ከገጠር እስከ ከተማ በኢትዮጵያውያን የሚዘወተር ትልቁ የማህበራዊ መስተጋብር መገለጫ ነው ቡና∷ ዘመድ አዝማድ߹ ጓደኛ߹ ጉረቤታም ሁሉ ሲገናኝ ለጫወታው ማድመቂያ የሚዘጋጅ ትልቁ ግብዣ ነው ቡና∷ በእጣን ጢስ ደምቆ፤ በቡና ቁርስ ታጅቦ የጨዋታውን አውድ ያደምቃል∷ ፖለቲካዊ߹ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ይነሳሉ፤ ይወድቃሉ∷ የመረጃ ልውውጦች ይደረጋሉ። እንዴት ከተባለ ለቀባሪው አረዱት ቢሆንብኝም ጥቂት ማለቱ ለጉዳያችን መነሻ ይሆነናልና ላንሳ። ሳያስቡት ቡና እየጠጡ ያልተወያዩበት፣ ያላበጠሩት፣ በጋራ ያልዳሰሱት ጉዳይ የለም።
እንግዲህ ቡና ዘመናዊ የመረጃ ማግኛ ዘዴ ላልነበራት ሀገር ከገጠር እስከ ከተማ አወያይ፣ የመረጃ መለዋወጫ መንገድ ነው ለማለት ይቻላል∷ እናም የቀደሙት እንዲህ ተወያይተው፣ ወስነው ብሎም አንድ ልብ ሆነው ብዙ ሃገራዊ ፋይዳ ያላቸው ሥራ ሰርተዋል፤ ወደፊትም ይሰራሉ። ልክ እንደቡና ሁሉ ኢትዮጵያን ሌላም በየክልሉ መረጃ የምንለዋወጥበት ስልክና ፖስታ ባልነበረት ዘመን ጭምር መረጃ የምናደርስበት ስርዓት ነበረን∷ በባህላዊ መንገድ መረጃ መቀበልና መስጠት ታዲያ በአፋሮች ዘንድ ዛሬም ድረስ ተጠናክሮ የቀጠለ መለያቸው ነው∷ የአፋሮች ‹‹ዳጉ›› አንዱ ኢትዮጵያዊ እሴታችን ነው። ዳጉ ምንድነው ካላችሁ ከተለያዩ ምንጮች ያገኘናቸውን አብነት በማድረግ ጥቂት እናስነብባለን።
‹‹ዳጉ›› የአፋሮች የመረጃ መለዋወጫ ስርዓት ነው∷ የየቀኑ መምሪያ (መርሃቸው)፣ ኑሯቸውን እንዴት እንደሚያስተካክሉ መጠቆሚያቸው ወዘተ ነው። በእርግጥ አፋር ክልልን ስናነሳ ከዚህ የላቁ በርካታ ባህላዊ እሴቶች ያሉበት ነው። በሁሉም ቅርስና ታሪክ የማንነታችን ማህተምም ለመሆኑ ነጋሪ አያሻውም፡፡
ከሰሞኑ እንኳን በየሚዲያው የሰማናው አዲስ ዜና የሰው ዘር መገኛ መሆናችን ከራሳችን አልፎ አለምን አጀብ አሰኝቷል። ስለዚህም አፋር ለአገሪቱ እንቁ ታሪክ ነጋሪ ነው። ግን ዛሬ አንድ ጉዳይ ላይ አይናችንን አሳርፈን እናውጋ። ምክንያቱም አንዱ ካልተመረጠ ስለአፋር ማውራት አባይን በጭልፋ
ይሆንብናል። እናም ዛሬ ስለ መረጃ ልውውጣቸው ሥርዓት ዳጉ ብቻ እናቀርባለን።
በክልሉ የአካባቢው ነዋሪዎች የሚኖሩት በእጅጉ ተጠጋግተው ነው። እናም ወደ አንድ ሰው መኖሪያ ሲዘለቅ ጎረቤቶችንም ማግኘት ግድ ይሆናል። ስለዚህም ከላይ መነሻችን እንዳደረግነው የቡና ወግ ሁሉ በዳጉም እንግዶች ሞቅ ያለ አቀበባል ተደርጎላቸው ቤት ያፈራውንም ከቀማመሱ በኋላ መረጃ ይለዋወጣሉ። አፋር ላይ አፋርኛ ብቻ አይነገርም። ምክንያቱም የሁሉም ብሔር መገኛ ስለሆነች። እናም በአንድ ቤት የተሰበሰበው ሰውም በአፋርኛ፣ በትግርኛና በአማርኛ፣ በኦሮምኛና በሌሎች ቋንቋዎች በሚገባው ልክ በዳጉ ስርዓት መረጃን ይቃርማል።
በስብስቡ መካከል በተደጋጋሚ ‹‹ዳጉ›› የሚለውን ቃል ግድ ነው። እናም በዳጉ ስርዓት የወቅቱ ገበያ ይዳሰሳል:: ሁሉም ከውሎው እና ከሰማው ለሌላው ያካፍላል:: የዋጋ መውጣት እና መውረድ ይታወቃል:: የት ቦታ ጥሩ ገበያ በእንዴት ያለ ሁኔታ እንደሚገኝም ይነገራል:: በእርግጥ በ ‘’ሞባይል’’ ስልክ ዘመን እንዲህ ይወራል የሚሉ አይታጡም። ግን መቶ በመቶው ያገሪቱ ህዝብ ይህን ቴክኖሎጂ ይጠቀማል ቢባል አይታመንምና ዳጉ ለተማረውም ላልተማረውም መረጃ የሚሰጥ ስለሆነ ከሞባይል መረጃ የላቀ ነው። በዚያ ላይ በሞባይል ያልተከወነ ነገርም መረጃ ሆኖ ይተላለፋል። በዳጉ ግን እውነት ብቻ እንደሚነገርበት የአካባቢው ነዋሪዎች ምስክር ናቸው።
የአፋር ሕዝብ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው በሚጓጓዝበት ወቅት በመንገዱ ለሚያገኘው ሰው መረጃ ሳይሰጥ አያልፍም። አንዱ አልፎት በመጣው አካባቢ ስላለው ሁኔታ በአጠቃላይ ለሌላው ይነግራል። ዘመናትን ያስቆጠረው ይህ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት የአካባቢው ነዋሪዎች ለክንውኖች ቅርብ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡
ዳጉ በቤት ብቻ አይደለም መረጃን የሚሰጥበት። በጉዞ ላይ ሁሉ ሆኖም መረጃን ማግኛ መንገድ ነው። ስለዚህም አፋሮች በበረሃ ሲያቋርጡ እንኳን መጠጥና ምግብ ከመጠያየቅ አስቀድመው መረጃ የሚለዋወጡት ለዚህ ነው። በዳጉ መረጃ አሰጣጥ ዙሪያ የሚዋሽ አለ ተብሎ አይታመንም። ስለዚህም መረጃው ትክክል እንደሆነ ይታመናል። ይህ ደግሞ ሥርዓቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕውቅና እያገኘ እንዲመጣና ከክልሉ ተወላጆች ባሻገር ብዙዎች ስለ ዳጉ መጠነኛም ቢሆን መረጃ እንዲኖራቸው አድርጓል።
ዳጉ መረጃ ከመለዋወጥ ጎን ለጎን ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚያጠናክር የመረጃ ሥርዓት ነው። በነዋሪዎች መካከል ላለው ቅርርብ የራሱን አስተዋጽኦም ያበረክታል። በእርግጥ ስለ ማኅበረሰባዊ ትስስር ሲነሳ የአካባቢውን ነዋሪዎች ኅብረት የሚያፀኑ ሌሎችም ባህላዊ እሴቶች በአፋሮች ዘንድ ሞልቷል። ይሁንና ዋናው ጉዳያችን ዳጉ ስለሆነ በእርሱ ላይ እንቆይ።
ዳጉ ማኅበራዊ ትስስር በግለሰቦች ግንኙነት ደረጃ የሚገለጽበት ሥርዓት ሲሆን፣ በአጋጣሚ ተገናኝተው በአንድ ጊዜ ዝምድናም ይፈጠርበታል። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ወዳጅነቱ ጠንክሮ ከግለሰቦቹ ባለፈ የቤተሰቦቻቸውንም ትስስር ያሰፋዋል። እናም እነዚህ የማኅበራዊ ትስስር መገለጫ የሆኑ ባህላዊ እሴቶች ከግለሰቦች ጀምሮ በማኅበረሰቡ ያለው ቅርርብ መሠረት መሆናቸው ይነገራል።
ባህላዊ እሴቶቹ ማኅበረሰቡ በኅብረት የቆመባቸው ናቸው። ምክንያቱም አንድ ሰው ራቅ ወዳለ ቦታ ሲሄድ ቢርበው ባገኘው ሰው ቤት ጎራ ብሎ ያሻውን ያደርጋል። ዕረፍት ያደረገበት ቤተሰብ ትስስርም ከአንድ ቀን በላይ ዘላቂነት እንዲኖረው ይገነባበታል። ስለዚህም ባህላዊ እሴቶቹ ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገሩ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ዳጉ ረዥም ዕድሜን ያስቆጠሩ የማኅበራዊ ትስስር መገለጫም ነው። ስለዚህ ግዙፍ የሆኑ የክልሉ ቅርሶች እንደሆኑ መረዳት ይቻላል። ይህ ደግሞ ዘመን ተሸጋሪ እንዲሆን ለማድረግም እንደተሞከረ የሚያሳዩ ነገሮች አሉ። ለአብነት ባህላዊ እሴቶቹ በመጽሐፍ ታትመው ስለክልሉ ባህላዊ እሴቶች መረጃ ማግኘት ለሚፈልጉ ግለሰቦች እንዲሁም ተመራማሪዎችም ቀርበዋል። ከዚያ ባሻገርም በዓለም አቀፍ ቅርስነት በማስመዝገብ ረገድ የተለያ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸው ያገላበጥናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።
እንደነዚህ አይነት የባህል እሴቶች ዘላለማዊና ማንነትን መስሪያ ይሆኑ ዘንድ ጥበቃና ተግባርን ይሻሉ። በተለይ ተተኪው ትውልድ ሊያስቀጥላቸውና ሊጠቀምባቸው ይገባል እያልን በዚህ እናብቃ። ለበለጠ መረጃ ለመረጃ ምንጭነት የተጠቀምንበትን ‹‹የአፋር ብሔረሰብ ባህላዊ እሴቶች›› በሚል ርዕስ በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተዘጋጀው ጥናት እንዲያነቡ እየጋበዝን ተሰናበትን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 3/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው