አሁን ቀልባችን ወደራሳችን የተመለሰበት ጊዜ ላይ የደረስን ይመስላል። ከቻይና የአልባሳት ውጤት ወጥተን አገር የሚተዋወቅበትን ልብስ በዲዛይን ማምጣትና ለገበያ ማቅረብ ጀምረናል። ይህንን ለማለት ያስደፈረን የባህላዊ ልብስ መሸጫ መደብሮችን ሰሞኑን አጥለቅልቆ የታየው ሀገርኛ አልባሳት ጉዳይ ነው። መቼም ምን አይነቶቹ እንደማትሉኝ እርግጠኛ ነኝ። ምክንያቱም ወደ ገበያ ማዕከላት ጉራ ያለ ከልጅ እስከ አዋቂ፤ የሴት እና የወንድ ልብሶች ሁሉ ኢትዮጵያዊ ኩራታችን በምንላቸው ፊደላት እና ቁጥሮች አምረው እና አሸብርቀው መመልከቱ አይቀርም። ብዙዎችም የአዲሱ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት አድርገው ተውበውበት እንደምናይም እገምታለሁ። እስከዛሬ ኢትዮጵያዊ ነኝ ለማለት በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ያሸበረቀ አልባሳት፣ የአንገት ልብስ እና በሌሎች መሰል መዋቢያና ማጌጫ እናደርግ ነበር። አሁን ደግሞ የሰንደቅ አላማት ቀለማትን ከመያዝ አለፍ ብለን የማነነታችን መታወቂያ የሆኑትን ሁሉ መዳሰስ ላይ እንገኛለን። ኢትዮጵያዊነት ኩራት ማለት ይሄው ነው።
የጎንደሩ ጃኖ፤ የአክሱሙ ጥርጥር፣ የኦሮሚያው ኦዳ ዛፍ… የመሳሰሉት መለያ ምልክቶችም የማንነታችን መለያ ጌጣችን ናቸው። ይህ ደግሞ ለውጪው ብቻ ሳይሆን ለአገር ውስጥ ማህበረሰብም ትልቅ መልዕክት ያስተላልፋል።
ለዛሬ ባህላዊ አልባሳት በሀገራዊ ምስሎች ቀለሞች ጥበቦች ተጠብቦ በምናገሽበት ሽሮሜዳ የገበያ ማዕከል ብቅ ብለናል። በዚህ ቦታ የኢትዮጵያን የእጅ ጥበብ ውጤቶች በስፋት ይታያል። አዲስ አበባን ዞር ዞር ብሎ ላልቃኘ ሰውም ከዚህ በፊት ያለመድናቸውን አዳዲስ የጥበብ የፈጠራ ውጤቶች እያየ አጀብ እንዲል ያደርገዋል።
በእርግጥ የባህል ልብስ ውበት ነው፤ የባህል ልብስ ‘ባህል’ ነው፤ በዓልና መለያም ጭምር ነው። እናም እኒህ አልባሳትም ይህንን ሁኔታ በእጅጉ አጉልተው ያሳዩናልና ብዙዎች ለምን ወደዷችሁት ማለት ያዳግታል። በተለይም ምንጫቸው የማንነት መለያ መሆኑ ይበልጥ ዓናችንንና ቀልባችንን እንድናሳርፍባቸው ያስገድዱናል። ለመሆኑ እኒህ አዲሱን ዲዛይን ይዘው ብቅ ያሉት የባህል አልባሳት የትኞቹ ይሆኑ? ካላችሁኝ መልሱ እንዲህ ነው። ኢትዮጵያዊ ቁጥሮችን “የግዕዝ ቁጥሮች” እያለ ለሚጠራው ማህበረሰባችን ማስተማሪያ የሚሆነውን ቁጥር የያዘ፤ ፊደላትን ማለትም ከሀ እስከ ፐ ያሉትን፣ አቦጊዳን፣ መልዕክተን በህትመት ልዩ አድርጎ የሚያቀርብ ነው።
ይህ የሚሆነው ደግሞ ቀሚስ ላይ ብቻ አይደለም። ከረቫትና ጫማም ላይ ውበቱን ያሳያል። በተለይ ለሴቶች ደግሞ በየዓይነቱ ነው ያለው። ነብሰጡር ለሆኑ፣ ለቀጭኖችና ለወፍራሞች በቅርጻቸው(በሰውነታቸው) ልክ ይሰራላቸዋል። በቲሸርትም ቢሆን እንዲሁ ለሱሪ ለባሽ ሴቶች በሚመጥናቸው ሁኔታ ይዘጋጃል። ይህ ማለት ለወንዶች የሚሆን የለም ማለት አይደለም። እንዳውም ከቲሸርትና ሸሚዙ አልፎ በከረቫት ለፈለጉ ተሰርቶ ይቀርብላቸዋል። በአንገት ልብስ መልኩ ደግሞ ለሴትም ሆነ ለወንድ ተዘጋጅቷል።
ይህ የጥበብ ውጤት ለሕጻናትም ቢሆኑ የአገራቸውን ባህልና ማንነት ተረድተው እንዲያድጉ በልካቸው ተሰርቶላቸዋል። ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ያልሆነውን ኢትዮጵያዊ ለማድረግ የሚጥሩ የማንነት መግለጫና ታሪክን መስበኪያ ናቸው። ለመሆኑ ገበያው እንዴት ነው፣ ዋጋና ስሜቱስ እንዴት ይገለጻል ስል በዚህ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የሽመና ባለሙያዎች እና ነጋዴዎችን አነጋግሬያለሁ።
በባህላዊ መንገድ ተሠርተው ከአራቱም የሃገሪቱ ማዕዘናት ጉዟቸውን ወደ አዲስ አበባ አድርገው የሚያርፉት ሽሮ ሜዳ ነውና በየዓይነቱ ማሰራት ይቻላል። በአንድ ባህላዊ የንግድ መሸጫ ጉራ ብዬ በመጀመሪያ ያነጋገርኩት ወጣት ማህደር መላኩ ነው። እርሱም በጉዳዩ ዙሪያ እንዲህ ብሎኛል።
ባህልን የማስተዋወቅ ስራ የአንድ ቀን አይደለም። ዘላለማዊ ኢትዮጵያዊነት ስሜት የሚፈጠርበት መሆን አለበት። ስለዚህም ታሪክ በነገረን መሰረት የራሷ ፊደልና ቁጥሮች ያሏትን ኢትዮጵያን ከአገር አልፎ አለም እንዲያውቃት ለማድረግ ይህንን የፊደላትና ቁጥሮችን ዲዛይን በልብሶች ላይ በማሳተም ይዘን ብቅ ብለናል።
እንደ ማህደር ገለጻ፤ ኢትዮጵያዊነት ከልብ ጋር በማህተም የታተመ ማንነት ነው። እናም ላለን ታሪክ ብዙ ሰው ከፍ ያለ ክብርና ትኩረት ይሰጣል። እኛም ለመጠቀምም ሆነ ለማስተዋወቅ ወይም በኢትዮጵያዊነታችን የሚሰማንን ስሜት ለማንጸባረቅ እንዲህ አይነት የጥበብ ስራዎችን እንድንሰራ ሆነናል። በእርግጥ ይህ እንዴት ይታያል ከተባለ ከሚገዛው ሰው ስሜት በመነሳት እንደሆነም ይናገራል።
ኢትዮጵያዊነትን የያዙ አልባሳት ከሁሉም ባህላዊ ልብሶች የተለየ ቅቡልነትና ትኩረት የመሳብ አቅም አላቸው።
ሽሮ ሜዳ ላይ አንዲት አነስ ያለች የባህል አልባሳት መሸጫ ሱቅ ከፍተው 20 ዓመታትን በስራው ላይ እንዳሳለፉ የሚናገሩት አቶ መኮንን ወርቁ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዳለም የገዛና የለበሰው፣ ዲዛይን ያደረገው ወይም የሚያደንቀውን ለዓመታት በአልባሳት ሽያጭ ስራቸው ያዩት እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ መሆኑ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ኩራት ምን ያህል ዋጋ እየተሰጠው እንደመጣ ያሳየናልም ብለዋል።
ገበያ ነውና ይህንንም ሆነ የቻይና እጅ ያረፈባቸውን አልባሳትን እንደሚሸጡ የሚያነሱት አቶ መኮንን፤ የኑሮ ነገር ነውና ሁሉም በአቅሙ እንዲገዛ እየሰራን ነው ይላሉ። ነገር ግን የሀገር ልብስን እንደመሸጥ የምደሰትበት የለም ይላሉ። ምክንያቱም ብር ሳይሆን ማንነቱ አብሮ ይሄዳል ባይ ናቸው። ‹‹የቻይኖቹን ገንዘብ ስለማገኝበት እሸጠዋለሁ። በእጅ ጥበብ የተሰራውን ግን ስሸጥ ከሚገባው ገንዘብ ይልቅ በትክክለኛው መንገድ እያጌጡ መሆናቸው ያስደስተኛል። ማንነታቸውንም እንዳወቁ ይሰማኛል›› ሲሉ በፈገግታ ስሜታቸውን አጫውተውኛል።
የዋጋ ልዩነቱ ማንነታችንን እያስቀማን ነው የሚሉት አቶ መኮንን፤ አሁን በአዳዲስ የዲዛይን ስራ መመጣቱ ልዩነቶችን እያጠበባቸው ቢመጣም መንግስት እዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ካልቻለ ግን አደጋ ውስጥ እንደምንገባ ይናገራሉ። ኢትዮጵያዊያን የኬንያ ዳኞችን አለባበስ ሳይቀር የቀየርን ነን። ምክንያቱም ታሪክ የሰራን ስለሆንንና ቀለማችንም ተመራጭ በመሆኑ። ስለዚህም ይህንን ሃያልነት ተጠቅሞ ራስን መስራት ደግሞ ለነገ የሚባል መሆን የለበትም። እናም ስንገዛም ሆነ ስንለብስ ይህ ጉዳይ ይታሰበብበት ይላሉ።
«በሸማኔ የሚሠሩ ባህላዊ ልብሶች ብዙ ውጣ ውረድ አልፈው ነው ለገበያ የሚበቁት። ከጥጥ ማምረት ጀምሮ፤ መፍተል እንዲሁም ከሳባ ወይም ከመነን ጋር አስማምቶ መሸመን ትልቅ ጥበብና ድካምን ይጠይቃል» የሚሉት አቶ መኮንን፤ በዲዛይንና በሀሳብ ማንነትን የመንገሩ ነገር አሁን መፈጠሩ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ይናገራሉ። ከመርካቶ በጣቃ መልክ መጥተው በሜትር የሚሸጠውን አቡጀዲ ገዝተው በህትመት ፊደላትን፣ ቁጥሮችንና አቦጊዳ ወዘተ በማድረግ በቅናሽ ዋጋ ሲሸጡ ታሪክ እየሰሩ እንደሆነ እንዲሰማቸው ሆነዋልና። ከሚያገኙት የገንዘብ ትርፍ ባለፈ ታሪክን እያወረሱ ኢትዮጵያዊነትን እያነገሱ መሆኑ ይሰማቸዋል፤ ይሄም እንደሚያስደስታቸው ይናገራሉ።
አቅሙ ያለው ደግሞ ጥራት ባለው ጨርቅ እነዚሁ የማንነት መገለጫ የሆኑት ፊደላት ይታተሙለታል። ከዚያማ አምሮና ደምቆ ራሱን ያያል ይላሉ። በእርግጥ ይላሉ አቶ መኮንን፤ በእርግጥ ይህ ፊደላትን የማሳተም ጉዳይ ራስን ከማስተዋወቅ አንጻር ብቻ የሚታይ አይደለም። ይልቁንም በአገርም መኩራትን ያላብሳል። ከዚያ ባሻገርም ለማህበረሰቡ መልካም ስብዕናን ይፈጥራል። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነት ይህ ነው ብሎ ስለሚናገር። እናም ሁሉም ባለው ልክ ራሱን በራሱ መስራትና ለራሱ ባህል መገዛትን ይለምዳል። ስለዚህ ሁሉም ቢጠቀምበት መልካም እንደሆነ ይመክራሉ።
ኢትዮጵያውያን በዓል በመጣ ቁጥር የሀገር ምርት በሆነው የባህል ልብሳችን ተውቦ መዋልን ልምድ እያደረግነው እንደመጣን ማወቅ የሚቻለው ሽሮ ሜዳ ላይ ሁሉም አቅሙ የፈቀደውን የበዓል ልብስ እየተጋፋ ሲጋዛ ማየት እንደ አንድ ማሳያ ነው። ነገር ግን ህዝቡ ወደ ባህል ልብስ ፊቱን ሲመልስ ዋጋውን መስቀል ደግሞ ማሸሽን ያመጣል።
ልብሱ በጣም ስስ ከሻማ የተሰራ ሲሆን፤ ዋጋው ግን ሚዛናዊ አይደለም። ሀብታሞች ቤት ብቻ እንዲገባ ለፊደላችን ታስቦ ሳይሆን ለትርፍ ታስቦ የተሰራ እንደሆነ ይናገራል። እናም ለትውውቅና ማንነትን በሰዎች ላይ ለመስራት ከሆነ ማንም ሳይጎዳ የሚሰራበት መንገድ ቢመቻች ሀሳቡ ይበል ያሰኛልና ትኩረት ይቸረው በማለት ለዛሬ አበቃን። መልካም አዲስ ዓመት!
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 3/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው