መስከረምን ከሚያደምቁ በዓላት አንዱ ኢሬቻ ነው። ምክንያቱም ወቅቱ ጭጋጋማው ክረምት አልፎ አደይ አበቦች መስኩን የሚሞሉበት፣ ምድሪቱ በለምለም ሳር የምትሸፈንበት ጊዜ ነው። ከዚያ ባሻገር ደግሞ መስከረም ከዘመን ዘመን መሸጋገርን፣ ብርሃን ማየትን፣ ልምላሜን መላበስን ይናገራልና ኦሮሞዎችም ይህንኑ ትልቅ ታሪካዊ በዓል በደመቀ መልኩ ያከብሩታል።
በኢሬቻ በዓል አዲስ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የብልጽግና እንዲሆን ምኞት ይገለጽበታል። ለፈጣሪም ምስጋና ይደርስበታል። ከክረምት ወደ ብርሀን መውጣትን ምክንያት በማድረግ የሚቀርብ ምስጋና በመሆኑም የሚሞገሰው ለምለም ቄጠማና አደይ አበባ የትዞም ነው። ይሄ የበዓሉ ልዩ መገለጫ ይሆናል። በዚህም ፈጣሪን እያመሰገኑ በቀጣይም መልካም ዘመን እንዲሆንላቸው ይመኛሉ። ታዲያ ይህ በዓል እስከዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዲ (ሐይቅ) ዳርቻ በድምቀት ሲከበር የቆየ ቢሆንም ዘንድሮ ደግሞ ሁሉም ብሄር ብሄረሰብ በጋራ በድምቀት እንዲያከብረው በአዲስ አበባ ክብረ በዓሉን ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል።
ኢሬቻ ምንድ ነው? እንዴት ይከበራል? ለምን ይከበራል? የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎች በማንሳት መስከረም 3 ቀን 2012 ዓ.ም በዓሉን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በተሰጠ ስልጠና ላይ አቶ ስንታየሁ ቶላ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል።
አቶ ስንታየሁ በጥናታቸው ላይ እንዳመለከቱት ኢሬቻ የፍቅር፣ የሰላም፣ የእርቅ፣ የይቅርታ፣ የምስጋና እና የምልጃ በዓል ነው። የኦሮሞ ህዝብ ሁሉን ነገር ለፈጠረው፣ ሁሉን ነገር ማድረግ ለሚችል ዋቃ (አምላክ) ምስጋናና ክብር የሚያቀርብበት ስርዓተ በዓልም ነው። በዚህም በበዓሉ ዕለት ላገኘው ጸጋና በረከት፣ ሰላምና ደስታ፣ ጤናና ዕድሜ፣ ፍቅርና ክብር ለሚያምንበት አንድ ዋቃ (አምላክ) ምስጋና ያቀርባል።
ኢሬቻ ከዘመን ወደ ዘመን ከአንድ ወቅት ወደሌላ ወቅት በሰላም ያሸጋገረውን አምላኩን የሚያመሰግንበትና መጪውን ዘመን የሰላም የደስታ እንዲሆንለት የሚለምንበት ስርዓተ በዓልም ነው። በዚህ በዓል ለሰላም፣ ለሰው ልጅና ለተፈጥሮ ይጸለያል። ለጤና፣ ለሰብል፣ ለእንስሳትና ለአራዊት፣ ለዝናብና ለአየር፣ ለዕጽዋትና ለተክል፣ ለህጻናት፣ ለቤተሰብ፣ ለጎሳ፣ ለአገር፣ ለመላዉ ዓለምና ለመላው የሰዉ ልጅ ሰላምና ደህንነት ፈጣሪውን ያመሰግናል፣ ይማጸናል፣ ይመርቃል። በመሆኑም ኢሬቻ የምርቃት፣ የምስጋና፣ የተማጽዕኖ፣ የዕርቅ፣ የይቅርታ፣ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የወንድማማችነት፣ የበረከትና የቃልኪዳን በዓል ተደርጎ ይወሰዳል።
ከዚህም ባሻገር ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ የጋራ ባህሉንና ታሪኩን፣ አንድነቱንና ወንድማማችነቱን የሚገልጽበት የሚያድስበትና የሚያጠናክርበት መድረክም ነው። የጾታ፣ የፖለቲካ አመለካከትና የሀይማኖት ልዩነት ሳይገድበው የማንነቱ መገለጫ ባህሉን ታሪኩን የሚያስታውስበትና የሚዘክርበት ጊዜው ነው። ይህ ሁኔታው ደግሞ ወንድ ሴት፣ ህጻን ሽማግሌ ሳይል፣ የፖለቲካ አመለካከትና የሀይማኖት ልዩነት ሳይወስነው፣ ጊዜና የቦታ ርቀት ሳያግደው በደቡብ ከቦረናና ከጉጂ በሰሜን እስከ ከሚሴና ራያ አዘቦ፣ ከሐረርጌ እስከ ምዕራብ ቄለም ኢሉአባቦራ ከዚያም ባሻገር እስከ ወንበራ ድረስ ያሉት የኦሮሞ ህዝብ የሚሳተፉበት ነው።
እንዲሁም የኢሬቻ በዓል መቼ መከበር እንደተጀመረ በትክክል መናገር ባይቻልም ከኩሽ ህዝቦች እምነት ጋር የተያያዘ መሆኑን የጥንታዊ ኩሽ ታሪክ ተመራማሪዎች ያረጋግጣሉ። ጥንታዊ ኩሾች በሰሜናዊ ምስራቅ አፍሪካ በኑቢያ ይኖሩ ነበር። ስለዚህም ከ6ሺ500 ዓመታት በፊት ኦስረስ ተብሎ የሚታወቅ እምነትን ይከተላሉ። ይህ ደግሞ የእምነት ሁሉ መሰረት የሆነውን በአንድ አምላክ ማመንን ያነገበ ነው። እናም የኦሮሞ ህዝብ ሀይማኖትም ከዚያ መጥቷል ተብሎ ይታመናል። ይህም ሀይማኖት ደግሞ ዋቄፋና እንደሚባል ይናገራሉ።
ዋቄፋና በአንድ ዋቃ ማመን ነው። ይህ አምላክ ደግሞ ጥቁር ሲሆን፤ ዋቃ ጉራቻ ይባላል። ጥቁርነት ከሀያሎች ሁሉ ሀያል ነው፤ ንጽህነት ነው፤ አምላክነት ነው። የኩሽ ህዝቦችም አፍሪካዊነት መገለጫ ናቸው። አንድ አምላክ ሆኖ ብዙ ስሞች አሉት፡- ዋቃ ሁሉም ቦታ አለ፤ ሁሉም የሆነው በእሱ ነው፣ ሁሉን የፈጠረ፣ ሁሉን ማድረግ የሚችል ነው። የጥንታዊ ኩሾች ባህል፣ ፍልስፍና፣ ዕውቀትና ስልጣኔ የዋቄፋና እምነት መሰረቶች ናቸው።
እሬቻ ለአምላክ ምስጋና የሚቀርብበት የፍቅር፣ የይቅርታ እና የሰላም በዓል ነው፤
ኢሬቻ በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚከበር የሚያስቀምጠው ጥናቱ፤ ኢሬቻ ቢራ /ኢሬቻ መልካ እና ኢሬቻ አፍራሳ /ኢሬቻ ቱሉ/ ተብሎ ይከበራል። የሁለቱም በዓላት የአከባበር ስርዓትና ልማድ ተመሳሳይ ቢሆንም የሚከበሩበት ወቅት ግን ይለያያል።
ኢሬቻ ቢራ /ኢሬቻ መልካ
ኢሬቻ ቢራ የክረምት ወቅት አልፎ ፀደይ ሲገባ ይከበራል፤ በአብዛኛው ከመስከረም እስከ ህዳር ድረስ የሚከበር ሲሆን፤ በተለይ በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ ከመስቀል በዓል ማለትም እፋኖ ወይም ጉባ ኮርማ በኋላ እሁድ ቀን ላይ ይከበራል።
በዓሉ በአብዛኛው በሐይቆች ወይም በወንዞች ዳር አደይ አበባ፣ ለምለም ሳር፣ ዘንባባ፣ ተይዞ ይከበራል። በተለይ አደይ አበባ የፀደይ ወቅት መለያ ተደርጎ ስለሚወሰድ ከእጅ ላይ አይጠፋም። በዚህም ከከባዱ የክረምት ወራት በሰላም ያሻገራቸውን፣ ዘመድ አዝማድ መገናኘት በመቻላቸው፣ ክረምቱን የዘሩት እህል ቡቃያ በማየታቸው፣ ፈጣሪያቸውን ዋቃ ያመሰግናሉ። መጪው የበጋ ወራት የሰላምና የጤና እንዲሆንላቸው የበቀለው ቡቃያ ፍሬ እንዲያፈራ ይለምናሉ።
ኢሬቻ አፍራሳ /ኢሬቻ ቱሉ/
ይህ ኢሬቻ በመጋቢት፣ ሚያዝያ እና በግንቦት ወራት ውስጥ የሚከበር ሲሆን፤ በአብዛኛው በሚያዝያ መጨረሻና ግንቦት መጀመሪያ ላይ በተራራና ከፍታማ ቦታዎች ላይ ይከበራል። ክረምትና በጋ የማይደርቀውን ሳር ይዘው ያከብራሉ። ደረቁ የበጋ ወራት ማለፊያና የክረምት መምጫ ዝናብ የሚታይበት ወቅት ነው። ከባዱን የበጋ ወቅት በሰላም ያሳለፋቸውን አምላካቸውን ያመሰግናሉ፤ ቀጣዩም የክረምት ወራት የሰላም እንዲሆንላቸዉ ይለምናሉ።
በባህሉ እንደ ወንዞች፣ ሀይቆች፣ ተራሮች፣ ኦዳ ዛፎች፣ ጫካ የመሳሰሉት ስፍራዎች የዋቃ መንፈስ እና ተአምራት የሚታዩባቸው ስፍራዎች እንደሆኑ ይታመንባቸዋል። በዚህም ኦሮሞ ለተፈጥሮ አካባቢዎች ትልቅ ከበሬታ እንዲሰጥ ሆኗል። ይህ ደግሞ ኢሬቻ የሚከበርባቸው ተፈጥሮአዊ ስፍራዎች ክብር እንዲኖራቸው አድርጓል። ይህ ማለት በስፍራው /በወንዙ በሀይቁ፣ በኦዳዉ፣ በተራራው ማመን ሳይሆን ሁሉን ለፈጠረው ዋቃ መንፈሱ አለበት ተብሎ በሚታመንበት ቦታ ክብር መስጠት መሆኑን ያብራራሉ።
ኢሬቻ የተፈጥሮ ህግና ስርዓት በዓል ነው። በዋቄፈና እምነት ሁሉም ነገር ከህግና ስርዓት ጋር ይዛመዳል። መልካ የራሱ ህግና ክብር አለው፤ ቱሉ የራሱ ስርዓትና ክብር አለው። በመሆኑም ኢሬቻ የዋቃ ስርዓት፣ ህግና ትዕዛዝ የሚሟላበትና ቀጣይነት እንዲኖረው የሚከበር በዓል ነው። ዋቃ ሁሉንም ነገር ስርዓት አበጅቶ ፈጥሮታል። እናም ያለስርዓት የተፈጠረ አንዳች ነገር የለም። በዚህም ፍጥረታት ሁሉ ስርዓታቸውን ጠብቀው ይኖራሉ። ይህ ተፈጥሮአዊ ህግ ሳይዛነፍ ኡደቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ለማመስገንና ለመለመንም ኢሬቻ ይከበራል።
ሌላው የመከበሩ ምስጢራዊነት ‹‹ማሬዎ ማሬዎ›› ማለት ሁሉም ነገር የተፈጥሮ ስርዓትን ጠብቆ ዞሮ መምጣቱን ያሳያል። በዚህም በዓል በፈጣሪና ፍጥረት መሀል ያለው ስርዓት ሳይቋረጥ ኡደቱን ጠብቆ በመካሄዱ የሚከበር የምስጋናና የምልጃ በዓል ነው።
ኢሬቻ መልካ የመዋለድ ምልክት ሲሆን፣ የውልደት ቀጣይነትን ይወክላል። ቱሉ ደግሞ የበጋ፣ ብቸኝነትና ጽናትን ይወክላል። እናም መልካና ቱሉ የሰው ልጅ የተፈጠረበትና ውልደት የተጀመረበት ስፍራ በመሆናቸው ትልቅ ከበሬታ ይሰጣቸዋል። ዋቃ ከፍተኛውን የፈጠራ ተአምር ያደረገበት ስፍራ ናቸው ተብሎ ይታመንባቸዋል።
በጥንት ዘመን የኦሮሞ ህዝብ የእሬቻ በዓልን መልካ ሞርሞር ፣ ሀሮ ዋላቡ፣ ቱሉ ዋላል፣ ቱሉ ነምዱሪ ወዘተ በሚባሉ ስፍራዎች ያከብር እንደነበር የሚገልጹት ደግሞ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ከበደ ዴሲሳ ናቸው። እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ኢሬቻ መሀል አገርም ስድስቱ የዋቃ ሐይቆች በሆራ ፊንፊኔ፣ ሆራ አርሳዲ፣ ሆራ ኪሎሌ፣ሆራ ዋርጦ… እና ስምንቱ የዋቃ ተራራዎች በሚባሉት ቱሉ ጩቃላ፣ ቱሉ ኤረር፣ ቱሉ ፉሪ፣ ቱሉ ቦሰት፣… ቦታዎች ይከበር ነበር። እናም ዘንድሮም ከስድስቱ የዋቃ ሐይቆች/ወንዞች/ የሆራ ፊንፊኔ እሬቻን ለማክበር የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች ተደርገዋል ብለዋል።
ኢሬቻ የራሱ የአከባበር ስርዓትና ክንውኖች አሉት የሚሉት አቶ ከበደ፤ በዋዜማው የሙዳ ስርዓት ይከናወናል። ይሄ በአባ ገዳዎችና በአባ መልካዎች የሚከናወኑ የምስጋና መስዋዕቶች፣ ጸሎት፣ ምርቃት፣ እርቅ፣ በሐይቁ ውኋ መጠመቅ… ይተገበራል። ወጣት ሴቶችና ወንዶች በህጻናት በአዛውንቶች በአባገዳዎች በጋራና በተናጠል የሚዘመር ህብረ ዜማ፣ ዘፈኖችና ጭፈራዎች፣ የጋብቻ ስነስርዓቶች በየደረጃው ይቀርባሉ። የተለያዩ ባህላዊ ምግቦችም ለዚህ በዓል አከባበር ልዩ ድምቀት እንደሆኑም አጫውተውናል።
እንደ አቶ ከበደ ማብራሪያ፤ በዓሉ በአባ ገዳዎችና በአባ መልካዎች የሚመራ ሲሆን፤ ወደ በዓሉ ስፍራ ሲሄዱ ከፊት ልጃገረዶች ቀጥሎ ሴቶች ከዛም አባገዳዎችና አዛውንቶች መጨረሻ ላይ ወጣቶች ባህላዊ ጭፈራዎችን እያሰሙ ይከተላሉ። ወንዙ ዳር ሆነው ታላቅ ታናሽ እንደቅደም ተከተላቸው ይመርቃሉ፤ መልዕክት ያስተላልፋሉ።
ኢሬቻ በንጹህ አዕምሮ በንጹህ መንፈስ፣ በሰላም፣ የሚከበር በዓል ነው። ንጹህና የኢሬቻ መሰረት ተደርጎ ይወሰዳል። እናም ኢሬቻን ለማክበር ከውስጥም ከውጪም ንጹህ መሆን ግዴታ ነው። ቂም፣ ክፋትን፣ ጥላቻን ይዞ ኢሬቻ ለማክበር አይኬድም። ምክንያቱም ልመናንና ምስጋናን ዋቃ አይሰማም። ስለዚህ ከኢሬቻ በፊት የተጣላ መታረቅ፣ የተቀያየመ ይቅር መባባል፣ የበደለ መካስ ይጠበቅበታል። ግጭቶች መፈታትም አለባቸው። ያጠፋ ይቅርታ መጠየቅ ይደረግለታልም። የተጣመመ ነገር መቃናት፤ የተሰበረ ነገር መጠገንም አለበት።
ኢሬቻ የፍቅር፣ የእርቅ፣ የወንድማማችነት፣ የይቅርታ፣ የሰላም፣ የደግነት /መልካምነት፣ የተስፋ፣ የብልጽግናና የአንድነት በዓል ነው። የመሻገርም በዓል ነው። በንጽህና ወደሚቀጥለው መልካም ጊዜ መሻገርን ይጠይቃል። ቂምና በቀል፣ ጥላቻና ጥል፣ ግጭትን ይዞ መሻገር አይቻልም። ቂም በቀል ጥልና ግጭት ይዞ ወይም ሳይፈታ ለእሬቻ መልካ አይወረድም፣ ቱሉ አይወጣም። ሁሉም ግጭቶች በእርቅና በይቅርታ መፈታት አለባቸው።
የኢሬቻ ፍልስፍና፣ እሴቶችና አስተምሮት ከአገር ግንባታ አንጻር ሲታይ ብዙ ነገር ማንሳት እንደሚቻል የሚናገሩት አቶ ከበደ፤ ኢሬቻ በብዝሀነት ላይ አንድነትን ይገነባል። ባህል፣ ሀይማኖት የፖለቲካ ርዕዮት ዓለም፤ ጾታ፣ ዕድሜ፣ ሙያ፣ ዜግነት፣ ድንበር ሳይገድበው በመከበሩ የአንድነት ተምሳሌት መሆኑን ይናገራል። እናም ይህ መነሻ ሆኖ በበዓሉ ላይ ልዩነት እንደውበትና ጥንካሬ ይወሰዳል። የኦሮሞ አንድነት ይወደሳል፤ ይዘመራል፣ ይገነባል፣ ይታደሳል፣ ይጠነክራል። የአንድነት፣ የፍቅር፣ የወንድማማችነት፣ የመቻቻል …ወዘተ ቃል ኪዳንም ይታደሳል። ዘንድሮም ይሄንን ከፍ አድርገን ኢሬቻን እናክብር። ሰላም!
አዲስ ዘመን መስከረም 11/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው