላው ይቀርና ያጠፉ በሕግ ተጠያቂ አልሆኑም፤ የተወሰደው ሀብት ለሕዝብ መጥቀም ሲገባው እስካሁን እንዲመለስ አልተደረገም። ያ መስመር ባልጠራበት ሁኔታ ለመጪው አመራር አስተማሪ እንዴት ሊሆን ይችላል? ደግሞስ ላለመቀጠሉ ምን ዋስትና አለን?
አዲስ ዘመን፡- እርሶ የሚጠቅሷቸውን ችግሮች ጨምሮ መንግሥት አማራጭ የሚለውን አዲስ አቅጣጫ ቀይሶ እየሰራ ነው፤ በተለይ ያለውን የብድር ጫና ለመቀነስ ሀብት ከሀገር ውስጥ ለማሰበሰብ ጥረት እያደረገ ነው፤ ይህ አካሄድ አገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንፃር ምን ያህል አዋጭ ነው ይላሉ?
አቶ አማሃ፡- እንግዲህ ባለው ሁኔታ አንዳንድ ችግሮችን ለመፍታት እየተሞከረ ነው፤ ለነገሩ ከእንግዲህ ወዲያ ብድርም ብንፈልግ የሚሰጠን የለም። ስለዚህ ብድርን መቀነስ መቻል አለብን። ያለውንም ቢሆን በከፍተኛ ቁጥጥር ሥራ ላይ ማዋል አለብን። ይህንን ለማድረግ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች መልካም ናቸው ባይ ነኝ። ግን የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ለማካካስ ሲል ብቻ አንዳንድ አትራፊ ድርጅቶቹንም ሳይቀር ለግል ባለሀብቶች ለመስጠት ማሰቡን አልደግፍም፤ ተቋማቱን የሚሸጥበትን መርህ በውል ሊያጤነው ይገባል። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የመሳሰሉ ድርጅቶችን መሸጥ አለበት ብዬ አላምንም። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ዳግመኛ ሊያጤናቸው ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ አማሃ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012
ማህሌት አብዱል